Thursday, April 26, 2012

የጎንደር ደብረ ኀይል ወደብረ ጥበባት በዓታ ለማርያም የአቋቋም ምስክር ትምህርት ቤት ግንባታ ውል ተፈረመ፡፡


(ከደጀ ብርሃን) ጅምሩ ጥሩ ነበር። የሰበሰባችሁትን የቤተክርስቲያን ገንዘብ  ከማስወረሳችሁ በፊት ወይም  ስትነግዱብን ኖራችሁ የሚሉትን ድምጾች ለማፈንና ይህንን የመሰለ ትሩፋት እየሰራን ነው ለማለት ያደረጋችሁት ይመስላል። ባካፋ ዝቃችሁ እጣንና ጧፍ ከመበተን ያለፈ ቋሚ ስራ ስትሰሩ አልነበራችሁም። ይሁን እንጂ ገንዘባችንን ከቀበራችሁበት ስላወጣችሁና ምንም ይሁን ምንም እንጥፍጣፊው ስለደረሰን አመስግነናል።

በእንዳለ ደምስስ
Gedamate 3ማኅበረ ቅዱሳን በሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት የሚገኘውን የደብረ ኀይል ወደብረ ጥበባት በዓታ ለማርያም የአቋቋም ምስክር ትምህርት ቤትን በ4.6 ሚሊዮን ብር ለመገንባት ሚያዚያ 12 ቀን 2004 ዓ.ም. የግንባታ ውል ስምምነት ከአስማማው አያሌው ሕንጻ ሥራ ተቋራጭ ጋር ተፈራረመ፡፡ በማኅበረ ቅዱሳን የማኅበራዊ ልማት ዋና ክፍል አስተባባሪነት የሚከናወነው ይኸው ፕሮጀክት ማኅበረ ቅዱሳንን በመወከል የማኅበሩ ዋና ጸሐፊ ዲ/ን ሙሉጌታ ኀ/ማርያምና የሕንፃ ሥራ ተቋራጩ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ አቶ አስማማው አያሌው አማካይነት የፊርማ መርሐ ግብሩ ተፈጽሟል፡፡
በማኅበረ ቅዱሳን ዋና ጽ/ቤት በተከናወነው የፊርማ መርሐ ግብር ላይ የማኅበሩ ዋና ጸሐፊ ዲ/ን ሙሉጌታ ኀ/ማርያም ባደረጉት ንግግር ‹‹ 4.6 ሚሊዮን ብር የሚፈጅ ፕሮጀክት ቀርጾ የአቋቋም ምስክር ትምህርት ቤት ለመገንባት ከዚህ በፊት አድርገነው አናውቅም፡፡ ይህ ትልቅ እድገት ነው፡፡ ምእመናንም ማኅበረ ቅዱሳንን ማመን የቻሉበት ነው፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ አውጥቶ ማኅበረ ቅዱሳን ይሥራው ለማለት መቻል ሙሉ ለሙሉ በማኅበሩ ላይ እምነት እንዳሳደሩ ነው የሚያሳየው፡፡ እኛም በታማኝነት ትኩረት ሰጥተን እንድንሠራ የሚያደርገን ነው፡፡ ጨረታውን ከብዙዎቹ የሕንጻ ሥራ ተቋራጮች ጋር ተወዳድሮ ያሸነፈው ድርጅት በማኅበሩ ውስጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረገና አብሮ የኖረ ነው፡፡ ሥራውንም በጥራትና ከተያዘለት ጊዜ ቀደም ብሎ በማጠናቀቅ ያስረክባል የሚል እምነት አለኝ፡፡ በማኅበረ ቅዱሳን በኩልም ሥራውን ለማፋጠን አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደርግ አረጋግጣለሁ›› በማለት ገልጸዋል፡፡
 የሕንፃ ሥራ ተቋራጩ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ አቶ አስማማው አያሌው ድርጅታቸውን በመወከል እንደተናገሩት ጨረታውን ስጋበዝ አሸንፋለሁ ብዬ አላሰብኩም፡፡ የገንዘቡ መጠን ከፍ ሲል ደግሞ የማኅበረ ቅዱሳን ጓዳውን ስለማውቀው ከየት አምጥቶ ነው ብዬ ስጋት ነበረኝ፡፡ ለዚህ ደረጃ በመብቃቱ ተደስቻለሁ፡፡ ጨረታውን ለማሸነፍ ካለኝ ጉጉት የተነሣ ማግኘት ከነበረብኝ ትርፍ 7 ፐርሰንት ቀንሼ ነው የተወዳደርኩት፡፡ ለማኅበረ ቅዱሳን ገንዘብ ከመስጠት ገንዘብ መውሰድ መጀመር የጥሩ እድገት ምልክት ነው፡፡ ፕሮጀክቱን ሰርቶ ለማስረከብ ከሚጠበቀው ጊዜ በፊት እንዲሁም ከሚጠበቀው ጥራት በላይ እንደባለቤት ሰርቼ አስረክባለሁ ብለዋል፡፡

ሕንፃ ተቋራጩ በ1998 ዓ.ም. እንደተቋቋመና የኮንዶሚኒየም ቤቶች ግንባታዎችን፣ የአንደኛ ደረጃ ት/ቤቶች ግንባታዎችን፣ ጤና ጣቢያዎችንና በአሁኑ ወቅት የጣና በለስ ስኳር ፕሮጀክትን በ6 ሚሊዮን ብር ውል በመገንባትና በማጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

