Saturday, May 19, 2012

ማኅበረ ቅዱሳን የስኳር ልማቱን እንደሚቃወም ባደፈጠ ጥናቱ ውስጥ ገለጸ!


ስለዋልድባ ገዳም ጥናት አዘጋጅቻለሁ ካለ በኋላ አድፍጦ የቆየው ማቅ የመምህር ዕንቍ ባህርይ ደብዳቤ እንደደረሰው ጥናቱን ካዘገየበት ቆፍሮ በሽንፍን ካባ ለመግለጥ ተገዷል። ማቅ ከየትኛውም ወገን ገለልተኛ ሆኖ የደረሰበትን የጥናት ውጤት በኦፊሴል ማቅረብ ሲገባው  ጥናት ሳይሆን ወሬ ሰብስቦ ገዳማቱ እንደዚህ ይላሉ፣ መንግሥት ደግሞ እንደዚህ እየሰራ ነው በሚል ገደምዳሜ ጎዳና ለመሸወድ የሞከረ ዲስኩር ለማቅረብ ሞክሯል።
ገዳማቱ የሚያሰሙትን ጩኸት ማንም ሰምቶታል። መንግሥትም እየሰራ ስላለው ልማትም በግልጽ ተናግሯል። ማቅ ሁለቱን ሃሳቦች ለማስታረቅ የሄደ ሽማግሌ ይመስል ዙሪያ ጥምጥም በመሄድ በእውቀት ላይ የተመሠረተ ሳይሆን እንደዚህ ተባለ፤ እንደዚያ ተደረገ የሚል ወሬ መለቃቀሙ ምናልባትም ያጠናውን ስውር ውጤት በይፋ ብገልጸው መምህር ዕንቍ ባህርይ በግልባጭ ባስታወቋቸው ብሄራዊ የመረጃና ደኅንነት፤ በፌዴራል ፖሊስ፤ በፌዴራል ጉዳዮች ወዘተ መስሪያ ቤቶች በተያዘብኝ የአሸባሪነት ጥቁር ስሜ  ወደ አደጋ ያደርሰኛል ብሎ በመስጋት በልቡ ያስቀመጣትን ሚጥሚጣ ጥናት እንደቀበረ እንገምታለን።
የመንግስትን የስኳር ልማት በግልጽ ብደግፍም ደግሞ በውጪ ሃገር ያሉ ደጋፊዎቼ ዓይንህን ላፈር ይሉኛል፤ መነኰሳቱም ለስንት ስንጠብቅህ፤ እንደዚህ ታዋርደናለህ? ይሉኛል ብሎ  እንዳደፈጠም የጫጫረው ወሬ በግልጽ ያሳብቅበታል።
አሁን ከማቅ መገለጽ ያለበት ኦፊሴላዊ መግለጫ መነኰሳቱ የሚናገሩትን ቃል መድገም  ሳይሆን ደረስኩበት ባለው ጥናት ላይ የስኳር ልማቱ የሚያደርሰው ጉዳት አለ ወይም የለም የሚል ቃል ብቻ እንጂ እንዲህ ተባለ፤ እንዲያ ተወራ የሚል ዲስኩር አይደለም።
ከዚያ ውጪ በሽብር ተግባር የተወጠረች ነፍሱን ለማቆየት ሸርተት፤ ሸርተት አያዋጣም።
 ይህንንም ያህል ለመጠንቀቅ ቢሞክርም ማቅ ባቀረበው የወሬ ዘገባ ላይ ቁና ቁና እየተነፈሰ አንዴ ስኳር ልማቱን እደግፋለሁ የሚልና በሌላ መልኩ ደግሞ ደጋፊዎቹ እንዳይቀየሙትም የስኳር ልማቱ አደገኛ ነው፤ እኔ የገባሁትን ውጥረት ተረዱልኝ የሚል ስሜት ያላቸውን የተቃውሞ ሃሳቡን አልፎ አልፎ ከዲስኩር ጽሁፎቹ መካከል ደንቅሮ ይታያል።


«በአንድ በኩል ልማቱን አንቃወምም፤ በሌላ መልኩ ደግሞ የስኳር ልማቱ አሉታዊ ተጽእኖ አለው» ማለት ምን ማለት ነው?
የሽወዳ ስልትን ጠንቅቆ የሚያውቀው ይህ ቀንድ አውጣ ማኅበር ከቅርፊቱ ውስጥ ተደብቆ ሁለቱንም ጽንፎች በርቀት ሲያሾፍባቸው ይታያል። ደግሞም ከወደ ተቃውሞው ጠጋ ብሎ የራሱ ሃሳብ እንዳልሆነ ያህል እንዲቆጠርለትና እንዲመዘገብለት እየፈለገ አሉታዊ ተጽእኖ እንዳለው የገዳሙ ማኅበርና ምእመናን ሃሳቦችን እየሰነዘሩ ናቸው ሲል አጎንብሶ ለማለፍ ይሞክራል።
በምእመናንና በመነኰሳቱ ምክንያት ስር የተሸሸገውን ሃሳቡን ልክ በሰም ኃይለቃል ሸፍኖ ወርቁን እንድንፈልግ የቅኔ ጫወታውን እንዲህ ሲል ይደረድራል።


መፍትሄው ምን ይሁን? ለሚለው ጥያቄ ማቅ መልስ የለውም። ምእመናንና መነኰሳቱ ይህንን ይላሉ ካለ በኋላ በእነርሱ ተከልሎ ቅኔውን እንድንፈታ ይጠይቀናል። እኛ ሀገር ውስጥ ያለነው ይህንን ያህል ፍንጭ ከሰጠናችሁ ከዚህ በላይ አቅም የለንምና እናንተ የዲሞክራሲው ሀገር ሰዎች ነገሩን አጥብቁ የሚል ውስጠ ዘ መልእክት ይሰጠናል። ስናጠቃልለው ድሮውንስ ቢሆን ማቅ አንድ ተራ የጽዋ ማኅበር እንጂ ጥናት አጥኚ አድርጎ የዚህን ያህል የከፍታ ቦታ ለእርሱ ማን ሰጠው?
ልክ የቤተክርስቲያኗ ተጠሪ የሆነ ያህል ሲኖዶሱ እያለ የእሱ በጥናት ዙሪያ ማሽቃበጥ ከወዲያ ወዲህ ነገር እያላጋ የተለመደ ሽብርና ሁከቱን ሊያስፋፋ ካልሆነ በስተቀር እሱን በዚህ ጉዳይ አይመለከተውም። እንቅልፋምም ይሁን ጠንካራ ይህንን ጉዳይ የሚመለከተው ያ ሲኖዶስ የሚባለው አካል እንጂ በጥባጭ የጽዋ ማኅበር አይደለም እንላለን። ጥናቱ በመነኮሳቱ ጥያቄ ስር የተከለለ የማቅ ተቃውሞ የተገለጸበት ሆኖ በጭብጥ ይቀመጣል።