ርእስ፤ ሀልዎተ እግዚአብሔር/Existence of God/
ደራሲ፤ ካሳሁን ዓለሙ
መግቢያ
የ20ኛው መ/ክ/ዘ ከየትኛውም የታሪክ ጊዜ በበለጠ ሳይንሳዊ ዕውቀት የመጠቀበት ክፍለ ዘመን እነደነበር ይታወቃል፡፡ ዘመኑ ሳይንሳዊ አስተሳሰብ የመጠቀበት ብቻ አልነበረም፤ በተቀራኒውም ዓለም በጦርነት የታመሰችበትና በኢ-ሞራል አስተሳሰብ የዘቀጠችበትም እንጂ፡፡ በተለይ ኢ-ሞራላዊነት ያደረሰው ጥፋት ወደርና ልክ የለውም ሊባል ይቻላል፡፡ ለዚህ ደግሞ የዘመኑ ፍልስፍናዊ አስተሳሰብ በቁሳዊ አመለካከት ላይ መመሥረቱና መንፈሳዊ የሚባሉትን የሰው ልጆች ሀብታት መሰረዙ ትልቅ ሚና ተጫውቷል፡፡ ይህ መንፈሳዊ አመለካከትን በሐሣባዊነት ቅርጫ አጉሮ የተመሠረተ ፍልስፍናም የሣይንስን ዕድገት በቁሳዊነት መርህ ብቻ እንዲመራ አድርጎታል፡፡ በዚህ የተነሣ ሃይማኖትም ተጠራርጎ በሐሣባዊነት መርህ በመፈረጅ የሳይንስ ፀር ተደርጎ ሊወሰድ ችሏል፡፡ ይህ መርህ በተለይ ከ2ኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ዓለም በሶሻሊዝም አስተምህሮ ተጠምቃ አዲስ የ‹እግዚአብሔር የለም› ትምህርትን ‹ክርስትና› እንድትነሣ አድርጓታል፤ ‹አዲስ ክርስቲያን ከጳጳስ ይበልጣል› እንደሚባለውም በአዲሱ አስተሳሰብ ተጠምቀው ሳይንቲስት የኾኑት የቁሳካላዊያን ልጆችም በ‹እግዚአብሔር የለም› አስተምህሯቸው ውጥንቅጧን አውጥተዋታል፡፡
ሀገራችን ኢትዮጵያም የገፈቱ ቀማሽ በመኾን አዲሱን ሃይማኖት ተቀብላ እንዲትጠመቅ የተማሩት ‹ምሁር ልጆቿ› በግልፅም በሥውርም ጥረውላታል፡፡ በዚህ ጥረታቸውም የሀገሪቱን ትምህርት በቁሳዊ ሳይንስ የአስተምህሮ መርህ በመቅረጽ፣ የሃይማኖትን የሥልጣኔ ፀርነት በሥርዓተ-ትምህርቱ በማራገብና የመንግሥት ተቋማትን ተቆጣጥረው በማስተማር ወትውተዋል፡፡ በዚህም ያልገባቸውን አዲስ የቁስአካላዊ አስተምህሮ በትውልዱ አዕምሮ አጭቀው አጭቀው ግራ ገብ ስላደረጉት ጭራሽ ለባሰው ለ‹ምንፍቅና›፣ ለ‹እኔ አምላክነት› ትምህርተ ዕምነት ሰለባ አድርገውታል፡፡ በዚህ የተነሣ እነ ኦሾ እንኳን እንደ ‹ፈጣን ሎተሪ› በነፃነት እየፋቁት ይገኛሉ፡፡ ከዘመኑ ትውልድም ብዙ ወጣት ‹ኒቼ እንዲህ ብሏል› ሲሉት የእሱ አቀንቃኝ፣ ኦሾን ሲሰማም የእሱ ደቀ መዝሙር፣ ሪቻርድ ዳዊኪንም ‹እግዚአብሔር ቅዠት ነው› ሲለው ቅዠታም፣ የእስጢፋኖስ ሃውኪንግን አዲስ የሳይንስ ግኝት ሲሰማ ወይም ሲያይም ኢ-አማኝ ሳይንቲስ ይኾናል፡፡ ይህ ብቻ ሳይኾን የቁሳካላዊ ዝግመተ ለውጥ አስተምህሮ የፈጠረበት የሥነ ምግባር አልባነት ተፅእኖም ኢ-ሞራላዊ ‹ሙሱን› እንዲኾን አድርጎታል፡፡
ይህ በአንድ በኩል ሲኾን በሌላ በኩል የዘመኑን መንፈሳዊ ጦርነት ተቋቁመው የሚገኙት የ‹አባቶች ልጆችም› ዘመናዊ መሣሪያ በማጣት ወደ መማረክ ወይም ‹አትከራከሩ ሳይንስና ሃይማኖት፤ ፍልስፍና እና ሃይማኖት ተቃራኒ ናቸው› በሚል መርህ ዝምታን መርጠዋል፤ አንዳንዶቹም በጦርነቱ እጅ ሰጥተዋል፡፡ ስለዚህ የዘመኑን መንፈሳዊ ወረራ ለመከላከልና ከመንፈሳዊ ቅኝ ግዛት ጭቆና ነፃ ለመውጣት ዘመናዊ መሣሪያ ታጥቆ መዋጋት ያስፈልጋል፡፡ ይህ መጽሐፍም ለዚህ የተወሰነ አስተዋፅኦ ይኖረዋል በሚል የተዘጋጀ ነው፡፡
