(by dejebirhan)
የኢትዮጵያ ሚሊኒንየም (እስራ ምእት) ከተከበረ እነሆ አራት ዓመታት እንደከነፉ አለፉ። አራት ዓመታትን እድሜያችን ሮጧል ማለት ነው። እያንዳንዷ ደቃቅ ሰከንድ እኰ የእድሜ የሩጫ ሰዓት ናት! የሚገርመው ደግሞ እኛ በእረፍት ዓለም እንቅልፍ ውስጥም ሆነን ቢሆን እድሜ መሮጡን አለማቆሙ ነው። ይሮጣል፣ ይሮጣል፣ ይሮጣል!!
የእድሜ ሩጫው አይታይም። አይሰማም። የሚታወቀው በእኛነታችን ላይ በሚያሳየው የሕይወት ለውጥ ብቻ ነው። እድሜ ሩጫውን የሚያበቃው ደግሞ ከዚህ ዓለም ምንም ዓይነት ሽልማት ሳይቀበል ወይም ባለእድሜውን ሳያማክር በገዛ ሥልጣኑ የባለእድሜውን የዚህ ዓለም ሕይወት ዘመን ለሞት በማስረከብ ነው። ያኔም እድሜ «ሩጫዬን ጨርሻለሁ» ብሎ ከእኛ ህልፈት በኋላ ሩጫውን ያቆማል። ሟችም ከእድሜው ሩጫ ጋር እኩል ሮጦ ከሆነ እኔም «ሩጫዬን ጨርሻለሁ፣ የጽድቅም አክሊል ተዘጋጅቶልኛል» ይል ይሆናል። የሩጫውን ውጤት የሚወስነው ሲያሯሩጠው የነበረው የእድሜውን ሩጫ ተከትሎ የሮጠበት የሩጫ ዓይነትና ይዘት ነው።
አንዳንዶች እድሜያቸው ሮጦ፣ ሮጦ ለሞት ካስረከባቸው በኋላ በሌሉበትና ባልኖሩበት የዚህ ዓለም ቆይታቸው ግንኙነት የሌለው የሩጫ ዜና ይሰራላቸዋል። ከመቃብራቸው በላይ «ሩጫዬን ጨርሻለሁ፣ የፅድቅም አክሊል ተዘጋጅቶልኛል» የሚል ጥቅስ ይሰፍርላቸዋል። ምናልባት ከእድሜአቸው ጋር የሮጡት ገንዘብ ለመሰብሰብ፣ በወለድና በአራጣ ለመክበር ሲሮጡ ሆነው ይሆናል። የተበደሩትን ቀምተው፣ በሚስታቸው ላይ ወይም በባላቸው ላይ ወስልተውም ይሆን ይሆናል። እንደክርስቲያን እያማተቡ ወይም ክርስቲያን ስለመሆናቸው አንገታቸው ላይ መስቀል አንጠልጥለው ወይም ክር አስረው ግን አንድም ቀን ክርስትናውን የሕይወታቸው አንድ አካል አድርገው አልኖሩበት ይሆናል። አንዳንዶች በ40 ቀናቸው ወይም በ80 ቀናቸው በእናታቸው ጀርባ ክርስቲያን ከተባሉ በኋላ እድሜ ለሞት ካስረከባቸው በኋላ ለሁለተኛና ለመጨረሻ ጊዜ በሳጥን ተጭነው ይሆናል ከክርስትናው ጋር የሚተዋወቁት። የእድሜ ፍጻሜ ምስክርነትን ባልዋሉበት ማግኘት ደግሞ አሳዛኙ ነገር ነው።
ብዙዎች ይህንን ኑረት ኖረው በእድሜአቸው ሩጫ ከተለያዩት በኋላ ባሸበረቀ የሀዘን መግለጫ ካርድ ወይም ዝናና መልካም ገመና ገላጭ በሆነው በሕይወት ታሪክ ጽሁፍ ሲመሰገኑ፣ ሲወደሱ ይታያል። የሚያስቆጨው ነገር ይህ ሁሉ የዝና ግርግር ለሌላኛው ዘመናቸው የማይጠቅም መሆኑን ማወቅ አለመቻል ነው።
እድሜ ይሮጣል፣ አብሮ የሚሮጥ ካለ የሩጫው ዓይነት የሩጫውን መጨረሻ ይወስናል። ልበ አምላክ ዳዊት የሩጫው ዘመን ትንሽነት ለዚያውም ይህንንም ለማግኘት የታደለ ካለ «ዘመኖቻችን ሰባ፣ ቢበዛም ሰማንያ ነው» አለ። እንግዲህ እድሜ የሚሮጠው ከዚያ ለመድረስ ነው። ሩጫው እዚያም ሳይደርስ ሊያቋርጥ ይችላል። ምንም ይሁን ምንም ከእድሜው ጋር ያልሮጠና የሩጫውን ዓይነት መወሰን ያልቻለ ከሀዘን እንጉርጉሮና ከሀዘን መግለጫ በዘለለ ተስፋ የሚሆነው ነገር አለው ለማለት ያስቸግራል። ተስፋ በሌለው ኑረት መኖር ደግሞ አስፈሪ ነገር ነው።
