Thursday, May 3, 2012

ይድረስ ለመልአከ ሰላም ቀሲስ ደጀኔ ሽፈራው



                                    a source from:www.abaselama.org   
                                       To read in PDF ( Click Here )
እርስዎ በብፁዕ አባታችን በአቡነ ጎርጎርዮስ ጥቂት ኦርቶዶክሳዊ እምነት ተምረው መልካም መንፈስ እንደነበረዎት ጓደኞችዎ ይመሰክራሉ፤ ለእግዚአብሔር ወንጌልም ቀናተኛ ደቀ መዝሙር ነበሩ። አሁን እያስተማሩት ያለው ትምህርት ግን በሰውም ሆነ በጌታ ዘንድ ያስጠይቀዎታልና በብሎግዎ ከጻፉት ላይ አንዳንድ ኦርቶዶካስዊ ያልሆኑ ትምህርቶችን እንዲያርሙ ልጠቁመዎት ወደድሁ። ከመንፈሳዊ ሰላምታ ጋር!
መልክአ ሚካኤል በሚለው ርእስ ከጻፉት ውስጥ፦
 «መልክዕ፦ ቅዱሳን የሚመሰገኑበት መንፈሳዊ ድርሰት ነው። ከራስ ጠጉራቸው ጀምሮ እስከ አግር ጥፍራቸው ድረስ ያለውን የአካላቸውን ክፍል እየዘረዘረ ያመሰግናቸዋል» ብለዋል።
 ቅዱሳን መላእክት ሰማዕታት እና ጻድቃን ክቡራን ናቸው። ያከበራቸውም ብቻውን ሌላ ሳይጨምሩ ሁልጊዜ በመንፈስ የሚያመልኩት ሕያውና ቅዱሱ አምላክ ነው። መላእክትም ይሁኑ ሰማዕታት ቅዱሳን ሁሉ የቅድስናቸው ምስጢር አንዱን አምላክ ማምለካቸው ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የምናውቃቸው ቅዱሳን ሁሉ ዝማሬያቸው፣ ምስጋናቸውና ቅዳሴያቸው ሁሉ ለአንዱ ለሥላሴ ብቻ ሆኖ ነው የምናገኘው። እርስዎ እንደሚያስተምሩት ቅዱሳን ሌሎች ቅዱሳንን ከራስ ጸጉራቸው እስከ ጥፍራቸው ድረስ ግጥም እየገጠሙ ምስጋና ሲያቀርቡላቸው አንድም ቦታ አናይም። እኛም የአባቶቻችን ነቢያትና ሐዋርያትን ፈለግ ተከታዮች ነንና አንዱን ቅዱስ አምላክ ብቻ ልናመሰግን ይገባል። ለምሳሌ ሙሴ ለአብርሃም ለይስሐቅና ለያዕቆብ የተገለጠውን አምላክ ስሙን እየጠራ አመሰገነ እንጂ የነርሱን ጸጉርና ጥፍር እየጠቀሰ ሲያመሰግን አናነብም። ኢያሱም የሙሴን አምላክ እንጂ ሙሴን ሲያወድስ አናይም፤ ነቢያትም ሁሉ ነገሥታትም ሁሉ ምስጋናቸው ለእግዚአብሔር ነው።
