Wednesday, April 4, 2012

ኑሮ በአገርኛ፤ ጾም ይበዛበታል!

 በፍቄ ከአዲስ አበባ፣

ባሕር ማዶ ካሉ ሰዎችጋ ስናወራ አንዳንድ የማይገቡን ወሬዎችን እየሰማን ጭንቅላታችንን እየናጥንወቸ ጉድ!” ማለታችን አይቀሬ ነው፡፡ ለኛ ባዳ ከሆነው ከቀላሉ “GPS” ጀምሮ፣ credit card ቢሉ፣ ምን ቢሉ ሁሉም ለኛ እንቆቅልሾች ናቸው፡፡ ወጉ ቀርቶብኝ በቅጡ በኮነነኝ እንዲሉ “GPS” ቀርቶብኝ እበላው ባገኘሁ የሚለው እስኪታወሰን ድረስ እንደመማለን፡፡ እዚህ GPS የለም፣ credit card የለም፣ ባቡር (ወይም subway station ብሎ ቋንቋ) የለም፣ smart phone የለም፣ wi-fi የለም (አለ እንዴ?) ለነገሩ የዚህ ጫወታ ጉዳዮች እነዚህ ሁሉ ስላልሆኑ እንኳን ደስ ያላችሁ፡፡ በርግጥ ግን ወደጫወታው አጀንዳ ለመድረስ አሁንም ዳር፣ ዳሩን መነካካት የግድ ነው፡፡አሜሪካኖች ለምን ወፋፍራም ሆኑ? ኢትዮጵያውያኖች ለምን ቀጫጭን ሆኑ?› ብለን ብንጀምርስ!
ያልተመጣጠነ ውፍረት 75 በመቶ አሜሪካውያን የጤና እክል እየፈጠረ ነው፤ 75 በመቶ ኢትዮጵያውያን ደግሞ (ይህ ቁጥር በጥናት አልተረጋገጠም እንጂ፣) ችግራችን ቅጥነት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ obesity ሳይሆን በምግብ እጥረት፣ በጨጓራ ሕመም የሚሰቃዩ ሰዎችን ነው ማግኘት የሚቻለው፡፡ ለምን ብለን የጠየቅን እንደሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በስልጣናቸው አፍላ ዘመን ቃል በገቡት መሠረትበቀን ሦስቴ መብላትባለመቻላችን ነው፡፡ በቀን ሦስቴ መብላት ማለት አሰሱን ገሰሱን ማግበስበስ ማለት አይደለም፡፡ በሦስተኛ ክፍል ሳይንስ ላይ እንደተማርነው የተመጣጠነ ምግብ መብላት ማለት ነው፡፡ የተመጣጠነ ምግብ ደግሞ ፕሮቲን፣ ካርቦሃይድሬት፣ ፋት፣ ቫይታሚኖችና ማዕድኖችን መያዝ አለበት፡፡

የኢትዮጵያውያንን አመጋገብ በጥቅሉ በአንድ መስመር መተረክ ይቻላል፡፡ ቁርስ፤ ዳቦ በሻይ (ሻይ ከተገኘ!) ምሳ፤ እንጀራ በሽሮ ወጥ፣ እራት፤ እንጀራ በሽሮ ወጥ፡፡ በዚህ የአመጋገብ ልምድ ውስጥ የሚካተቱት ጤፍ፣ ስንዴ፣ ባቄላ እና ውሃ ናቸው፡፡ በርግጥ በስንዴ ውስጥ ካርቦሃይድሬት፣ በጤፍ ውስጥ iron (ብረት ነክ ማዕድን) በባቄላ ውስጥ ፕሮቲን አለ፡፡ ፋት ግን ምናልባት እንደሽሮፕ በማንኪያ በምትጨመረው ዘይት ውስጥ ካልሆነ በቀር የለም፤ ስለዚህ የሚያወፍረን ምንም ነገር የለም፡፡ በምግብ ዝርዝራችን ውስጥ የሚያወፍር ነገር አለመኖሩ እሰዬው፣ ነገር ግን በሽታ የመከላከል አቅማችንን የሚያጎለብት÷ የፍራፍሬና የአትክልት dessert እንዳይኖር እርጥብ አገራችንን ያደረቃት ማነው?

የልምድ Vegetarians
ኢትዮጵያውያን የኑሮ ነገር ሁኖብን ከጥንትም ጀምሮ የምንመገበው የምግብ ዓይነት vegetarian የሚያሰኘን ነው፡፡ የጤፍና ባቄላ ድምር!!! በርግጥ ብዙዎቻችን የምግብ ምርጫችን ምን እንደሆነ ስንጠየቅ ቁርጥ ወይም ክትፎ ልንል እንችላለን፡፡ የምግብ ምርጫችን ግን አምሮታችን እንጂ÷ ‘የምናዘወትረው የምግብ ዓይነት ነውየሚል ትርጉም እንደሌለው ሁላችንም ይገባናል፡፡

ቬጂቴሪያንነትም ሆነ ቅጥነት ዕድሜን እንደሚቀጥል ምሁራኑ ይናገራሉ፤ ይሁን እንጂ የወፋፍራሞቹ አሜሪካውያን አማካይ ዕድሜ 70 ሲዘልቅ፣ የቀጫጭኖቹና የልምድ ቬጂቴሪያኖቹ ኢትዮጵያውያን ዕድሜ ግን ሃምሳ መድረስ አቅቶታል፡፡የዘመኑ ምርጫ፣ ምን እና ቀጫጫየተባለውን እውነታ አፈርድሜ አስበልቶ፣ ውፍረትን እንደምቾትና እንደጤነኝነት ባገራችን እንዲቆጠር ያደረገው ማነው?

