የ6ኛው ፓትርያርክ ምርጫ እርግጥ መሆኑ ከተነገረበት በፊት አንስቶ ብዙ ተወርቷል፣ ብዙም ተብሏል። ግማሹ ከምርጫው ይልቅ
እርቁ ይቅደም ይል ነበር። ገሚሱም በተለይ ከሀገር ቤት እርቅ ማለት አንድ ማኅበር፤ አንድ መንጋ ማለት እንጂ ያረጀ ስልጣን ማደስ
አይደለም ማለቱም አይዘነጋም። ከምርጫው ይልቅ እርቁ ይቅደም ከሚለው ወገን የሚመጣው ሃሳብ አብዛኛው በቅንነትና ለቤተክርስቲያን
አንድነት ከማሰብ ልባዊ ስሜት እንደሆነ ይገመታል። አንዳንዱም እርቅ የሚለው ነገር ከግቡ እንደማይደርስ እያወቀ ወይም ስውር ዓላማውን
ከኋላው አድርጎ ሐቀኛ መስሎ ለመታየት የሚያደርገው ጫወታም እንደሆነ ካለፉት እንቅስቃሴዎች ተነስቶ ግምት ማስቀመጥ ይቻላል። በዚህም
ይሁን በዚያ እርቅ የተባለውን ነገር ገቢር ለማድረግ ከስሜትና ከቅናት በፊት ግንዛቤ ውስጥ ሊገቡ የሚገባቸው ብዙ ሥረ ነገሮች መኖራቸውን
አለመረዳት ቅን ሃሳቦች ሁሉ ትክክለኞች ቢሆኑ እንኳን አፈጻጸማቸውን
አርቆ መመልከት አለመቻል በራሱ ችግር ነው። እንደምንሰማው የውጪው ሲኖዶስ መፈንቅለ ፓትርያርክ ያደረገው ወያኔ ነው እያለ ወያኔ
በሚመራው ሀገር እንዴት ሆኖ ነው ተመልሶ ፓትርያርክ መሆን የሚችለው ለሚለው ግዙፍ ጥያቄ ምላሽ የሚያሻው ይመስለኛል። የውጪው ሲኖዶስ
መፈንቅለ ፓትርያርክ አድርጎብኛል ካለው መንግሥት ጋር የእርቅ ድርድር ያደርጋል ወይስ መንግሥት ጥፋቱን አምኖ እንዲመለሱ በመፍቀድ
ዋስትና ይሰጣል? ብለንም ተጨማሪ ጥያቄ ለማቅረብ እንገደዳለን።
የአቡነ ጳውሎስ ኅልፈት ብቻውን ፈነቀለኝ ባሉት መንግሥት ሀገር ለመመለስ የሚያስችል
አዲስ ግኝት ነው ወይ? እርቅ ለም? ከማን ጋር? እንዴት? ለሚሉት ጥያቄዎች ምላሽ ሳያገኝ እየተጠራሩ መነጋገር ብቻውን መፍትሄ
እንደማይሆንና ከሚጠየቁት ነጥቦች አንጻር መሳካት አለመቻሉን አስቀድመን በመገመት በዚህ ዙሪያ ጽፈንበት ነበር። ወደፊትም የውጪ ሲኖዶስ ሳይሆን የውጪ ጳጳሳት ተብሎ ወደሀገር ቤት ተመልሶ ባለው አንድ ሲኖዶስ ስር ከሚኖሩ
በስተቀር እንደአቻ ሲኖዶስ የሚደረግ ድርድር ሊኖር እንደማይችል ከመጻዒ አመለካከቶች አንጻር አስቀድሞ መተንበይ ይቻላል። የሚነሳው እውነታ ሲኖዶስ ያለው የት ነው? የሚለው ጥያቄ ነው። እልህና ቁጣ
በሚፈጥረው ስሜት እስካልተመራን ድረስ የኢትዮጵያ ሲኖዶስ ያለው አዲስ
አበባ ነው። ኢትዮጵያውያን አሜሪካ በመኖራቸው ብቻ አሜሪካ፤ ኢትዮጵያ ልትባል አትችልም።
ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው መንግሥት አንባ ገነን ይሁን
ዲሞክራሲያዊ ሀገሪቱ ከዓለም ካርታ ላይ እስካልጠፋች ድረስ የኢትዮጵያ መንግሥት ይባላል። ሲኖዶሱም መንግሥት ባለበት ሀገር የኢትዮጵያ
ሲኖዶስ ይባላል። እውነታውን ለመቀበል ባንፈልገውም እንኳን አለመቀበላችን እውነታውን አይለውጠውም። አንዳንዶች ታሪክ እያጣቀሱ ስለስደት