በመሠረቱ በዜማ፣ በቅኔና በዝማሬ በቤተ መቅደስ ቆመን የምናቀርበው ምሥጋና አምልኮ ነው። ክቡርና ቅዱስ የሆነ ሰውን በአካል አግኝተን የምንሰጠው ሰላምታ አክብሮት ነው። ይኸውም ዝቅ ብሎ እጅ በመንሳት ጉልበት በመሳም እጅ በመሳም፤ ከተቀመጥንበት ብድግ በማለት፤ እንደየባህላችን የምናደርገው እንግዳን የመቀበል ሥርዓት ነው። በማህሌት እና በዜማ በጌታ አደባባይ የምናቀርበው ግን አምልኮ ነው። ቅዱሳን መላእክት ለዳንኤልና ለዮሐንስ በተገለጡላቸው ጊዜ በግንባራቸው ተደፍተው ራሳቸውን ዝቅ አድርገው ተቀብለዋቸዋል። ይህም በድንገት የተገለጠ ነገር ስለሆነ ነው እንጂ በየወሩ ቀን እየቆጠሩ ያደረጉት ነገር አይደለም። መላእክትም ቅዱሳን  ናቸውና እንኳንስ በየቀኑ የሚሰጣቸውን ስግደትና አምልኮ በእንግድነት በተገለጡ ጊዜ የተደረገውን ከሚገባው በላይ የሆነ አክብሮት አልተቀበሉትም። እርሱም፦ «እንዳታደርገው ተጠንቀቅ፤ ከአንተ ጋር ከወንድሞችህም ከነቢያት ጋር የዚህንም መጽሐፍ ቃል ከሚጠብቁ ጋር አብሬ ባሪያ ነኝ፤ ለእግዚአብሔር ስገድ አለኝ» ይላል  ራዕይ 229
ዛሬ እኛ እያደረግን ያለው ግን በየቀኑና በየወሩ ቀን መድበን ላልተገለጠልን መልአክ ምስል አቁመን ምስጋና እና ስግደት ማቅረብ ነው። ይህ ስሕተት ነው እላለሁ። እነ ዳንኤል ተገልጦላቸው ነው በግንባራቸው ተደፍተው ዝቅ ብለው የተቀበሉት። እኛ መልአኩ መቼ ተገልጦልን ነው ስግደትና አምልኮ የምናቀርበው? ወይስ ምስል መገለጥ ነው ሊሉን ነው? ዳንኤል በግንባሩ የተደፋው ምስል መስሎ ነው ወይስ መልአክ ተገልጦለት? ይህን ጥያቄ ከመልክአ ሚካኤል ወይም ከድርሳነ ሚካኤል ሳይሆን ከዚያው ቤተ ክርስቲያናችን ከምትቀበለው ከሰማኒያ አንዱ መጽሐፍ እንዲመልሱልን እጠይቃለሁ።
መልክኣ ሚካኤል ስለ ሚካኤል ጸጉር፣ ጥፍር፣ ጥርስ፣ ኩላሊትና አንጀት እያነሳ የሚያመሰግን ድርሰት ነው። ለመሆኑ የዚህ መልክዕ ደራሲ የሚካኤልን ጸጉር የት አየው? ሚካኤል አካል ያለው መንፈስ ነው ዕብ 114 የሚካኤል  ጥፍርስ ምን አይነት ጥፍር ነው? ኩላሊትና አንጀት ለምግብ ሥራ የተሠሩ የሥጋ ለባሽ ብሎቶች ናቸው። ደራሲው ስለመልአኩ አንጀትና ኩላሊት እያለ የማያውቀን ረቂቅ ፍጡር ሲያመሰግን ከየትኛው የእግዚአብሔር ቃል ተነሥቶ ነው? ዳንኤልና ዮሐንስ መልክአ ሚካኤል እያዜሙ ጥፍሩንና ጸጉሩን እያሳመሩ በየወሩ ምስጋና ሲያቀርቡ ታይተዋልን? ለምን ወደ እውነቱ አንመለስም?
