Thursday, May 24, 2012

በፍርድ ፈንታ ደም ማፍሰስ በጽድቅ ፈንታ ጩኸት(ኢሳ. 5÷7)


                      ምንጭ፦ቤተ ጳውሎስ ብሎግ  

አንዲት ሕጻን ልጅ ሞታ የጎጃሟ አልቃሽ፡-
                         ምን ዓይነት ቄስ ናቸው የማይጠብቁ ዕቃ
                      እበተስኪያን ጓሮ እጣኒቱ ወድቃ
በማለት የሀዘን ቅኔ (ሙሾ) አሰምታለች፡፡ የቄሱ አንዱ ሥራ ዕጣን መጠበቅ ሲሆን ዋነኛው ሥራቸው ግን ሕጻናትን መጠበቅ ወይም ማሳደግ ነው፡፡ ሕፃናት ከቤተ ክርስቲያን አደባባይ ሊቀመጡ አባቶቻቸውን እያዩ ሊማሩ ሲገባ ከቤተ ክርስቲያን ጓሮ ከመቃብር ውስጥ ሲወድቁ ማየት አሳዛኝ ነው፡፡ አልቃሿ በሕፃናት ማለቅ ቀሳውስቱ ለምን አይጸልዩም ማለቷ ሲሆን ከዚያ ባሻገር ግን ትውልድን ለምን ይቀጫሉ? ማለቷ ነው፡፡ አባቶች አደራቸውን ባለመወጣታቸው ትውልዳችን የሞት ልጅ ሆኗል፡፡ ራሱን በራሱ እየመራ የዘመን ምርኮኛ፣ የኃጢአት ግዞተኛ ሆኗል፡፡ ይልቁንም በአባቶች ፈንታ እንዲተኩ ከዐውደ ምሕረቱ ሊቀርቡ የሚገባቸው ወጣቶች እየተገፉ ወደ መቃብር ስፍራ መውረዳቸው ዛሬም ልብ ያለውን የሚያስለቅስ ነው፡፡
ነቢዩ ኢሳይያስም፡- “አሁን ስለ ወዳጄና ስለ ወይን ቦታው ለወዳጄ ቅኔ እቀኛለሁብሏል (ኢሳ. 5÷1)፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ ለእግዚአብሔር አዝኖ ወዳጅነቱን ለመግለጥ የሀዘን ሙሾ አሰምቷል፡፡ ስለ ወዳጅ ይለቀሳል፡፡ ወዳጅ በሞት ስለተለየ ብቻ ሳይሆን የጠበቀው እንዳልጠበቀው ሲሆንበት ይልቁንም ልጁን በሞት ሲያጣ ለወዳጅ ይለቀሳል፡፡ እግዚአብሔር ሕያው ወዳጅ ነው፤ ነቢዩ ኢሳይያስ ግን ያለቀሰው ሞትን ስለመረጡት ትውልዶች ነው፡፡ እግዚአብሔር መንግሥቱ የማይነካ ነው፤ ነቢዩ ኢሳይያስ ግን ያለቀሰው ከእግዚአብሔር ፍቅር ለተፈናቀሉት ነው፡፡ እግዚአብሔር የማይጎድልበት ነው፤ ነቢዩ ኢሳይያስ ግን ያለቀሰው ሰላማቸውን ስላላወቁ ሕዝቦች ነው፡፡ በእውነት ካጣ ሰው ይልቅ አግኝቶ ያላወቀበት እጅግ ሊለቀስለት ይገባል፡፡ እግዚአብሔርን ያህል ጌታ ለገፉ፣ ገነትን ታህል ቦታ ችላ ላሉ ልቅሶ ይገባል፡፡ ኢሳይያስ ግን ያለቀሰው ለሟቾቹ ሳይሆን ለወዳጁ ለእግዚአብሔር ነው፡፡ የሰው ልጆች እንዳፈቀራቸው አለመገኘታቸው፣ እንዳደረገላቸው አለማመስገናቸውን ባሰበ ጊዜ ለወዳጁ አለቀሰ፡፡


