Thursday, April 26, 2012

ሰበር ሰሚ ችሎት ለመንፈሳዊ ፍርድ ቤት የወረወረው የካህናት ጩኸት!

 መንፈሳዊ ፍርድ ቤቶች አቅም ግንባታ የላቸውም!
ለዚህ ጽሁፍ መነሻ የሆነው ሪፖርተር ጋዜጣ በሚያዚያ 17/2004 ዓ/ም እትሙ ያወጣውን ስለሃይማኖት ተቋማት ይልቁንም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የወርቁ ሠፈር ማርያም ቤተክርስቲያን  አገልጋይ በነበሩት 6 ካህናት ላይ «ሰበር ሰሚ ችሎት» የሰጠውን ብይን አስመልክቶ «ደጀ ሰላም» ብሎግ ደስታውን በመግለጽና የሪፖርተርን ዘገባ በማድነቅ መልሶ መረጃውን ለማስተጋባት የሄደበት መንገድና ስለመንፈሳዊ ፍርድ ቤት በማቀንቀን የተጓዘበትን የምኞት መንገድ ስህተት ለማሳየትና መልስ መስጠት በማስፈለጉ ይህን ጽሁፍ ማቅረብ አስፈልጓል።
የሰበር ችሎት የህግ ትርጉምን በተመለከተ፣
በመዝገብ ቁጥር 18419 ግንቦት 4 ቀን 1998 ዓ.ም. የቀረበለትን የይግባኝ አቤቱታ የተመለከተው ሰበር ሰሚ ችሎት የሰጠው ብይን በስር ፍርድ ቤቶች ሁሉ አሳሪ የሆነውን ውሳኔ የሰጠው የጠቅላይ ፍርድ ቤትን ሥልጣንና ኃላፊነት ለማቋቋም በወጣው አዋጅ ቁጥር 42/97 አንቀጽ 2/4 ላይ ላይ የተሰጠውን መብት በመጠቀም መሆኑ ይታወቃል።

ይሁን እንጂ በግፍና ፍጹም ርህራኄ በጎደለው መንገድ ከስራና ከደመወዝ የተባረሩት 6ቱ ካህናትና ከዚያም በኋላ በዚህ የሕግ ትርጉም ሳቢያ ከስራቸው ተባረው ሜዳ ላይ ከነቤተሰቦቻቸው የተጣሉት በመቶዎች የሚቆጠሩ የቤተክርስቲያኒቱ ካህናት ኢትዮጵያዊ ስለመሆናቸውና የኢትዮጵያ ሕጎች ሊጠብቋቸው ወይም በነሱ ላይ ተፈጻሚ ሊሆኑ ስለመቻላቸው አንዳንድ ቁልፍ ነጥቦችን በማቅረብ የሰበር ችሎቱንና አራጋቢዎቹን ለመጠየቅ እንሞክራለን።
የስር ፍርድ ቤቶች አሰሪና ሰራተኛን በተመለከተ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 3 ንዑስ አንቀጽ 3 ፊደል ተራ «ለ» ላይ የተመለከተውን የሕግ አግባብ ተከትለው የካህናቱን የህግ አቤቱታ እየተቀበሉ ሲያከራክሩና ሲወስኑ መቆየታቸው ይታወቃል። ይህንን ዳኝነት የሰጣቸው የአሰሪና ሰራተኛ አዋጁ ማንኛውንም የስራ ክርክር ጉዳዮችን በሃይማኖት ተቋማት ላይ ተፈጻሚ እንዳይሆን በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ እስካልወጣ ድረስ ክርክሮቹን እንዳይመለከቱ የሚያደርጋቸው አግባብ ባለመኖሩ ብቻ ነው። ህጉ ምን እንደሚል እዚህ ላይ ይጠቀሳል።
«የሃይማኖት ወይም የበጎ አድራጎት ድርጅቶች በሚመሰረቱት የስራ ግንኙነቶች ላይ ተፈጻሚ እንዳይሆን የሚኒስትሮች ምክር ቤት በደንብ ሊወስን ይችላል» የሚል ነው።
 ህጉ ይህንን ቢልም ተፈጻሚ እንዳይሆን የማይከለክለውን ይህን ድንጋጌ ወደ መከልከል ያሸጋገረው  የፌዴራል ሰበር ሰሚ ችሎት በይግባኝ የቀረበለትን የስድስት ካህናት ውሳኔ ከመረመረ በኋላ በሰጠው የህግ ትርጉም የተነሳ ነው። የህግ ትርጉም የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ቢኖሩ የሰበር ችሎት የህግ ትርጉም እንደተጠበቀ ሆኖ በዚህ አዋጅ ላይ የሰጠው የህግ ትርጉም ግን ለትርጉም አሻሚ ያልሆነና በግልጽ የተቀመጠ ቢሆንም ተገቢ ያልሆነ የህግ ትርጉም በመስጠት ራሱን እንደ፤