ወንጌላችን ግን ተስፋችን ከሀዘን እንጉርጉሮ በዘለለ እድሜ በሞት አብቅቶ እንደአዲስ የመብቀል ማንነት ስለመሆኑና ተስፋቸው ለሞተ ወይም ተስፋ ማድረግን ከአእምሮአቸው ለፋቁ እንዲህ ይላል።
«ነገር ግን ሰው፣ ሙታን እንዴት ይነሣሉ? በምንስ ዓይነት አካል ይመጣሉ? የሚል ይኖር ይሆናል። አንተ ሞኝ፥ አንተ የምትዘራው ካልሞተ ሕያው አይሆንም፤ የምትዘራውም፥ ስንዴ ቢሆን ከሌላም ዓይነት የአንዱ ቢሆን፥ ቅንጣት ብቻ ነው እንጂ የምትዘራው የሚሆነውን አካል አይደለም» ፩ኛ ቆሮ ፲፭፣፴፭፣፴፯
ሰው ከሰባ ወይም ከሰማንያ ዘመኑ ወይም ከዚያ በፊት በሚያበቃው የእድሜው ሩጫ ጋር አብሮ መሮጥ ያለበት በእድሜው ፍጻሜ በሞት ተዘርቶ ስለሚበቅልበት ማንነት እንጂ የሕይወት መጨረሻ ተደርጎ በሚነበበው የሕይወት ታሪክ ወይም እንጉርጉሮ የሚያበቃ ማንነት እንዳለው መሆን የለበትም።
እድሜው ሲሮጥ መሮጥ ያለበት በሁለት ዐበይት ነጥቦች ላይ ተመስርቶ ነው።
1/ የመጀመሪያው እርከን በዚህ ምድር የተሰጠውን የቀዳማይ አዳማዊ ኑረትን ለሥጋው ለማሟላት፣
2/ በሁለተኛው እርከን ደግሞ በዚህ ምድር የተሰጠውን የካልአይ አዳማዊ ጸጋን ለነፍሱ ለማሟላት መሆን ይገባዋል።
ሚዛናዊ ማንነት ይኖር ዘንድ ይጠበቅበታል።
«ሊሰራ የማይወድ አይብላ» እንዳለው ጳውሎስ፣ ሥራን የምንሰራው ለመብላት ነው። ያ ማለት ግን የምንኖረው እየበላን ለመሞት ብቻ ነው ማለት አይደለም። ከእድሜ ጋር አብረን ሮጠን እድሜ ወስዶ ከሚያስረክበን ሞት በኋላ የምንቀበለው የሩጫችን ሽልማት ለመቀበልም ጭምር መሆን ይገባዋል። የዚህ ዓለም ሰዎች ሮጠው የሚያገኙት የሽልማት አክሊል ከሞት በኋላ ምንም አይጠቅምም። ሰው በእድሜው እኩል ሮጦ በተስፋ የሚጠብቀው ከሞት በኋላ ያለው አክሊል ግን ዘላለማዊ ነው።
«የሚታገልም ሁሉ በነገር ሁሉ ሰውነቱን ይገዛል፤ እነዚያም የሚጠፋውን አክሊል ሊያገኙ ነው፥ እኛ ግን የማይጠፋውን» ፩ኛ ቆሮ ፱፣፳፭ እንዳለ ሐዋርያው ልንጠብቀው የሚገባው የማይጠፋውን አክሊል ነው።
ሰው የዚህ ዓለሙን ሩጫ ተወዳድሮ የሽልማት አክሊል ማግኘት አልቻለም ማለት በዚህ ምድር መኖር አበቃለት ማለት አይደለም። ሌላ እድልና ሌላ ዝግጅት ይኖረዋል። ነገር ግን ሰው በእድሜው እኩል ዛሬ ሮጦ ከሞት በኋላ ለሚሰጠው ለዘላለማዊ አክሊል አልበቃም ማለት ለሌላ የሩጫ እድል የሌለውና ለሽንፈትም የሚሰጥ የሁለተኛው ሞት አክሊል የተዘጋጀ ሆኗል ማለት ነው።
ሐዋርያው ጳውሎስ ግን እዚህ ምድር ሳለ ከሮጠው እድሜ ጋር የሮጠውን የሩጫ ተስፋ እንዲህ ብሎታል።
«መልካሙን ገድል ተጋድዬአለሁ፥ ሩጫውን ጨርሼአለሁ፥ ሃይማኖትን ጠብቄአለሁ፣ ወደ ፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል፥ ይህንም ጻድቅ ፈራጅ የሆነው ጌታ ያን ቀን ለእኔ ያስረክባል፥ ደግሞም መገለጡን ለሚወዱት ሁሉ እንጂ ለእኔ ብቻ አይደለም» ፪ኛ ጢሞ ፬፣፰-፱