እግዚአብሔር ለሕዝቡ ያደረገው እንክብካቤ ሊገለጥ የማይችል ነው፡፡ ኢሳይያስ ይህን ሲገልጥ፡- “ለወዳጄ በፍሬያማው ኮረብታ ላይ የወይን ቦታ ነበረው፡፡ በዙሪያው ቈፈረ÷ ድንጋዮችንም ለቅሞ አወጣ÷ ምርጥ የሆነውንም አረግ ተከለበት በመካከሉም ግንብ ሠራ፡፡ ደግሞም የመጥመቂያ ጒድጓድ ማሰበት፤ ወይንንም ያፈራ ዘንድ ተማመነ÷ ዳሩ ግን ሆምጣጣ ፍሬ አፈራይላል (ኢሳ. 5÷1-2)፡፡
እግዚአብሔርን ወዳጅ አለው፡፡ እንደ እግዚአብሔር ያለ ወዳጅም ከቶ አይገኝም፡፡ ከሰዎች ወገን የነገ ወዳጃችን ማን መሆኑን መናገር አንችልም፡፡ እግዚአብሔር ግን የዘላለም ወዳጃችን ነው፡፡ ቃሉ፡- “ኢየሱስም ከፋሲካ በዓል በፊት÷ ከዚህ ዓለም ወደ አብ የሚሄድበት ሰዓት እንደ ደረሰ አውቆ÷ በዚህ ዓለም ያሉትን ወገኖቹን የወደዳቸውን እስከ መጨረሻው ወደዳቸውይላል(ዮሐ. 13÷1)፡፡ እስከ መጨረሻው የሚወድ እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ ወዳጅ ገበና ሸፋኝ፣ ምሥጢር ጠባቂ ነው፡፡ እግዚአብሔርም ኃጢአታችንን የከደነ፣ ከልብስ ከቤት ከእናት ይልቅ የሸፋፈነን ነው፡፡ ወዳጅ ያለው አይራቆትም፣ ድካሙ በአደባባይ አይወጣም፡፡ እግዚአብሔር የጓዳ ሽባዎቹን የአደባባይ ጀግና እያደረገ ያቆመናል፡፡ ወዳጅ ያለው ተከራካሪ አለው፡፡ እግዚአብሔርም በከሳሾች ፊት የሚሟገትልን የጠላቶቻችንን ጉባዔ እየደባለቀ ከምክራቸው የሚያድነን ነው፡፡ ወዳጅ ከወንድም ይልቅ የሚጠጋጋ ነው፡፡ ማሰሪያው የሥጋ ሳይሆን የነፍስ ነውና፡፡ እግዚአብሔርም ከእናት ይልቅ ቅርብ ከአባት ይልቅ አሳቢ ነው፡፡ ወዳጅ ያለው አይከፋም፣ እግዚአብሔርም መጽናናታችን ነው፡፡ በአጠቃላይ የወዳጅ ወዳጅ እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ የሰዎች መልካምነታቸው በቶሎ ያልቃል የእግዚአብሔር መልካምነቱ ግን ለዘላለም ይኖራል፡፡