1/ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ተፈጻሚነቱን ለመወሰን ደንብ ሳያወጣ ራሱን እንደሚኒስትሮች ምክር ቤት በመሰየም የህጉን ተፈጻሚነት የሚከለክል ደንብ ያወጣ በመሆኑ፤
2/   አዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 3/3/ለ  የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚያወጣው ደንብ ብቻ ከተፈጻሚነቱ ሊታገድ እንደሚችል ህጉ እስካሁን እየተናገረ ቢገኝም ሰበር ችሎት ያለደንብ በትርጉም የሻረው መሆኑ  በተለጠጠ የህግ ትርጉም ህጎች ሁሉ በጣልቃ ገብ ብይኖች እንዴት እንደሚሻሩ ከሚያሳይ በስተቀር የስራ ክርክር ችሎቶችን ችግር ያልፈታ በመሆኑ፣ ብይኑ ህገ ወጥ ነበር።
ስለሆነም  አዋጁ ስለመሻሻል ወይም ተፈጻሚ መሆንን ስላለመቻል  የተቀመጠውን አግባብ ሽሮ ሰበር ችሎቱ የሰጠው ብይን ትክክል ካለመሆኑም በላይ ትርጉም የተሰጠበትን የመንፈሳዊ ተቋም የስራ ግንኙነት ለሁለት ከፍሎ የሚገባቸውና የማይገባው ሲል መገኘቱ ሌላው ትልቁ ስህተት ነው። ከእነዚሁም ውስጥ በቢሮ ስራ እንደጸሐፊ፣ መዝገብ ቤትና ስታትስቲክ ክፍል ያሉት በቀጥታ ከመንፈሳዊ አገልግሎቱ ጋር ግንኑኘት የሌላቸው ሰራተኞች ክርክር በአዋጁ ይሸፈናል ማለቱ ሌላው አስገራሚ ብይን ነው። በዚህ ብይን መሰረት፣
1/ ቀዳሾችና አወዳሾች አዋጁ የማይመለከታቸውና መብታቸውን  በአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ማስከበር የማይችሉ ሰዎች ናቸው።
2/ የቢሮ ሰራተኞች የስራ ክርክሮች ሁሉ  በአዋጁ የሚሸፈኑና መብትና ግዴታቸው የሚከበርላቸው ዜጎች ናቸው። የአንድ ተቋም ሰራተኞችን የሚከፋፍል፣ የስራ ዋስትናቸውን በአዋጁ የሚሸፍንላቸውና ከአዋጁ ውጪ የሚያደርግባቸው በማድረጉ ትርጉሙን አሳዛኝ ያደርገዋል።
የዚህ  ህግ ትርጉም ሌላው ትልቁ ስህተቱ  ደግሞ በህገ መንግስቱ የተቀመጡ የዜጎችን የህግ መብት የሚንድና የሚሽር መሆኑ ነው።
የህገ መንግሥቱ አንቀጽ 25 «ሁሉም ሰዎች በህግ ፊት እኩል ናቸው» ይላል። ይሁን እንጂ የአንድ ተቋም ሰራተኞች በህግ ፊት በእኩል መዳኘት እንዳይችሉ ሰበር ችሎት በተለጠጠ የህግ ትርጉም ከልክሏል። ስለዚህ ቀዳሽና አወዳሽ ሰራተኞች ከቢሮ ሰራተኞች ጋር በአንዲት ቤተክርስቲያን ውስጥ ቢገኙም እንኳን አቤቱታ የማቅረብ ህገ መንግስታዊ መብታቸው በተሰጠው ትርጉም ተዘግቷል ማለት ነው። እኩል የመዳኘት መብታቸውን ለመሻር ሰበር ችሎት ስልጣኑን ከየት አገኘ? ህገ መንግስቱን በመሻር የአንድ መስሪያ ቤት ሁለት ሰራተኞችን አንተ ትችላልህ፣ አንተ ደግሞ አትችልም በማለት ማን ደልዳይ አደረገው? በህግ ፊት እኩል የመሆን መብትን መከልከል ህግ መንግስቱን መናድ አይደለምን? ብለን ብንጠይቅ ምናልባት ሰበር ሰሚ ችሎት ወደዚህ ህገ ወጥ የህግ ትርጉም የተገፋው በወቅቱ ከ200 በላይ የክስ መዝገቦች ያስጨንቁት የነበረው የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የክስ ፋይሎች እንዲዘጉለት በሆነ መንገድ ያሳደረው ተጽእኖ ሊኖር እንደሚችል ይጠረጠራል።