እንግዲህ ቆም ብለን ልናስተውል የሚገባን ነገር አለ። እድሜአችን ይሮጣል፣ እኛም እንሮጣለን። ግን የሩጫችን ፍጥነት፣ ዓይነትና ይዘት እድሜአችን ሲያበቃ ስለእኛ ውሳኔ ይሰጣል። ሌላ ማንም አይደለም። ሐዋርያው ጳውሎስ በዚህ ዓለም ሳለ የሮጠው ሩጫ የሚጠብቀውን አክሊል ወስኖታል። ይዘጋጅልኛል ወይም እንደሚዘጋጅልኝ ተስፋ አደርጋለሁ አላለም። «ተዘጋጅቶልኛል» ነው ያለው። ያንን እንዲል ያስቻለው የሮጠው የሩጫ ፍጥነት፣ዓይነትና ይዘት ነው። ከብዙዎች ጋር ተጋድሏል፣ ከብዙዎችም ጋር ሮጦ ጨርሷል፣ ሃይማኖቱን ጠብቋል፣ ስለዚህ የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶለታል።
ኢትዮጵያዊው ኃይሌ ገ/ ሥላሴ ሳንባው አብጦ መተንፈስ እስኪቸግረው ድረስ ተጋድሎ፣ ሯጮቹን ሁሉ አልፎ፣ የሩጫውን ሕግ ጠብቆ ቀዳሚ ከሆነ የሩጫውን አክሊል እንደሚያገኝ ገና ሳያሸንፍ ያውቃል። አክሊሉ የተዘጋጀው እንደዚያ ላሉት ነውና።
ሰማያዊው አክሊልም በእድሜአቸው ሁሉ ሰማያዊውን ሩጫ ለሮጡ የተዘጋጀ ነው። ምንም እንኳን ሩጫው በእድሜአችን ርዝመት የተነሳ ረጅም ሊሆን ቢችልና የሩጫው ዓይነትና መጠን ሰፊ ቢሆን፣ መውደቅ መነሳቱ ቢበዛ፣ ተስፋ መቁረጡ፣ ሃዘንና መከራው ቢከብድ እንኳን ተስፋውን በተስፋ ጠብቆ ከሩጫው ሜዳ ሳይወጣ እስከመጨረሻው የሮጠ አክሊሉን ይቀበላል። በዚህ የሩጫ መጨረሻ ላይ ቀድሞም ይሁን ዘግይቶ፣ እየወደቀ እየተነሳም ይሁን ጸንቶ የገባ ሁሉም አክሊሉን ያገኛል። ተፈላጊው ነገር መሮጥና ሩጫውን አቋርጦ አለመውጣት ወይም ወድቆ አለመቅረት ብቻ ነው።
እናስ፣ ምን እናድርግ?
የባከነ እድሜ ካለንም እግዚአብሔር ዛሬም እጃችንን ይዞ እንድንሮጥለት ይሻልና እንነሳ! በኃጢአትና በዐመጽ ከሩጫው የወጣን ወይም ነገር ዓለሙ ሁሉ የጠፋብን ካለን የማይጠላንና የማይጸየፈን አምላክ ዛሬም ቢሆን እንሰከነ ጉድፋችንንና በደላችን ይፈልገናል። ነገ የምንለው የኛ ቀን የለም።እድሜያችን የሚሮጠው ለሞት ሊያስረክበን ነው። ሌላ ሥራ የለውም።
በሚሮጠው እድሜአችን ሸክማችንን ይዘን ወደሚያግዘን እንሩጥ። የተባልነው ያንን ነውና!
«እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፥ ወደ እኔ ኑ፥ እኔም አሳርፋችኋለሁ» ማቴ ፲፩፣፳፰
ዘመናችን ሰባ፣ ቢበዛም ሰማንያ ነው። ያውም እዚያ የሚደርሱት የታደሉ ናቸው። ቁም ነገሩ ሰማንያ ዘመን መድረስ ወይም ከዚያ ያነሰ መሆኑ ሳይሆን እድሜአችን የሚሮጠው ወደሞት ነውና እኛም አብረን እንሩጥ። ንስሐ እንግባ! ሩጫችንም ወደ ጽድቅ አክሊል ይሁን!! እንደሰው ቃሉን የማይለውጥ ሰማያዊ አባት ላዘጋጀልን የጽድቅ አክሊል የበቃንለት እንሆን ዘንድ በነገሮች ሁሉ ያግዘናል! ለዚሁም ይርዳን፣አሜን!!