Friday, April 13, 2012

«ስቅለተ ዓርብና እርግማን!»

መድኅነ ዓለም ክርስቶስ የአዳምን ልጆች በደልና የሕግ እርግማን ተሸክሞ ቀራንዮ ላይ መሰቀሉን እናውቃለን። የእግዚአብሔር አንድያ ልጅ ኢየሱስ  ቤዛ ይሆን ዘንድ ያስገደደው ለሰው ልጆች ያለው ፍቅር ብቻ ነው። ይህንንም አባ ሕርያቆስ በቅዳሴው «ፍቅር ሰሀቦ ለወልድ ኃያል እመንበሩ ወአብጽሖ እስከ ለሞት» ሲል ለእኛ ያለውን ጥልቅ ፍቅር ገልጾታል። ከዚህ ውጪ ሌላ ዓላማ አልነበረውም።

«ስለ ጻድቅ የሚሞት በጭንቅ ይገኛልና፤ ስለ ቸር ሰው ግን ሊሞት እንኳ የሚደፍር ምናልባት ይገኝ ይሆናል
ነገር ግን ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቶአልና እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያስረዳል» 
ሮሜ ፭፣፰
እንግዲህ ይህ ፍቅር ለእኛ የተደረገው እኛ ደጎች ስለነበርን ሳይሆን የእኛ በደል ከፍቅሩ ውጪ ስላወጣን ዳግም በማያልቀው ፍቅሩ ውስጥ እንድንኖርለት ስለፈለገ ብቻ ነው። ወሰን በሌለው ፍቅሩ ውስጥ እንድንኖርለት አርአያውና ፍለጋውን ሁሉ ሰርቶ አሳይቶናልና የሕይወታችን አንድ አካል እንዲሆንለት ይሻል። ለእኛ የተሰጠው አምላካዊ ፍቅር በእኛ ውስጥ መኖር ይገባዋል። እኛ ኃጢአተኞች ሳለን ከተወደድን ልንጠላው የሚገባው የሰው ልጅ  የለም ማለት ነው። 
በክርስቶስ ደም  የተመሠረተው ወንጌል እኛን ጠላቶቹ ሳለን ወደ ፍቅሩ መመለስን ብቻ ሳይሆን «ጠላትህን ጥላ» የሚለውንም የጥል ሕግ አፍርሶ «ጠላትህን ውደድ» የሚልም ትእዛዝ ትቶልናልና ነው።

« ባልንጀራህን ውደድ ጠላትህንም ጥላ እንደ ተባለ ሰምታችኋል።
እኔ ግን እላችኋለሁ፥ በሰማያት ላለ አባታችሁ ልጆች ትሆኑ ዘንድ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፥ የሚረግሙአችሁንም መርቁ፥ ለሚጠሉአችሁም መልካም አድርጉ፥ ስለሚያሳድዱአችሁም ጸልዩ፤ እርሱ በክፎዎችና በበጎዎች ላይ ፀሐይን ያወጣልና፥ በጻድቃንና በኃጢአተኞችም ላይ ዝናቡን ያዘንባልና» ሮሜ ፭፣፵፫-፵፭
 የሰማዩ አባታችን ልጆች እንሆን ዘንድ ለእኛ ለተጠላነው ጥልቅ ፍቅሩን በልጁ ሞት ስላሳየ እኛም እንዲሁ በፍቅሩ የልጅነት ሕይወት ውስጥ ለመቆየት የግድ ጠላቶቻችንን መውደድ፣ የሚረግሙንን መመረቅ፣ ለሚጠሉን መልካም እንድናደርግ ይፈልጋል። ከጥላቻና ከእርግማን ጎራ ወደ ፍቅርና በጎነት መንፈሳዊ ዓለም እንድንገባ ያዘናል። ያለበለዚያማ ልጆቹ ልንሆን እንዴት ይቻላል? ፍቅርና እርግማን መቼም ቢሆን ስምምነት ይኖራቸው ዘንድ አይታሰብም። ስለዚህም የፍቅር አባት ልጆች ረጋሚዎችና ጥላቻን የተሞሉ ሊሆኑ በፍጹም አይችሉም። 
በእርግጥ በአፋችን የሰማዩ አባታችን ልጆች ስለመሆናችን እንናገር ይሆናል። ልዩነቱን ግን  በእኛ ላይ የሚገልጠው ልጅነታችንን ስላወራን ሳይሆን የሚመሰክርብን ፍቅር የራቀው ማንነታችን  ነው። ቃሉን የሚያወሩ እንጂ የማያደርጉ ስለሆንን ስንት የእርቅ በሮችን ዘግተን በጥላቻና በእርግማን ዓለም ውስጥ ዛሬም ድረስ አለን።
«ቃሉን የምታደርጉ ሁኑ እንጂ ራሳችሁን እያሳታችሁ የምትሰሙ ብቻ አትሁኑ » ያዕ ፩፣፳፪

 እንግዲህ ፍቅር ማለት ለክርስቲያኖች የክርስቶስ ሞትና ትንሳዔ ዋጋ እንደመሆኑ መጠንና ይህንኑ ፍቅር በሕይወታችን ውስጥ የክርስትናችን ክፍል አድርጎ ማሳየት እንደሚገባን ከተነገረን የእግዚአብሔር ፍቅር በተገለጸልን በእለተ ዓርብ የክርስቶስ ስቅለት መታሰቢያ  የጸሎት እርግማን ከየት የተገኘ ትምህርት ነው? ብለን እንጠይቃለን።
በእለተ ዓርብ የሰርክ ጸሎት አንዱ ክፍል ሆኖ የሚጸለየው  ጌታውን በሠላሳ ብር በመሸጥ አሳልፎ የሰጠውና ከሐዋርያት እንደ አንዱ ተቆጥሮ የነበረው ይሁዳን የሚረግምበት ክፍል አለ። እርግማኑ ለይሁዳ ብቻ ሳይሆን ዘር ማንዘሮቹ ሁሉ ከምድረ ገጽ እንዲጠፉ፤ ትውልዶቹ ሁሉ ሥረ መሠረታቸው ተነቅሎ እንዲጠፋ፤ እንደይሁዳ የካዱ ሁሉ መቼም ቢሆን የንስሐን እድል ሳያገኙ ሲኦል እንዲወርዱ የሚዘንብባቸው  የዓርብ ስቅለት ጸሎተ ሰርክ ክፍል  ለምን ይሆን የይሁዳ ትውልድና እንደ ይሁዳ የካዱ ሁሉ የሚረገሙበት? 
ይሁዳ ጌታውን በሠላሳ ብር እንደተነገረበት ትንቢት መሸጡን እምቢ ብሎ ማስቀረት ይችል ነበር ወይ ብለን እንጠይቃለን? ጌታስ ሳይሸጥ ይሰቀላል የሚል ትንቢት ተጽፏል? ለዓለሙ ሁሉ የሚዳረስ ሰማያዊውን በግ በትንሽ ገንዘብ በመሸጡ ይሁዳ ለራሱ ከሚከስር በስተቀር ከተሸጠው የእግዚአብሔር በግ ዓለም አላተረፈችም ማለት ነው?  
ይሁዳን እዚህ ድረስ ያደረሰው ነገር አስቀድሞ የሙዳየ ምጽዋት ገንዘብ ያዥ ሆኖ ከዚያው ይሰርቅ እንደነበር ተጽፎልናል። ዛሬስ በየአብያተ ክርስቲያናቱ ውስጥ ስንቱ ካህን ነው የሙዳየ ምጽዋት ገንዘብ የሚሰርቀው? በስርቆት ካዝናቸው ባዶ የሆኑና የሚከፍሉትን ያጡ አድባራት የሉንም? ስንቱ ይሁዳ ነው የዘረፈውን ሳይበላ በሞት የተቀሰፈው?  የስንቱስ ይሁዳ  ገመና ነው በፍርድ ቤት አደባባይ የተሰቀለውና ሁሉም ያየው የሰማው? 
ሙዳየ ምጽዋት የሚገለብጡ አስተዳዳሪዎች፣ ጸሐፊዎች፣ ሂሳብ ሹሞች፣ ቁጥጥሮች ወዘተ በእለተ ዓርብ ጸሎት ይሁዳን የሚረግሙት ለእነሱ ተግባር የተቀደሰ ሆኖ ነው? በገንዘብ ስርቆቱ እንዲህ ዓይነቱ ሌባ ከይሁዳ የሚለው በምንድነው? ቢሰርቅም ጌታን አልሸጠም የሚል ቢኖር እውነታው ግን የጌታን ጸሎት ቤት ሙዳየ ምጽዋት መስረቅ ዛሬም መታመኑን ከድቶ እንደይሁዳ ጌታን በገንዘብ አሳልፎ እንደሸጠው  መቆጠሩ ሀቅ ነው። በመቅደሱ አለን እያሉ የሚያመነዝሩ፣ የሚሰርቁ፣ የሚዋሹ፣ የሚያታልሉ ሁሉ ዛሬም በፍቅሩ የጠራቸውን ጌታ ለመውደድ ያልፈለጉ ናቸው። እንግዲህ እነዚህን ሁሉ ነው «ይሁዳ ውሉደ ውሉዱ ይደምሰስ» እያልን ስንራገም የምንውለው! 
ጌታን በአካለ ሥጋ አግኝቶ ይሁዳ እንደተተነበየበት ይሽጠው እንጂ  በጭለማ መንፈስ ሥራና በክፉ ግብራቸው የሚሸጡ አያሌ ይሁዳዎች ዛሬም አሉ። አመልካች ጣታችንን በይሁዳ ላይ ስንቀስርና በመራራው አፋችን ስንራገም የግብር ማንነታችንን የሚከተል እርግማን በራሳችን ላይ እየመሰከርን መሆኑን ልብ ልንል ይገባል። 
የዚህ ጽሁፍ ዓላማ ስለይሁዳ ክፉ መሆንና አለመሆን ለመከራከር አይደለም። እርሱ እንደ ተነገረበት ሆኖ አልፏል። ቢፈርድበትም፣ ቢምረውም የፈጠረው አምላክ እንደወደደ ከፍሏል፣ ግን እኛ ይሁዳን የምንረግመው ለምንድነው? እኛ ንጹሐን  መሆናችንን ራሳችን እያወጅን ይሁዳ ግን ምንም ዓይነት ምህረት የማይገባውና ከሲኦል በቀር ቦታ ሊሰጠው እንደማይገባ አምነን ለዘመናት መራገማችን  ስለክርስትና ያለንን እውቀት ጥርጣሬ ውስጥ ይከተዋል ። ይሁዳ ጠላት ነው ብንል እንኳን የፍቅር አምላክ «ጠላቶቻችሁን ውደዱ» እንጂ ተራገሙ የሚል ትምህርተ ክርስትና አልተወልንም። ደግሞም ስንራገም እርግማናችን በግብራቸው ይሁዳን የመሰሉ ሁሉ ፍጹም ወደ ድኅነት ሳይሆን ወደ ሲኦል ይውረዱ ስንል እኛ ማን ሆነን ነው? ጸልዩላቸው የተባለውን አልፈን በመሄድ ኃጢአተኞች ሳይድኑ  መጨረሻቸው ሲኦል ይሁን ብለን የምንፈርድ ከቶ ለምን ይሆን? 
የዛሬዋ ቤተክርስቲያን ብዙ ይሁዳ መሳይ ሌቦችን፣ ሻጮችን፣ ለዋጮችን፣ ዘማዎችን፣ አታላዮችን፣ ሳጥን ገልባጮችን ተሸክማለች። የእነዚህን ሥራ በመግለጥ ወደ ንስሐ እንዲመለሱ እንጂ በዚያው ክፉ ግብራቸው ጸንተው መመለስ ወደማይቻልበት ወደ ሞት የፍርድ ዓለም እንዲሄዱ፣ አንረግማቸውም። አንመኝልላቸውም። ይሁዳ የተከፈለው ዋጋው ምንም ይሁን ምንም ፋይሉ በተዘጋበት ማንነቱ ላይ እርግማንን አናወርድም። በማንም ላይ በፍጹም እርግማን የምናወርድ አይደለንም። ለእኛ እርቅና ፍቅር ከሰማይ የተደረገልን ሞት የሚገባን ሆነን ሳለ ነውና አንራገምም። ይልቁንም እንጸልይላቸዋለን እንጂ!
ክፉ ሥራቸውን እንዲተዉ የተከደነ ክፋታቸውን በእግዚአብሔር ቃል እንገልጣለን። ኃጢአታቸውን እንዲጠሉት በቃሉ ገልጸን እንንግራቸዋለን። ወደ ንስሐ እንዲመጡ፣ ከቀደመ ግብራቸው እንዲመለሱ ቀናውን የሕይወት መንገድ እናሳያቸዋለን እንጂ እነሱም ይሁኑ ልጅ ልጆቻቸው ኃጢአታቸው እንዳይደመሰስና ከእግዚአብሔር ዘንድ ምንም ዓይነት ይቅርታ እንዳያገኙ አንጸልይም። 
ረጋሚዎቻችን ከዳዊት ዝማሬ ላይ ቆንጥረው የእርግማን እሳት ለማምጣት የሚያወርዱት ድግምት ይህንን ይመስላል።