በአጠቃላይ  ሰበር ችሎት የሰጠው የህግ ትርጉም በምንም መለኪያ መጠኑን ያለፈና ዜጎችን ያፈናቀለ ሆኖ አልፏል።
በሌላ መልኩም መንፈሳዊ ፍርድ ቤቶች የካህናቱን ጉዳይ ይመልከቱ የሚሉ አቀንቃኞች ከቤተክርስቲያን ውስጥ ይደመጣሉ። ስንፈትሸው ችግሮቹ በአስተዳደር ጉድለት ላይ ይሽከረከራል።
የቤተክርስቲያንን መንፈሳዊ ፍርድ ቤት በተመለከተ፤
እዚህ ጽሁፍ ላይ ቤተክርስቲያን ስንል ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን የተመለከተ ነው። ሌሎች አብያተ ክርስቲያናት በይበልጥም ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት የነቃና የተደራጀ የሰራተኛ ማኅበራት ስላሏቸው መብታቸውን በዚያ እንደሚያስከብሩ ይታወቃል። እንኳን የሰራተኛ ማኅበር ለማቋቋም ይቅርና ስሙን እንኳን ከወሬ ባለፈ ሰምቶ የማያውቀው ኦርቶዶክሳዊው ካህን ግን ከዚህ ሁሉ ርቆ በሰበር ችሎቱ የህግ ትርጉም የስራ ዋስትናውን እያጣ መገኘቱ አመታት ተቆጥረውበታል። ይህንን የስራ ዋስትና ያስከብራል ተብሎ በሲኖዶስ ተብዬውና በአቀንቃኙ ማኅበር በኩል የሚስተጋባው የሰራተኛን ጉዳይ የሚመለከተው መንፈሳዊ ፍርድ ቤት ስለማደራጀትና ስለማቋቋም የሚለፈፈው ነገር ከታች በምናቀርባቸው ጭብጦች የተነሳ በፍጹም ውጤታማ ስራ መስራት አይችልም።
1/ ብዙ ጊዜ ሰራተኛ ካህናትና ዲያቆናት ከስራ ስንብት እርምጃ የሚወሰድባቸው የህግ እውቀት በሌላቸውና የአስተዳደር« ሀሁ»ን የማያውቁ ይልቁንም «አድርግ፣አታድርግ» በሚል አንባ ገነን ባህሪይ እድሜአቸውን የፈጁ፣ አጎብድዱልኝ፣ ከጫማዬ ስገዱልኝ፣ መስቀሌን ሳሙልኝ፣ የቀሚሴን አቧራ ጥረጉልኝ  በሚሉ አስተዳዳሪዎችና  ሊቃነ ጳጳሳት በሚወሰዱ እርምጃዎች የተነሳ ነው። አንዳንዶቹ በራሳቸው ስለማይተማመኑ ሁለት ወይም ሶስት ዲያቆናት አንድ ላይ ቆመው ካዩ በእኔ ላይ እየዶለቱ ነው በሚል ሰበብ እርምጃ የሚወስዱ ስለመኖራቸው ይታወቃል። በገንዘብ ዘረፋ፣ ያለአግባብ ቅጥር፣ ደመወዝ ጭማሪ፣ ከደረጃ ዝቅ ማድረግ፣ ማዛወር የሚወሰደው በነዚሁ የስራ መሪዎች በኩል ነው። እንግዲህ እነዚህን ሰዎች ለመክሰስ ወይም የተወሰደውን የመብት ጥሰት ለማስከበር በየትኛው ነጻ ፍርድ ቤት ነው ካህናቱ መብታቸውን የሚጠይቁት? መንፈሳዊ ፍርድ ቤት ቤተክርስቲያኒቱ የምታቋቁመው፣ ራሷ የምትሾመው፤ የምትሽረው እንጂ የሙያ፣ የስራ፣ የህግ ነጻነትና እውቅና ያለው አይደለም። ስለዚህ በምንም መመዘኛ የካህናቱን መብት አስከብሮ ከጳጳሳት ጉያ የማይጠፉትን አስተዳዳሪዎችና አለቆች ወይም በስልጣን ይቀመጥ ዘንድ በተሾመው ሰው ላይ እርምጃ ወስዶ የተበዳዩን እምባ ያብሳል ተብሎ እምነት አይጣልበትም። አንድን ሰራተኛ ምንም ዓይነት ስራ ሳይሰጡት ፣ከስራ ውጭ ሲያደርጉት በቤተክህነቱ አካባቢ «አንሳፈፉት» ይባላል። እንደዚሁ ሁሉ ፓትርያርኩ ያንሳፈፉት አንድ አባት በአንድ ወቅት ፍርድ ቤት ከሷቸው ችሎት ከመቆም ይልቅ ወደ ሥራ ለመመለስ ተስማምተው ካህኑ ውዝፍ ደመወዛቸውን ተቀብለው ከስራ እንደተመደቡ እናውቃለን። ያ ባይሆን ኖሮ የትኛው መንፈሳዊ ፍርድ ቤት ይዳኝ ነበር?
