Friday, April 27, 2012

አዲስ አበባ በሚገኙ አንዳንድ የ"ማኅበረ ቅዱሳን" ሱቆች ላይ የማሸግ እርምጃ ተወሰደ!

ሊያደርግ ያቀደውን የእግር ጉዞ ለሌላ ጊዜ አስተላለፈ
አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኙ የ"ማኅበረ ቅዱሳን" ሱቆች ላይ የማሸግ እርምጃ መወሰዱን የደረሱን መረጃዎች አመለከቱ፡፡ በተለይም በኡራኤልና በሜክሲኮ አካባቢ የሚገኙ የ"ማኅበረ ቅዱሳን" ሱቆች ላይ "ባልተፈቀደ የንግድ ሥራ ላይ ስለተሠማራ ሱቁ ታሽጓል" በሚል ማስታወቂያ የታሸጉት እነዚህ ሱቆች፣ "ማኅበረ ቅዱሳን" ከማንኛውም አካል የንግድ ሥራ ፈቃድ ሳይወስድ የሚሠራባቸው መደብሮች መሆናቸው ታውቋል፡፡
"ማኅበረ ቅዱሳን" በፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ እንዲሁም በቤተክርስቲያን ስም እና በራሱ ስም እያዛነቀ ሚናው ባልለየ እንቅስቃሴ ውስጥ እዚህም እዚያም የሚነከር በመሆኑ በሰሞኑ ከሕግ ጋር ለመፋጠጥ ተገዷል ተብሏል፡፡ ከንግድ ሥራ ጋር በተያያዘም ለመንግሥትም ሆነ ለቤተክርስቲያን ተገቢውን ገቢ ሳያስገባ ዝም ብሎ የሚዘርፍ ድርጅት እንደመሆኑ መጠን ሕጋዊ መሥመር እንዲይዝ ሲደረግ ጨርሶ ፈቃደኛ ሊሆን አለመቻሉ ተገልጿል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለም "ማኅበረ ቅዱሳን" ከ20ኛ የምሥረታ በዓሉ ጋር አያይዞ "ሐዊረ ሕይወት" በሚል ርዕስ ያዘጋጀው የእግር ጉዞ ለሌላ ጊዜ ያስተላለፈ ሲሆን፣ ጉዞውን ለማስተላለፍ ያበቃውን ሁኔታ በበዓላት ምክንያት ቢያሳብብም በቂ ተመዝጋቢ ባለማግኘቱ ሳይሆን አይቀርም የሚል ግምት አሳድሯል፡፡ ይሁን እንጂ "ማኅበሩ" በስውር ሲያራምደው የኖረው ፖለቲካዊ አጀንዳው የተጋለጠበት በመሆኑ በግንቦት 20 መቃረቢያ ላይ የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎቹ በራሱ ማንነት ላይ የበለጠ ትርጉም ስለሚሰጡ እጅና እግሩን ሰብስቦ መቀመጥ እንደሚሻለው ብዙዎች አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
"ማኅበረ ቅዱሳን" ከ20ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉ ጋር በተያያዘም ትልቅ የፕሮፖጋንዳ ትርፍ ለማግኘት ሲል በመላው ዓለም በሚገኙ ንዑሳን ማዕከላቱ አማካይነት ጉባዔዎችን፣ የእግር ጉዞዎችን፣ የመባዕ መሰብሰብና ልዩ ልዩ መርሐ ግብሮችን ለማካሄድ ቢያቅድም ሳያስበው ከገባበት ወጥመድ ለመውጣት የሚዳክርበት፣ በየአጥቢያው የሚገኙ የንግድ መደብሮቹን ንብረት ስለሚያሸሽበትና ራሱን በጥዋ ማኅበራት ከፋፍሎ የመደበቅ ስትራቴጂ ንድፍ ሥራ ውስጥ ተጠምዳል የሚሉ መረጃዎች ከየሥፍራው ብቅ ብቅ እያሉ ናቸው፡፡ 
source= dejeselaam-dejeselaam.blogspot.com