Thursday, April 19, 2012

ማህበረ ቅዱሳንና ሰለፊያ!! ግልባጩ ማነው?

                                                                                              source:awdemihret.blogspot.com
የማህበረ ቅዱሳን ሰለባ የሆኑ ብዙ የቤተክርስቲያን አባቶችና ልጆች ማቅን በአሸባሪነት ከፈረጁት ዓመታት የተቆጠሩ ቢሆንም፣ ማቅ ግን እንዲህ የሚሉኝ ለቤተ ክርስቲያን ጥብቅና ስለቆምኩ ነው በሚል ራሱን ሲከላከል ቆይቷል። ማህበሩ አሸባሪ የመሆኑ ጉዳይም በአንዳንዶች ዘንድ እንደ ስድበ ሲቆጠር መቆየቱ ይታወሳል። ለማኅበሩ ይህ ስም የተሰጠው በከንቱ አልነበረም። ስራው በአክራሪ ሙስሊሞች ከሚካሄደው የበለጠ እንጂ ያላነሰ ሆኖ ስለተገኘ ነበር ይህ የግብር ስም የወጣለት።

 ዕድሜ የሰጠው ሰው ብዙ ያያልና ይኸው የማህበሩ የግብር ስም ከትናንት በስቲያ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በኤፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር በክቡር አቶ መለስ ዜናዊ ጸድቋል። በማኅበሩ ሲገፉና ሲነቀፉ ለኖሩ የቤተ ክርስቲያን ልጆች ይህ እንደ አንድ ትልቅ ድል የሚቆጠር ነው። እንኳንም በትክክል የወጣለት የግብር ስም በማኅበሩ ዘንድ እንደ ስድብ ከመቆጠር አልፎ ትክክለኛ የማህበረ ቅዱሳንን ማንነት የሚገልጥ ስም ሆኖ ተነገረ! ይህን የተናገሩት ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትራችን መሆናቸው ትልቅ ግምት የሚሰጠው ብቻ ሳይሆን ማኅበረ ቅዱሳን ቤተክርስቲያንን ከማሸበር አልፎ አገርንም ለማተራመስ ትልቅ አላማ እንዳለው በመንግስት በኩል የተደረሰበት መሆኑን ያመለክታል።   

በአሁኑ ጊዜ ማኅበረ ቅዱሳን ማነው? ምንስ ነው የሚሰራው? አላማው ምንድነው ነው? ለሚሉት ጥያቄዎች ምላሽ የሚፈልገው የህብረተሰብ ቁጥር እየበዛ ይገኛል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ  ሰለፊያን አስመለክተው ሲናገሩ ሰለፊያ የማኅበረ ቅዱሳን ግልባጭ መሆኑን በግልጽ ቋንቋ እንዲህ ሲሉ ነግረውናል። “አንዳንድ የሰለፊ እምነት ተከታዮች አንዳንድ የማኅበረ ቅዱሳን አባላት የሚያራምዱትን ግልባጭ ሲያራምዱ ይታያሉ።” ማኅበረ ቅዱሳን ለክፋት መምህር እንጂ ደቀመዝሙር እንደማይሆን የተረዱት ጠቅላይ ሚኒስትር ማኅበረ ቅዱሳን ስልቶቹንና አካሄዱን ለሰለፊያ ማውረሱን በማያሻማ መንገድ ገልጸዋል፡፡
መቼም ማቅ የሚሰራውን ስራ አስተውሎ ያየ ሰው በማቅና በሰለፊያ(ወሀቢያ) መካካል ያለውን የመንፈስ አንድነት በቀላሉ ይረዳል። ለማስረጃ ያህል፡-