ፍሬያማው ኮረብታ፡- ፍሬያማው ኮረብታ መንፈሳዊ ዓለም ነው፡፡ መንፈሳዊው ዓለም የብዙ ጀግኖች የእግር ዱካ ያረፈበት፣ የእምነት ገበሬዎቹ ብዙ ያፈሩበት ነው፡፡ በመንፈሳዊው ኮረብታ የጨነገፉ፣ ደግሞም ከፍሬ የመከኑ የሉም፡፡ የአንዱ ሠላሣ ፍሬ፣ የሌላው መቶ መሆኑ ነው እንጂ ሁሉም ፍሬ አለው፡፡ ፍሬ አልባ በለሶች በመንፈሳዊው ኮረብታ የሉም፡፡  መንፈሳዊው ኮረብታ ላይ እነ አቤል፣ እነ ኖኅ፣ እነ አብርሃም፣ይታያሉ፡፡ እግዚአብሔር ለእነዚህ ቡሩካን ያሳየውን ቸርነት፣ ያደረገውን ጥሪ ለእስራኤልም አላጓደለም፡፡ ስለዚህ ከጠላት ጋር ተዋግቶ እስራኤልን ከግብፅ ባርነት አውጥቷል፡፡ ከግብፅ ባርነት ያወጣትም የአምልኮ ሕዝብ፣ የንጉሥ ካህን እንድትሆን እንጂ ለሥጋ ዓላማ ብቻ አልነበረም፡፡ ያቺ የወይን ቦታ እስራኤል ናት፡፡ ዳዊት፡- “ከግብፅ የወይን ግንድ አመጣህ፤ አሕዛብን አባረርህ እርስዋንም ተከልህ” (መዝ. 79÷7) ብሏል፡፡
ወይን መባሉ ይደንቃል፡፡ ወይን የከበረ ፍሬ ነው፡፡ እግዚአብሔርም ሕዝቡን ያከብራል፡፡ አክባሪያችን ይጠብቅብናል፡፡ ሁላችንም ብንሆን ከምናከብራቸው የምንጠብቃቸው ነገሮች አሉ፡፡ እግዚአብሔር ከእኛ የሚጠብቀው ስለሚያከብረን ነው፡፡ ወይን እንደ ሌሎቹ ፍሬዎች ሳይሆን ልዩ እንክብካቤ ይፈልጋል፡፡
ወይን ቦታ ይፈልጋል፡- ወይን ማንኛውም ቦታ የሚያፈራ ሳይሆን ቦታ ይፈልጋል፡፡ መንፈሳዊነትም የራሱ የሆነ ቦታ ይፈልጋል፡፡ ይህ ማለት ከሌሎች ጋር ኅብረት ማድረግ፣ ቃሉን መስማት ብለን ልንተረጉመው እንችላለን፡፡
ወይን ውሃ ይፈልጋል፡- ስለዚህ ከወይኑ አጠገብ ጉድጓድ ተቆፍሮ ውሃ መጠራቀም አለበት፡፡ በክረምት ወይም በበልግ ዝናብ ብቻ አያፈራም፡፡ እንዲሁም መንፈሳዊ ሕይወት እንደ ዓመት በዓል በየዓመቱ በየመንፈቁ ወደ ቤተ ክርስቲያን በመሄድ ብቻ ለፍሬ አይበቃም፡፡ክርስትና በዓመት አንድ ጊዜ የምንቆርሰው የልደት ኬክ ሳይሆን በየዕለቱ የምንመገበው እንጀራ ነው፡፡
ወይን አካባቢው ሊፀዳለት ያስፈልገዋል፡- እንዲሁም መንፈሳዊ ሕይወት እንዲያፈራ ከክፉ ባልንጀሮች፣ ጊዜአችንን ከሚበሉ ንባቦችና ፊልሞች መለየት ይጠይቃል፡፡
ወይን ምርጥ ዘር መሆን አለበት፡- የወይን መልካም አረግ ካልተገኘ ፍሬው ያማረ አይሆንም፡፡ እጅግ መራራ ፍሬ ያፈራል፡፡ ስሙ ወይን ነው፣ ከዘሩ የተነሣ ግን መራራ ፍሬ ሊያፈራ ይችላል፡፡ እንዲሁም ስሙ ክርስትና ሆኖ መራራ ፍሬ እንዳናፈራ ከእግዚአብሔር ከመልካሙ ዘር መወለድ አለብን፡፡
