Wednesday, February 20, 2013

ሰላም ለተዋሕዶ እምነት ተከታዮች

በይትባርከ ገሠሠ

 (ይህ ጹሑፍ በሰንደቅ ጋዜጣ 8 ዓመት ቁጥር 389 ረቡዕ የካቲት 13/2005 ታትሞ የወጣ ነው)

በመጀመሪያ የጠራ እምነትና ቃልን መሠረት ማድረግ ይገባል። ስለ እምነት ስንናገር የቁልምጥ ቃላትን ልንጠቀም አይገባም። ዘወትር የክርስቶስ ትምህርት 4 ወንጌላትን ማንበብ ይገባል። ፈሪሳዊያንና ሰዱቃዊያን በስሕተት ጥያቄ ሲዳፈሩት ክርስቶስ ኃይለ ቃል ያለበትን መልስና ትምህርት ያቀርብ ነበር።
በቴክሳስ የተደረገው ጉባኤ እንደ እምነት ወግ የዘገየ ቢሆንም ሙከራው መልካም ነበር ማለት ይቻላል። መሠረተ ይዘቱ ስንመረምር ግን የተጣላች ቤተ ክርስቲያን አይደለችም፡ አንድ ናትና። የተጣላ እምነት አይደለም። እምነት ወይም አምላክ አንድ ነውና። እኔ ልሾም እኔ ልበልጽግ በማለት የተጣሉት መነኮሳት ናቸው እንጂ። ህዝበ ክርስቲያኑ በማያውቀው ምሥጢር እርስ በራሱ ተለይቶ ይኖራል። ምንኩስና ሥርዓት ለሥልጣኑ ሲል በሚፈጥረው ሰበብ ከረጅም ጊዜ ጀምሮ ህዝበ ክርስቲያኑ ሲጨፈጨፍ ሲጣላ ኖሮአል። እንዲህ ሊሆን የቻለውም የምንኩስና ሥርዓት ያለ ታሪኩ፡ ያለ መደቡ፡ ያለ ቦታው፡ ያለ ውሉና……የመሳሰሉትን ሁሉ ረግጦ ከቤተ ክርስቲያንዋ ቁንጮ ወጥቶ ስለ ተከመረ ነው። አሁንም የሚነታረኩ ለራሳቸው ሥልጣን እንጂ ለቤተ ክርስቲያን ክብርና ለምእመናን አንድነት እንዳይደለ በድርድራቸው ኂደት ማወቅ ይቻላል። መነኩሴና መነኩሴ ተደራድረው የሚፈይዱት ውጤት እንደማይኖር አስቀድሞ ማወቅም ብልህነት ነው። ለዚህ መድኀኒቱ ሌላ ነው። እሱም ሊቃውንት፣ ካህናትና ህዝበ ክርስቲያን አንድ ኃይል ፈጥረው ተዋሕዳዊ መሠረተ ሕግ ካልጣሉበት በቀር እየተድበለበሉ፡ ህዝበ ክርስቲያኑን እያሳዘኑና በነጣቂዎች እያዘረፉ መኖር ነው።
ለመሆኑ አቡነ መልከጼዴቅ ማን ናቸው?