«ሢም ላእሌሁ ኀጥአ፣ ወሰይጣን ይቁም በየማኑ፤
ወሶበሂ ይትዋቀሥ ይፃእ ተመዊኦ፣ ወጸሎቱሂ ትኩኖ ጌጋየ፤
ወይኩና መዋዕሊሁ ኅዳጠ፣ ወይኩኑ ደቂቁ ዕጓለ ማውታ፣
ወብእሲቱሂ ትኩን መበለተ፣ ይትሀወኩ ደቂቁ ይፍልሱ ወያስተፍእሙ፣
ወይስድድዎሙ እምአብያቲሆሙ፣ ወይበርብሮ በዓለ ዕዳ ኵሎ ንዋዮ፣
ወየሐብልዮ ነኪር ኵሎ ተግባሮ፣ ወኢይርከብ ዘይረድኦ፣
ወኢይመሐርዎሙ ለዕጓለ ማውታሁ፣ወሠረዉ ደቂቁ ፤በአሐቲ ትውልድ ትደምሰስ ስሙ፣
ወትዘከር ኃጢአተ አቡሁ በቅድመ እግዚአብሔር፣ ወኢይደምሰስ ጌጋያ ለእሙ፣
ወየሀሉ ቅድመ እግዚአብሔር በኵሉ ጊዜ ። መዝ ፻፰/፻፱