ምግብ አጥቂውን ነው የሚያጠቃው
ይህች አባባል አገልግሎት ላይ የምትውለው ብዙ በሊታ ከሲታዎችን ለመተቸት ነው፡፡ ይሁን እንጂእውን በሊታ ከሲታዎች አሉ?› ብለን ከጠየቅን ውዥንብር ውስጥ መውደቃችን አይቀሬ ነው፡፡ አንዳንዴ አሰሱን ገሰሱን ማግበስበስ ሆድን ከመቆዘርና፣ ጨጓራን ለበሽታ ከመዳረግ ያለፈ ፋይዳ የለውም፡፡

ምግብ አጥቂውን ነው የሚያጠቃውየሚለው አባባል እንደየሃገሩ የተለያየ ትርጉም ይኖረዋል፡፡ ምንም እንኳን እኛጋ ብዙ የሚበሉት ናቸው የሚከሱት ብሎ ለመሳለቅ ቢያገለግልም፤ ወፋፍራሞቹ ዓለም ግን ብዙ መብላት ለውፍረት፤ ውፍረት ደግሞ ለበሽታ ወይም ሞት ይዳርጋል የሚል አንድምታ አለው፡፡ ዞሮ ዞሮ ምግብ አጥቂውን ነው የሚያጠቃው፡፡

እኛ አገር ግን ምግብ ይከበራል፡፡ገበታ ንጉሥ ነውነው ከነአባባሉ፡፡ ሁሉም ንጉሥ ከሚሊዮን አንድ ነው፤ ታዲያ ገበታን ከንጉሥ እኩል ምን አደረገው ብለን ስንጠይቅ መልስ ሊሆን የሚችለውገበታ በሃገራችን ከሚሊዮን አንድ ነውየሚል ይሆናል፡፡ ሌላው ዓለም በሌለ መልኩ ኢትዮጵያ ውስጥ ምግብ ከንጉሥ እኩል ይከበራል፣ ይዘፈንለታል፡፡ በዘፈን ክሊፖቻችን ሳይቀር ለእንቁልልጭ ይቀርባል፡፡ ለምን? ምግብ ብርቅ ነዋ! ምግብን ከጥንት እስከዛሬ በሃገራችን ብርቅ ሆኖ እንዲቀር ያደረገው ማነው?


 ማነውማነው?
ኢትዮጵያ ውስጥ ሁለት ዓይነት ጾመኞች አሉ፡፡ የውዴታ እና የግዴታ! በሃይማኖታዊ ሰበብ የሚጾሙት ምናልባት ወደጽድቅ ይጠጋሉ፡፡ ሳይጾሙ በእጦት የሚጾሙት ደግሞ ባይኮነኑም ይህ እንደበጎ ምግባር ተቆጥሮ ለጽድቅ ነጥብ አያስይዝላቸውም፡፡ የሆነ ሆኖ ኢትዮጵያውያን (በተለይም ከተሜዎቹ) ከገቢያቸው በአማካይ 60 በመቶ ለምግብ ያወጣሉ፡፡ (ገጠሬዎቹ አንዳንዴ ገቢያቸው ሆዳቸው ላይ ብቻ ሊውል ይችላል!) ይሄ አማካይ ለብዙሐኑና ገቢያቸው ዝቅተኛ ለሆነ ሰዎች ገላጭ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ምግብ ውድ ነው፡፡ ሙሉ ገቢያቸውን ለምግብ ብቻ የሚያውሉ ዜጎች አሉ፡፡ ሠርቶ ለምግብ ይሏችኋል ይሄው ነው፡፡
በአሜሪካ የማክዶናልድን በርገር (እዚያ በርገር ለምሳ መዳረሻ መሆኑን ልብ ይሏል!) 2 ዶላር በላይ አይከፍሉም፡፡ እኛ አገር በርገር ከተበላ፣ ምሳ ተበላ ማለት ቢሆንም ዋጋው (በማክዶናልድ ደረጃ ካሰብነው፤) 40 ብርስ ይገኛል? አንዳንዶች ዶላርን በብር እየመነዘሩ ተመጣጣኝ ነው ሊሉ ይዳዳቸዋል፡፡ እነዚህ ሰዎች ያልገባቸው ነገር፣ ኢትዮጵያውያን ምንዳ የሚከፈላቸውም ሆነ የሚገበያዩት በብር መሆኑ ነው፡፡ 80 በመቶ ሕዝቦቿ አርሶ እና አርብቶ አደር በሆኑባት አገር ውስጥ ውዱ ነገር ምግብ መሆኑ አያሳዝንም? ግብርና መር ኢንዱስትሪ እየተከተልኩ ነው በምትል ሃገር ውስጥ በምግብ ራስን መቻል ቀርቶ ዘመናዊ የከተማ ችጋር ሰንሰለት ውስጥ መግባት፣ ባለሰማያዊ መስታወት ፎቆች እና የቀለበት መንገድ ስር ራሱን በራሱ የሚፈጭ ጨጓራ ይዘው የሚንከራተቱ ዜጎችን ማፍራትስ የማን ጥፋት ነው? ‘ከነገሩ፤ ጦም እደሩብለን ካልተውነው በስተቀር ከድህነት አረንቋችን እንዳንላቀቅ የሁለት አሥርት ዓመታት ድርሻውን የተጫወተው ማን እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት የኑሮ ውድነቱ መንስኤ የውጭ (ያደጉ ሃገራት) የኢኮኖሚ ቀውስ ነው ይለናል፡፡ የዋጋ ንረቱ አንደኛ ተጠያቂ ግን በሃገር ውስጥ የሚመረተው ምግብ ነው፡፡ ለዚህ እማኝ መጥቀስ ካስፈለገ የአክሰስ ካፒታል የምርምር ክንፍ ያወጣውን ሪፖርት ማገላበጥ ይቻላል፡፡ በጥናቱ ውስጥ አገራችን ከቤላሩስ ቀጥሎ በዓለማችን ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት በማስተናገድ ላይ ያለች ሁለተኛዋ አገር ተብላ ተጠቅሳለች፡፡ (በነገራችን ላይ የአክሰስ ካፒታል መስራች አቶ ኤርምያስ አመልጋ ከብሔራዊ ባንክ ጋር የተቀያየሙትበማያገባቸውየአገር ጉዳይ ስለሚገቡ ይሆን እንዴ?)

