የአቡነ ማትያስን ፓትርያርክ መሆን ኅሊና እንዳለው ሰው ምልከታ በራሱ ጉዳት አለው ብለን አስበን አናውቅም። ችግሩ የሚመጣው አቡነ ማትያስን ፓትርያርክ ለማስደረግ የሚደረገውን ሩጫ ስንመለከትና ሯጮቹን ስንመረምር እጅግ ያሳስበናል፤ ያስፈራናልም። የአቡነ ማትያስን ፓትርያርክነት የሚፈልጉ ቡድኖች ሁለት ስልት ይዘው የሚንቀሳቀሱትን እነማን መሆናቸውን ስናይ ምርጫውን አጥብቀን ለመቃወም እንገደዳለን። በምርጫ ሚዛን ከአቡነ ሳሙኤል ይልቅ አቡነ ማትያስ የተሻለ ኳሊቲ ሊኖራቸው ይችላል። ይሁን እንጂ አቡነ ሳሙኤልን የሚጠሉ ቡድኖች በአንድ በኩል የጥቅሞቻችን ጠላት የሚሏቸው አቡነ ሳሙኤልን ለመጣልና በሌላ በኩል የራሳቸውን ጥቅሞች ለማስከበር ሲሉ ለአቡነ ማትያስ መመረጥ ዐመጽና ዘመቻ ውስጥ መግባት ለቤተ ክርስቲያን ከጉዳት በስተቀር ትርፍ ካለማምጣቱም በላይ ተገቢም፤ መንፈሳዊም አይደለም። እንደዚሁ ሁሉ የአቡነ ማቴዎስ መመረጥ በብዙ ሚዛን ቢለካ ፓትርያርክ ለመሆን የሚያስችል ብቃት እንዳላቸው እናምናለን። ይህን ብቃት ለማግኘት የግድ የቡድንና የዐድማ ዘመቻ ውስጥ መገባት አለበት ብለንም አናስብም። የአቡነ ማቴዎስን ፓትርያርክ መሆን የሚፈልጉ ቡድኖች አቡነ ማቴዎስ ለቤተ ክርስቲያን እንዲሰሩ ፈልገው ሳይሆን በር ከፋችና ዘጊ ሆነው በቤተ ክርስቲያን ጉያ ዐቃቤ ኆኅት አድርገው ራሳቸውን ለመትከል ከመፈለግ የመነጨ በመሆኑ አሁንም እንቃወማለን። የአቡነ ሕዝቅኤልንም ፓትርያርክነት እንዳንቀበል የሚያደርገን ጉልህ ችግር አለ ብለን አስበን አናውቅም። ችግሩ ያለው አቡነ ሕዝቅኤል ፓትርያርክ እንዲሆኑ የሚፈልጉ ወንዘኞች የመራወጣቸው ነገር ነው። ምንም እንኳን ከሰው ልጅ ጉድለት የመኖሩ ነገር ጠባይዓዊ መሆኑ ባይካድም ከጉድለታቸው ይልቅ ብቃታቸው ያመዝናልና ፓትርያርክ ሆነው ሁሉም መታጨታቸው በራሱ ችግር ላይኖረው ይችላል። ችግሩ የሚነሳው እነሱን ፓትርያርክ ለማድረግ የሚራወጡት ኃይሎችና ቡድኖች እያደረጉት ያለው ጉዞ ነው። የማያውቋት ቤተ ክርስቲያን አሳስቧቸው ሳይሆን በዚህም ይሁን በዚያ ጥቅሞቻቸውን ለማስከበር ከታቀደ ዓላማ የመነጨ በመሆኑ ድርጊታቸውን አጥብቀን እንጸየፈዋለን። በሌላ መልኩም ራሳቸው እጩዎቹ እነዚህን ዙሪያቸው ተሰልፈው እናነግስዎታለን ባዮችን በመቃወም ምርጫው በመንፈሳዊ ዓይን ተካሂዶ የሚመጣውን ውጤት በቅንነት ከመጠበቅ ይልቅ ከተሰላፊዎቹ ጋር መቆም ወይም ሰልፉን በዝምታ መቀበላቸው በራሱ ፓትርያርክ የመሆን ብቃታቸውን ያወርደዋል። በዚህም የተነሳ ለፓትርያርክነት የቆሙበትን መንገድ አጥብቀን እንቃወመዋለን።
