Saturday, February 23, 2013

ቅዱስ ሲኖዶስ ከታሪክና ከትውልድ ወቀሳ ለመዳን ምርጫውን ሊያዘገይ ይገባል!


አሁን ነገሮች እየጠሩ ወደ መቋጫው ደርሰዋል። ፓትርያርኩ ማን መሆኑም እየታወቀ ሄዷል ከማለት ይልቅ ታውቋል ማለት ይቀላል። ከሁሉም የሚያሳስበውና የሚያሳዝነው በእነ ኑረዲን ኢሊያስ፤ በእነ እጅጋየሁ ኤልዛቤል፤ በእነእዝራ የዐመጽ አለቃ ፤ በእነ ፋንታሁን የከሰረ ዐረብ፤ በእነ ኃ/ሥላሴ ሆድ አምላኩ  በመሳሰሉ የ21ኛው ክ/ዘመን የቤተ ክርስቲያን ሸክሞች ግፊትና ዘመቻ የሚመረጥ ፓትርያርክ ሊኖረን መሆኑን ስናስበው ያሳዝናል፤ ያበሳጫልም። ትልቁ ሃዘናችን  የአቡነ ማትያስን  ድክመትና ጥንካሬ በመመዘን ሳይሆን ባሉበት ሁኔታ ውስጥ ሆነው እንኳን ቀጣዩ ፓትርያርካችን አድርገን እንዳንቀበላቸው የሚያስገድዱን ነገሮች ገና ፓትርያርክ ሳይሆኑ ዙሪያቸውን ተሰልፈው ያሉትን ጎግ ማንጉግ ስንመለከት ነው። መንግሥት ደግሞ በኃላፊነት ስሜት ሂደቱን በማገዝ አድማውን፤ ዐመጹን፤ ዘመቻውን፤ ሰልፉንና ጦርነቱን በማስቆም  የካርድ ምርጫ ከመንፈሳዊ ምርጫ ጋር የሚስማማ ባይሆንም እንኳን አጠቃላይ ምእመናን በነጻና በግልጽ የተሳተፉበት ምርጫ እንዲመስል ማድረግ ሲገባው ከወሮበሎች ጋር ግንባር መፍጠሩ አሳዛኝም፤ አሳፋሪም ነው። የሾለኩ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት አቡነ ማትያስ በሀገረ ስብከታቸው ሳሉ ከከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣን የስልክ መልእክት እንደተደረገላቸውና መመረጣቸው እርግጥ በመሆኑ ጓዛቸውን ሸክፈው አዲስ አበባ እንዲገቡ መደረጉን ነው።  ምርጫው ላይ መንግሥት ስውር እጅ መስደድ ምን ትርፍ ለማግኘት ይሆን? የተሳሳተ ስሌትና በስሜት የሚነዳ ተግባር ከመሆን አያልፍም።

በሌላ መልኩም ዜግነታቸው አሜሪካዊ ቢሆንም በአሜሪካ ሕግ ሁለት ዜግነት መያዝ ስለሚቻል አቡነ ማትያስም በዚሁ ሁለት ዜግነት እየተጠቀሙ መገኘታቸውን መረዳት ተችሏል።  ምንም እንኳን የኢትዮጵያ ሕግ ሁለት ዜግነትን ባይፈቅድም ላለፉት በአሜሪካ ኖረው ከደርግ ውድቀት በኋላ  ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ ኢትዮጵያዊ ዜግነትን አድሰው በኢትዮጵያ የጉዞ ዶኩሜንት እንደሚጠቀሙ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል። በአሜሪካዊ ዜግነታቸው ደግሞ አሜሪካ ውስጥ የራሳቸው የግል  ቤተክርስቲያን አላቸው። የጡረታ ባለመብት ናቸው።  ይሁን እንጂ ለፓትርያክነት ሥልጣን እርግጠኛ  የሆነ  ዋስትና ካገኙ አሜሪካዊነትን የማይጥሉበት ምክንያት አይታየንም። ምክንያቱም አሜሪካዊ ሆነው አርጅተውበታልና እንደወጣትነት ዘመን አያጓጓቸውም። ይልቅስ ከሰለቹበት አሜሪካዊነት ይልቅ ያላዩት ፓትርያርክነት ይናፍቃልና ዜግነታቸውን መልሰው ለመቅረብ የመቻላቸው ነገር ብዙም አይከብዳቸውም። ደግሞስ ፓትርያርክን ያህል ሥልጣን ለመስጠት ከተቻለ አሜሪካዊ ነህ፤ አይደለህም ብሎ ማንኛው ሰው ይሆን ሀሞት ኖሮት የሚመረምረው?