የዋጋ ግሽበቱ ዓመታዊ ንጽጽር በጥር ወር በጣት በሚቆጠሩ ፐርሰንቶች መቀነሱን አስመልክቶ ጠቅላይ ሚኒስትሩ (ጉዳዩን አስቀድመው ለሰሙት የፓርቲ አጋሮቻቸው) በፓርላማ በኩል ሲናገሩ÷ የመንግስት እርምጃዎች ውጤት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ እውነታው ግን ሌላ ነው፡፡ አርሶ አደሮቻችን ምርታቸውን ለገበያ በገፍ የሚያቀርቡት ከታሕሳስ ወር ጀምሮ በመሆኑ፣ በጥር ወር የእህል ዋጋ በመጠኑ መቀነሱ የተለመደ ታሪካችን ነው፡፡ የዋጋ ግሽበቱ ዓመታዊ ንጽጽርም የዚሁ የአርሶ አደሮቻችን ውጤት አንጂ የመንግስት ግራ ገብቶት፣ ግራ የሚያጋባን ፖሊሲ ውጤት አለመሆኑን ግንቦት ላይ የምንመለስበት ይሆናል፡፡

ወቅቱ የጾም ነው፣ ስለምግብ ይህን ያህል ማውራት አልነበረብኝም፡፡ ነገር ግን ፋሲካ ይመጣል፡፡ ፋሲካ ሲመጣ ብቻውን አይመጣም፤ የመብላት ፍላጎት ይዞ ይመጣል፡፡ ወሩ ደግሞ ግንቦት የሚቃረብበት ነው፡፡ ገበሬዎች ለመጪው ክረምት እህላቸውን ይቆጥባሉ፡፡ እንደተለመደው የምግብ ዋጋ ይንራል፤ ኑሮ ያሻቅባል፡፡ እንደተለመደው የዘንድሮም ፋሲካ ከአምናው የከፋ ይሆናል፡፡ እንደተለመደው እስከመች ይኖራል?

እንደተለመደው ሳይሆን የተሻለ ኑሮ ለመኖር፣ ፋሲካንም ለመፈሰክ፣ መፈንቅለ መንግስት ብቻ ሳይሆን መፈንቅለ አእምሮም ያስፈልገናል፡፡ [አሁን ደግሞ እመርቃችኋለሁ፤] ሁለት ወር ሁዳዴ፣ ስለሰማዩ መንግስታችን ብቻ ሳይሆን ስለምድራዊው መብታችንም በአርምሞ የምናስብበት ይሁን፣ ያለመንግስት ተመርታ የማታውቀው ሃገራችን በሕዝቦቿ ፈቃደኝነት የምትመራበት ዘመንን የሚያመጣ አዕምሮይስጠን መጾም መጸለይ ብቻ ሳይሆን መሥራትና መታገልም እንወቅበት፣ ፋሲካ ብቻ ሳይሆን freedom ይናፍቀን፣ ስልጣኔም ይናፍቀን፡፡ አሜን!
Befqe.blogspot.com