Thursday, April 12, 2012

ማኅበረ ቅዱሳን በዲ/ን ያረጋል አበጋዝ ላይ የስለላ መዋቅሩን ዘረጋ

    • “የቤተክርስቲያን አባቶች የጻፉትን መጻህፍትም ሆነ የቤተክርስቲያን አባቶችን መቶ በመቶ አንቀበልም። መቶ በመቶ የምንቀበለው መጽሐፍ ቅዱስንና ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ብቻ ነው።”                                                                               ዲ/ን ያረጋል አበጋዝ                               source: awdemihret.blogspot.com
ማኅበረ ቅዱሳን በየወሩ በሚያካሂደው የማኅበሩ አባላት የሆኑ አገልጋዮች ውይይት  ላይ የማኅበሩ አፍ ሆኖ በተለያዩ ቦታዎች እና አዳራሾች በግንዛቤ አስጨብጣለሁ ስም፣ ያለ አንዳች ማስረጃ እውነተኛ የቤተክርስቲያን ልጆችን “ተሀድሶ - መናፍቃን ናቸው” እያለ መግለጫ ሲሰጥ የነበረው ዲ/ን ያረጋል አበጋዝ በቤተክርስቲያን ታሪክ «አውጣኪ መናፍቅ ነው» የተባለው ያለ ተጨባጭ ማስረጃ ነው ሲል ለአውጣኪ ተከላከለ።

የካቲት 29 2004 ዓ.ም. በአዲስ ቪው ሆቴል በተካሔደው በዚህ ወርሀዊ ጉባኤ ላይ ለጥናት የቀረበው ርዕስ “ቅድመ ኬልቄዶን ጉባኤ የኬልቄዶን ጉባኤ እውነታና ድኅረ ኬልቄዶን ጉባኤ” የሚል ሲሆን፣ የጽሁፉም አቅራቢ የማህበሩ ቀኝ እጅ ዲ/ን ያረጋል አበጋዝ ነው። የጥናቱ ዋና ትኩረት የአውጣኪና የፍላብያኖስን ጠብና የአውጣኪን መወገዝ የተመለከተ ነው። ያረጋል እንዳለው በዚህ ጉዳይ ዙሪያ የተቻለውን ያህል ልዩ ልዩ መዛግብትን ለማገላበጥ የሞከረ መሆኑን ጠቅሶ፣ ከዚህም በመነሳት የደረሰበት ድምዳሜ “አውጣኪ የተወገዘው መናፍቅ ሆኖ ሳይሆን በወቅቱ ስልጣን ላይ በነበሩት በነፍላብያኖስ ጥላቻ ነው” የሚል ነው። ይህም እንደ ጥናቱ ባለቤት እንደ ያረጋል አመለካከት “በወቅቱ አውጣኪ ላይ የቀረበው ክስ በእምነት ሳይሆን በጥላቻ የቀረበ ነው። ከዚህም በመነሳት ክሱ መሠረታዊውን አጀንዳ የሳተ እና በሀይማኖት ሽፋንነት የቀረበ ነው ወደሚል ድምዳሜ ያደርሰናል።” ብሏል።

ያረጋል ይህንን ሀሳቡን ሲያጠናክር በዋነኛነት እንደ ምክንያት የሚከተለውን አቅርቧል፤ “አውጣኪን መናፍቅ የሚያደርግ አንድም መረጃ አልተገኘም። አውጣኪ የተወገዘው በትክክለኛ እምነቱ ነው። በገዳሙ ውስጥ በእውነተኛ እምነቱ እና በትክክለኛ የምንኩስና ህይወቱ ይኖር የነበረ ሲሆን፣ በጉባኤው ላይ የመገኘት ፍላጎት አልነበረውም። በጉባኤው ላይ ላለመገኘትም ሕመምና የተለያዩ ምክንያቶችን አቅርቦ እንደ ነበር ያካሄድኩት ጥናት ያስረዳል። ይሁንና ያኔ ስልጣን ላይ የነበሩት አካላት በግፍ በጉባኤው ላይ እንዲቀርብና ምንም አይነት ሀሳብ ሳያቀርብ ጥያቄም ሳይጠየቅ መልስም ሳይሰጠው መናፍቅ ነው ብለው ብዙ ጫና አድርገውበታል።” ሲል ለአውጣኪ ትክክለኛ መሆኑን ለማስረዳት ሞክሯል።

አክሎም «አውጣኪ ምንም አይነት ሃይማኖታዊ ችግር የለበትም። የሃይማኖት ችግር እንዳለበት የሚያሳይ ማስረጃ በጽሁፍም ሆነ በቃል ከአውጣኪ አፍ አልተገኘም።» ሲል አብራርቷል። በማስከተልም «በጉባኤው ላይ የሃይማኖቱን መሰረት በሚመለከት አዘጋጅቶት የነበረውን ጽሁፍ በጉባኤው ላይ ማቅረብ አልቻለም» ሲል ገልጾአል።

