ዋሾ፤ ቀጣፊ
(ከደጀብርሃን)
እንዲያው ቅጥፍ አርጎ የነገር አበባ
ሳይሸተው የሚያበን የዲስኩር ገለባ
የሰው አረማሞ የሆነ ፍሬ አልባ
መጎንጎን ማፍተልተል፣ተንኮልና ደባ
ሳይጠሩት የሚጮህ ፣ጣልቃ የሚገባ
በከቸቸ ዓይኑ፤ እንደአዞ የሚያነባ
ነጩን የሚያጠቁር ክፋት የሚቀባ
ሰው መሳይ በሸንጎ ፣ለብሶ የእድሜ ካባ
አለ በሰፈሩ፣ አለ በሀገሩ፣
በዋሾ የተወጋ፣ አለ በመንደሩ፣
ያለቀሰም
አለ፣ እንባን የፈሰሰ፣ ኑሮን ያመረረ
ተወግቶ የደማ ፣ ውስጡ የጠቆረ፣
ትዳሩ የፈረሰ፣ ሜዳ ላይ የቀረ
ተሰርቶበት ነገር፣ ውድቀት የቆጠረ፣
ጓደኛን የጠላ፣ ጸብን ያከረረ፣
አለ የተወጋ፣ አለ የተነካ በዋሾ ቀጣፊ
በሀሰት ዲስኩሩ፣ በነገር ፈልሳፊ
በሃይማኖት ስፍራ፣ አለ መስቀል ይዞ፣
እያለቃቀሰ ልክ ፣ እንደአዞ፣
ጸብን እየዘራ፣ በሀሰት ደንዝዞ፣
አለ በየቢሮው፣ ወንበር ተደግፎ፣
አብስሎ ሚያበላ፣ የተንኮልን ገንፎ፣
አለ በአስኳላው፣ ደብተር ተሸክሞ፣
አጋጭቶ የሚስቅ፤
በክፋት አላትሞ፣
አለ በየቦታው ዋሾና ቀጣፊ
በምታልፈው እድሜ፣ ሳይመስለው አላፊ።
በምታልፈው እድሜ ሳይመስለው አላፊ፣
ዛሬም ገና አለ
ዋሾና ቀጣፊ........
ዛሬም ገና አለ
ዋሾና ቀጣፊ........