Friday, April 27, 2012

ፍትወተ - ሥጋ


- ትንሹ እሳት (የዓለም፣ የሥጋ፣ የሰይጣን እሳት)
በመሠረቱ  ማንኛውም እሳት ኃይል ነው (አለው)፡፡ በትክክል ከሠሩበት ጠቃሚ ነው፡፡ ያለ አግባብ ከሠሩበት ደግሞ አጥፊና ደምሳሽ ነው፡፡ በዘህ ክፍል ውስጥ ከሚገኙት የእሳት ዓይነቶች ውስጥ አንዳንዶቹ ምንም ጥቅም የማይገኝባቸው፣ እንዲያውም አጥፊ ብቻ የሆኑ እሳቶች ሲሆኑ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ በአግባቡና በእግዚአብሔር ፍቃድ መሠረት ከተሠራባቸው ለበረከት የሚሆኑ፣ በሥጋ ምሪት ከተሠራባቸው ደግሞ የኩነኔ መሰላሎች የሆኑ እሳቶች ናቸው፡፡
1. ፍትወተ - ሥጋ (Sex) - እግዚአብሔር ለሰዎች ከሰጣቸው ጠቃሚ ኃይሎች አንዱ የሆነው ፍትወተ ሥጋን በአብዛኛው ለክፋት መገልገያነት ሲውል ማየታችን መጥፎ እንደሆነ አድርገን እንድንመለከተው አድርጎናል፡፡ በእግዚአብሔር ቃል ላይ ተመርኩዘን ስለዚህ ጉዳይ ያጠናን እንደሆነ ግን መልካም ስጦታ እንደሆነ ነው የምናገኘው፡፡ ይህን ስጦታ በአግባቡ ለተጠቀመበት ሰው የበረከት ምክንያት ይሆንለታል፡፡ ከጌታ ፍቃድ ውጪ ለሠራበት ደግሞ የጥፋት መሣሪያ ይሆንበታል፡፡ "እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፣ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው፡፡ እግዚአብሔርም ባረካቸው፣ እንዲህም አላቸው፡- ብዙ ተባዙ ምድርንም ሙሉአት...." (ዘፍ. 127-28) ከሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያው ገጽ ጥቅስ አንስቶ በመላው መጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ውስጥ ጋብቻና የጋብቻ ውጤቶች የሆኑት ልጆች የእግዚአብሔርን ቡራኬ ሲቀበሉ እናያለን፡፡ በጋብቻ ውስጥ ውትወተ ሥጋ አለ፣ ቀጥሎም ልጆች ይገኛሉ፡፡ ስለዚህ በቃል ኪዳን መሐላ ማኅተም በታሰረ ጋብቻ ውስጥ የባልና ሚስት ግንኙነት የተቀደሰ ተግባር እንጂ፣ ርክሰት አይደለም፡፡ በዚህ መልኩ ብቻ ከተሠራበት የፍትወተ-ሥጋ እሳት ጠቃሚና ቅዱስም ይሆናል፡፡ ከዚህ ውጪ ግን የገሃነመ እሳትን የመጀመሪያ ነበልባሎች እዚህ ምድር ላይ የሚጭር እርኩስ እሳት ይሆናል፡፡ ፍትወተ-ሥጋ እሳት ስለመሆኑ ቅዱስ ጳውሎስ በተለያዩ መልእክቶቹ አመልክቷል፡፡ ለምሳሌ 1 ቆሮ. 78-9 ላይ እንዲህ ይላል - "ላላገቡና እንዲሁም ባሎቻቸው ለሞቱባቸው ሴቶች የምለው እንዲህ ነው፤ ሳያገቡ እንደ እኔ ቢኖሩ መልካም ነው፡፡ ነገር ግን ራሳቸውን መቈጣጠር ቢያቅታቸው ያግቡ፤ ምክንያቱም በሥጋ ምኞት ከመቃጠል ይልቅ ማግባት የተሻለ ነው፡፡" የሥጋ ምኞት (ፍትወት) ለምን ያቃጥላል; መልሱ ግልጽ ነው እሳት ስለሆነ፡፡ እዚህ ላይ .ጳውሎስ ስለዚህ እሳት መልካምነት ይናገራል፡፡ በሌላ ቦታ ግን ያለአግባቡ በጥቅም ላይ ስለዋለ ርኩስ እሳት ይናገራል፡፡ 