መላከ ሰላም ነገር ሲያጋንኑ እንዲህ ብለዋል፦
 «ምስጋና መቅረብ ያለበት ለእግዚአብሔር ብቻ እንጂ እንዴት ለፍጡራን ይቀርባል? እንዲህ ዓይነቱ መንገድ የእግዚአብሔርን ክብር መጋፋት ነው፤ የሚሉ አሉ። ዞር ብለው ደግሞ ትንሽ ውለታ የዋለላቸውን ሰው አፋቸውን ሞልተው ሲያመሰግኑ ይሰማሉ፥ የባሰባቸው ደግሞ «እኔ እንዲህ ዓይነት ሰው ነኝ፤ ብለው ራሳቸውን ሲያወድሱ ይደመጣሉ»
ይህ አባባልዎ አስተዋይ ልብ ላለው ሰው ትዝብት ላይ የሚጥልዎት ነው። እኛ ውለታ የዋለልንን ሰው የምናመሰግንበት መንገድና የቤተ ክርስቲያናችን የዋሕ ምዕመን እርስዎን ጨምሮ መላእክትን የሚያመሰግኑበት መንገድ የተለያየ ነው። ውለታ የዋለልንን ሰው «እግዚአብሔር ይስጥልኝ አመሰግናለሁ፤ እግዚአብሔር ይባርክህ» ብለን ለበጎ ውለታው በጎ ምላሻችንን እንሰጣለን እንጂ ውለታ ለዋለልን ሰው አመት፣ ወርና ቀን መድበን በከበሮና በጸናጽል በዝማሬና በምስጋና አናመልከውም። ለመላእክት እያደረግን ያለው ግን ከራስ ጸጉራቸው እስከ እግር ጥፍራቸው ድረስ እያነሳን በየቀኑ ምስጋና ማቅረብ ነው። ይህ ልዩነት የለውምን? ይህ የእግዚአብሔርን ክብር መጋፋት አይደለም ይላሉ? እስኪ አንባቢ ይፍረደን፦ ውለታ ለዋለልን ሰው የምንሰጠው ምላሽና በየወሩ በአል ተዘጋጅቶ ለመላእክት የሚቀርበው አንድ ነው? ውለታ ለዋለልን ሰው «አርዳኝ ፈጥነህ ድረስልኝ አድነኝ ማረኝ ይቅር በለኝ» ብለን እናውቃለን? አይደለም! ይህ ልመና መቅረብ ያለበት ሁሉን ለሚሰማው ለእግዚአብሔር ብቻ ነው። ቅዱሳንን ግን ሥራቸውንና እምነታቸውን በማድነቅ እናከብራቸዋለን ስለነርሱም እግዚአብሔርን እናመሰግናለን እንጂ ወር እና ቀን መድበን አምልኮ መሰል ምስጋና ማቅረብ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አይደለም።
ከዚህ ባዕድ አምልኮ ጋር ጌታን ለመጨመር የሞከሩትን እንመልከት፦
«በአዲስ ኪዳን በመልክአ ቅዱሳን ቅዱሳንን ማመስገን እንዲገባ አብነት ሆኖ መንገድ ያሳየ፥ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ይኸውም፦ «የእናንተ ግን ዓይኖቻችሁ ያያሉና፥ ጆሮዎቻችሁም ይሰማሉና ብፁዓት ናቸው።» በማለት ደቀመዛሙርቱን በማመስገኑ ታውቋል። ማቴ ፲፫፥፲፮።  በዚህ የጌታ ቃል ውስጥ፦ «ለአዕይንቲክሙን እና ለአዕዛኒክሙን» እናገኛለን። «የእናንተስ የራስ ጠጉራችሁ ሁሉ እንኳን የተቈጠረ (የከበረ) ነው። ከሚለው ደግሞ «ለስእርተ ርእስክሙ፤» የሚለውን እናገኛለን» ብለዋል።