በአጠቃላይ አውጣኪን መናፍቅ የሚያሰኝ በቂ ማስረጃ ከጉባኤው በፊት በጉባኤው ወቅትም ሆነ ከጉባኤው በኋላ በቃልም ይሁን በጽሁፍ ያልተገኘ መሆኑን አረጋግጧል። ይህን ከዚህ ቀደም በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ተሰምቶ የማያውቅ አዲስ ምስክርነት የሰሙት የጉባኤው ተሳታፊዎች የነበሩት የማህበሩ አገልጋዮች፣ ልዩ ልዩ ጥያቄዎችን አንስተው የጦፈ ክርክር ያደረጉ ሲሆን፣ ያለምንም ስምምነትና ጉባኤው ለሁለት ተከፍሎ እንደተለያዩ ለማወቅ ተችሏል። በብስጭት በእልክና በቁጣ ከተነሱት ጥያቄዎች መካከል ጥቂቶቹ፡-
1.     በቤተ ክርስቲያናችን አውጣኪ መናፍቅ እንደሆነ ነው የሚታወቀው። አንተ ግን መናፍቅ አይደለም እያልክ ነው። ስለዚህ ቤተክርስቲያናችን ተሳስታለች ማለት ነው ወይ?
2.     በቤተክርስቲያናችን መጻህፍት አውጣኪ መናፍቅ መሆኑ በግልጽ ተቀምጧል። አንተ ግን ልክ አይደለም። መጻህፍቶቹ ተሳስተዋል እያልክ ነው ወይ?
3.     “የቤተክርስቲያን አባቶች አይሳሳቱም፤ አስተምህሮዋቸው ትክክል ነው” ስንል ነው የኖርነው። አንተ ግን ይሳሳታሉ፤ አስተምህሯቸውም ተሳስቷል እያልክ ነው?
4.     አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ “አውጣኪ መናፍቅ ነው” ብሏል። አንተ ደግሞ “የመኳንንቱ ሴራ ነው እንጂ መናፍቅ አይደለም” እያልክ ነው። ማንን እንመን? አባ ጊዮርጊስን ተሳስቷል ብለን እንመንን?

ጥያቄው የቀረበለት ዲ/ን ያረጋል ለተነሱት ጥያቄዎች መልስ ሲሰጥ በጣም በተጎዳና ሀዘን በተሞላ መንፈስ ነበር። መልሱንም ሲሰጥ በመጀመሪያ በተማጽኖ ድምጽ “እባካችሁ በዕውቀት ላይ በር አትቆልፉባት። እስከ ዛሬ ድረስ በቤተክርስቲያናችን በር የተቆለፈባት ይበቃል።” በሚል ተማጽኖ ነበር የጀመረው። በመቀጠልም “የቤተክርስቲያን አባቶች የጻፉትን መጻህፍትም ሆነ የቤተክርስቲያን አባቶችን መቶ በመቶ አንቀበልም። መቶ በመቶ የምንቀበለው መጽሐፍ ቅዱስንና ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ብቻ ነው። ስለዚህ የቤተክርስቲያን አባቶች የጻፉዋቸው መጻሕፍትና እነርሱ ራሳቸው ጥናት ያስፈልጋቸዋል። እነርሱም የማይሳሳቱበት ምክንያት የለም። እነርሱ የተጠቀሙበትን መረጃዎች ከየት እንዳገኙና ከምን ተነስተው እንደ ጻፉ መጠናት አለበት እንጂ ሁሉንም በደፈናው መቀበል ትክክል አይደለም። ለምሳሌ፣ አባ ጊዮርጊስ አውጣኪን አዎን መናፍቅ ብሏል ግን ከምን ተነስቶ? በምን አይነት ማስረጃ የሚለው ምላሽ ያስፈልገዋል። በሁለቱ መካከል የነበረው ቢያንስ የአንድ ሺህ ዓመት ልዩነት መዘንጋት የለበትም። ከዚህ በመነሳት አባ ጊዮርጊስም ቢሆን በአውጣኪ ጉዳይ ሊሳሳት የሚችልበት ክፍተት ሰፊ ነው።” ሲል ዲ/ን ያረጋል ምላሽ ሰጥቷል።

ከዚህ መልስ በመነሳት በማህበሩ አገልጋዮችና በዲ/ን ያረጋል መካከል ትልቅ ልዩነት በመፈጠሩ እነ ዲ/ን ብርሃን አድማስ ጣልቃ ገብተው ልዩነቱን ለማጥበብ ጥረት ሲያደርጉ ነበር። በዚህ አለመግባባት መሀል የጥናት ጽሁፍ አቅራቢው ዲ/ን ያረጋል እውቀትን ለማፈንና ያለበቂ ማስረጃ የሚቀርቡ ውንጀላዎችን በሚመለከት “ነፍሴ በጣም አዝናለች ከዚህ ሀዘኔ የሚያወጣኝም አካል ያለ አይመስለኝም” ሲል ሀሳቡን አጠቃሏል።

