የአቡኑ ገዳም
ተራራ ወጥቼ፣ ከአቡኑ ዘንድ ሄጀ መስቀል ለመሳለም
ክረምቱ በረታ፣ ምንም አልተቻለ፣ ያሰብኩት ሳይሞላ፣ ሳይሆንልኝ ቀረ
ዳመናው ዝናቡ፣ ጉምና ጭጋጉ፣ ይህ የዛሬ ክረምት መች ያነቃንቃል!
ደጁን አጨቀይቶት፣ ወንዙም ጐርፍ ሞልቶት፣ እጅጉን አስፈሪ፣ በጣም ያስጨንቃል
በታምር በፀሎት፣ ከተራራው አፋፍ፣ ከዳመናው በላይ የገደሙት ገዳም
ደካማው ጉልበቴ፣ እንደምን ይቻለው፣ ጭቃውን ሸርተቴ፣ የኖኁን ዝናም
ዛሬ፣ ነገ እያልኩ ሰማዩና ምድሩን ሳስስ ስመለከት፣ ስቃኝ አድማሱን
ዓይኖቼም ደከሙ፣ አለቀ ጉልበቴ፣ መቃብር ቁፋሮ፣ ሰርክ መማሱን!
ማለዳ-ማለዳ ደረትዋን ገልብጣ፣ ድምጿንም ከፍ አደርጋ የምትጮኸው ወፍ
እየቀሰቀሰች እንቅልፍ ነሳችኝ፣ ሽፍንፍን ብዬ፣ ተኝቼ በሰላም በደህና እንዳላርፍ!
ምድር-ዓለሙ ክዶኝ፣ ሁሉም ጥሎኝ ሄዷል፣ ጠያቂም የለኝም ከቶ ሚያጽናናኝ
ወፊቱስ የት ሄደች? ከጠፋች ቆይታለች፣ ድምጿንም እልሰማሁ፣ እንዳታዝናናኝ…
ደጋግሞ እየቆየ የሚነፍሰው ነፋስ ላለው መጥፎ ጠባይ፣ ኃይለኛ አዙሪት
የጐጆየን ክዳን በትኖ እያነሳ፣ ምን ዓይነት ተንኮል ነው፣ ምን ዓይነት እብሪት!
መቸ ይኸ ብቻ! ሰማዩን ተርትሮ አስደንጋጭ ብልጭታ መብረቅ ሲፈነጥቅ
አከታትሎ ይሏል የሰማይ ነጐድጓድ ቤቱን አንቀጥቅጦ ጆሮ እስኪሰነጥቅ
ተራራ አልወጣህ፣ ታቡን ዘንድ አልደረስኽ፣ መስቀል አልተሳለምክ ብሎ ነው መሰለኝ
ከዚያ ላይ ስወጣ ገደል ከምገባ፣ ወድቄ ከምሞት፣ ወይም አንሸራትቶኝ ከሚሰባብረኝ
ከዚሁ ከቤቴ ካልጋዬ ተኝቼ፣ በንፋስ፣ በመብረቅ ነጉዶ አንጐዳጉዶ እንዳሻው ያድርገኝ!
ገ/ኢ ጎርፉ