በኢትዮጵያ ኪነ ጽሑፍ ሥርዓት ጽሑፉ ቦታ እንዳያጣ የቀድሞ የክብር ስማቸው ተቀምጦአል። የተዋሕዶ እምነትና የንጉሡም ክብደት ተጨምሮበት ሊሆን ይችላል፡ አንድነትዋንና ክብሯን ሊጠብቁላት የመጨረሻው የክብር ቦታዋ አንድ ደረጃ በቀረው ላይ ሰየመቻቸው፤ አከበረቻቸው። ይሁን እንጂ አገር ውስጥ ሳሉም ለግላቸው ይጠቀሙባት እንደ ነበሩና ለተዋሕዶ እምነት አስተዳደር የማይታዘዙ እንደነበሩ ሕይወት ታሪካቸውን መመልከት ያስፈልጋል። አሁንም ውጪ ሀገር ኄደው ከመጀመሪያ ግንጠላው ጀምሮ የግንጠላው ተጠያቂ እሳቸው ራሳቸው ብቻ መሆናቸውን ማረጋገጥ ይገባል። ለክብራቸው ለኑሮአቸው ሲሉ ቤተ ክርስቲያንዋን የከፈሏት እሰቸው ናቸው። አቡነ መርቆሬዎስ በፍጹም በዚህ ጉደይ ተጠያቂ ሊሆኑ አይገባም። ግንጠላው ሲከናወን አልነበሩምና። አገር ውስጥ ነው የነበሩ። ኋላ ከጥቁሩ ባሕር ኄደው ተቀላቀሉ እንጂ። አዘጋጁ እንደሚያውቀው አቡነ ይስሐቅም በእሳቸው ተገፋፍተው ፈጸሙት እንጂ አላሰቡበትም ነበር።
ወደ መሠረታዊ አጭር ታሪክ እንግባ። 1983 . የውጪው ተደራዳሪ ሲኖዶስ ነኝ የሚለው ሲገነጠል በመጀመሪያ የዘመኑ ምስክር አዘጋጁ እንደ ሆነ ማስቀደም ይገባል። ሐምሌ ወር 28 ሐሙስ ቀን ኒውዮርክ ከተማ ውስጥ ሰሚናሪ ኮሌጅ ከሚባል ቦታ ስብሰባ ተጀመረ። በየዓመቱ የአሜሪካ ርክበ ካህናት በአቡነ ይስሐቅ መሪነት ስንሰበሰብ ነበርንና ነው። በየዓመቱ የማይቀሩ የነበሩ በጣም የሚመለከታቸው ካህናት ቄስ አስተርአየ ጽጌና መምህር ፍሥሐ ጽዮን ካሣ የሚባሉ የዋሺንግቶን ዲሰ. ኑዋሪዎች ኢንፎርሜሽን ሳይኖራቸው አይቀርም ፤አንኄድም ብለው ቀሩ። አዘጋጁ ግን ከሥራው ያለ ክፍያ የሳምንት ፈቃድ ወስዶ ከዋሽንግቶን ዲሲ ወደ ኒው ዮርክ ከተማ ኄደ።
ከላይ እንደ ተጠቀሰው ስብሰባው የተጀመረው ሐሙስ ቀን ነበር። ከሐሙስ እስከ ቅዳሜ ስብሰባው ሲከሃኄድ ተሠውሮበት ነው መሰል የሰማው ነገር አልነበረም። ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ ከኢትዮጵያ ሲኖዶስ እንገነጠላለን የሚል ሐዲስ ሐሣብ ሰማ። ሀላፊነቱ የአቡነ ይስሐቅ የነበረ ቢሆንም ተገንጣይ ስብሰባውን የመሩት ሊቀጳጳስ መልከጼዴቅ ነበሩ። ለግንጠላው ትልቅ ምክንያት ሆኖ የቀረበውም አባ ጳውሎስ ፓትርያርክ ሆነው (በነሱ አቀራረብ ሆኖ) ከኢትዮጵያ ሲኖዶስ ኅብረት አይኖረንም ነበር። ከዚህ ችግር የደረሰው የሰሜን አሜሪካ፣ የደቡብ አሜሪካና የኢሮፕ ሀላፊ ሊቀጳጳስ የነበሩት አቡነ ይስሐቅ ሳያስቡትና ሳይፈልጉት በአቡነ መልከጼዴቅ ግፊት ግንጠላው ተፈጽሞአል። እኛ ራሳችን ጠንቅቀን የምናውቀው ቢሆንም ኋላ ራሳቸው አቡነ ይስሐቅ ሳላስበው አሳስተውኛል ብለዋል። በመጀመሪያ በዚሁ ግንጠላ የተቃወሙት 1. አባ ሐዲስ ግደይ ከኒውዮርክ አሁን ሲያትል። 