በማኅበረ ቅዱሳን የማኅበራዊ ልማት ዋና ክፍል የቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሮ ዓለም ፀሐይ መሠረት ፕሮጀክቱን አስመልክቶ እንደገለጹት የአቋቋምGedamate 2 ምስክር ትምህርት ቤቱ ባለሁለት ፎቅ ሕንፃ ሲሆን በምስክር ትምህርት ቤቱ ውስጥ የሚገኝ ማንኛውም ተማሪ ድጋፍና ወርሃዊ ቀለብ እንዲያገኝ ማድረግ የማኅበራዊ ልማት ዋና ክፍሉ ዓላማ ነው፡፡ በተጨማሪም የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠና፣ የስብከተ ወንጌል፣ የሐይማኖት ትምህርትና የሥራ ፈጠራ ሥልጠና በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ የተማሪዎቹ ማደሪያ ቤት የምግብ ማብሰያ ቤት፣ መጸዳጃ ቤትና የገላ መታጠቢያ እንዲሁም ጉባኤ ቤት የሚኖረው ሲሆን ለፕሮጀክቱ የገንዘብ ወጪውን 3.5 ሚሊዮን ብር የሸፈኑት በደቡብ አፍሪካ ነዋሪ የሆኑ 3 የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ልጆችና በጎ አድራጊዎች ሲሆኑ ፤ በአሁኑ ወቅት 1.7 ሚሊዮን ብር ለማኅበራዊ ልማት ክፍል ገቢ አድርገዋል፡፡ ቀሪውን ደግሞ ወደፊት የሚሸፍኑት ይሆናል፡፡ ተጨማሪውን ወጪ ለመሸፈን ዋና ክፍሉ የራሱን እቅድ በመቀየስ በጎ አድራጊ ምእመናንን  በማስተባበርና እንዲሳተፉ በማድረግ በጋራ ለመሥራት ነው የምናስበው ብለዋል፡፡

የምስክር ት/ቤቱ በአሁኑ ጊዜ ከ70 እስከ 80 ተማሪዎችን ብቻ የሚያስተናግድ ሲሆን፣  የአቋቋም ምስክር ት/ቤቱ ሲጠናቀቅ እስከ 170 ተማሪዎችን መቀበል የሚችል ነው፡፡  ተማሪዎቹ በከፍተኛ ሁኔታ የማደሪያ ቤት ችግር ስለሚያጋጥማቸው በሁለት ዓመት መጨረስ የሚገባቸው ወረፋ በመጠበቅ አራት ዓመታት ይፈጅባቸዋል፡፡ የጎጆ ወረፋ በመጠበቅ ረጅም ጊዜ ይቃጠላል፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን ዓላማ ያደረገው ይህንን ችግር መቅረፍ ነው፡፡ ይህ ግንባታ ዛሬ ላሉት ተማሪዎች ብቻ ትኩረት ያደረገ ሳይሆን ወደፊት ማማር ለሚፈለጉ ሁሉ ደረጃውን የጠበቀ ጉባኤ ቤቶችን መገንባት ነው በማለት ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

የማኅበሩ መሐንዲስ የሆኑት ኢንጂነር ያሬድ ደመቀ ፕሮጀክቱን በሚመለከት እንደገለጹት የአቋቋም ምስክር ትምህርት ቤቱ ለተማሪዎቹ አገልግሎት የሚሰጡ ቁሳቁሶችን የሚያሟላ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ በየማደሪያ ክፍሎቹ ጠረጴዛና ወንበሮች ፤ ልብስ ማስቀመጫ ቁም ሳጥኖችና አልጋን ያካትታል፡፡ ግንባታው 1 ዓመት ከ6 ወራት እንደሚፈጅ፣ ከሕንፃ ተቋራጩ ጋር ከፊርማው በኋላ ባሉት ሰባት ቀናት ውስጥ የሳይት ርክክብ እንደሚካሄድና በ14 ቀናት ውስጥ ደግሞ ግንባታውን እንደሚጀምር በውሉ ላይ መካተቱን ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ እየሠሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

በፊርማ መርሐ ግብሩ ላይ ከተገኙ ወንድሞችና እኅቶች በተሰጡ አስተያየቶችም ዛሬ በማኅበረ ቅዱሳን ታሪክ ታላቅ ነገር የታየበት ነው ብለዋል፡፡ ከ12 ዓመት በፊት ይህ ክፍል ሙያ አገልግሎትና ተራድኦ ክፍል እያለ ለገዳማት ጧፍ በመላክ ነው የጀመረው፡፡ ዛሬ ታላላቅ ቅዱሳት ቦታዎች ላይ በሚሊዮን በሚቆጠር ገንዘብ ወጥቶ ሥራዎችን እንድንሠራ እግዚአብሔር ስለፈቀደልን ወደ ኋላ መመለስ አንችልም፡፡ ወደፊት ከዚህ በላይ የሆኑ ፕሮጀክቶች ይጠብቁናልና ሁላችንም በእግዚአብሔር ፈቃድ ታጥቀን መነሣትና መተባበር ይገባናል፡፡  ገጽታችን ገዘፍ እያለ ሲመጣ ጠላት ይደነግጣል፡፡ ክፉ ለሚያስቡልን ደግ እንዲያስቡ አቅም የሚፈጥር ነው፡፡ በጎ ተጽእኖ መፍጠር ያስችላል በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ይህ ፕሮጀክት 2ኛው ዙር የአብነት ት/ቤቶች በተለይም የምስክር ት/ቤቶችን ትኩረት ያደረገ መርሐ ግብር ሲሆን በመጀመሪያው ዙር የቅድስት ቤተልሔም የመጻሕፍትና የጉባኤ ቤት ተገንብቶ አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኝ ይታወሳል፡፡