2/ ቀደም ባሉ ዘመናት የነበሩ የስራ መሪዎችና ጳጳሳት መንፈሳዊነቱ ያይልባቸው ስለነበር አጥፊ ካህናት ቢኖሩ እንኳን በመምከር፤ በመገሰጽ፣ በማስተማርና በይቅርታ የሚያልፉ ሲሆን የዛሬዎቹ ደግሞ ዘመናዊነቱና አልፎ አልፎም አንባ ገነንነቱ ስለሚያይልባቸው ፈጥኖ ወደእርምጃ መውሰድ ይንደረደራሉ።  አንድ ጳጳስ ያሰናበተውን ወይም ከደረጃ ዝቅ ያደረገውን ወይም ተመሳሳይ እርምጃ የወሰደበት ካህን በየትኛው መንፈሳዊ ፍርድ ቤት ነው የክስ አቤቱታ የሚያቀርብበት? አንተ ብጹእ አባታችንን ትከሳለህ ወይ? ብሎ የሚጠይቅና የጳጳሱን ክብርና ዝና በመጠበቅ ጋሻ ከሚሆን ውጪ የካህኑን አቤቱታ የሚመለከት የተለየ መንፈሳዊ ፍርድ ቤት በፍጹም ማቋቋም አይቻልም።  ዝም ብለህ አጥፍቻለሁ ብለህ ይቅርታ ጠይቀህ ታረቅ፣ በማለት ባለመብቱን እንደአጥፊ ከመቁጠር ባለፈ ከጳጳሳቱ ጋር መጋጨት የሚፈልግ መንፈሳዊ ፍርድ ቤት አሁን ባለችው ቤተክርስቲያን ውስጥ ፈጽሞ የማይታሰብ ነው።
መደበኛ ፍርድ ቤት ግን ሁሉም ሰው በህግ ፊት እኩል በመሆኑ በቁራጭ የመጥሪያ ወረቀት ጆሮውን ጎትቶ በማቅረብ መብት ረጋጭና ተረጋጭን እኩል ያከራክራል። ሽፍንፍን አስወልቆ ይጠይቃል፣ ያፋጥጣል። እንዲያውም መድረሻ ያጣውና መብቱ በአንባ ገነኖች የሚደፈጠጠው ካህን እንደሰው እኩል የሚታይበት ቦታ ቢኖር መደበኛ ፍርድ ቤት ችሎቶች ውስጥ ከሳሽና ተከሳሽ ግራና ቀኝ ሲቆሙ ብቻ ነው።
3/ ሰበር ሰሚ ችሎት በብይኑ ካህናቱን ለሁለት ከፍሏል። መንፈሳዊ ፍርድ ቤት ይመለከት ዘንድ የሚፈለገው በመደበኛ ፍርድ ቤት አቤቱታ ማቅረብ አይችሉም የተባሉትን ካህናት ነው ወይስ የህግ ድጋፍ የተሰጣቸውንም ካህናት ያጠቃልላል?  ሰበር ሰሚ ችሎት ፈቃድ የሰጣቸውን ካህናት ጉዳይ በመደበኛ ፍርድ ቤት ማየት እንዳይቻል ለማስደረግ ቤተክርስቲያኒቱ ትወተውታለች ማለት ነው? ጉዳዩን ስናየው በህግ ከማስተዳደር ይልቅ ጉልበተኝነታቸው በህግ እንዳይጣስ የሚከራከሩ ይመስሉናል።
ሰዎች ፍርድ ቤት የሚሄዱትና አቤቱታ የሚያቀርቡት  ለመዝናናት አይደለም። የመብት ጥሰት በሰፈነበት የቤተክርስቲያን አስተዳደር በመማረር መሆኑ ይታወቃል። ስለመብታቸው የሚደረገው ጩኸት ለማፈን ከመፈለግ ይልቅ የመብት መከበርን ለማስፈን ቤተክርስቲያን ምን ያህል ዝግጁናት? ብለን ብንጠይቅ መልሱ ምንም የለም ይሆናል። የጫወታው ህግ ካለህ አለህ ነው፣ ከሌለህ የለህም!