2. ስም ዘነጋሁ የቤርሙዳ ተወካይ ካህን። 3. ታናሹ አባ ይስሐቅ ከሚኒሶታ የመጡ። 4. ራሱ የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ከዋሺንግቶን ዲሲ ነበርን። ደጋፊዎች፡ 1 አቡነ ይስሐቅ 2. ሊቀጳጳስ መልከጼዴቅ 3. ሊቀ ካህናት ምሳሌ ከካናዳ 4. ቄስ ከበደ ከምዕራብ ስቴቶች 5. ስማቸውን የረሳሁት ከኒውዮርክና ከሌላም። እነዚህ ሁለቱ ሊቃነ ጳጳሳት 5ኛው ፓትርያርክ እንዲመረጥ በቅድሚያ ኢትዮጵያ ውስጥ ተስማምተው ፈርመው እንደ ነበሩ በብዙ የቤተ ክርስቲያን ሰዎች ይታወቃል።
ግንጠላው ሲፈጸም አቡነ መርቆሬዎስ አገር ቤት ስለነበሩ የግንጠላው መሪ ወይም ተባባሪ ሊባሉ አይገባም።  


ኋላ በኂደቱ ክስተት የተገኙ ናቸው። እሑድ የሰንበት አገልግሎት አድርሰን ዕረፍት ነበር። ሰኞ ከአባ ሐዲስ በስተቀር ሁሉም በመገንጠሉ ተስማምተዋል። ሰኞ ጧት ስብሰባው እንደ ቀጠለ፡ ወደ 550 ሰዓት ገደማ በአቡነ ይስሐቅ ጠሪነት የኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጠኛ መጣ። በመጀመሪያ አቡነ ይስሐቅን አነጋገረ። አቡነ ይስሐቅ ከአሁኗ ደቂቃ ጀምሮ በእምነት ሳይሆን በአስተደደር ከኢትዮጵያ ሲኖዶስ ተገንጥለናል አሉ። ለኢትዮጵያ ሲኖዶስ አንታዘዝም በማለት መግለጫቸውን ሰጡ። በመቀጠል እያንዳንዱን ተሰብሳቢ ከጠየቀ በኋላ ጋዜጠኛው ተሰናብቶ ኄደ። ከዚያ ምሳ በላንና የሰዓት በኋላ ስብሰባው ቀጠለ። ስብሰባው ሲጀመር አዘጋጁ ተነሣና የእውነት የሐይማኖት ሥራ መስሎኝ ሥራዬን ትቼ መጥቼ ነበር። ይሁን እንጂ ወደ አልሆነ አቅጣጫ ስለ አመራ ከእምነቴና ከፍላጎቴ ጋር እንደማይስማማ አረጋግጬአለሁ። ስለሆነም ከዚቺ ደቂቃ ጀምሮ ከእናንተ ጋር ኅብረት አይኖረኝም በማለት ስብሰባውን ረግጦ ወጣ። ከጸሎታቸውና ስብሰባቸውም ኅብረት ኖሮት አያውቅም። ችግር ስለ ሆነ በለቅሶ ጊዜ ብቻ ይገናኝ ነበር። አንድም የተዋሕዶ እምነት ባለሥልጣን ሳይሰማ በመጀመሪያ ግንጠላውን የተቃወመ አዘጋጁ ነበር። እንዲህ በቅድሚያ ስለ ተቃወመ ከዚያ በኋላ መነኮሳቱ ለስብሰባ አዘጋጁን ጠርተውት አያውቁም። ምክንያቱም የመደባቸው ቁንጮ ስለ ተነካ ነበር። የተደረገ ቢደረግ ለእምነቱ ሳሆን የሚጨነቁት ለመደባቸው በጣም ጥንቁቆች እንደሆኑ ያረጋግጣል። ሁለተኛ አባ ሐዲስ እንደ ተቃወሙ ስብሰባውን ጨርሰው ኄደዋል። አባ ሐዲስ ይህን በመፈጸማቸው የአቡነ ጳውሎስ ባለ ውለታ ሆነው ዘልቀዋል። ከላይ ካልተፈቀደ፣ በመንፈስ ቅዱስ ካልተላከ ሊሆን አይችልምና ባይሳካም ለጵጵስናም ተመልምለው ነበር። በሁለቱም ወገን ተወጋግዘው እያሉ የሁለቱም ቦታ መነኮሳት አብረው ይቀድሱ እንደነበሩ ብዙ ምእመናን ያውቃሉ። የምንኩስና ሥርዓት ከሕገ ቤተ ክርስቲያን ጥበቃ ይልቅ ለራሱ ክብር ለመደቡ ጥንቃቄ እንደሚያደርግ በኂደቱ የተረጋገጠ ነውና።

አቡነ መልከጼዴቅ በሥልጣን ላይ እያሉ የአንድነት ሰላም እናያለን ብሎ መጠበቅ ሞኝነት እንደሚያስመስል ማወቅ በተገባ ነበር። ተስፋ የሚያደርጉ ምእመናን ካሉም፣ በውጪው ዓለም በተለይ በሰሜን አሜሪካ ውስጥ ያላቸውን ካፒታልና ክብር ባለ ማወቅ ሊሆን ይችላል። ዐሥራት በኩራት የታዘዘ ቢሆንም በስመ ሕገ አምላክ ለፖለቲካ ክንውን የሚያውሉትን በተለያየ ጊዜ በዓላትን አደረግን በማለት የዋሁ ህዝብን እንዴት እንደሚዘርፉት ለመገመት የሚከብድ አይደለም። ለብዙ ዓመታት ፖሊቲካል ሳይንስን የተማረውን ተመራማሪ ምሁር መነኮሳት እንዴት እንደ ሚያታልሉት ለመገመትም በጣም ከባድ ነው። የኢትዮጵያ ሲኖዶስን ከሚከተል ህዝብ በእጥፍ የነሱ ይበልጣል። የጸሎት ቤታቸው ዐቅምና ጉልበትም በዚያ ልክ ነው። እና ተቀናቃኝ በሌለው መድረክ ላይ ሆነው በነፃነት ያለ ገደብ ዶላርን እያፈሱ ከሚኖሩበት ዓለም ተነቅለው ወደ ንዝንዝ ይመጣሉ ብሎ መጠበቅ የቀድሞ የአባ ሀብተ ማርያምን የሥራ ልምድ ካለ ማወቅ በላይ መጃጃልም ነው ሊያስብል ይችላል። ከዚያ ያሉ የነሱ አቢያተ ክርስቲያናት (በእምነት አልተገነጠልንም) ስለ አሉ ነው። በኢትዮጵያ ሲኖዶስ ሥር ይሁን ቢባል ይስማማሉ ብሎ የሚያምን ምእመን የነሱን መደራጀትና አስተሳሰብ ባለ መረዳት ሳይሆን አይቀርም። ምናልባት ኂደቱ ካልተበላሸ በቀር ከአንድ ሰው ዕድሜ በኋላ ሊሆን ይችል ይሆናል። በአሜሪካ ውስጥ ያለው የኢትዮጵያ ሲኖዶስን ይከተላል የሚባል ቤተ ክርስቲያንም ሁሉ የአገልጋዩ መነኩሴ ንብረት ነው። ሀብትነቱ ወይም አካውንቱ በኢትዮጵያ ሲኖዶስ ሥር ይሁን ቢባል በዚሁ የሚስማማ አንድም ካህን መነኩሴ አይገኝም። ሁሉም እንደነ እንቶኔ ይሸፍታል። ስለ ዚህ ቤተ ክርስቲያንዋ በውጪው ዓለም ወጥ የሆነ ሥርዓት የላትም ቢባል እውነቱን ሊያጎላው ይችላል።
አቡነ መርቆሬዎስ