ይህ ሁሉ ቢሆንም የዘንደሮው የፓትርያርክ ምርጫ አሳዛኝ፤ ታሪክ የሚያበላሽ፤ ቤተ ክርስቲያንን የሚያቆስል ከመሆን ያለፈ አይሆንም። ከዚህም የተነሳ ለመንግሥትና ለቅዱስ ሲኖዶስ ከታች የተመለከተውን ጩኸት ለትልቁ ጆሮአቸው ማሰማት እንወዳለን።


በተለይ ለኢትዮጵያ መንግሥት፤


መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው የሚል ሕግ ቢኖርም እንደኢትዮጵያ ባሉ ሀገሮች ይህንን የአሜሪካውያንን ሕግ ለመተግበር ይቻላል ብሎ ማሰብ ራስን ማታለል ነው። በአንድም ይሁን በሌላ ምክንያት እነዚህ ሁለት ክፍሎች ግልጽም ስውርም ግንኙነት አላቸው። በዚህ ጽሁፍ ያንን ወደማብራራት አንገባም። ነገር ግን ማሳሰብ የምንወደው ነገር እንደዜጋም፤ እንደ እምነት ሰውም የምንናገረውን ሊሰማን ይገባል። ምንም እንኳን የኛ ማሳሰቢያ ሚዛን ባይደፋ፤ ማሳሰቢያችንን  መስማት የሚችልበት እድል ባይኖር  የመንግሥት ጆሮ ትልቅና  ከዝሆን የተሻለ ነው ብለን ስለምንገምት ጥቂት መናገር አስፈልጎናል።

1/ መንግሥት ካለፈው ስህተት ከመማር ይልቅ ስህተትን እንደተመረቀበት ሙያ መደጋገም የለበትም። የፈረንጆቹን አባባል በመዋስ በአጭር ቃል ላስቀምጥ። «በመጀመሪያ ስታልፍ የመታህ የድንጋይ እንቅፋት፤ ዳግመኛ ስትመለስ ቢመታህ ድንጋዩ አንተ ነህ» ይላሉ። ስለዚህ ዳግመኛ ስህተት መሥራት የለበትም።

2/ አሁን ላለው የቤተ ክርስቲያን ቀውስና ምስቅልቅል ሙት ወቃሽ አያድርገኝና የምናከብራቸው አባት አቡነ ጳውሎስ ትልቅ ድርሻ ነበራቸው። ማንን መሾም እንዳለባቸው ያለማወቃቸው፤ ገንዘብና አስተዳደር ላይ የነበራቸው ድክመት፤ ሥርዓተ አልበኞች እየተፈለፈሉና እየፋፉ የሚሄዱበትን ሁኔታ ለማስቆም የሚያስችል  ሥራ  ባለመሰራቱ ይህንን ሁሉ ወዝፈው አልፈዋል። ዛሬ ያንን የተረዳ፤ ማስወገድ የሚችል ብርቱ፤ በሥራው የተመሰከረ፤ ለተግዳሮቶች ራሱን ያዘጋጀ መሪ እንዲኖረን እንፈልጋለን። ስለዚህ መንግሥት ያለፈ ስህተቱን በመድገም እኔን ብቻ የማይቃወም ይሁን በሚል ስሌት ይህችን ጥንታዊ ቤተ ክርስቲያን ማጥፋት የለበትም።

3/ እርግጥ ነው፤ መንግሥት ቤተ ክርስቲያን  ራሷን ችላ በመንፈሳዊ እድገት፤ በልማትና በማኅበራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ እንድትገባ ይፈልጋል። ድጋፍም እንደሚሰጥ ይገመታል። ነገር ግን የእርስ በእርስ መጠላለፋችንን እያየ እጁን ለማስገባት መሞከሩ ነገሩን ከማባባስ በስተቀር ጤና የሚሰጣት አይሆንም። ስለዚህ  መንግሥት ከራሱና ከጥቂት የቤተ ክርስቲያን ሹመኞች ጋር ብቻ የሚያደርገውን ግንኙነት በልክ አድርጎ የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ያገባኛል ከሚለው ነገር ግን ቦታ ካልተሰጠው ሕዝብ ጋር ሆኖ የእውቀት፤ የታሪክ፤ የባህል፤ የቅርስ፤ የትውፊት ባለቤት የሆነችውን ቤተ ክርስቲያን ወደፊት እንድትሄድ ድጋፍና እገዛ ማድረግ ይገባዋል።


4/ አሁን እየተደረገ ባለው የማፊያዎች የምርጫ ግርግር ውስጥ ራሱን በመክተት የመንግሥትነት ክብሩን፤ስሙንና ታሪኩን ማቆሸሽ የለበትም ።  ቢቻል በትክክል የምናውቃቸውን እነዚህን ዐመጸኞች ሥራ ካላቸው ወደየሥራቸው እንዲሄዱ፤ ዐመጽ ይሻለናል ካሉም ለዐመኞች ወደተዘጋጀ ሥፍራ ሊወስዳቸው ይገባል። የምርጫው ውጤት አስቀድሞ ታውቋል። መንግሥት የሚፈልገውን ለማስቀመጥ ከዐመኞች ጋር እየሰራ መሆኑ ይነገራል። እየተባለ እንደቆየው የታሰቡት አቡነ ማትያስ ቢሾሙ የምእመናን ፓትርያርክ ሳይሆኑ ሁለተኛው የኢህአዴግ ፓትርያርክ መባላቸው አይቀርም። ስለዚህ ከዚህ የቆሸሸ ስም ለመውጣት ዐመጸኞችና ዐድመኞች በሌሉበት ሁኔታ ሁሉም ያመነበትና የተቀበለው ምርጫ እንዲደረግ ማገዝ አለበት።  መንግሥት ለሕዝቡ ጥቅም፤ ለሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ብሎም ለራሱ መልካም ስምም ሲል ይህንን ያድርግ እንላለን።  አሁን እየሄደ ያለበትን መንገድ ቆም ብሎ ያስተውል፤ ዐመጸኞችንና አድመኞችን አደብ አስገዝቶ የተካረረውን አየር ቀዝቀዝ ያድርግልን። የረጋ ቂቤ ወተት ይወጣዋል እንዲሉ ግርግር የሚጠቅመው ሌቦችን እንጂ ሰላማውያንን አይደለም።

በአንድ በኩል ከእስላም አክራሪዎች ጋር የዘገየ ሰዶ ማሳደድ ውስጥ ገብቶ በሌላ በኩል ደግሞ የክርስቲያኑን ቀምቶ በራሪዎችን ደግፎ መቆም፤ ኡኡታ የሚከተለውን የህዝብ የጥላቻ ድምጽ ለማስተናገድ ይህንን ጊዜ ማበላሸት የለበትም። በጊዜው ሊደረግ የሚገባው አለመደረጉ አለጊዜው ለማድረግ የሚያስገድድ ነገር ያስከትላል።