 "... ሴቶቻቸውም ለባሕሪያቸው የሚገባውን ሥራ ለባህሪያቸው በማይገባ ለወጡ፤ እንዲሁም ወንዶች ደግሞ ለባሕሪያቸው የሚገባውን ሴቶችን መገናኘት ትተው እርስ በርሳቸው በፍትወታቸው ተቃጠሉ፤ ወንዶችም በወንዶች ነውር አድርገው በስህተታቸው የሚገባቸውን ብድራት በራሳቸው ተቀበሉ፡፡" (ሮሜ. 126-27) ለሰው ልጆች ጥቅም ከአምላክ የተሰጠው ይህ ስጦታ ከተወሰነለት ዓላማ ውጪ በተግባር ላይ ሲውል ምን ያህል አስከፊ እንደሆነ ይህ ጥቅስ ያስረዳል፡፡ ግብረ ሰዶም (Homosexuality) በቅ.ጳውሎስ ጊዜና አሁንም በዘመናችን ብዙዎችን በጨለማ ዓለም ያሠረ ርኩስ ሰይጣናዊ እሳት ነው፡፡ መጨረሻውም ዘላለማዊ እሳት ነው፡፡ "ሴሰኞች ወይም ጣዖት አምላኪዎች ወይም አመንዝራዎች ወይም ከወንድ ጋር ዝሙት የሚያደርጉ ወንዶች... የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም፡፡" (1ቆሮ. 6 1-10) በሎጥ ዘመንስ ቢሆን እሳትና ዲንን ከሰማይ የጠራ ይኸው ርኩስ እሳት አልነበረምን? "ግብረ-ሰዶም" ወይም "የሰዶም-ሥራ" የሚለው መጠሪያውም የተገኘው የሰዶም ሰዎች በዚህ ኃጢአት ጌታን ስላሳዘኑና ቅጣታቸውንም ስለተቀበሉ ነው፡፡ (ዘፍጥ. 1816-1929 ተመልከት) "እግዚአብሔርም በሰዶምና በገሞራ ላይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ከሰማይ እሳትና ዲን አዘነበ፤ እነዚያንም ከተሞች በዙሪያቸውም ያለውን ሁሉ በከተሞቹም የሚኖሩትን ሁሉ የምድሩንም ቡቃያ ሁሉ ገለበጠ፡፡" (ዘፍ. 19 24-25)፡፡ ይህ እንግዲህ የፍትወተ ሥጋ እሳት እጅግ በከፋ መልኩ ሲገለጽ ነው፡፡ ከዚህ ባነሰ መልኩም ቢሆን በኃጢአት ላይ ከዋለ የጥፋት መሰላል መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ያስረዳናል፡፡
አመንዝራነትም የፍትወተ ሥጋን እሳት በክፋትና ለጥፋት የማዋያ አንዱ ገጽታ ነው፡፡ ቅጣትንም የሚያስከትል መዘዘኛ ተግባር ነው፡፡ ሰሎሞን በመጽሐፈ ምሳሌው ላይ ስለዚህ ጉዳይ በስፋት ያናገራል፡፡ በምዕራፍ 6 ቁጥር 24-33 ላይ ስለዚህ ጉዳይ ሲናገር አመንዝራነት አደገኛ እሳት እንደሆነ ያሳያል፡፡
"አመንዝራም ሴት የሰውን ሕይወት ታጠምዳለች፡፡ በጉያው እሳትን የሚታቀፍ፣ ልብሶቹስ የማይቃጠሉ ማን ነው? በፍም ላይ የሚሄድ፣ እግሮቹስ የማይቃጠሉ ማን ነው? ወደ ሰው ሚስት የሚገባም እንዲሁ ነው፡፡ የሚነካትም ሁሉ ሳይቀጣ አይቀርም፡፡ ... ከሴት ጋር የሚያመነዝር ግን አእምሮው የጐደለ ነው፡፡ እንዲሁም የሚያደርግ ነፍሱን ያጠፋል፡፡" (. 26-29,32) በጉያው እሳትን ታቅፎ ልብሱና ገላው የማይቃጠል ማንም እንደሌለ ሁሉ፣ በፍም ላይ እየተራመደም እግሮቹ ሳይቃጠሉ የሚቀር ማንም እንደሌለ ሁሉ፣ ከሰው ሚስት ጋር አመንዝሮ ከቅጣት እሳት የሚተርፍ ማንም የለም፡፡ ይህ ምሳሌ የአመንዝራነትን አደገኛ እሳትነት እጅግ ግልጽ በሆነ መንገድ ነው የሚያቀርብልን፡፡ እንኳን እሳትን መታቀፍ ወይም በእሳት ላይ መሄድ ይቅርና በጣታችን እንኳ ትንሽ ነካ ካደረግነው ምን ያል እንደሚፈጀን እናውቃለን፡፡ እሳቱ ከአካላችን ጋር ተገናኝቶ የቆየውን ያህል ጉዳቱም እየጨመረ ይሄዳል፡፡ ለብዙ ጊዜ በእሳቱ ላይ ከቆየን ሙሉ ለሙሉ ሊያጋየንም ይችላል፡፡ ምን ያህል ሰዎች በደምሳሽ እሳት ውስጥ ተበልተው እንደቀሩ ጋዜጦቻችንና