በመጨረሻም የጉባኤው ተሰብሳቢዎች በጥናታዊ ጽሁፉ ባለመስማማት ጉባኤውን በጸሎት ሳይዘጉ አንድ በአንድ እየለቀቁ የወጡ ሲሆን፣ ጉባኤውም በጥቂት ሰዎች በጸሎት መዘጋቱን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ዲ/ን ያረጋልን በቅርብ የሚያውቁት እንደሚመሰክሩት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከሰዎች ራሱን ማግለሉንና በሀሳብ ተመስጦ በትካዜ የሚቀመጥ መሆኑን ይናገራሉ። ይህ ያሳየው የባህሪ ለውጥም በማታ ክፍለ ጊዜ በሚማርበት በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ በተማሪዎች ዘንድ መነጋገሪያ ሆኗል። ምናልባት እንዲህ ያደረገው ማንም በነፃነት በማይኖርበት በዚያ የብርሀን ጭላንጭል በማይታይበት የጨለምተኞች ስብስብ በሆነው ማህበረ ቅዱሳን ውስጥ ለራሱ “እውነት” የመሰለውን ሃሳብ ማንጸባረቅ መጀመሩ ያስከተለበት ነቀፋና ልወጣበት አልችልም ያለው ሀዘን ሊሆን ይችላል የሚል ጥርጣሬ አለ።

ምንም እንኳ አውጣኪ አለውም አላለው የእርሱ ትምህርት ነው ተብሎ የሚታመንበት ስህተትና እንዲወገዝ ያደረገው ትምህርት በትምህርተ ስጋዌ ላይ “መለኮት ሥጋን ውጦታል” ማለቱና “ክርስቶስን አምላክ ብቻ” በማለት ሰውነቱን መካዱ ነው። በርግጥ ይህ ትምህርት በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ አስተምህሮ ተቀባነት የሌለው ኑፋቄ መሆኑ እሙን ነው፡፡ ይሁን እንጂ ዲያቆኑ እውነትን ፍለጋ የጀመረው ጉዞ በገዛ ወንድሞቹ ሾተላያዊ ባህሪ አስወግዞ ከመስመር ካላወጣው እዛ ላሉት ወንድሞቹ የለውጥ ፊት አውራሪ ሊያደርገው ይችላል ተብሎ ይገመታል፡፡

 ይህ በእንዲህ እንዳለ ለሰው ልጅ ማሰብና የማገናዘብ ነፃነት ቅንጣት ታክል ቦታ የሌላቸው የዚህ ጨለምተኛ ድርጅት ስውር አመራሮች ከየትኛውም ነፃ አስተሳሰብ ጀርባ ሌላ ሰው ወይም የሐይማኖት ድርጅት ይኖራል በሚል የተለመደ አሰራራቸው በዚያው ሰሞን ተሰብስበው በዲ/ያ ያረጋል አበጋዝ ላይ 8 አባለት ያሉት የክትትል ቡድን እንዳሰማራ ከታመኑ ምንጮች የደረሰን ዘገባ ያመለክታል፡፡

በአንድ ወቅት ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ተማሪዎች ምረቃ ላይ “እስከ ዛሬ ድረስ አራት ኪሎ ተቀምጣችሁ በየጋዜጣውና በየዌብሳይቱ በሐሜት ትወቅጡን ነበር፡፡ አሁን አውቃችሁዋል፡፡ ተመርቃችኋል፤ እንኳን ደህና መጣችሁ አብረን እንወቀጣለን፡፡” ማለታቸውን አስታወስን፡፡ ምንም የተባለው ተምረው ለተመረቁት ቢሆንም የዕውቀትን ሀሁ፣  ሀ ማለት ለጀመረው ያረጋል አበጋዝ ከእውነተኞቹ ጋር ተቆጥረህ ሰላይ ስለተመደበብህ እንኳን ለዚህ ክብር በቃህ እንለዋለን፡፡ ምንም እንኳ ሌሎቹ ወንድሞች መከራ እየተቀበሉ ያሉት እንዳንተ ለአውጣኪ ተከራክረው ባይሆንም ይህ እውነትን የሚፈልግ መንፈስህ የት እንደሚያደርስህ ባልንጀሮችህ ለማየት ያብቃቸው፡፡
ማህበረ ቅዱሳን ለቤተክርስቲያን ተስፋ የሚሆኑ ሰዎች ሲነሱ በምቀኝነት እየተመለከተ፣ «ተሀድሶ መናፍቅ» የሚል ስም በመለጠፍ የሚያደርገውን ፍረጃ ትቶ፣ በስርዓት ለእውነትና ለእውቀት በማድላት ነገሮችን በጥንቃቄ መመርመር እንዲጀምር በቁርጥ ቀን ልጁ በዲ/ን ያረጋል ምክር እንዲህ እንለዋለን። “እባካችሁ በእውቀት በር አትቆልፉባት። እስከዛሬ ድረስ በቤተክርስቲያናችን በር የተቆለፈባት ይበቃል።