በሌላ መልኩም ዐድመኞቹና ሰልፈኞቹ መንግሥትና ሕግ ባለበት ሀገር እንደፈለጉ መፏለል የቻሉት እንደመርፌ ትንሽ ሆነው
ስለሚንቀሳቀሱና መንግሥት እነሱን ለማየት አጉሊ መሳሪያ ስለሚያስፈልገው አይደለም። የማይጠቅመው ሲሆንና ያልፈለገው ነገር ሲያጋጥመው
ዐድመኞችን እንዴት እንደሚያስታግስ በደንብ እናውቃለን። እነዚህን ዐድመኞችና ሰልፈኞች ግን እንደውሻ በቤተ ክህነቱ ግቢና ጀርባ
ቹ ብሎ የለቀቃቸው ጠቃሚ የአክላባት ቡድን ስለሆኑለት ብቻ ነው መውሰድ ይቻላል። እኛ የምናየውን ድርጊት እሱ እንዴት ማየት ተሳነው? ያ ካልሆነ ደግሞ እስኪ ሲያስታግሳቸው እንይ?
አሁንም ደግመን ደጋግመን የምንለው የፓትርያርክነት ምርጫው መንፈሳዊነት ቢጎድለው እንኳን ቢያንስ ነጻና ፍትሃዊ ለመሆን
ይቻል ነው። የእነ አቡነ ሳሙኤልን የአድማ ቡድን በማስቀረት ምራቁን ዋጥ ያደረገ ቢያንስ ከ60 ዓመት በላይ እድሜ የሆነ አዲስ
የምርጫ ሕግና አስመራጭ ተመርጦ ምእመኑ ተወያይቶና አስተያየት ሰጥቶበት ምርጫው እንዲደረግ ጊዜ ይሰጠው የሚል አቋም እናራምዳለን።
የምርጫውና የአመራረጥ ሥርዓቱ ቅሬታ ተሰተካክሎ መራጭ ያመነበትን የሚመርጥበት ስልት ከተዘጋጀ ምንም እንኳን ተገቢ ነው ባይባልም በእሳቸው ፍቅር የተቃጠሉ ደስ እንዲላቸው አቡነ ማትያስን
አስቀድሞ ከተመራጮች ውስጥ ማስገባትም ቅር አያሰኝም። ጉዳዩ እነማን ታጩ ሳይሆን እንዴት ተመለመሉ? እንዴትስ ሊመረጡ ተፈለገ? የሚለው የምርጫው ሂደት ነው አሳሳቢው። መንግሥት እጁ አለበት ተብሎ የሚቀርብበትን ስሞታ ለማፍረስና ነጻ መሆኑን በመግለጽ ሂደት ላይ ዐድመኞችን፤ ሰልፈኞችንና ጥቅመኞችን በማስታገስ በኩል ምእመኑ ያመነበትን እንዲመርጥ በማገዝ በተግባር ያሳየን።
የአሁኑ የፓትርያርክ የምርጫ ሂደት ቅንነት የጎደለው፤ የዐድማና የሰልፈኞች ምርጫ እና የተቀነባበረ የጀርባ ኃይሎች ድጋፍ
ያለበት ስለሆነ ምርጫው ከመከናወኑ በፊት ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል የታወቀበት አስቀያሚ የታሪክ አጋጣሚ ክስተት ነው ብሎ አፍን
ሞልቶ መናገር ይቻላል። ቅዱስ ሲኖዶስም ይህንን የምርጫ ሂደት ከተቀበለ የዚያ ታሪክ አካል ሆኖ ዘመንና ትውልድ በታሪክ ጠባሳነቱ
ሲያስበው የሚኖር ይሆናል።
ደግመን ደጋግመን የምንቃወመው ነገር ዐድማና ዘመቻው ለቤተክርስቲያን ሳይሆን ለግለሰቦች ጥቅም የሚውል በመሆኑ ነው!