ወይን ተሸካሚ ይፈልጋል፡- ወይን ለአረጉ ሳይሆን ለፍሬው ተሸካሚ ይፈልጋል አሊያ ይወድቃል፡፡ እንዲሁም ክርስቲያን ሲደክም ብቻ ሳይሆን ሲበረታ ይበልጥ ጥበቃ ያስፈልገዋል፡፡ ፍሬውን እንደ ተሸከመ እንዳይወድቅ መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡
ወይን የመጥመቂያ ጉድጓድ ይፈልጋል- ወይኑ ለመጠጥነት፣ ለእርካታ እንዲደርስ በመጥመቂያ ጉድጉድ ይረገጣል፡፡ የመጠመቂያው ጉድጓድ ከዓይን የተሰወረ፣ ከመሬት የጠለቀ ነው፡፡ በውስጡም መረገጥ አለበት፡፡ ካልተረገጠ አይጠጣም፡፡ እንዲሁም አርኪ የክርስትና ሕይወት እንዲመጣ መገፋት፣ መናቅ፣ በመከራ ውስጥ ማለፍ ግድ ይላል፡፡ ካልተጨመቀ ክርስቲያን አይጠጣም (አያረካም)፡፡
ወይን ይገረዛል፡- መገረዙ ይበልጥ እንዲያፈራ ይረዳዋል፡፡ የሚገረዘው ግን በስለት ነው፡፡ መቆረጥ፣ መድማት፣ መለየት ያለበት ነው፡፡ በክርስትናም ብዙ ለማፍራት ሕመም ያለባቸውን ሥርዓቶችን ማለፍ ግድ ይላል፡፡
እግዚአብሔር ለእስራኤል ያደረገው እንክብካቤ ገበሬው ለከበረው ፍሬ ለወይኑ እንዳደረገው እንክብካቤ ነው፡፡ ገበሬ ተሞኝቶ የሚደክም ሳይሆን ፍሬ አገኛለሁ ብሎ ተማምኖ የሚደክም ነው፡፡ እግዚአብሔርም ፍሬን ፈልጎ ደከመ፡፡ ውጤቱ ግን ወይኑ ሆምጣጣ ፍሬ አፈራ፡፡ እንደ ወይን ጣፋጭ የለም፣ መልካም ካልሆነ ደግሞ እንደ ወይን መራራ የለም፡፡ እንዲሁም እንደ ክርስቲያን ጣፋጭ የለም፣ ካልተባረከ ደግሞ እንደ ክርስቲያን አሳዛኝ የለም፡፡ ክርስትናው የራቀው ክርስቲያን ሰብአዊነት እንኳ ይለየዋል፡፡ ለዚህ ነው ከምድራውያን ነገሥታት የክፉ ጳጳሳት ግፍ የሚበልጠው፡፡ ለዚህ ነው ከዓለማውያን የክርስቲያኖች ጠብ የማይበርደው፡፡
ጌታ ተናገረ፡- “አሁንም እናንተ በኢየሩሳሌም የምትኖሩ የይሁዳ ሰዎች ሆይ፣ በእኔና በወይኑ ቦታዬ መካከል እስኪ ፍረዱ፡- ለወይኔ ያላደረግሁለት ከዚህ ሌላ አደርግለት ዘንድ የሚገባኝ ምንድር ነው? ወይንን ያፈራል ብዬ ስተማመን ስለ ምን ሆምጣጣ ፍሬ አፈራ?” በማለት ይጠይቃል (ኢሳ. 5÷3-4)፡፡