ሲኖዶስ ስነሞገት ለመግጠም ይዳዳሉ።
ከ50 ሚሊዮን በላይ ኦርቶዶክሳዊ ምእመናንን የሚመራው ማነው? ብንል ምድር ላይ ያለው እውነታ
የሚናገረው በሀገረ ኢትዮጵያ ውስጥ ሲኖዶስ መሆኑን ነው።
ሃይማኖትና ፖለቲካ የተቀላቀለ በመሆኑ በውጪ አለሁ የሚለው ሲኖዶስ የራሱን
አባላት ይዞ ለሚስማሙት ደጋፊዎች አገልግሎቱን ከሚሰጥ በስተቀር የኢትዮጵያ ሲኖዶስ የሚያሰኘው ምንም ነገር የለም። ብንስማማም፤
ባንስማማም ይህም ምድር ላይ ያለ እውነታ ነው። ኢትዮጵያ አለች፤ አሜሪካም ኢትዮጵያ አይደለችም።
በዚህ ዙሪያ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ እውነቱን በመናገራቸው
ብዙ ተነቅፈውበታል። ብዙ ችግራችንና ተቃውሞአችን የሚነሳው ከእኛ ሃሳብ ጋር የማይስማማውን እውነት ለመስማት ካለመፈለጋችን እንጂ
እኛ የምንለው ሁሉ ከሌላው የተሻለ እውነት ሆኖ በሌሎች ስለተረጋገጠ አይደለም። ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር እስካለች ድረስ ሲኖዶስ
የሚኖረው በዚያች ሀገር ውስጥ ነው። የፕሮፌሰር ጌታቸውን ሃሳብ ስጋራ በግድ ተሰደድኩ የሚሉ ፓትርያርክ እንጂ በግድ የተሰደዱ ጳጳሳት
ባለመኖራቸው ሲኖዶስ ተከፍሏል አይባልም። ስደተኛው ፓትርያርክ የራሳቸውን ሲኖዶስ ቢያቋቁሙ በአሜሪካ ያለ የፓትርያርኩ ሲኖዶስ ይባላል እንጂ ሕጋዊ የኢትዮጵያ ሲኖዶስ አይባልም። ኢትዮጵያ
የምትባል ሀገር አሜሪካ ውስጥ በህግ አልተመሰረተችምና። ይህን እውነት መናገር፤ ማንንም እንደመደገፍ ወይም እንደመቃወም መቆጠር
የለበትም። ለምሳሌ የኢህአዴግ 10 ሚኒስትሮች ወደ አሜሪካ ቢኮበልሉና በአሜሪካ የኢትዮጵያ ሚኒስትሮች ምክር ቤትን ቢያቋቁሙ ቀልድ
ከመሆን አልፎ የአዲስ አበባው መንግሥት የሚተካውን አጥቶ ቤቱ አርፎ ይቀመጣል? ስደተኛው ምክር ቤት ፤ሕጋዊ ምክር ቤት እኔ ነኝ ቢልስ መንግሥታት ከዚህ ስደተኛ
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ጋር ነው ግንኙነት የሚያደርጉት? መቀለድ ይቻላል፤ ቀልድ ሁሉ ግን እውነት አይደለም።
የውጪውን ሲኖዶስ ሃሳቦች ትተን ሃሳቦቻቸውን የሚያንጸባርቁ ብዙ ሰዎችን ለመጠየቅ የምንገደደው ነገር የተሰደደው ማነው?
ሲኖዶስ ወይስ ፓትርያርኩ? እርቅ ከማን ጋር? እንዴት? የሚሉትን ነጥቦች በዝርዝርና ለመስቀለኛ ጥያቄዎች ሁሉ መልስ በሚሰጡ መልኩ የእርቁን ሃሳብ ማንሸራሸር እንጂ በስሜትና በመንፈሳዊ ቅናት በደረቁ
የምንመኛቸው ሁሉ ክዋኔ ያገኛሉ ለማለት አስቸጋሪ ነው።
ስለዚህ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሲኖዶስ ያለው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው።