በአንድ ወቅት መጠሪያ ስሙ «ማሞ» የሚባል ሰው የፍተሻ ኬላ ላይ ጠባቂ ያስቆመውና
የይለፍ ወረቀት እንዲያሳይ ይጠይቀዋል። አቶ ማሞም በፎቶግራፍ የተደገፈ ማንነቱን ገላጭ መታወቂያ ከኪሱ መዘዝ ያደርግና ለኬላ ጠባቂው
ያሳያል። ኬላ ጠባቂውም በአካለ ሥጋ ከፊቱ የቆመውን አቶ ማሞንና የመታወቂያው ላይ የማሞን ፎቶ ቢያስተያይ ጨርሶውኑ የሚመሳሰሉ
አልሆን ይለዋል።
ኬላ ጠባቂ
ቢቸግረው ጊዜ ስማ ሰውዬው ስምህ ማነው? ብሎ ይጠይቀዋል።
አቶ ማሞም « ማሞ» እባላለሁ በማለት መልስ ይሰጣል።
ኬላ ጠባቂውም
እንደገና- ይኼ መታወቂያ እኮ ማሞ የሚል ስም የለውም! ይለዋል።
አቶ ማሞም አዎ ልክ ነው። «ማሞ» የሚል ስም የለውም ይላል እያረጋገጠ።
አንተ ማሞ የምትባል ከሆነ ማሞነትህን የሚያረጋግጥ መታወቂያ ማሳየት ሲገባህ
ለምን ማሞ ያልሆነ መታወቂያ ታሳየኛለህ? ይላል ኬላ ጠባቂው በንዴት።
እውነተኛው ማሞም ስለማንነቱና እውነተኛ ስላልሆነው የማሞ መታወቂያ ማስረዳት
ጀመረ።
እኔን ለማወቅ የፈለጉ ኬላ ጠባቂዎች የምላቸውን እንዲሰሙኝ እኔ እስከነ ሕይወቴ ቆሜ ለማስረዳትና፣ መታወቂያ ማየት
ሲያምራቸው ደግሞ ይህንን የኔን ማንነት የማይገልጸውን የወንድሜን መታወቂያ ይዣለሁ ብሎ እብደት ቀመስ ማብራሪያውን አቀረበ።
ያኔም ኬላ ጠባቂው እንደእብድ ሳይሆን ሆን ብሎ እንደሚያምታታ ገብቶት፣
«ማሞ ሌላ መታወቂያው ሌላ» ብሎ ሲያበቃ ሰውዬው ማንነቱን የሚገልጽ መታወቂያ ባለመያዙና የራሱ ያልሆነ መታወቂያ አላግባብ ይዞ
በመገኘት ወንጀል እንዲጠየቅ ወደማረፊያ እንዲሄድ የመደረጉን ታሪካዊ ወግ ከዓመታት በፊት አዳምጠናል።
ይህንን ገላጭ ወግ እዚህ ላይ ያነሳነው ያለምክንያት አይደለም። በትናንትናው
ምሽት የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ስለ «ኢስላማዊው ሰለፊና ስለኦርቶዶክሱ ማቅ ሰለፊ» ማንነት የተነተኑበት የመንግሥታቸውን አቋም ተንተርሶ «አንድ አድርገን» ብሎግ ምሬቱን
ሲገልጽ አግኝተነዋል።
በጥምቀት በዓል አከባበር ላይ« አንድ ጌታ፣ አንድ ሃይማኖት፣ አንዲት ጥምቀት»
የሚሉ ካናቴራ ለባሾች ቢኖሩ የወንጌሉን ቃል ከመፈጸም በስተቀር ከአክራሪነት ጋር የሚያገናኘው የለም ብቻ ሳይሆን ሃይማኖትን ማጥበቅ
አክራሪ አያሰኝም ሲል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የእውቀት ጉድለት እንዳለባቸው ለማሳየት ሞክሯል።
እርግጥ ነው፤ ወንጌል በኤፌሶን ፬፣፭ ላይ «አንድ ጌታ፣ አንድ ሃይማኖት፣
አንዲት ጥምቀት» ይላል። ያ ማለት ግን ኦርቶዶክስ ወይም ካቶሊክ ወይም ፕሮቴስታንት ማለት እንዳልሆነ ብዙ ምርምር አይጠይቀንም።
ሁሉም እኔ፣ እኔ ከሚሉ በስተቀር ራሳቸውን ጥለው ከዚህ የወንጌል ቃል ውጪ ነኝ ይሉ ዘንድም አንጠበቅም። በአንድ በኩል አንድ ሃይማኖት ብቻ ኢትዮጵያ ውስጥ አለመኖሩ ከታወቀ፣ በሌላ መልኩም ያሉት ሁሉ ለየራሳቸው እኔ ነኝ ትክክለኛው እንደሚሉ ከተረዳን በነዚያ መካከል አዋጅ ነጋሪ ጨርቅ በሰውነት ሰሌዳ ላይ ሰቅሎ መገኘት ሌላውን አንተ አይደለህም እንደማለት ካልተቆጠረ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ውስጥ ይህች «አንዲት ሃይማኖት» የምትለየዋን መምረጥ ያስፈለገበትን ምክንያት ሊያስረዱ ይገባቸዋል ። ወንጌሉም አንዱንም
ሃይማኖት ለይቶ በስም የጠራበት ሁኔታ ስለሌለ ይህ ቃል እኔን ብቻ ነው ሊመለከተው የሚችለው በማለት ማንም እንዳይጠቀምበት ለመከልከል
የሚያስችል የባለቤትነት ማረጋገጫ ለማቅረብ ይገደዳሉ ማለት ነው። ሕገ መንግሥቱ ያንን አይልምና በሌሎች መካከል ያንን መግለጽ ወንጀል ነው ቢባል ስህተት የሚሆነው በምን ሂሳብ ነው?
ከዚያም ባሻገር ወንጌሉ የተናገረውን ቃል ሳይጠብቁ ራሳቸው የተለያየ ስም
ለራሳቸው ሰጥተው ሲያበቁ አንዲት ሃይማኖት ያልያዙ ሆነው ሳለ በምንም መልኩ የወንጌሉ ቃል የሚገልጸው እኔን ነው ሊሉ አይችሉም።
በመግቢያችን ላይ ያቀረብነው አቶ ማሞም ማንነቱን ገላጭ መታወቂያ
ማቅረብ ሳይችል ሌላ መሸፈኛ ለማሳየት መሞከሩ እሱነቱን ሊከልለው እንዳልቻለው ሁሉ ወንጌል «አንዲት ጥምቀት፤ አንድ ሃይማኖት»
ማለቱ እኔን ያሳያል ቢሉ ማንነታቸውን እንደመግለጽ ሊቆጠር አይችልም። ወንጌል የሚኖሩት ሕይወት እንጂ የሚደሰኩሩት የርእዮት መጽሐፍ አይደለም።
አቶ መለስም በዚህ ሀገር ላይ «አንድ ሃይማኖት» ብሎ በለበሰው ካኔተራ ላይ
መግለጫውን ይዞ በብዙ ሃይማኖተኞች መካከል አደባባይ ላይ መገኘት ከሌላው ሰው መብት ጋር በመጋጨት ሕገመንግሥቱን መጣስ ነው! ቢሉ
እንዴት ሊያናድድ ይችላል? አቶ መለስ በፖለቲካ አቋማቸው ይጠሉ ወይም ይደገፉ ይሆናል። ያንን ተጠግቶ ግን የሚናገሩት እውነታ ካለ ግን ዓይናችንን ጨፍነን ማውገዙ ገደል ከሚከተን በቀር የትም አያደርሰንም። ይልቅስ ዓይናችንን ገልጠን ለእኛ ትክክል መስሎ የሚታየን፣ በሌሎች ዘንድ ግን እንደስህተት የተቆጠረውን ነገር እንመርምር!