እዚህ ላይ የምጠቅሰው ከቤተክርስቲያኒቱ ፍትህ ማጣት የተነሳ ሜዳ ላይ ከነቤተሰቦቹ የተጣለና መውደቂያ ሲያጣ ወንጌላውያኑ ያነሱትን ካህን የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ በቅርብ ያውቃል።
ስለሆነም የመንፈሳዊ ፍርድ ቤቶች ቲዎሪ፤
ሀ/ አሁን ባለው የቤተክርስቲያኒቱ መዋቅር መንዛዛትና አስተዳደሩ ሁሉ በግፋ በለውና በምን አገባህ ጉልበታም ህግ የሚመራ እንደመሆኑ መጠን በምንም መለኪያ የካህናቱን መብት አያስከብርም።
ለ/ አሁን ካህናቱ እየተዳደሩ ያሉት በአራት መንገድ መሆኑን በግልጽ እናውቃለን። እሱም አንደኛው አንገቱን ደፍቶ፣ ድምጹን አጥፍቶ፣ ልጆቼን ላሳድግበት ብሎ እያየ እንዳላየ፣ እየሰማ እንዳልሰማ ሆኖ ሲሆን ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ምን አባቱ ያደርገኛል? «ግፋ ቢል አዶላ ነው፣ አንሳ ቢል አካፋ ነው» በሚል መንገድ መብትን በማስፈራራት የማስጠበቅ አሰራር ነው። ከዚህ ባለፈ ደግሞ በሶስተኛው ደረጃ፣ በእጁ እየሄደ ወይም የወንዜ ልጅ እያለ ሸንተረር እየቆጠረ ካልሆነ በስተቀር በህግና በህግ ብቻ አይደለም። ሌላውና የመጨረሻው ደግሞ ካህናቱ የሚጠቀሙት የሰበካ ጉባዔ አባላት የካህናቱ የንስሀ ልጆች በመሆናቸው ለአድማና ለብጥብጥ ቅርብ አጋሮች ስላላቸው በዚህ የተነሳ  አስተዳዳሪዎች በካህናቱ ተባረሩ እንዳይባሉና በበላዮቻቸው በኩል ለተሻለ እድገት እንቅፋት እንዳይሆንባቸው አመላቸውን ሳይወዱ ለመቅበር ይገደዳሉ። ያም ሆኖ አንድ በአንድ ነጥሎ በመምታት፤ በመከፋፈል እኩይ ግብራቸውን ያለህግ በጉልበት ከመፈጸም አያርፉም።
መፍትሄው ምን መሆን አለበት?የሚለውን ደግሞ የመጨረሻ አማራጭ መሆን ባይችልም ለመነሻ ሃሳብነት ይህንን አስቀምጠናል።
1/ እስካሁን ድረስ አስተዳዳሪ ባሰናበተው ሰራተኛ ክስ የተነሳ ሲፈረድ ከካዝናው አውጥቶ የሚከፍለው ቤተክርስቲያኒቱ ናት። ይህ አሰራር መለወጥ አለበት። ስለሆነም አስተዳዳሪው ወይም እርምጃውን የወሰደው ኃላፊ ለወሰደው እርምጃ  መጠየቅ ያለበት ራሱ እርምጃ ወሳጁ ሰው መሆን ይገባዋል። ይህም  ከሕግ ውጪ ለሚወስደው ተጠያቂነት ኃላፊነቱ የእሱ መሆኑን ካወቀ እርምጃውን ሁሉ በህግ አግባብ ለማድረግ ይገደዳል። ቤተክርስቲያኒቱ በአንባ ገነን የስራ መሪ ካዝናዋን ልታራቁት አይገባትም።
2/ የወረዳ፣ የአውራጃና የሀገረ ስብከት የህግ ክፍሎችን( የህግ ክፍል መንፈሳዊ ፍርድ ቤት አይደለም)የህግ ክፍሎችን በባለሙያ ማደራጀትና ማንኛውንም የመብት መጣስ አቤቱታዎችን ከመደበኛ ፍርድ ቤቶች በፊት መመርመር እንዲችል ቢደረግ የተሻለ ነው።