ወይኑ ብዙ በተደረገለት መጠን ብዙ ጨነገፈ፡፡ እጀ ሰባራ የሚያደርግ ከተቀበለው ተቃራኒ የሚሰጥ፣ የገበሬውን ልብ የሚያሳዝን ነበር፡፡ እግዚአብሔር ያላደረገልን ምን አለ? ከጎደለን ስለምንጀምር እንጂ ካለን ነገር ተነሥተን ብናወራ የጐደለን ሳንደርስ ቀኑ ይመሻል፣ ክረምቱ ይጠባል፡፡ እግዚአብሔር ለእኛ ያላደረገው ምን አለ? ከእኛስ ያገኘው ምን መልካም ነገር አለ? መልካም እየበላን ክፉ የምናፈራ መሆናችን ያሳዝናል፡፡ እግዚአብሔር በዘመናችን ያደረገው እንክብካቤ ከቃላት በላይ ነው፡፡ የሚንቆረቆረው ዝማሬ፣ የሚፈስሰው የእግዚአብሔር ቃል፣ የሚፋጠኑት አገልጋዮች፣ የተደረገው መንፈሳዊ ሕክምና፣ የተጻፉት መጻሕፍቶች ብዙ ናቸው፡፡ ውሃ እያጠጣ አረካን፣ ድንጋዮችን ለቅሞ አወጣልን፡፡ የማይጠይቅ ትውልድ በኖረበት ምድር የሚጠይቅና የከበረውን ከተዋረደው የሚለይ ወገን ተነሣልን፡፡ እግዚአብሔር የወይኑን ስፍራ እንዲህ ተንከባከበው፡፡ ከዝማሬው፣ ከቃሉ ሙላት፣ ከመንፈሳዊ መረዳት በኋላ እግዚአብሔር ከእኛ የጠበቀው ነገር ነበር፡፡ እኛ ግን ሆምጣጤ አፈራን፡፡ በዘመረ አፋችን ተሰዳደብን፣ ቃሉን በሰማ ጆሮአችን የወንድሞቻችንን ክስ ሰማን፣ ተያይዘን እንዳልዘመርን አሳልፈን ተሰጣጣን፡፡ ሆምጣጤ አፈራን፡፡ ይህንን ግርግር በትኖ ሰላምን፣ ሐሜትን አጥፍቶ ፍቅርን የሚመሠርቱ መሪዎችን ተመኘን፡፡ ነገር ግን በእሳቱ ቤንዚን የሚያርከፈክፉ ሆኑ፡፡ ለማስተማሩ የሌሉበት ለግዝት ጀግኖች ሆኑ፡፡ እግዚአብሔር ሕዝቡን አየ አዘነ፣ አባቶችን አየ አዘነ፡፡
ለእኛ ያላደረገው ምን ነበር? ከግብፃውያን መንፈሳዊ ባርነት ተላቀን ከራሳችን ልጆች ጳጳሳትን ሾምን፣ ከመንፈሳዊ ተቋማት ብዙ ወይኖችን አፈራን፡፡ ነገር ግን ዛሬ እየደረሰ ያለውን ጥፋት ስንመለከት የግብፅ ጳጳሳት ከዚህ በላይ ምን አደረጉ? ያሰኛል፡፡ ቤተ ክርስቲያን የግፍ መወዳደሪያ ስፍራ፣ የቡድን ቤት፣ የነፍስ ማሳደጃ፣ የወርቅ መቀበያ፣ የድሀ መጨቆኛ ቦታ መሆኗ እጅግ ያሳዝናል፡፡
እግዚአብሔር ከዚያች ወይን የጠበቀውን ተናገረ፡- “የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር ወይን ቦታ እርሱ የእስራኤል ቤት ነው፡፡ የደስታውም አትክልት የይሁዳ ሰዎች ናቸው፤ ፍርድን ተስፋ ያደርግ ነበር፤ እነሆም ደም ማፍሰስ ሆነ፡፡ ጽድቅን ይተማመን ነበር፣ እነሆም ጩኸት ሆነይላል (ኢሳ. 5÷7)፡፡ እግዚአብሔር ድሃ ተበደለ፣ ፍርድ ጎደለ እንድንል ይፈልጋል፡፡ ፍርድ ለሰው ሳይሆን ፍርድ ለእግዚአብሔር ነው፡፡ ነገ ጥቅሜን ያጎድልብኛል፣ ስሜን