በምድሪቱ ላይ ያለውን እውነታ ክዶ በመሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ውስጥ ለመደበቅ መሞከር
ክርስትናን እንደመጠበቅ ሳይሆን ያልያዙትን መታወቂያ ለማሳየት እንደሞከረው «ማሞ» ዋጋ የሚያስከፍል መጨረሻ እንዳለው አለመረዳት
ይሆናል።
እየተባለ ያለው ወንጌል «አንድ ጌታ፣ አንድ ሃይማኖት፣ አንዲት ጥምቀት»
ስለሚልና እኔም ይህንኑ የማምን ስለሆነ ወንጌል የተናገረው ስለእኔ ነው ማለት አመክንዮአዊ አይደለም።
«ወንጌል የክርስቲያኖች መመሪያ ነው፣ ስለዚህ ክርስቲያኖች ሁሉ በወንጌል ይመራሉ» ብንባል ሎጂካዊ አይደለም
የሚል መልስ ልንሰጥ የግድ ነው። ምክንያቱም ሁሉም ክርስቲያኖች መመሪያውን አይጠብቁምና ነው። ሁሉም ክርስቲያኖችም ወንጌልን እንደመመሪያ
ስለጠቀሱት የወንጌል ሰዎች ሆነዋልም ሊባል አይቻልም። ህግ በዳኞች እየተጠቀሰ መገኘቱ ብቻውን ዳኞችን ባላቸው የሕግ እውቀት ከተጠያቂነት
ነጻ አያደርጋቸውም። ልዩነቱ ማወቁ ሳይሆን የሚያውቁትን ሆኖ መኖር ብቻ ነው ቁምነገሩ።
በሌላ መልኩም ኢስላሙ« ላ ኢላሃ ኢለላህ» አላህ አንድ ነው! አይወርድም
አይወልድም! ብሎ አዋጅ ቀመስ ካናቴራ ለብሶ አደባባይ ቢወጣ ይህንን ያልተቀበላችሁ ወየውላችሁ ከማለት የተለየ ሊሆን አይችልም። የማይስማሙ ሁለት ጽንፈኞች አደባባይ ላይ የሃሳብ ቡጢ ብቻ ሳይሆን ግብግብ ቀመስ
ነገርን ላለማመንጨታቸው ዋስትና የለም።የድርጊታቸው መነሻና ምንን ለመግለጥ እንደፈለጉ የተነሱበት ዓላማ ግልጽ ስለሚሆን መልእክታቸው
ቀድሞ ያመነና የተከተላቸውን ለማሳወቅ ሳይሆን ይህን የኔን አባባል የማትቀበል ወየውልህ ለማለት ከመፈለግ የተነሳ ካልሆነ ስለምን
ይሆን ብሎ መጠየቅም አግባብነት አለው።
ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ብቻዋን የኢትዮጵያ ሃይማኖት ሆና ብትዘልቅ ኖሮ እሰየው!
እንዳለመታደል ሆኖ ይሁን ወይም እኛ ለእግዚአብሔር እንዳልተመቸነው ምክንያቱን ባናውቅም እንደምንመኘው አልሆነም። ይህ ባልሆነበት
ሁኔታ ወንጌሉን እኛ እንኖርበታለን ወይስ ወንጌሉን ለማይኖሩበት እንዲኖሩበት እንጭንባቸዋለን? ሀገሪቱ ውስጥ አንድ ሃይማኖት አለመኖሩ
ከታወቀ ወንጌሉ የሚለውን «አንዲት ሃይማኖት» ማን ላይ ነው ለማኖር የሚፈለገው?
ነገሩ ዞሮ ዞሮ አጸፋዊ መልስ ነው እንጂ ያለጦርነት ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ
እምነት መመስረት አይቻልም። እስልምናዊው ሰለፊ ሲያከር፣ «ኦርቶዶክሳዊው ሰለፊ ማቅ» ደግሞ በማክረር ምላሽ ለመስጠት የተደረገ
ካልሆነ በስተቀር ሌላ ምክንያት የለውም።
2/ወንጌል በድንበር ሳትወሰን እስከ ዓለም ዳርቻ!
ወንጌል ሁሉን መርምሩ ትላለች። ሁሉን መርምሮ ጥያቄ ለሚያቀርብ ደግሞ መልስ
ትሰጣለች። መልስ የሌላቸው «ሃይማኖተኞች» ደግሞ ከምንለው ውጪ መመርመር ወይም መጠየቅ አትችልም! ቢሉስ ምን ይከተላል?
አንዳንዶች መመርመርና መጠየቅን በጥቂት ክልል የተወሰነና የተከለለ አድርገው
በማሰብ ድንበር እንደማፍረስ ይቆጥሩታል። ወንጌል ግን በድንበር የተወሰነች ሳትሆን በምድርም ከዚያም በላይ በሰማይ የሕይወት ርስት
ናት። [ luke 18:22]
በዚህ ምድር የትም ሥፍራ ቀድሞ ባለበት ድንበር የቆየ ወይም ሳይፈርስ የቆመ
ነገር የለም። ሕግም እንኳን ብዙ ለውጥ ደርሶበታል። የኦሪቱ በአዲሱ የኪዳን ሕግ ፍጻሜ አግኝቷል። ሰዎች ግን ራሳቸው በከለሉት