አንዳንድ የዋሆችና የደርግን ዘመን ዘመነ ፍዳን ምንም የማያውቁ ንጹሐን ብራናዎች አቡነ መርቆሬዎስ ወደ ፕትርክናው ይመለሱ የሚል መጠይቅ አጥማጆችን አስነብበዋል። ሞኝና ወረቀት የያዘውን አይለቅም እንደተባለው (ይህ ሹመት በአንድ ሀገር በአንድ ዘመን ቢሆን ለሁለት ሰው ልትሆን አይገባም። ይህ ከተደረገ ግን አስቀድሞ ለተሾመው ትፅና) የሚለውን የግብጸዊው ፍትሐ ነገሥት ጠቅሰው ያላዝናሉ። በዚህ ዝግጅት የአቅራቢው ውሳኔ ግን ይህ ንባብ አቡነ መርቆሬዎስን የማይመለከት ቢሆንም፡ ፍትሐ ነገሥት ግን እንዲህም ይላል። አማፂ ጳጳስ ከኀዲ ንጉሥ ከተነሡ ህዝቡ ተባብሮ ከሥልጣናቸው ያወርዳቸዋል ይላል። ወደ ፍሬ ነገሩ እንመለስና የማያስመልሳቸው በዘመናቸው የተፈጸሙ እንዲህ ሆነ እንዲህ ተደረገ የሚለውን ትልቅ ታሪክ ትተን ምክንያቱም ብዙ እና ከባድ ስለ ሆነ፡ በቀላሉ ስንመለከተው 1. በዕድሜ የገፉ ይመስለኛል። አንድ ሰው ከመነኮሰ ለሥራ የተፈቀደ ባይሆንም ካልሠሩ ከወንበር መቀመጡ ፋይዳ ሊኖረው አይችልም። 2.በቤተ ክህነት ሠራተኞች እንደ ሚባለው በአቡነ መልከጼዴቅ አማካሪነት ለሲኖዶስ ማመልከቻ ጽፈው እንደ ወረዱ በአጠገባቸው የነበሩ የሚያረጋግጡት ነገር ነው። ስለ ሆነም 21 ዓመት በኋላ ወደ ወንበር ይመለሱ ማለት የልጆች ጨዋታ ቢመስልም 2000 ዘመን ውስጥ ይህን መሰል በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተፈጸመ ታሪክ ይኖራል ተብሎ አይገመትም። ስሜትም አይሰጥም። አገራቸውን ገብተው በክብር መሰንበት ግን ተገቢና አኩሪም ሊሆን ይችላል፡ ላገርም ክብር ነውና።
መፍትሔ
በአሁኑ ጊዜ በዚሁ በተለመደው እየተድበለበለ ይቆይ። ለረጅም ፕሮገራም ለወደፊት ግን ቤተ ክርስቲያንዋን ሊታደጋት የሚችል የሊቃውንት፣ የሕጋዊያን ካህናትና ምእመናን የሆነ ኀይል ተፈጥሮ ካልደረሰላት በቀር መደብ ጠባቂ መነኩሴና መነኩሴ ተደራድሮ የተሻለ ዐቅም ይፈጥርላታል የሚል ተስፋ ከዚሁ ቢዘጋ እውነትነትን ሊያረጋግጥ ይችላል። ለምሳሌ ከተደራረዳሪው ቡድን ውስጥ ንቡረ እድ ኤልያስና ሊቀ ካህናት ምሳሌ እንደ ሁለተኛ ፍጡር ሆነው የተጠቀሱት ምን ለማለት ነበር? ንቡረእድ ከቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት አንደኛው ናቸው። በዕውቀትና በሥነ ሥርዓት ከማንም በላይ ቤተ ክርስቲያንን ሊወክሉ የሚችሉ ናቸው። ሊቀ ካህናት ምሳሌም መገንጠላቸውን ሳናስታውስ በሕገ ዘካርያስ የፀኑና ሕገ ቤተ ክርስቲያንን የጠበቁ ናቸው ማለት ይቻላል። ሌላዎች ግን እውነቱን እንናገር ከተባለ የክርስቶስና የሓዋርያት ትዕዛዝ አያውቃቸውም ቢባል እውነትነቱን ያረጋግጣል። በራሳቸው ሥልጣን በራሳቸው ስብሰባ በራሳቸው ውሳኔ ያደጉ ናቸውና ነው። አንድ ሰው ከመነኮሰ በኋላ ሹመትስ ይቅርና ወንድም፡ እኅት፡ አባትና እናት የለውም። አገር፡ ንብረት፡ ልጅ የለውም። በዚህ ዓለም የተሰደደ፡ የፈለሰ፡ የሞተ፡ የተናቀ፡ የወደቀ ነው። እነሱ ግን በአሁኑ ቤተ ክርስቲያንዋን የምእመናን ሃብት መሆንዋን ረስተው ክደው የእነሱ የአባታቸው ነብረት አድርገው ቆጠሩአታል። ‹‹መጽሐፈ ሰዋስው ወግሥ አለቃ ኪዳነ ወልድ›› ተመልከት። ስለ ዚህ የክርስቶስና የሐዋርያት ትዕዛዝ ሥራቸውን የሚጸየፋቸው መሆናቸውን እንዴት አያውቁም? የእምነትዋ አባላት ሁሉ ይህን ማወቅ ይገባቸዋል። የእምነት ውሳኔ ሲወሰን፣ በማን ለማን ምን የሚለውን በትክክል መታወቅ አለበት።
የቤተ ክርስቲያንዋ አባለት ሁሉ ልብ በሉ። የፖለቲካና የግል ተጠቃሚዎች ህዝቡን የሚያወናብዱበት ልዩ ጎራ መፍጠራቸውን አትዘንጉ። ሳይንስን ሊመራመሩ በቴክኖሎጂ አገርን ሊያሳድጉ ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው የወጡ፣ ያለ ቦታቸው ተዘፍቀውና ለራሳቸው ተደናግረው ህዝበ ክርስቲያንን ሲደናግሩ የሚታዩ ብዙ ናቸው። የውጪ ሲኖዶስ የግቢ ሲኖዶስ እያሉ ዐውቀው በእኩልነት እያወዳደሩ የዋህ ህዝበ ክርሰቲያኑን እያመሱት ነው ለመሆኑ ስለ ቤተ ክርስቲያንዋ በየፊናው የሚጽፉ ያሉና ህዝቡን የሚያተራምሱት ያሉ እነ ማን ናቸው? ከደጀ ሰላምዋ ከትምህርት ቤትዋ ጓሮ የሰነበቱና ያደጉ ናቸው? በድርጅትና በጓደኛነት እየተሰባሰቡ የሚያምሱአት ባለቤት በመጥፋቱ ነው። የሚመለከተው ባለቤት ሁሉ ጥግ ጥጉን ይዞ ዝም ብሎ ይመለከታቸዋል። ለመሆኑ የውጪ ሲኖዶስ የግቢ ሲኖዶስ ማለት ምን ማለት ነው? ከፈለጉ አገራቸው ነው ይምጡ መብታቸውን ይጠቀሙበት። አለዚያ አሜሪክ የዓለም ህዝብ አገር ነችና የፈለጉትን ጠርተው ከዚያ መኖር እንደ ጀመሩት በዚያው ይግፉበት። በሀገሩ ውስጥ የሚኖር የኢትዮጵያ ህዝብ በሀገሩ ውስጥ ያለ የነበረ ሲኖዶስ በቀር ሌላ የሚያውቀው ሲኖዶስ ሊኖር አይችልም ማለት ይገባል። እንዲያ ቢሆንም በማንኛውም ጊዜ ወደ ሀገራቸው ሲመጡ እንደ ኢትዮጵያዊ ሁሉ የተፈጠሩባት ሀገር ስለ ሆነች ማንም የሚከለክላቸው ወይም የሚቸራቸው ኃይል ይኖራል ተብሎ መገመት የለበትም።
አንድ ትልቅ ዋርካ አለ እንበል። የዋርካውን ፍሬ እየመጠመጡ ከሚኖሩ ብዙ ወፎች አምስት ስድስት ወፎች ተደናግረው ወደ ሌላ ዋርካ ኄደው ቢቀሩ፣ ትልቁ ዋርካ ምን ይጎድልበታል? ፍሬው ልምላሜው እንዳለ ይቀጥላል። በዚሁ መሠረት ሲመጠምጡአት የነበሩ ንዝንዛቸውን ይዘው ከዚያ ኄደው ቢቀሩ የኢትዮጵያ ተዋሕዶ ዕምነት ምን ይቀርባታል። በተለይ ውጪ ሀገር ኄደው የሚመለሱ መነኮሳት አስፈላጊ ያልሆነ የተለያየ ፈሊጥ ይዘው ነው የሚመለሱ። ለምሳሌ፡ እስከ እኛ ዕድሜ ድረስ የኢትዮጵያ ተዋሕዶ እምነት ትባል የነበረቺቱን ወደ ግሪክ ኄደው