Thursday, April 5, 2012

ጌታ ኢየሱስ የመገበው ስንት ሰው ነው? 4ሺ ወይስ 5ሺ ሰዎችን?

የማቴዎስ ወንጌል
14፥21
ከሴቶችና ከልጆችም በቀር የበሉት አምስት ሺህ ወንዶች ያህሉ ነበር።
የማቴ ወንጌል 15፥38
የበሉትም ከሴቶችና ከልጆች በቀር አራት ሺህ ወንዶች ነበሩ።
በማርቆስ ወንጌል ላይም እንደዚህ የሚል ተጠቅሷል።

የማርቆስ ወንጌል
6፥44
እንጀራውንም የበሉት ወንዶቹ አምስት ሺህ ነበሩ።
8፥9
የበሉትም አራት ሺህ ያህል ነበሩ።
8፥19
አምስቱን እንጀራ ለአምስት ሺህ በቈረስሁ ጊዜ፥ ቍርስራሹ የሞላ ስንት መሶብ አነሣችሁ? እርሱም፦ አሥራ ሁለት አሉት።
8፥20
ሰባቱን እንጀራስ ለአራት ሺህ በቈረስሁ ጊዜ፥ ቍርስራሹ የሞላ ስንት ቅርጫት አነሣችሁ? እርሱም፦ ሰባት አሉት።
ታዲያ የተመገቡት ትክክለኛው የሰዎች ቁጥርና የተነሳው የቁርስራሽ ቁጥር ስንት ነው? ወንጌላውያኑስ ለምን ቁጥሮቹን አበላልጠው ዘገቡ? አልገባኝምና መልስ እሻለሁ
መልስ
(ከደጀብርሃን)
ጥቅሶቹን አበዛሃቸው እንጂ ጥያቄህ በማቴ 14፤21 እና በማቴ 15፣38 ላይ የተመገቡት ሰዎች ቁጥርና የተነሳው ቁርስራሽ መጠን የተለያየው ለምንድነው? የሚል ይመስለኛል።
ከዚህ አንጻር በአጭሩ ስመልስልህ አዎ፤ 4 ሺህ ሰዎችና 5 ሺህ ሰዎች መግቦ አንዴ 7 ቅርጫት፣ አንድ ጊዜ ደግሞ 12 ቅርጫት አትረፍርፏል። ይህንንም በአጭሩ ላብራራ።
1/ በማቴ 14፣20-21 ላይ የተመለከተው 5 ሺህ ሰዎችና 12 ቅርጫት ቁርስራሽን በተመለከተ፣
ነገሩን ለመረዳት እንድንችል ከማቴዎስ ምእራፍ 13 እንጀምር። ማቴዎስ 13 የምሳሌዎች ምዕራፍ ተብሎ በነገረ መለኰት ምሁራን ይጠራል። ምክንያቱም የዘሪው ምሳሌ ማቴ 13፣3 ፣ የሰናፍጭ ምሳሌ ማቴ 13፣31 የእንቁ ምሳሌ ማቴ 13፣44፤ የመረብ ምሳሌ ማቴ 13፣47 ፤ የተነገረበት ምዕራፍ ነው። እዚህ ላይ የምሳሌዎችን ምዕራፍ ማንሳት ያስፈለገበት ምክንያት ምሳሌዎችን ለመተንተን ሳይሆን ምሳሌዎቹ የተነገረበት ቦታና ሁኔታ በነገረ ጭብጥነት እንድንይዝ በማስፈለጉ ነው። በዚሁ መሰረት ይህ የምሳሌ ምዕራፍ ታሪክ በኢየሱስ የተነገረው ከቤቱ ወጥቶ በባህር ዳሩ አጠገብ መሆኑን ነው።
«በዚያን ቀን ኢየሱስ ከቤት ወጥቶ በባሕር አጠገብ ተቀመጠ፤እርሱም በታንኳ ገብቶ እስኪቀመጥ ድረስ ብዙ ሰዎች ወደ እርሱ ተሰበሰቡ፥ ሕዝቡም ሁሉ በወደቡ ቆመው ነበር» ማቴ 13፣1-2
ይህም ከቤቱ ሲል ከናዝሬት (ሉቃ 4፣16) ሲሆን የባህሩ ዳር ደግሞ ገሊላ (ማር 1፣16) መሆኑን ጥቅሶቹ ያረጋግጡልናል። ያም ማለት ከናዝሬት ወደ ገሊላ ሄዶ «የምሳሌዎቹን ታሪክ» ከባህሩ ዳር አስተማረ ማለት ነው። ከዚያስ በኋላ ወደየት ሄደ? የሚለውን ስንከተል ደግሞ ይህንን እናገኛለን። ማቴ 13፣53 ላይ ተቀምጦልናል።


«ኢየሱስም እነዚህም ምሳሌዎች ከጨረሰ በኋላ ከዚያ ሄደ፣ወደ ገዛ አገሩም መጥቶ እስኪገረሙ ድረስ በምኩራባቸው ያስተምራቸው ነበር፤ እንዲህም አሉ። ይህን ጥበብና ተአምራት ይህ ከወዴት አገኘው?»
ይህም ማለት ከገሊላ ወደ ናዝሬት ተመልሶ በምኩራባቸው ያስተምር እንደነበር ነው። ኢየሱስ ከናዝሬት ቀጥሎ የሄደበትን ቦታ ማቴዎስ 14፣13 እንዲህ ሲል ያስቀምጠዋል።
«ኢየሱስም በሰማ ጊዜ ከዚያ ብቻውን ወደ ምድረ በዳ በታንኳ ፈቀቅ አለ፤ ሕዝቡም ሰምተው ከከተማዎቹ በእግር ተከተሉት»
እዚህ ላይ ልናነሳ የሚገባን ጥያቄ ኢየሱስ ወደናዝሬት በመግባት በምኩራብ ያስተምር ከነበረ እንደገና በመመለስ የገሊላን ባህር ተሻግሮ ወደምድረ በዳው ፈቀቅ ያለው ለምንድነው? የሚል ይሆናል። ዋናው ምክንያት መጥምቁ ዮሐንስ በአራተኛው ክፍል ገዢ በሄሮድስ አንገቱ ስለተቆረጠና ይህንኑ ለኢየሱስ ስለነገሩት ነበር። (ማቴ 14፣12)
ከዚያም ከባህሩ ማዶ ካለው ምድረ በዳ ሲያስተምር ቆይቶ ስለመሸ ሐዋርያቱ ምንም ከማይገኝበት ከዚህ ምድረ በዳ ሕዝቡን የሚበላውን እንዲያገኝ ሲጠይቁት እናያለን።
ከዚያም መሄድ እንደሌለባቸውና ሐዋርያቱ በእጃቸው ያለውን እንዲያመጡለት አድርጎ ከባረከ በኋላ ከአምስቱ እንጀራ እና ከሁለቱ ዓሳ 5 ሺህ ሰው በልቶ 12 ቅርጫት ቁርስራሽ መነሳቱን ማቴ14፤21 ይነግረናል።
እንግዲህ ከዚህ የምንረዳው ነገረ ጭብጥ ከናዝሬት ወደገሊላ፣ እንደገና ወደናዝሬት ከዚያም የዮሐንስን ሞት እንደሰማ ወደገሊላ ሄዶ በታንኳ ከተሻገረ በኋላ ከምድረ በዳው ሲያስተምር አምሽቶ እንደመገበ እንረዳለን። ስለዚህ ስለ ማቴ 14፤21 የሚነሳ ግርታና ጥያቄ በዚህ መሰረት ምላሽ ያገኛል። አሁን ደግሞ ስለ 4 ሺህ ሰዎችና ስለ7 ቅርጫት ቁርስራሽ ጉዳይ እናምራ።
1/ ማቴ 15፣37-38
«ሁሉም በሉና ጠገቡ፥ የተረፈውንም ቁርስራሽ ሰባት ቅርጫት ሙሉ አነሡ።የበሉትም ከሴቶችና ከልጆች በቀር አራት ሺህ ወንዶች ነበሩ»
ይህንን ሃሳብ ለመረዳት ምዕራፍ 15 ን እንቃኝ። በዚህ ምዕራፍ ስለሕጋቸው መጠበቅና ሐዋርያት ስለመሻራቸው ኢየሱስን ፈሪሳውያን ሲጠይቁት እናያለን።
«በዚያን ጊዜ ጻፎችና ፈሪሳውያን ከኢየሩሳሌም ወደ ኢየሱስ ቀረቡና፣ደቀ መዛሙርትህ ስለ ምን የሽማግሎችን ወግ ይተላለፋሉ? እንጀራ ሲበሉ እጃቸውን አይታጠቡምና አሉት» ማቴ 15፣1-2
ስለሕጋቸው የቀረበውን ጥያቄ ከመለሰ በኋላ ወደ ጢሮስና ሲዶና ሄዶ ለከነዓናዊቷ ልጅ ፈውስን አድርጓል።
«ኢየሱስም ከዚያ ወጥቶ ወደ ጢሮስና ወደ ሲዶና አገር ሄደ» ቁ፣21
ከዚያም ወደገሊላ ባህር በመመለስ ወደተራራ ወጥቶ አንካሶችን፣ እውሮችን፣ ሽባዎችን፣ ዲዳዎችን ቁጥሩ ብዙ የሆነ ሕዝብ ሲፈውስ ሦስት ቀናት አብረውት ውለዋል።
«ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱን ጠርቶ። ሕዝቡ ከእኔ ጋር እስካሁን ሦስት ቀን ውለዋልና የሚበሉት ስለ ሌላቸው አዝንላቸዋለሁ፤ በመንገድም እንዳይዝሉ ጦማቸውን ላሰናብታቸው አልወድም አላቸው» ቁ፤33
ከዚያም ሐዋርያቱ የነበራቸውን 7 እንጀራና ጥቂት ትናንሽ ዓሳ ባርኰ ከሰጣጠው በኋላ 4ሺህ ሰው ተመግቦ ትራፊውም 7 ቅርጫት ሆነ። ይህ ቡራኬ ለተሰበሰቡና ፈውስን ሽተው ሶስት ቀናት አብረውት ለቆዩ ድውያን እንደሆነ እንረዳለን።
ማጠቃለያ፤
ከየምእራፎቹ ዐውድ የምንረዳው ነገር ድርጊቱ የተከናወነው በተለያየ ነባራዊ ሁኔታ፣ ወቅትና ቦታ ውስጥ ቢሆንም ብዙ ጊዜ የባርኰቱ ዓይነት መመሳሰልና የቁጥሮቹ አለመገጣጠም ግር እያሰኘ የሆነ ስህተት ያለ የሚመስለው ሰው ጥቂት አይደለም። ስለዚህ ይህን ነገር ለመግለጥ ሲባል ሰፊ ዝርዝር መስጠት አስፈልጓል።
ስለሆነም ለጠያቂውም ይሁን ይህን ሃሳብ ለመረዳት ለሚፈልጉ ሁሉ የተጠቀሱት ተአምራት ሁሉ ተደርገዋል። ግን በተለያየ ጊዜና ቦታ እንዲሁም ሁኔታ ውስጥ የተፈጸሙ የተለያዩ መሆናቸው እንጂ አንዱ ተአምር በተለያየ ቁጥር የተቀመጠ አይደለም።