መላከ ሰላም - ጌታ እንደርስዎ አስተሳሰብ ለማለት ፈልጎ አይደለም እንደዚህ ያለው። ይህ ቃል እራሱ ጌታ ቅዱሳን ከተገለጠላቸው መለኮታዊ ምሥጢር የተነሳ ያገኙትን ከፍተኛ ክብር ለመግለጥ ተናገረው እንጂ ለጆሮአቸውና ለዓይኖቻቸው በየወሩ ምስጋና እንድናቀርብ ያሳየን መንገድ አይደለም። ነቢያት ያላዩትን፣ አባቶቻቸው ያልሰሙትን እራሱን ክርስቶስን በአካል ተገልጦ በማየታቸው እድለኛ መሆናቸውን በዚህም ደስ እንዲላቸውና አምላካቸውን እንዲያከብሩ የገለጠላቸው ቃል ነው። እርስዎ ግን «በመልክአ ቅዱሳን ቅዱሳንን ማመስገን አብነት ሆኖ ያሳየ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው» ብለዋል፤ በእውነት ይህ ቃል ጌታ በመልካቸው ቅዱሳንን እንድናመሰግን ያስተማረው ትምህርት ነው? እስኪ ረጋ ብለው በመንፈሳዊ ልብ ያስተውሉት።
«የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ለማኑሄና ለሚስቱ ተገልጦ የእግዚአብሔርን መልእክት በነገራቸው ወቅት፥ «ነገርህ በደረሰ ጊዜ እንድናከብርህ (መታሰቢያህን እያደረግን፥ ስምህን እየጠራን እንድናመሰግንህ) ስምህ ማን ነው? ብለውታል። እርሱም «ስሜ ድንቅ ነውና ለምን ትጠይቃላችሁ? ብሎአቸዋል። መሳ ፲፫፥፲፯። የነቢያት አለቃ ሙሴ በመዝሙሩ እንደተናገረ ድንቆችን የሚያደርግ እግዚአብሔር ነው። ዘጸ ፲፭፥፲፩። በመሆኑም የቅዱስ ሚካኤል ስሙ ከእግዚአብሔር ድንቆች አንዱ ነው። ከዚህም መልክአቸው «ለዝክረ ስምከ፤ ብሎ ድንቅ ከሆነው ስማቸው እንደሚጀምር እንረዳለን»
 ለማኑሄ የተገለጠው መልአክ ሚካኤል መሆኑን የጠቀሱት ጥቅስ አይናገርም። ለማኑሄ የተገለጠው መልአክ ቅዱስ ሚካኤል መሆኑን ከየት አገኙት? «ድንቆችን የሚያደርግ እግዚአብሔር ነው» ማለትዎ ትክክል ነው «ስሜ ድንቅ ነው» ያለው ሚካኤል ነው ሲሉ ግን ስለ እግዚአብሔር ከተናገሩት ጋር ይጋጫል።  እርሱ ራሱ ሊገልጠው ያልፈገውን ስም እኛም ዝም ብንል የተሻለ ይሆናል።

«ቅዱሳን መላእክት በኃይልም በሥልጣንም ገናና ሆነው መፈጠራቸውን መካድ አይገባም። ቅዱስ ማቴዎስ ወንጌላዊ የመልአኩን መልክዕ፥ ኃይልና ሥልጣን ሲመሰክር፦ «እነሆ ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፥ የእግዚአብሔር መልአክ ከሰማይ ወርዶአልና፥ ቀርቦም ከመቃብሩ አፍ ላይ ድንጋይዋን አንከባሎ በላይ ተቀመጠ። መልኩም እንደ መብረቅ፥ ልብሱም እንደ በረዶ ነጭ ነበረ። እርሱንም ከመፍራት የተነሣ መቃብሩን የሚጠብቁ ታወኩ፥ እንደ በድንም ሆኑ፤» ብሏል። ማቴ ፳፰፥፪-፬።»
 በዚህ እንስማማለን ምክንያቱም መላእክቱ ከጌታ ተልከው ሲመጡ በጌታ ክብር ነውና የሚመጡት የጌታ መልእክተኞች ሥልጣናቸውም ሆነ ክብራቸው ታላቅ ነው። በዚህ ሁኔታ በሚገለጡልን ጊዜ እራሳችንን ዝቅ አድርገን በትሕትና አክብረን እንቀበላቸዋለን፤ ምስጋናችንን ግን ሞገስ ክብርና ኃይል ለሆናቸው ለኃያሉ አምላክ እንሰጣለን። እነርሱም የቆሙት ለእግዚአብሔር ክብር ስለሆነ አገልግሎታቸውም ለመንግሥቱ ስለሆነ በምስጋናችን ደስ ይላቸዋል። እነርሱ ከርሱ የተነሣ ነው ይህን ክብር የተጎናጸፉት፤ እኛም አምላካችንን እነደነርሱ ብንታዘዘው ያከብረናል ሞገስ ይሆነናል።