ትርጉም፣
በላዩ ኃጢአተኛን ሹም ሰይጣንም በቀኙ ይቁም።
በተምዋገተም ጊዜ ተረትቶ ይውጣ ጸሎቱም ኃጢአት ትሁንበት።
ዘመኖቹም ጥቂት ይሁኑ ሹመቱንም ሌላ ይውሰድ።
ልጆቹም ድሀ አደግ ይሁኑ፥ ሚስቱም መበለት ትሁን።
ልጆቹም ተናውጠው ይቅበዝበዙ ይለምኑም፥ ከስፍራቸውም ይባረሩ።
ባለዕዳም ያለውን ሁሉ ይበርብረው፥ እንግዶችም ድካሙን ሁሉ ይበዝብዙት።
የሚያግዘውንም አያግኝ። ለድሀ አደግ ልጆቹም የሚራራ አይኑር።
ልጆቹ ይጥፉ በአንድ ትውልድ ስሙ ይደምሰስ።
የአባቶቹ ኃጢአት በእግዚአብሔር ፊት ትታሰብ የእናቱም ኃጢአት አትደምሰስ።
በእግዚአብሔር ፊት ሁልጊዜ ይኑሩ መታሰቢያቸው ከምድር ይጥፋ።

 እኰ ለምን? በኃጢአተኞችና በበደለኞች ላይ እርግማን ለክርስቲያኖች ከየት የተገኘ ትምህርት ነው?
«ሞኝ የተከለውን ብልህ አይነቅለውም» ሆኖ ነው እንጂ ክርስትና የእርግማን ሳይሆን የፍቅርና የይቅርታ ሃይማኖት ነው።
«ጠላቶች ሳለን ከእግዚአብሔር ጋር በልጁ ሞት ከታረቅን፥ ይልቁንም ከታረቅን በኋላ በሕይወቱ እንድናለን»
እንጂ ስንራገም የምንኖር አይደለንም።
ስለሆነም እርቅ የተፈጸመበትን ስቅለተ ዓርብን ስናስብ እርግማንን በማዝነብ በምንም መለኪያ እርቅ ፈላጊዎች መሆናችንን አያሳይም። እርቅ ሳይሆን እርግማን ላይ ጠበቅ ብለን በትራችንን ስለወረወርን እርቅ ርቆናል። ሰይጣንም በትር በመወርወር ወይም በመራገም አይጠፋም። ሲሆን በዚህ ዓይነቱ ግርግርና የዱላ ሁካታ መካከል ሆኖ ይሳለቅ ይሆናል ይሆናል እንጂ ዱላ ፈርቶ እንደማይሸሽ እርግጠኞች ነን። እርሱን የሚያስጠላውና የሚያንገሸግሸው እርቅ ብቻ ነው። በእርቅና በምህረት ምትክ እርግማን ሲወርድ እሰየው ከሚል በስተቀር ይሁዳና ግብረ ይሁዳዎች  ሲረገሙ በምንም መመዘኛ ሰይጣን አይከፋውም። እንዲያውም ደስተኛ ይሆን ይሆናል።እርግማንና ውግዘት  ለክርስቲያኖች የተሰጠ መለያ አይደለምና ይህንን በሚያደርጉት ላይ ሰይጣን አንዳች ቅሬታ የለውም።  ይልቁንም ዘወትር የሚራገሙትንና የሚሳደቡትን ይሻል። አትራገሙ ከሚለው ከጌታ ቃል የወጡ ስለሆነ እነዚህኞቹን በየዓመቱ፣ ቢቻል በየዕለቱ ቢራገሙለት ይፈልጋል። ስለዚህ ከእርግማን ወጥተን እርቅን እንስበክ!! ያኔም የሚያስተራርቁ ብጹአን የእግዚአብሔር ልጆች እንባላለን። ወንጌል እርቅ ናት። ዕለተ ዓርብም እርቅ የተፈጸመባት እንጂ እርግማን የሚዘንብባት አይደለችም።
«ስቅለተ ዓርብና እርግማን»አብረው አይሄዱም!!