መጽሐፉ በአጠቃላይ በሦስት ዕይታዎች የተቃኘ ነው፡- በፍልስፍና፣ በሳይንስና በሃይማኖት አስተምህሮዎች፡፡ የአቀራረብ ስልቱ በመጀመሪያ የፍልስፍና ዕይታን በተጠየቅ ሙግት አስቀምጦ ያብራራል፤ በአብዛኛው የፍልስፍና ሙግቶች የቀረቡት በዚህ መልክ ነው፡፡ ይሁንና በተወሰነ ደረጃ ካልኾነ በስተቀር ጸሐፊው የፍልስፍና አስተምህሮዎችን ማጨቅ አልፈለገም፡፡ ስለኾነም የፍልስፍና ዕይታ አቀራረብን በአብዛኛው አመክንዮአዊ (logical) ለማድረግ ሞክሯል፡፡ ሳይንሳዊ ዕይታዎችን በሚመለከት የተከተለው አቀራረብ መላምቱን በፍልስፍናዊ መሠረቱና አተያዩ በማቅረብና የተወሰነ ትችታዊ አስተያየት በመስጠት ላይ የተወሰነ ነው፡፡ ለዚህም ዋናው ምክንያት ጸሐፊው የሳይንስ ዕውቀት መሠረቱ ፍልስፍና፤ ማጠንጠኛው ደግሞ የእውናዊው ዓለም ሥርዓታዊ ቅንብርና አስተሳሰብ ነው የሚል እምነት ስላለው ነው፡፡ በተቻለ መጠንም ለተነሳበት ርዕስ አስፈላጊ ናቸው ያላቸውን ሳይንሳዊ መላምቶች ለማካተት ሞክሯል፡፡ ሃይማኖታዊ አስተምህሮችንም እንደ ፍልስፍናው ተጠየቃዊ ለማድረግ ጥሯል፡፡ ይሁንና የዕይታ አንግልን መስመር ለማስያዝ ሲባል የአቀራረብ ሙግቱ በክርስትና ሃይማኖት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ቢኾንም በዚህ መጽሐፍ በአንድ ምዕራፍነት ሊካተት የነበረ ‹ነገረ ድኅነት ለእግዚአብሔር ሀልዎት› የሚል የክርስትና አስተምሮ ሙሉ ለሙሉ እንዲወጣ ተደርጓል፡፡ ለዚህም ኹለት ምክንያቶችን ተጠቃሽ ናቸው፡፡ አንደኛ በመጽሐፉ መነሻነት የትኛውም ሰው ወይም የየትኛውም እምነት ተከታይ በነፃነትና ተፈጥሮን መሠረት አድርጎ ብቻ በመመርመር የእግዚአብሔርን ሀልዎት እንዲረዳ ለማድረግ ሲኾን፤ ኹለተኛም በአንድ ምዕራፍ የተቀመጠው የነገረ-ድኅነት አስተምሮ ሰፋ ተደርጎ በአንድ መጽሐፍነት ቢዘጋጅ የተሻለ ግንዛቤን ይፈጥራል በሚል እሳቤ ነው፡፡
ከአቀራረቡ ጋር በተያያዘ ጸሐፊው በተወሰነ ደረጃ ከሚፈለገው ሐሣብ ጋር አብሮ ይሔዳል ብሎ ያሰበውን ግጥም ወይም ቅኔ ወይም አባባል አብሮ ለማቅረብ ሞክሯል፡፡ ይህም መጽሐፉ ከያዘው ሐሣብ ጥንካሬ አንጻር ውበት ለመስጠትና ሐሣቡንም በዚያው ለማጎላመስ፣ እንዲሁም የገጣሚያንና የባለ ቅኔዎንች ዕይታም ለማሳየት ተብሎ የተደረገ ነው፡፡ ይሁንና አንዳንዶቹ ግጥሞች (ቅኔያት)
አጠቃላይ የመጽሐፉን ዓለማ ካልኾነ በስተቀር ከንዑስ አሳቡ ጋር
አብረው የማይሔዱበት ኹኔታ ይኖራል፡፡ እንዲሁም ግጥሞቹ ከተለያዩ ገጣሚያን ወይም ባለቅኔዎች የተሰበሰቡ በመኾናቸው አንዳንዶቹ የተገጠሙበት ዕይታ በዚህ መጽሐፍ በቀረቡበት መልኩ ላይኾን ይችላል፡፡ ለዚህም ለገጣሚዎቹና ለቅኔ ሊቃውንቱ ይቅርታ መጠየቅን ይወዳል፡- ጸሐፊው፡፡ በተጨማሪም ጸሐፊው በእንግሊዘኛ የተጻፉ ግጥሞችን እንደነበሩ ትቷቸዋል፤ አልተረጎመም፡፡ ምክንያቱም ወደ አማርኛ መመለሱ መልዕክታቸውን ስላደበዘዘው እንደነበሩ ቢጠቀሱ ይሻላል ብሎ ስላሰበ ነው፡፡