ሰሰለፊያ(ወሀቢያ) ሃሳቡን ለማስፈጸም እስከ መጨረሻው ጥግ ድረስ ሄዶ ሰዎችን ሊገድል ይችላል። ማቅም ከአባቱ ከዘርኣ ያዕቆብ ተምሮ በመንፈሳዊነትና በሀይማኖት ፍቅር ስም ሰዎችን ማሰቃየት መደብደብና መግረፍ ተገቢ ነው ብሎ ያምናል። እያደረገ ያለውም ይሔንን ነው። ከመቀሌ እስከ ቦረና ከሐረር አስከ ጋምቤላ ከጎንደር እስከ ሐዋሳ እንዲሁም በክብረመንግስት፣ በሻኪሶ፣ በአለታወንዶ፣ በአላባ፣ በድሬዳዋ፣ በደሴ፣ በባኮ እና በአዲስ አበባ የፈጸማቸው ድርጊቶች ለዚህ ትክክለኛ ምሳሌ ናቸው፡፡
  
2.    ሰለፊያ ትምህርቱን ለማስተላለፍ የሚጠቀምበት መንገድ የሃይማኖቱን በጎ ጎን ማሳየት አይደለም፤ የእነርሱ የሀይማኖት ማስፋፋያ መንገድ አሉታዊ ነው። ማቅም ስለቤተክርስቲያን ትምህርቶች መጽሀፍ ቅዱስን ተመርኩዞ የሚያስተምረው መሰረታዊ ነገር የለውም። የማቅ ዶግማ “መናፍቃን ተሀድሶ” የሚሉትን የስድብ ስሞች እያነሳ የቤተክርስቲያንን ልጆች ማሳደድ ብቻ ነው። በየቀኑም እንዲህ አደረጉ ይህን ፈጸሙ እያለ ሽብር በመንዛት ለኦርቶዶክሳውያን “እኔ ባልኖር ኖሮ መንፈስ ቅዱስማ ቤተ ክርስቲያንን መጠበቅ አቁሟል፤ “የጊዜው መንፈስ ቅዱስ” እኔ ነኝ፤ ትክክለኛው የቤተ ክርስቲያን ጠባቂ” በማለት በመንፈስ ቅዱስ ቦታ ራሱን አስቀምጦ እኔን ብቻ ስሙ እያለ ምእመኑ በእምነት ሳይሆን በስጋት እንዲመላለስ እያደረገ ይገኛል።
3.    ሰለፊያ የአጭር ጊዜ እቅዱ መጅሊሱን መቆጣጠር ሲሆን፣ የረጅም ጊዜ እቅዱ ደግሞ የመንግስትን ሥልጣን መያዝ ነው። ማቅ ልክ እንደ ወሀቢያ የአጭር ጊዜ እቅዱ ቤተክህነትን መቆጣጠር ሲሆን የረዥም ጊዜ እቅዱ ደግሞ የመንግስትን ስልጣን መያዝ ነው። ቤተክህነትን ለመቆጣጠር በሙሉ ሀይሉ እየሰራ ይገኛል። ጳጳሳትን በተለያዩ ስጋዊ  ጥቅሞች በመደለልና በማሳሳት፣ አልሆን ሲለው ደግሞ በነውራቸው በማስፈራራት የማህበሩ ፍላጎት አስፈጻሚ ለማድረግ እየተጋ ይገኛል። እስካሁንም በእግዚአብሔር እርዳታ የሚፈልገውን ነገር መስፈጸም አልቻለም እንጂ በተለይ በሲኖዶስ ስብሰባዎች ሁሉ ማቅ አጀንዳ በአንዳንድ የሲኖዶስ አባላት በኩል አስቅርቦ የሚፈልገውን ውሳኔ ለማስወሰን አመራሮቹ እንቅልፍ አጥተው እንደሚያድሩ ቤተ ክህነቱን በቅርብ የምናውቅ ሰዎች የምናስተውለው እውነት ነው። የመንግስትን ስልጣን በተመለከተ ያላቸው ሀሳብ ምን እንደሆነ እንኳን ማህበሩን ቀርበን አይደለም በሩቅም አይተነው የምንረዳው ሀቅ ነው። በተለያየ ጊዜ የግል ጋዜጣን ፈንድ አድርጎ ከማቋቋም ጀምሮ ክፍተት ባገኘ ቁጥር ጭንቅላቱን ለማስገባት የሚያደርገውን ጥረት ለተመለከተ ማህበሩ ፖለቲካዊ እንጂ መንፈሳዊ አቋም እንደሌለው በቀላሉ ሊረዳ ይችላል።
4.    ሰለፊያ ቀድሞ በመጮህ የሙስሊሙን ህብረተሰብ አመለካከት ለመሳብ በአህባሽ ላይ የተቀነባበረ ዘመቻ እንዳደረገ ሁሉ ማቅም እውነተኛ የቤተክርስቲያን ልጆችን ያልሆኑትን ሆኑ ያላደረጉትን አደረጉ፣ ያልረገጡትን ወረሱ እያለ በሀሰት የስም ማጥፋት ዘመቻ በማድረግ የዋሁን ሕዝባችንን በማሳሳት ላይ ይገኛል።
5.    ሰለፊያ ፍላጎቱ እስካልተሳካ ድረስ በመስጊድ አካባቢ የፈለገው ነገር ቢፈጸም ግድ የለውም። ማቅም አላማው ይሳካ እንጂ ህዝቡ የእግዚአብሔርን ቃል ቢማር ባይማር ወጣቱ ወደ ቤተክርስቲያን ቢመለስ ባይመለስ ምንም ግድ የለውም። ወጣቱ እግዚአብሔርን አውቆ የእነርሱ እጅ ያን ቤተ ክርስቲያን መቆጣጠር ከሚተው ይልቅ እነርሱ ያን ቤተ ክርስቲያን ተቆጣጥረው ወጣቱ ወደ ጫት ቤት ቢገሰግስ ይመርጣሉ። ካለፈው አንድና ሁለት ዓመት ወዲህ በስብከተ ወንጌልና በመንፈሳዊ ዝማሬዎች ወጣቱን ትውልድ ወደ ቤተ ክርስቲያን እየመለሱ ያሉትን የቤተክርስቲያን ልጆች ስም በማጥፋት ከፍተኛ ገንዘብ መድቦ በከፈተው ዘመቻ እየተገኘ ያለው ውጤትም የሚያሳየው ያንን ነው። ብዙዎች ከቤተክርስቲያን እየሸሹ ነው። ማኅበሩ ለመቆጣጠር እጁን ባስገባባቸው አንዳንድ አድባራት ውስጥ የሚታየው ነገርም እጅግ አሳሳቢ ነው። በወጣቱ ትውልድ ደምቀው ይታዩ የነበሩ የሰርክ መርሀግብሮች የመቃብር ቤት እንደሚመስሉ ዘወትር የምናየው እውነት ነው።
በአጠቃለይ ማቅንና ሰለፊያን የማያመሳስላቸው ነገር ቢኖር እቅዳቸውን የሚያስፈጽሙበት ቀዳሚው ቦታ ብቻ ነው፡፡ ሰለፊያ መጅሊሱን ሲፈልግ ማቅ ደግሞ ሲኖዶሱን መቆጣጠር ይፈልጋል፡፡ ሁለቱም ይህን እቅዳቸውን ቢያሳኩ(አያሳኩም እንጂ) ቀጣዩ ኢላማቸው ስልጣን በመሖኑ እኔ እሻል እኔ እሻል የሚለው አስተሳሰባቸው ወደ ለየለት ጦርነት ሊያመራቸው ይችላል፡፡ ሁለት የአሸባሪ ቡድኖች በአንድ ከተማ ላይ መኖር እንደማይችሉ እኔ እበልጥ በሚል ስሜት አገሪቱን ከማጥፋታቸው በፊት አንድ ሊባሉ ይገባል፡፡