Monday, May 7, 2012

የሰንበት ማደራጃና መምሪያ ኃላፊ የነበሩት አባ ኅሩይ ከሥልጣናቸው ተነሱ

                                source: http://awdemihret.blogspot.com
አቀርቅሮ ወጊውና የማቅ ቀኝ እጅ መሆናቸውን በይፋ ያረጋገጡት የሰንበት ማደራጃና መምሪያ ኃላፊ የነበሩት አባ ኅሩይ ከሥልጣናቸው ተነሱ፡፡ በምትካቸውም መምህር ዕንቁባህሪ ተተክተዋል፡፡  እጅግ በሆነ መሰሪ አቀራረብ የሰንበት ማደራጃውን ሚስጢር ለማኅበረ ቅዱሳን አሳልፈው እየሰጡ ቤተክርስቲያንና ማደራጃውን ወደ ማቅ አቅጣጫ እየመሩ የነበሩት አባ ኅሩይ መነሳታቸው ለእውነተኛ የቤተክርስቲያን ልጆች እጅግ አስደሳች ዜናና የጸሎታቸውምም ምላሽ ነው፡፡
ስልጣን ላይ ከወጡበት ጊዜ ጀምሮ በድብቅ የማቅ ተላላኪ በመሆን የሰንበት ማደራጃውን አሰራር በሙሉ ለማቅ ለማስረከብ ተዘጋጅተው የነበሩት አባ ኅሩይ ከዚህ በፊት አብረውኝ የሚሰሩ ሰዎች ሁሉ በስራዬ ላይ እንቅፋት ስለሆኑ ይነሱልኝ ብለው ጠይቀው እንደነበር ይታወቃል፡፡ በወቅቱ ጥያቄያቸው ምላሽ አግኝቶ ቢሆን ኖሮ በቦታው ላይ የሚተኩት ሰዎች በማቅ በኩል ተዘጋጅቶላቸው ነበር፡፡ እኝህ ሰው እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ ከነበሩበት ጊዜ ጀምሮ ዜግነት እስተቀበሉባት አሜሪካ ድረስ መፍቀሬ ንዋይነታቸው በእጅጉ የታወቀ ስለነበር በሰንበት ማደራጀው ላይ በተሾሙ ጊዜ፤ ሹመታቸው ብዙዎችን የቤተክርስቲያን ልጆች አሳዝኖ  ነበር፡፡ የሰውየውን የባህሪ ክፍተት አሜሪካ ባሉ ባልደረቦቻቸው የሰሙት የማቅ አመራር አባላት አባ ኅሩይ አዲስ አበባ በገቡ ጊዜ በቀላሉ በማግኘትና የንዋይ ፍቅራቸውን በማርካት ከጎናቸው እንዲቆሙ አድርገዋቸዋል፡፡ ከዛም ቤተክርስቲያንን የሚጎዳ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ እንደነበር ይታወቃል፡፡
በቅርቡ እንኳ ማቅን በሚመለከት የአሰራርን ግልጽነት ለማስረጽ የሚረዳ ደብዳቤ እንደይወጣ ማህተም ይዞ እስከመሰወር የደረሰ አሳፋሪ ድርጊት የፈጸሙ ሰው ናቸው፡፡ ከዛ ጊዜም በኋላ በስራ ገበታቸው ላይ ያልተገኙ ሲሆን ከሰዎች ጋር ያላቸውም ግንኙነት በስልክ ብቻ የተወሰነ ነበር፡፡ የእለት ዕለት የስራ ዕንቅስቃሴ የሚያስፈልገው የማደራጃ መምሪያው የስራ ገበታ ክፍት ስለሆነና የሰውየውም አካሄድ አደገኛ በመሆኑ መነሳታቸው አስፈላጊ ሆኗል፡፡
በአባ ኅሩይ ቦታ የተሾሙት መምህር ዕንቁባህሪ ሲሆኑ እሳቸውም ከዚህ ቀደም በመምሪያው ኃላፊነት የሰሩና እስካሁንም ድረስ ደግሞ በምክትል ኃላፊነት የቆዩ ሰው ናቸው፡፡ ለመምህር እንቁባህሪም የሹመቱ ደብዳቤ የደረሳቸው መሆኑ ተረጋግጧል፡፡