በአጠቃላይ መጽሐፉ 8 ምዕራፎች አሉት፡፡ በመጀመሪያው ምዕራፍ
ወጣቶች በየሻይ ቤቱና በሌሎችም ሥፍራዎች የሚያደርጓቸውን ኢ-መደበኛ ክርክሮች
የሚያንፀባርቅ ክፍል ቀርቧል፡፡ ይህ ርዕስም በመጀመሪያ የቀረበበት ምክንያት ጸሐፊው ቀድሞ መጽሐፉን ያዘጋጀበት ስልት በውይይት መልክ ስለነበር
ስልቱን ከቀየረ በኋላም ይኸኛው ርዕስ ከዋናው የአቀራረብ ፍሰት በፊት ቢገባ ችግር አይኖርውም በሚል እምነት ሲኾን በተጨማሪም በቀላል ለመጀመር ይረዳል፤ እንዲሁም የወቅቱን የወጣቶች የክርክር ኹኔታም ያንፀባርቃል በማለት ነው፡፡
በኹለተኛው ምዕራፍ በእግዚአብሔር ህልውነት ላይ ያሉ ሦስት አማራጭ የክርክር አቋሞች ቀርበውበታል፡፡ ከአቋሞቹም መካከል የኹለቱን ማስረጃዎች በተጠየቅ
ያቀርባል፡፡ አንደኛውን አቋም ግን በመከራከሪያነት ደግፎ ወደሌሎች ምዕራፎች ያሸግረዋል፡፡ በሚቀጥለው በምዕራፍ ሦስት አጠቃላይ የእግዚአብሔርን ሀልዎት ከጠባያቱ ምንነት አንጻር ያሳይና በዚያ ላይ የኹለት ሰዎች ሙግትን በተቃርኖዊ ዕይታ ያቀርባል፡፡ ይህም በእግዚአብሔር ጠባያት የተለያየ አመለካከት ያላቸውን ሰዎች አቋም ያንፀባርቃል በሚል የቀረበ ነው፡፡
ከምዕራፍ ሦስት በኋላ ያሉት አራት ምዕራፎች ጸሐፊው የእግዚአብሔርን ህልውነት ለማረጋገጥ ያስችሉኛል ያላቸውን ማስረጃዎች ያቀረበባቸው ምዕራፎች ናቸው፡፡ ምዕራፍ አራት ማጠንጠኛው በኹለት ሐሣቦች ላይ ነው፡- የዓለመ-ፍጥረቱ (universe) መገኘትና ፍፅምናን መፈለጉ፡- የእግዚአብሔርን መኖር ያጠይቃል በሚል፡፡ የምዕራፍ አምስት ማጠንጠኛ ሐሳብ ደግሞ በአጠቃላይ በፍጥረቱ ሥነ ሥርዓታዊ አኗኗር ላይ ነው፡፡ በዚህም ከጠቅላላ የዓለመ-ፍጥረቱ አኗኗር ጀምሮ እስከ የሕይወት ትንሽ ሕዋስ ድረስ ፍጥረት እንዴት ሥርዓትን በመጠበቅ እንደሚገኝ ለማሳየት ተሞክሯል፡፡ ከዚያ ቀጥሎ ያለው ምዕራፍ ስድስት ሕይወት ካላቸው ነገሮች ሰውን ነጥሎ ምን ያህል እንቆቅልሽ እንደኾነ ማንነቱን ይመረምራል፡፡ ቀጣዩ ምዕራፍ ሰባት ደግሞ በሞራል ላይ የሚያጠነጥን ምዕራፍ ነው፡፡ በዚህም ሞራል የበላይ ኃላፊን እንደሚፈልግ በማሳየት የእግዚአብሔርን ህልውነት ለማረጋገጥ ያለውን ማስረጃነት ይቃኛል፡፡
የመጨረሻው ምዕራፍ ስምንት የማጠቃላያ ነጥቦችን
የያዘ ነው፡፡ በዚህ እግዚአብሔር ‹አለ›ም ኾነ ‹የለም› የሚሉ ተከራካሪዎች የሚያቀርቧቸውን ማስረጃዎች ጥቅል ፐርሰንት ተሠጥቷቸው የሚኖራቸው የማስረጃነት ክብደት ተመዝኗል፡፡ የተሰጠውን ነጥብም ከነባራዊ የማስረጃ እውነታ ጋር በማገናዘብ ለመተንተን ተሞክሯል፡፡ በተጨማሪም በእግዚአብሔር ህልውነት ዙሪያ ያሉ አማራጮችን በተጠየቅ በመመዘን ትክክለኛው መደምደሚያ ላይ ለመድረስ ተጥሯል፡፡ በዚህ መልክም ምዕራፉ ማጠቃላያ በመስጠት ያሳርጋል፡፡
መልካም ንባብ ይሆንልዎ!! ደጀ ብርሃን