Sunday, May 6, 2012

"ማኅበረ ቅዱሳን" በአርቤጎና ከተማ ጥዋ ማኅበራትን በአንድነት ስም ለመጨፍለቅ ያደረገው እንቅስቃሴ ተቃውሞ ገጠመው


                                     source:http://dejeselaam-dejeselaam.blogspot.com
 "ማኅበረ ቅዱሳን" በሲዳማ፣ ጌዴኦ፣ አማሮና ቡርጂ ሀገረ ስብከት፣ በአርቤጎና ከተማ በሚገኘው የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ሥር ያሉትን ልዩ ልዩ የጥዋ ማኅበራትን በአንድ ጥላ ሥር ለማደራጀት ሙከራ ቢያደርግም ተቃውሞ እንደተነሳበት ከአካባቢው የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡ የጥዋ ማኅበራት መመሥረትና መደራጀት እንዲሁም የምዕመናን መሰባሰብ እንደጦር የሚያስፈራው "ማኅበረ ቅዱሳን" በተለያዩ ፃድቃን፣ ሰማዕታትና መላዕክት ስም የተመሠረቱትን የጥዋ ማኅበራት በማፍረስ እንቅስቃሴ መጠመዱን በተጨማሪ የደረሰን መረጃ ያሰረዳል፡፡

የአርቤጎና ከተማ አማንያን በተለያዩ የጥዋ ማኀበራት ተደራጅተው ለዘመናት የቆዩ ሲሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአንድ ተደራጁ የሚለው "ማኅበረ ቅዱሳን" መመሪያ በከፍተኛ መደናገር ውስጥ እንደከተታቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡
"ማኅበረ ቅዱሳን" የጥዋ ማኅበራትን ለመጨፍለቅ ሙከራ ሲያደርግ የመጀመሪያ ጊዜው አይደለም ያሉ ወገኖች እንዳስረዱት፣ ቀደም ሲል በሀዋሳ ከተማ በሚገኘው የቅዱስ ገብርኤል ገዳምም ተመሳሳይ እንቅስቃሴ አድርጎ የከሸፈበት መሆኑ በተጨማሪ ታውቋል፡፡ በገዳሙ እሰከ 40 የሚደርሱ የጥዋ ማኅበራት የሚገኙ ሲሆን በቅድስት አርሴማ፣ በኪዳነ ምሕረት፣ በቅዱስ ገብርኤል እና በቅዱስ ሚካኤል ስም ብቻ እስከ አሥር፣ አሥር የሚደርሱ የጥዋ ማኅበራት ያሉ ሲሆን፣ ሌሎች የጥዋ ማኅበራትም ተደራጅተው በእህትማማችና በወንድማማች መንፈስ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ፡፡
ሆኖም "ማኅበረ ቅዱሳን" በገዳሙ ሰበካ ጉባዔ በኩል ሰርጎ በመግባት ለቁጥጥር ያመቸኛል በሚል ማታለያ አንድ ላይ ለመጠፍጠፍ ሙከራ ቢያደርግም የየጥዋ ማኅበራቱ ዓላማ፣ የካፒታል አቅም፣ የአባላት ስብጥር፣ ዕድሜ፣ ጾታ፣ የትምህርት ደረጃ፣ የርስ በርስ ትውውቅና መንፈሳዊ ጥንካሬ የተለያየ በመሆኑ ማኅበራቱን አፍርሶ በአንድ ለማጠቃለል ያደረገው ሙከራ ሳይሳካለት ቀርቷል፡፡ ይሁን እንጂ፣ "ማኅበሩ" ጀብደኝነትና በካህናቱ ንዝህላልነት የተቆጡ አንዳንድ ማኅበራት በየቤታቸው በዙር ለመሰባሰብ ቅጥር ግቢውን ለቀው የወጡ መሆኑን መረጃ ደርሶናል፡፡
 የጥዋ ማኅበራት ፃድቃንን፣ ሰማዕታትን፣ መላዕክትንና ፈጣሪ አምላካችንን ለመዘከር ቢመሠረቱም የአባላት ስብጥራቸው ግን ሊለያይ ይችላል ያሉ ታዛቢዎች እንደሚሉት፣ ጥዋ ማኅበራት በሀገር ተወላጆች፣ በወንዶች ብቻ፣ በሴቶች ብቻ፣ በሁለቱም ጾታ፣ በታዳጊ ወጣቶች፣ በወጣቶች፣ በአዛውንቶች፣ በመሥሪያ ቤት ወዘተ በመቀራረብና በመደጋገፍ ዙሪያም ጉዳት ያለባቸውን ወገኖች በመርዳት፣ በሐዘን፣ በደስታ፣ በተለያዩ ዓላማዎች ላይ ተመሥርተው ሊቋቋሙ ይችላሉ፡፡ በዚያ ላይ፣ የገብርኤልን ከማርያም፣ የመድኃኔዓለምን ከሚካኤል፣ የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስን ከጊዮርጊስ፣ አጣምሮ የማዋሃድ ሃሳብ ከየት የመጣ እንደሆነም ግራ የሚያጋባ ነው ተብሏል፡፡

"ማኅበረ ቅዱሳን" በሊቃነጳጳሳት ቸልተኝነት በገጠር እስከሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ድረስ ዘልቆ በመግባት ጠቅላላ የቤተክርስቲያኒቱን መዋቅር ከላይ እስከ ታች የተቆጣጠረ ሲሆን፣ ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን እንደአረም አንቆ በመያዝ በጥፋት ጎዳና ላይ እየመራት ከመሆኑም በላይ ራሱን እንደጥገኛ ህዋስ ከቤተክርስቲያን ጋር አጣብቆ የሚንቀሳቀስ ፖለቲካዊ ድርጅት መሆኑ የብዙዎች እምነት ነው፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!!!
አሜን!!!