ይበክለዋል እያሉ ፍርድን መተው በሰማይ በምድር ያስጠይቃል፡፡ በኬንያ ከሌባው ለማምለጥ ሙጥኝ ያልነው ፖሊስ ብዙ ብር ይዘርፈናል፡፡ ፍርድ የሚፈለግበት ፍርድ አልባ ሲሆን እንደውም ደም አፍሳሽ ሲሆን እግዚአብሔር ያዝናል፡፡ የኬንያን ፖሊስ ያየ ውሻ ነከሰኝ ብሎ ለጅብ አቤት የሚል ይመስላል፡፡ የበለጠ ይበላል ማለት ነው፡፡ ‹‹ውሃ ሲጎድል ተሻገር፣ ዳኛ ሲኖር ተናገር›› እንደሚባለው ዝም ያሉ ሁሉ ስህተተኛ ስለሆኑ ሳይሆን ዳኛ ስላጡ መሆኑን ማስተዋል ይገባል፡፡ ፍርድን ሁሉ ሰው ተጠምቷል፡፡ የቅን ፈራጅ ጠፍቷል፡፡ በዳግማዊ ሚኒልክ ዘመን የገበሬውን ሚስት ደፍሮ ኖሮ ገበሬው ለአጥቢያው ዳኛ አቤት አለ፡፡ የአጥቢያው ዳኛም የወታደሩን ስህተት ቢያውቅም ወታደሩን ፈርቶ፡- “መበደሉን ወታደር በድሏል ነገር ግን ገበሬ ይካስብሎ ፈረደ ይባላል፡፡ በዚህ ጊዜ፡-
እግዚኦ ለአራዳ ዳኝነት
 እኔው ተበድዬ እኔው ለካስኩበት አለ ይባላል፡፡
ዛሬም የአራዳው ዳኝነት በዳይ ይካስ እየተባለ፣ ወንጌል እየተገፋ ወንጀል እያበበበት ነው፡፡ እግዚአብሔር ፍርድ ይፀናል ብሎ ጠብቆ ነበር፡፡ ነገር ግን ደም ማፍሰስ ሆነ፡፡ ፍርድ የተጓደለበት እንደውም ደሙ ፈሰሰ፡፡ ይህ የመንፈሳዊው ቤት ግፍ የዘመናችን አበሳ ነው፡፡
ጽድቅንም ይተማመን ነበር እነሆም ጩኸት ሆነእውነት በጩኸት ተዋጠች፡፡ እውነት በእውነት ጉባዔ ተገፋች፡፡ በድምጽ ብልጫ አማንያን መናፍቅ፣ ኢአማንያን የእምነት ጠባቂ ተባሉ፡፡ በድምፅ ብልጫ ሰዶማዊነት ሕጋዊነት በሆነበት በሰለጠነው ዘመን አማኙም ከሃዲ ተብሎበታል፡፡ እውነት ግን በጣት ቆጠራ ሳይሆን በራሷ ትቆማለች፡፡ ከጩኸታቸው የተነሣ የተሳቀቃቸው ጆሮ ይሁንላቸውና ፀጥ ይበሉ፣ ገበሬው ተበድሏል ግን ይሙትላቸው ተባለ፡፡ ታዲያ ምን ይጠበቅ ይሆን፡-
አሁንም በወይኔ ላይ የማደርገውን እነግራችኋለሁ÷ አጥሩን እነቅላለሁ፤ ለማሰማሪያም ይሆናል፤ ቅጥሩንም አፈርሳለሁ፤ ለመራገጫም ይሆናል፤ ባድማ አደርገዋለሁ፤ አይቈረጥም÷ አይኰተኰትም፤ ኲርንችትና እሾህ ይበቅልበታል፤ ዝናብንም እንዳያዘንቡበት ዳመናዎችን አዝዛለሁይላል (ኢሳ. 5÷5-6)፡፡
የእግዚአብሔር ልጆች እግዚአብሔር ሲምርም፣ ሲፈርድም ያስደስታቸዋል፡፡ ቀጥሎ ይህ ይሆናል፡፡ ምስጋና ለእግዚአብሔር፣ ለእኛም ማስተዋል ይሁንልን!