ቅይጥ ቴኦሎጂ (ነገረ መለኮት) ሸምተው በሚመጡ መነኮሳት ኦርቶዶክስ የሚል ቅይጥ ስምንም ይዘው በመምጣታቸው ኦርቶዶክስ እየገነነ ተዋሕዶ እየተዋጠ ካለንበት ደርሰናል። የእምነታችን ፍጹማዊ ትርጉምም ተዋሐደ ከሚለው የተገኘ ተዋሕዶ ብቻ ነው። እስከ 60ዎቱ . . ድረስ የሀገር ቤት ሊቃውንት ኦርቶዶክስ የሚለውን ቅጽል ስም አያውቁትም ነበር።
በሌላ ወገን ልጅ ኢያሱ የአያታቸው የዓፄ ምንሊክ ዙፋን ይዘው ነገሡ። ስለአልቻሉበት ወይም እግዚአብሔር በቃህ ስላላቸውና ለምክንያትም እኅታቸው ስለ ወለደች እኅቴን ልጠይቅ በማለት ከአዲስ አበባ ወደ ሐረር ኄዱ። የኢትዮጵያ መኳንንት ተሰብስበው መክረው የዓፄ ምንሊክ ሴት ልጅ ንግሥት ዘውዲቱን ከላስታ አምጥተው አነገሡ። ራስ ተፈሪን አልጋ ወራሽ ብለው ሾሙ። የልጅ ኢያሱ አባት የወሎ ገዥ የነበሩ ንጉሥ ሚካኤል ንጉሥ ነኝና በማለት ህዝባዊ ከሆነው ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ሰገሌ ላይ ጦርነት ገጠሙ። ግን ግለኛ ንጉሥ ስለ ሆኑ አላሸነፉም፡ ከመንግሥት ጋር ለመወዳደር አልቻሉም። ልጅ ኢያሱም በዚያው ቀሩ። አሁንም ከዚያ ኄዶ ራሱ ሲኖዶስ ነኝ ስለ አለ ሁለት ሲኖዶስ እያሉ መጥራት አግባብ ሊሆን አይችልም። ሁለት ሲኖዶስ ካሉ ሁለት አምላክ አላቸው ማለት ነው። እኛ ግን በሀገራችን አንድ አምላክ አንድ ሲኖዶስ አለን። ሁለት ሲኖዶስ ሁለት አምላክ አናውቅም። አምላካችን አንድ ነው ሲኖዶሳችንም አንድ ነው። የሃይማኖት ምሥጢር ሳይገባው የሚፈነጥዘው ሁሉ መንፈሳዊ ትዕግሥትን ሊላበስ ይገባል። ምክንያቱም ስለተማረ እንጂ ስለ መነኮሰ ያውቃል ማለት አይደለምና ነው።
እውነተኛ የተዋሕዶ እምነት ተከታዮች ቢሆኑማ መነኮሳት የጻፉት መጽሐፋቸው መጽሐፈ መነኮሳት እንደ ሚነበበው ሆሊውድ ከሚገኝበት ወደ ካሊፎርኒያ ከመሰደድ ይልቅ ወደ በረሃ ወደ ጫካ ወደ ገዳም ባመሩ ነበር። ዲያቆን እየተነሳ ስለ ቤተ ክርስቲያን ምሥጢር ማስተማር አይችልም። ( ዲያቆን ኢይምሰልከ ዘተክህንከ) ዲያቆን ሆይ የተካንክ አይምሰልህ፤ይላል መጽሐፉ። የህክምና ቋንቋ የራሱ የሆነ አለ። የኮምፒዩተር ቋንቋ የራሱ የሆነ አለ። የቤተ ክርስቲያንም እንደዚሁ ነው። ስለ ዚህ እናንተ ጸሐፊያን ሁሉ በቃችሁ ህዝቡን አታውኩት። እባካችሁ ስለ ፈጣሪ እንዳልላችሁ በጽሑፋችሁ እንደተረዳሁት ነጋዴዎችና ቀዳዳ ፈላጊዎች ስለ ሆናችሁ ልትሰሙት አትችሉም በማለት ነው። ፍላጎታችሁን ለማሳካት፡ ቤተ ክርስቲያናችን ትፈርሳለች ትቀጭጫለች የምትሉ ሁሉ የእምነታችሁ አለ መስተካከል ያመለክታል። ቤተ ክርስቲያንዋን የሚጎዳ አንድም ፍጡር ሊኖር አይችልም። ምክንያቱም የመሠረታት ክርስቶስ ተጠቃሚ ሊመለከተው የማይችል እርስዋን የሚጠብቅበት ሥውር ሰፍ አለውና ነው።
ከሚገርመው የቅዱስ አትናቴዎስን ታሪክ ሲጠቅሱ እናያለን። ምን ለማለት ነው? አቡነ መርቆሬዎስን አትናቴዎስ፡ በኢትዮጵያ ያለፉትንና የሚተኩትን ፓትርያርኮች የአርዮስ ተከታዮች፡ ኢህአደግን የአርዮስ ተከታይ የነበረ ትንሹ ቆስጠንጢኖስ ማድረጋቸው ነው። ራሳቸውን ተንከባካቢዎች በሚያቀናብሩት ችግሩን አይፈታውም። ከዚህ ያሉም እንደ እውነተኛ ታሪክ ተመልክተውት መልስ አይሰጡበትም። ሊቃውንት፡ ካህናትና ምእመናን ከዚህ ላይ እንዳትሞኙ። እነሱ መነኮሳቱ ቢራራቁም ቢጣሉም መደባቸውን በሥውር የሚጠብቁ መሆናቸውን እንዳትዘነጉ።
አሁን 6ኛው ፓትርያርክ አስመራጭ ኮሚቴ መሠየሙ ወይም መቋቋሙ እንደ ነቃፊዎቹ ሳይሆን አግባብ ያለው ነው። ትክክለኛ ኂደት ነው። በዚሁ መሥመሩን ይዞ ሊቀጥል ይገባል። ፀሐይ እሰከሚወጣ ለድብልብሉ ዘመን የሚመረጥ ርስሰ አበውም ከትምህርት ቤትዋ የሰነበተ፣ ከልጅነት እስከ ዕውቀት ባህልዋን ያካበተ፣ ከቅድስትዋና ቅኔ ማኅሌትዋ ያደረ፣ከደጀ ሰላምዋ ያረፈደ፣ቋንቋዋን የሚሰማና እምነትዋን ያልቀየጠ መሆን ይገባል። የውጪ ቋንቋን የሚያውቅ ስንል እምነትንም የሚቀይጥ መሆኑን መዘንጋት አይገባም። ዓፄ ኃይለ ሥላሴም ብትርክናውን ከግብጽ ለማምጣት ከግብፅ ጋር ሲስማሙና ሲፈራረሙ፣ ከገዳም የሚኖር ፍጹም ባሕታዊ፣ ሀገራዊ ትምህርትን የተማረና ህዝብ የሚወደው ርእሰ አበው እንዲመረጥ ነበር የተስማሙት። ደርግ ይህንን ዶክዩሜንት አይቶ ነው አቡነ ተክለ ሃይማኖትን ከበረሃ አስመጥቶ ያስመረጠ። አሁን ግን ውስጠ አዋቂዎች እንደሚሉት በዝግ አንደር ግራውንድ ፕትርክናው ከጳጳሳት እንዳይወጣ ሲኖዶስ ወስኖአል ተብሎ ይነገራል። ማን ነው የወሰነው? እነሱ። ለማን? ለራሳቸው። በማን? በራሳቸው። ይገርማል የህዝቡ ዓይነ ልቡና ምን ያህል ቢታወር ነው እንዲህ የሚደረገው? በሌላ ቋንቋና ባህል እንዲሁም እምነት የተበረዘ ርእሰ አበው እናደርጋለን ቢባል የቤተ ከርስቲያንዋን ቋንቋ ስለ ማይሰማና ባህልዋን ስለ ማያውቅ እንደ አለፈው ዘመን ከመሰሎቹ ከመነኮሳትና ከዘመዶቹ ጋር ብቻ ተግባብቶ ከሊቃውንት፡ ከካህናትና ከምእመናን ያለመግባባት ተራራን መገንባት ማለት ነው።
ከእንግዲህ ወዲህ ሁለት ሲኖዶስ ብሎ የሚጠራ ሁሉ አገሩ ኢትዮጵያንና እምነቱን ያቃለለ እንደሚሆን ማወቅ ይገባል። ነጋዴና ገበሬ እንኳን አዳብሎ አይጠራም። ገበሬ ገበሬ ነው። ነጋዴ ነጋዴ ነውና። እግዚአብሔር ቤቱንና በጎቹን ይጠብቅ። ለባለ ዋጋ ዋጋውን ይክፈል።