ሬዲዮኖቻችን ሊነግሩን ይችላሉ፡፡ ከዚህ ግዙፍ እሳት በላይ ነፍስን የሚደመስሰው የምንዝርና እሳት ግን፣ የምን ያህል ሰዎችን ነፍሳት እንዳጠፋ በመገናኛ ብዙኃን እንኳ ባይለፈፍለትም፣ አካባቢያችንን ብቻ በመቃኘት ልናየው እንችላለን፡፡ ግዙፍ እሳት ሲነካን በፍጥነት ከእርሱ እንሸሻለን፡፡ ምክንያቱም ስለሚፈጀንና ኃይሉም ስለሚሰማን ነው፡፡ ምንዝርና ግን መፋጀቱ ሲገኙበት ሳይሆን ኋላ ነው፤ ስቃዩ እያደር የሚሰማ ስለሆነ፣ እያታለለ ለረጅም ዘመናት በእርሱ ውስጥ እንድንቆይ ለማድረግ ይችላል፡፡ ከሁሉ የከፋ አደገኛ የሚያደርገውም ይህ ጠባዩ ነው፡- ነፍስን ለዘላለማዊ የጥፋት እሳት እያዘጋጀ ሳለ ትኩሳቱንና መርዙን መሸፋፈን ይችላል፡፡ ወዳጅ ተመስሎ ነፍስን ያመነምናል፡፡ ነፍስና ሥጋን ጭራሽ ካወደመ በኋላ ትኩሳቱን ማሰማት ይጀምራል፡፡ ያን ጊዜ ግን የማምለጫ ሰዓት አይሆንም፤ ምክንያቱም እግሮች ተቃጥለዋል፤ ኃይል ተሟጦ አልቋል፡፡ ቀሪው ከተስፋ መቁረጥ ጋር ወዳበረታውና ማለቂያ ወደሌለው ዘለዓለማዊ እሳት ዓይን እያየ ጆሮ እየሰማ መግባት ብቻ ነው፡፡
አንዲት እንቁራሪትን በሚፋጅ ውኃ ውስጥ ብንከታት ወዲያውኑ ዘላ ትወጣለች፡፡ ምክንያቱም ሙቀቱ ቶሎ ስለሚሰማት ነው፡፡ ነገር ግን በቀዝቃዛ ውኃ ውስጥ ከከተትናት በኋላ፣ ውኃውን በጣም ቀስ ብለን እያሞቅነው ብንሄድና እስከሚፋጅ ድረስ ብናደርሰው፣ ሙቀቱን እርሷም ቀስ በቀስ እየለመደችው ደስ እያላትም ትቆያለች፡፡ መፋጀት በሚጀምርበት ጊዜም እንኳ ሳይታወቃት በውኃው ውስጥ ትዝናናለች፡፡ ለምን? ቢባል ተላምዳዋለቻ! ዳሩ ምን ያደርጋል፣ ሲለበልባት ዘላ ለመውጣትም ብትሞክርም ኃይሉ አድክሞአት ይቆይና እዚያው ትቀራለች፡፡ ምንዝርናም እንዲሁ ነው፡፡ ትኩሳቱ በፊት አስቀድሞ ቢሰማው ኖሮ አመንዝራው ዘሎ በወጣ ነበር፡፡ ግን እየጣፈጠው ሳይታወቀው እሳቱን እየታቀፈ ይኖርና፣ አንድ ቀን በዚያው ሁኔታ ወደባሰው ግለት ይሸጋገራል፡፡ ሰሎሞን እንዳለው ምንዝርና የአእምሮና የነፍስ ቀውስ ነው፤ በመጨረሻ የሚያስከፍለው ዋጋው እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ ይኸውም የነፍስ ጥፋት ነው፡፡ ጥፋቱም ዘለዓለማዊ ነው፡፡
የከበሩና ትልልቅ ስጦታዎች ብዙ የአያያዝ ጥንቃቄን ይጠይቃሉ፡፡ የፍትወተ ሥጋ ስሜትም፣ ለትልቅ አገልግሎት ለሰው ከእግዚአብሔር የተሰጠው ስጦታ እንደመሆኑ መጠን በጥንቃቄ ጥቅም ላይ መዋል ይገባዋል፡፡ በቀላሉ ሊበላሽ የሚችልም ተሰባሪ ነገር ነው፡፡ ሰው በራሱ ችሎታና ኃይል ብቻ ተደግፎ ሊጠብቀውና በትክክል ሥራ ላይ ሊያውለው አይችልም፡፡ ስለዚህም የአምላኩን እርዳታ በመጠየቅ፣ በእርሱ አመራር ስር ራሱን አስገዝቶ ሊጠቀምበት ይገባዋል፡፡ እግዚአብሔርም እኛን ለመርዳት ዘወትር ዝግጁ ነው፡፡ ከለመንነው የድጋፍ ኃይሉን ይሰጠናል፡፡ የፍትወት እሳታችንን ለመደምሰስ ወይም ለማጥፋት ሳይሆን በትክክል ለመቆጣጠርና በሥራ ላይ ለማዋል የሚሰጠን ኃይልም መለኮታዊ እሳቱን ነው፡፡ ምክንያቱም መለኮታዊው እሳት ፍጥረታዊውን እሳት ይገራዋል፣ ይመራዋል፣ በትክክል አገልግሎት ላይ እንዲውል ሊያደርገውም ይችላል፡፡
 ከሲታውያን መነኰሳት በኢትዮጵያ  በፈቃድ የተወሰደ