«ሚካኤል ሆይ! . . . የተጨነቁትን ዘወትር እንደምትረዳቸው ሁሉ እኔንም ለመርዳት ክንፍህን ዘርግተህ ፈጥነህ ድረስልኝ፤ ይላል። እስራኤል ዘሥጋ የፈርዖን ሠራዊት ደርሶባቸው ሞትን በመፍራት በተጨነቁ ጊዜ የደረሰላቸው፥ በደመናም የጋረዳቸው መጋቤ ብሉይ ቅዱስ ሚካኤል ነው» ዘጸ ፲፬፥፲፱።
መላከ ሰላም- ፈጥነህ ድረስልኝ ብለን መጸለይ ያለብን ወደ ሚካኤል አምላክ ወይስ ወደ ራሱ ወደ ሚካኤል? ወደ ሚካኤል የጸለዩ የእምነት ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ አሉን? «አንተ ግን ስትጸልይ፥ ወደ እልፍኝህ ግባ መዝጊያህንም ዘግተህ በስውር ላለው አባትህ ጸልይ፤ በስውር የሚያይ አባትህም በግልጥ ይከፍልሃል።» አለ ጌታ። ማቴ 66 መላከ ሰላም ይህን የጌታ ቃል ያምኑታል? አባታችን ማን ነው? ሚካኤል ወይስ እግዚአብሔር? ጌታ በስውር ላለው አባትህ ጸልይ ብሎ አስተማረን እርስዎ ደግሞ ወደ ሚካኤል መጸለይ እንደሚገባ እያስተማሩ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስን እንስማ ወይስ እርስዎን? መናፍቁ ማን ነው? ጸሎት አምልኮ ነው። በምስጋና፣ በትሕትና፣ በጸጥታና በእምነት ከሰማዩ አባታችን የምንነጋገርበት ቋንቋ ነው። ዋናው አምልኮ ጸሎት ነው። እውነተኞች ኦርቶዶክሳውያን ሲያስተምሩን «ጸሎት ብሂል ተናግሮ ምስለ እግዚአብሔር» ትርጉም፦ ጸሎት ማለት ከእግዚአብሔር ጋር መነጋገር ማለት ነው ብለውናል። ጸሎት ማለት ከሚካኤል ጋር መነጋገር ነው ብለው ግን አላስተማሩንም። ይህን ባዕድ ነገር ወደ ቤተ ክርስቲያን ያስገባብን ዘርዐ ያዕቆብ ነው ብለው ነግረውናል። እርስዎስ ለምን የዘርዐ ያዕቆብን ስሕተት  ይደግሙታል?
«እስራኤል የፈርዖን ሠራዊት ደርሶባቸው በተጨነቁ ጊዜ ፈጥኖ ደርሶ በደመና የጋረዳቸው ሚካኤል ነው» ብለዋል። በጠቀሱት ጥቅስ ላይ ግን ሚካኤል በደመና ጋረዳቸው የሚል ቃል አናገኝም። እርስዎ ከምን አገኙት? የእግዚአብሔርን ምስጋና እንዲህ ለፍጡራን አሳልፎ ለመስጠት ይህን ያህል ጥልቅ ጉድጓድ የሚቆፍሩት ለምንድር ነው? ቃሉ የእስራኤል ረዳት ማን እንደነበር ሲናገር «ሙሴም ለሕዝቡ አትፍሩ ዛሬ የምታዩአቸውን ግብጻውያን ለዘለዓለም አታዩአቸውምና ቁሙ፤ ዛሬ ለእናንተ የሚያደርጋትን የእግዚአብሔርን ማዳን እዩ እግዚአብሔር ስለእናንተ ይዋጋል እናንተም ዝም ትላላችሁ» ይላል። ዘጸ 1413-14  የእግዚአብሔርን ማዳን እዩ፤ እግዚአብሔር ስለናንተ ይዋጋል አለ እንጂ የሚካኤልን ማዳን እዩ ሚካኤል ስለናንተ ይዋጋል አይልም። ቃሉ ያላለውን ሚካኤል ነው ማለት የስሕተት ትምህርት ነው። ማህበረ ቅዱሳን የስህተት ትምህርት ያስተምራል እያልን የምንጮኸው ለክስ አይደለም። የእግዚአብሔር ቃል የማይለውን በፈጠራ ስለምታስተምሩ ነው እንጂ።