ለሊቃነ ጳጳሳት፤


እግዚአብሔርን የሚፈራ ስለመኖሩ እጠራጠለሁ። ባይሆንማ ኖሮ ሲነዱት የሚነዳ፤ ሳይጠሩት የሚመጣ መሪ ማየት ባልቻልንም ነበር። የጽድቁን ነገር እናንተና እግዚአብሔር የምትነጋገሩበት የግል ጉዳያችሁ አድርገን እንተወውና እባካችሁ ይህች ቤተ ክርስቲያን በእናንተ ጊዜና ዘመን አትጥፋ፤ ለታሪክም ለትውልድም እዘኑ። አንድ ቀንም ቢሆን ወደኅሊናችሁ ተመለሱ፤ ገበናችሁን መሸፈን፤ ንግግራችሁንና እንቅስቃሴአችሁን መገደብ ቢያቅታችሁ ቤተ ክርስቲያን ላይ ለምን ጥፋት ትፈርዳላችሁ? ቀድሞውኑ ጵጵስና የተቀበላችሁት ይህችን ቤተ ክርስቲያን ለትውልድ ለማስተላለፍ አልነበረም? እነ ጴጥሮስ ከጣሊያን ጋር ተዋድቀው ያቁዩአትን እናንተ በአየርና በላንድ ክሩዘር ዞራችሁ መጠበቅ አቃታችሁ? እናንተን ለመምከር የደፈርኩት ከተቀበላችሁት አደራ ጋር የሚመዛዘን ቀርቶ የሚቀራረብ ነገር ባላገኝ ነው። እስኪ እንደ ሊቀጳጳስ መሆን ቢያቅታችሁ አንድ ቀን እንኳን ሞት እንዳለ እንደሚያስብ የፈሪሃ እግዚአብሔር ሰው ሁኑ! ሁለቱ ሊቀጳጳሳት ከምርጫ ማግለላቸው እውነት ከሆነ የሚያስመሰግን ተግባር ነው። እንዲያውም ሲኖዶስ የዘንድሮውን ምርጫ ማቆም አለበት። ለዚህም አደራ አለባችሁ። እኛ የፈለግነው ሰው እንጂ ሥልጣን ላይ የሚቀመጥ አይደለም። ሰው የሆነ ሰው መምረጥና ሥልጣን ላይ የሚቀመጥ ሰው መምረጥ ሁለት የተለያዩ ነገሮች ናቸው። ስለዚህ የካቲት 21 የሚደረገውን የምርጫ ቀን በመሰረዝ የተረጋጋ፤ ሰላማዊ፤ ሁሉ የወደደው፤ ለቤተ ክርስቲያን የሚበጅ አባት እንድንመርጥ ይህንን እድል ተጠቀሙበት። ያለበለዚያ ታሪክና ትውልድ ሲወቅሳችሁ ይኖራል። ቤተ ክህነቱ አሁን ባሉት ዐቃቤ መንበሩ እየተመራ ይቆይ። ካልቻሉም ሌላ ዐቃቤ መንበር ይሰየም። የሁከት መንፈስ ከቤተ ክህነት ግቢ እስኪወጣና ሕዝቡ እስኪረጋጋ የምርጫ ጊዜው ወደፊት ይቀጠር። በሀገር ዐቀፍ ደረጃ ምእመናኑ የመወያያ ጊዜ ይሰጠው። የምርጫ ህጉ ክፍተት የማይሰጥ፤ ሁሉን ያሳተፈ እንዲሆን ይሻሻል፤ አስመራጭ የሚባሉትን በሕዝብ ተወካዮች ይመረጡ፤ የቤተ ክርስቲያኒቱን ሕግና፤ የሀገሪቱን ሕግ የሚያከብር፤ ከዘረኝነት፤ ከጠባብነት የራቀ በመንፈስም፤ በልማትም ሊሰራ የሚችል አባት እንድንመርጥ እድል ይሰጠን።

ቅዱስ ሲኖዶስ ያላመነበትን ወይም መንግሥት ሾመብን ወይም እነኤልዛቤል የመረጡትን ሰው አምኖ እንደማይቀበል ቢታወቅም ምን አገባኝ ደመወዝና መኪናዬ አይቅርብኝ እንጂ በሚል እሳቤ ራሱን በምድራዊ አስተሳሰብ ውስጥ ከማስገባት ወጥቶ ታሪክ ይስራ፤ መንፈሳዊ አደራውን ይወጣ ወቅታዊ ጥሪያችን ነው።