3/ ከካህናቱን በኩል ህግ የማያከብሩ፣ የቤተክርስቲያኒቱን ሥርዓት የሚጥሱ ስለሚኖሩ በቅድሚያ ማስተማር፤ የሚቀጠሩበትን የሚሰሩትን ደንብና መመሪያ ማሳወቅ፣ የስራ ውሉ ከዚያ የመነጨ ስለመሆኑ የታወቀና የተወሰነ ስምምነት ማድረግ መቻል፣ ማወያየት፣ ማነጋገር ወዘተ የመሳሰሉትን መከተል የተሻለ ነው።
ይኼውም፤ ጉዳዮችን በድርድር፤ በሽምግልና፣ በቤተክርስቲያኒቱ መተዳደሪያና በመደበኛ ህጎችም ጭምር ለማየት እድልና የመፍታት አማራጮች ይኖረዋል ተብሎ ይገመታል።
እንደኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሁሉ እስልምናውም የራሴ ፍርድ ቤት ስላለኝ በሸሪአ ፍር ቤት ከሚታይ በስተቀር ሲል ይደመጣል።ይህ ሸሪአ ደግሞ ለመብት ጥሰት እውቅና የሚሰጥ ፍርድ ቤት በመሆኑ እስላሞቹ በአብዛኛው አይቀበሉትም። ለምሳሌ ሚስቱን ለመፍታት በሸሪአው ህግ ባልየው ሶስት ጊዜ «ፈትቼሻለሁ፤ ፈትቼሻለሁ፣ ፈትቼሻለሁ» ካለ በቂው ነው። ይህን የሸሪአ መንፈሳዊ ፍርድ ቤት ይሉታል ወይስ የግፍ ፍርድ ቤት?
መንፈሳዊ ፍርድ ቤቶች በቆየ ልምድ፤ ባህል፣ ወግና ሃይማኖታዊ መሰል ህግ የሚመራ እንጂ እንደዘመኑ፣ ከዘመኑ ጋር የማይራመድ ስለሆነ መብትን በተመለከተ ውጤታማ ሊሆን አልቻለም። ውጤታማ እናደርገዋለን የሚሉ አካላት በቅድሚያ ውስጣዊውን ውጫዊውን ሁኔታ በሰፊው አጥንተው የሚገቡበት እንጂ ድሮ ስለነበረ አሁን እናስቀጥለዋለን በሚል በስብሰባ ጭብጨባ ዘው የሚባልበት መሆን አይገባውም።
ስናጠቃልል ሰበር ሰሚ ችሎት ይሁን፣ ሪፖርተር ወይም ደጀ ሰላም አንድም የተጨበጠ ነገር ከ1998 ዓ/ ጀምሮ መብታቸው ለተገፈፈ ካህናት የሚሆን መፍትሄ ባለማቅረብ ከዚያ ወደዚህ ለማላጋት የሃሳብ አዙሪት ማስተጋባቱ ምንም ፋይዳ የለውም እንላለን። ካህናቱም መብቱን በመደበኛ ፍርድ ቤት ለማስከበር ይችል ዘንድ የሰበር ሰሚ ችሎት የህግ ትርጉም ውድቅ እንዲሆን ለፌዴሽን ምክር ቤት የህግ መንግስት አጣሪ ጉባዔ በጋራ መጮህ ይገባዋል።  መንፈሳዊ ፍርድ ቤት የሚባለው አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ መስራት የማይችል አካል ስለሆነ እንጂ ከዘመኑ ጋር የሚራመድ የህግ እውቀትና አተገባበር ከነ አፈጻጸሙ ቢኖር የሚጠላ ማንም የለም። ይህ እስኪሆን ሌላ ዘመን ስለሚጠይቅ መደበኛ ፍርድ ቤቶቹ መተኪያ የሌላቸው የመጪኺያ መድረኮች ናቸው።ሐዋርያው ጳውሎስ እንኳን ወደ አውግስጦስ ቄሳር ይግባኝ መጠየቁ ስህተት እንዳልሆነ ሁሉ ካህናቱም ወደሚመለከተው መንግሥታዊ አካል መጮህ ስህተት አይደለም እንላለን።
  መሪጌታ ዘነበ ወጉ ከሳር ቤት