የኅሊና ድንበር ውስጥ ሁሉም ሰው በተሰጠው ካሬ ሜትር ውስጥ እንዲንቀሳቀስ ብቻ ይፈልጋሉ። ለምን? ብሎ ከጠየቀ አንተ ድንበር አፍራሽ
ከማለትም በዘለለ «ጸረ አንዲት ሃይማኖት»ብለው ሊያሸብሩት ይችላሉ። ይህም ሲሆን በተግባር አይተነዋል። የአንዲት ሃይማኖትና ጥምቀት
መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቃልን ገልብጠው ላላወቁ ለማስተማር ሳይሆን መንፈሱን የሚጠቀሙበት እኛ ብቻ ነን ለዚያ ስም
የተሰጠነው በማለት ለማስተጋባት ሲፈልጉ እናያቸዋለን።
በጥቅሉ «ከመምህሩ ደቀ መዝሙሩ» እንዲሉ ሲኖዶሱ እያለ ማቅ የሌለው ሥልጣንና
መብት ለራሱ ሰጥቶ ፍትሕ መንፈሳዊ ሳያጣቅስ እየፈረጀ ያሻበረው ሰው ቁጥሩ ቀላል እንዳልሆነ የሚካድ አይደለም። ስለሆነም ክቡር
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኢስላማዊ ሰለፊ ጋር ማኅበረ ቅዱሳንን በማነጻጻር መግለጣቸው ከመጠኑና ከስፋቱ አንጻር ካልሆነ በስተቀር በተሰለፉበት
ዐውድ ባህሪያቸው ተመሳሳይነት ስላለው ተገቢነቱን ልንክድ አይገባም። በካናቴራው ላይ ያቀረበው የጽሁፍ ባጅ ሕገ መንግሥቱ ላይ የሰፈረውን
የብዙኀን እምነት ሀገር፤ ሰነድን አሸብሯል ቢሉም ትክክል ነው። ወንጌል ቃሉን ለሚቀበሉ እንጂ ቃሉን ለማያምኑ አዋጅ! አዋጅ! የሚባልበት
ማስፈራሪያ ወይም ማስጮኺያ መሳሪያ አይደለም። በሌላ መልኩም «ማቅ» ተቋቁሜበታለሁ የሚለው ዲስኩር እንደሚያስረዳው የቤተክርስቲያኒቱን ክፍተት ለመሙላት ነው ካለ አሁን ያለው የቤተክርስቲያኒቱ ክፍተት «አንዲት ሃይማኖት» የሚልን ባጅ አልብሶ ማሰማራት ነው ወይ ብለንም ልንጠይቅ አግባብነት አለው። ችግር ባልሆነ ጉዳይ ላይ ችግር ለመፍጠር መሞከር ጤናማነት አይደለም።
ማቅ ክርስቲያናዊ ሰለፊ ሆኖ ሳለ «ማሞ ሌላ መታወቂያው ሌላ እንዲሉ» ወንጌልን
መጥቀሱ ግብሩን አይከድንለትም። እራሱን ማረም የማይችል እንደሆነ ብናውቅም ምንልባት ቢታደል ራሱን በንስሐ አርሞ ወደ እውነታው
ያለማሸበር ሕይወት ተመልሶ እንዲኖር እንመኝልታለን። ከዚያ ባሻገር ከዚህ ቀደም ስንል እንደቆየነው ሁሉ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር
ከማሸበር ማማው ላይ እንደሚሰበርና በነበር እንደሚነገርለት ቅንጣት አንጠራጠርም። በአንድ ወቅትም ቴዎዳስ ዘግብጽ በ400 ወታደሮች የትም አልደረሰም። በ40 ሺህ አባላትና በተረፈ ንዋይ መመካትም የትም አያደርስም። ይልቁንም ቁጥር እያጣቀሱና የክንድን ፍርጥምና እያሳዩ ተተክሎ እንደሚቆም ጽኑ ግንብ ራስን ከመቁጠር «የቆመ የሚመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ» እንዳለው ቃሉ ራስን ዝቅ አድርጎ ንስሐ መግባት ይበጃል። ያሰደዱትን፣ የገፉትን፣ የደበደቡትን፣ ከማኅበራዊ ኑሮው የገፈተሩትን እንባ የሚመለከት አምላክ ዋጋ መቀበያ ጊዜያቸው የደረሰ ይመስለናል።
ማቅ የሚያከትምለት ሰዎች ስለጠሉት አይደለም። በመሠረቱ ከእውነት ጋር ሊስማማ የማይችል
ተፈጥሮ ያለው ማኅበር ስለሆነ ብቻ ነው። «ማሞ ሌላ መታወቂያው ሌላ» ከመሆን ይልቅ ማንነትን ገላጭ መታወቂያ በመያዝ ከሽብሩ ኬላ
መውጣት የግድ ይሆናል። ያለ በለዚያ የተሰማው ሁሉ እውን ይሆናል። መጪውን የሲኖዶስ ጉባዔም ማወክና በአባላቱ በኩል «አንዲት ማኅበር» ያቺም ማቅ ናት የሚል አጀንዳ ሲያራገብ በተለመደው የማሞ መታወቂያው እናገኘዋለን።