እሥራኤልን ከፈርዖን ያዳናቸው ሚካኤል ቢሆን ኖሮ ባሕሩን ከተሻገሩ በኋላ ባቀረቡት ምስጋና እና ዝማሬ «ንሴብሖ ለእግዚአብሔር ስቡሐ ዘተሰብሐ» በማለት ፈንታ «ንሴብሖ ለሚካኤል ስቡሐ ዘተሰብሐ» ባሉ ነበር። ቃሉ «በዚያን ጊዜ ሙሴና የእስራኤል ልጆች ይህን መዝሙር ለእግዚአብሔር ዘመሩ እንዲህም አሉ፤ በክብር ከፍ ከፍ ብሏልና ለእግዚአብሔር እዘምራለሁ ፈረሱንና ፈረሰኛውን በባሕር ጣለ ጉልበቴ ዝማሬዬም እግዚአብሔር ነው» ዘጸ 151 ዳዊትም ከረጅም ዘመን በኋላ «መርሖሙ መዓልተ በደመና ወኩሎ ሌሊተ በብርሃነ እሳት» ቀን በደመና መራቸው፥ ሌሊቱንም ሁሉ በእሳት ብርሃን» አለ መዝ 7814 በየትኛውም የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ውስጥ እስራኤልን በደመና የመራቸው እግዚአብሔር መሆኑን ይናገራል እንጂ ሚካኤል ነው የሚል አናገኝም።
«የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ  ይሰፍራል ያድናቸውማል» የሚለው ቃል ትክክል ነው እንቀበለዋለን እርስዎ የተረዱት ግን በተሳሳተ መንገድ ነው። መልአኩ የሚሰፍረው እግዚአብሔርን በሚፈሩ ሰዎች ዙሪያ እንጂ እራሱን መልአኩን በሚፈሩ ሰዎች ዙሪያ አይልም። የነገር ሁሉ መጀመሪያው እግዚአብሔርን መፍራት ነው። እግዚአብሔርን ሳያከብሩ ሚካኤልን አከብራለሁ እያሉ የሚያሾፉ ሰዎች አሉ። ሚካኤል ግን እግዚአብሔርን ሳንታዘዝ የርሱ ወዳጅ መስለን ብንቀርብ አይቀበለንም «ሄሮድስም እግዚአብሔርን ስላላከበረ የጌታ መልአክ መታው በትልም ተበልቶ ሞተ» የሐዋ 12 ይላል። መልአኩ ማዳን ብቻ ሳይሆን ይገድላል፤ ይህ ፍርድ ግን እግዚአብሔርን በመታዘዝና ባለመታዘዝ የሚወሰን ነው።
ስለዚህ ዛሬ የቤተ ክርስቲያናችን ምዕመን በጥንቆላ፤ በዝሙትና በባእድ አምልኮ እንዲሁም በአጋንንት ሥራ ተጠምዶ ከርሞ ገብርኤል ወዳጄ ሚካኤል አማላጄ እያለ ዳቦ እየጋገረ በየወሩ የሚያደርገውን ቀልድ ቢያቆም ከመቀሰፍ ይድናል እላለሁ። ሚካኤል በዳቦ አይታለልም፤ እግዚአብሔርን ስናመልክ ያከብረናል እግዚአብሔርን ካላመለክን ግን ይቀስፈናል።
መላከ ሰላም ቀሲስ ደጀኔም ከመጸሐፍ ቅዱስ ያላገኙትን የስሕተት ትምህርት ቢያርሙ ጥሩ ነው። ተሳስተው ከሆነም ከዚህ በኋላ አይድገሙት፤ ንስሐም ይግቡበት፤ እምቢ ካሉ ግን የማህበረ ቅዱሳን ዶክትሪን እንጂ የኦርቶዶክስ እምነት አድርገው አያስተምሩት። በሕግ አምላክ!
ይቀጥላል
መሪጌታ ገረመው ነኝ