Thursday, February 7, 2013

ሰበር ዜና፦ የ6ኛው ፓትርያርክ ምርጫ ቀን ተወሰነ!



የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የ6ኛውን ፓትርያርክ ምርጫ የካቲት 21/2005 ዓ/ም ለማካሄድ  መወሰኑን ያገኘነው መረጃ ያስረዳል።


ቅዱስ ሲኖዶሱ ዛሬ ጥር 30/2005 ዓ/ም ባደረገው  አስቸኳይ ጉባዔ ላይ ያሳለፈው ውሳኔ እንደጠቆመው ለምርጫው ሂደት የተሰየሙት አስመራጮች በሚያቀርቡት ተመራጮች ላይ ድምጽ በመስጠት የ6ኛውን ፓትርያርክ ምርጫ ለማከናወን እንዲቻል አስፈላጊው ሁሉ ከወዲሁ እንዲደረግ ትእዛዝ መስጠቱም ታውቋል።

ከሊቃነ ጳጳሳቱ መካከል የሚያጉረመርሙና ባለተራዎች ነን እስከሚሉቱ ድረስ የተወሰነ መሳሳብ ውስጥ ውስጡን የነበረ ቢሆንም ይህንን ክፍተት ለመሙላት ምንም እንዳልተፈጠረ ለማድረግ በተወሰኑ የነጻ ሚዲያ ዘገባዎች ላይ የክስ ፋይል በመክፈት ዝም የማሰኘቱ ሂደትና መረጃዎች እንዳይሾልኩ ለመከላከል የተወሰዱት እርምጃዎች በተወሰኑ መልኩ ውጤታማ መሆናቸው ታይቷል። አንዳንዶቹ ጳጳሳት ለቤተክርስቲያኗ ከማሰብ ይልቅ እኔ ወይም እኛ እያለን፤ እነ እገሌ ፓትርያርክ ሊሆኑ ነው? ከሚል የቅናት መሰል በትር የተነሳ ስብሰባ በመርገጥ ወይም በስብሰባው አንገኝም ከሚል የደጋፊ  ፍለጋ እምቢታ ድረስ ቢጓዙም ያሰቡትና የተመኙት ሊሳካ ሳይችል ቀርቶ የምርጫው ሂደት አይቀሬ ስለመሆኑ የተሰጠው ውሳኔ አረጋግጧል።

ሲኖዶሱ ያቋቋመው የአስመራጭ ኮሚቴ ሰብሳቢ ብጹዕ አቡነ እስጢፋኖስ የጅማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ጥር 30 ቀን 2005 .. በመንበረ ፓትርያርክ በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፣ የካቲት 21 ቀን ለሚፈጸመው የፓትርያርክ ምርጫ የሚቀርቡት አምስት ዕጩ ፓትርያርኮች የካቲት 18 ቀን ለሕዝብ ይፋ ይሆናሉ፡፡



ስድስተኛውን ፓትርያርክ የሚመርጡት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት መምሪያ ኃላፊዎች ጥንታውያን ገዳማትና አድባራት፣ ካህናት፣ ምዕመናን የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶችና የማኅበረ ቅዱሳን አባላት መሆናቸውና ቁጥራቸውም 800 መሆኑን ሰብሳቢው አስረድተዋል፡፡

ካህናት፣ ምዕመናንና የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች በሚያቀርቡት የአባልነት ማስረጃ በዕጩ ፓትርያርክ ጥቆማ ከየካቲት 1 ቀን እስከ የካቲት 8 ቀን 2005 .. ድረስ መሳተፍ እንደሚችሉ የገለጹት ሰብሳቢው፣ ካህናትና ምዕመናን ከየካቲት 1 እስከ 8 ቀን 2005 .. ድረስ አምላካቸውን በጸሎት እንዲጠይቁ ከየካቲት 1 ቀን ጀምሮ ለአንድ ሱባኤ የሚቆይ የጸሎት ጊዜ መታወጁንም አስታውቀዋል፡፡

ስድስተኛው ፓትርያርክ ምርጫ ሐሙስ የካቲት 21 ቀን ተካሂዶ በዚሁ ዕለት ከምሽቱ 12 ሰዓት የተመረጠው አባት በመገናኛ ብዙኀን አማካይነት ለሕዝብ ይፋ እንደሚሆን፣ በዓለ ሲመቱም እሑድ የካቲት 24 ቀን በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እንደሚፈጸም ተጠቅሷል፡፡

ምርጫውን ቅዱስ ሲኖዶስ በምርጫ ሕጉ በወሰነው መሠረት የአራቱ እኅት አብያተ ክርስቲያናት [ግብፅ፣ ሶርያ፣ አርመን፣ ሕንድ] የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ማኅበር፣ የአፍሪካ አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ተወካዮችና በቋሚ ሲኖዶስ የሚመረጡ ምዕመናን እንዲታዘቡ መጋበዛቸውም ታውቋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ለ6ኛ ፓትርያርክነት ምርጫ  5 አባቶች እንደሚቀርቡ እንጂ 5ቱ እጩዎች ለመጨረሻ ምርጫ  ከስንት ተጠቋሚዎች መካከል ተመርጠው እንደሚቀሩ በግልጽ አልተቀመጠም። ይህም አሰራር አስመራጭ ኮሚቴው ከ3 ያላነሰ፤ ከአምስት ያልበለጠ እጩ ያቀርባል በሚለው የምርጫ ደንብ መሰረት በራሱ ወንፊት አበጥሮ ህገ ደንቡን አክብሮ ለሲኖዶሱ እንደሚያቀርብ እንጂ ይህንን አልፎ ተጠቋሚዎችን ሁሉ ማቅረብ ስለመቻሉ የተባለ ነገር ባለመኖሩ ፉክክሩን ቀለል ያደርገዋል ተብሎ ይታሰባል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ የምርጫው ሂደት በእጣ እንደማይሆን ሲታወቅ እንደቀበሌ ምርጫ በካርድ ድምጽ የመስጠቱ አሰራር በራሱ የክዋኔው ሂደት፤ የመራጮች ማንነትና የድምጽ አቆጣጠር ስልት ምን እንደሚመስል በግልጽ የታወቀ ነገር የለም። ለመጀመሪያ ጊዜ በቁጥር 800 መራጮች እንደሚገኙ በአኃዝ ከመቀመጡ በስተቀር በመራጮች ላይ የሚኖር የምረጡኝ ዘመቻ ተጽእኖ ይኖር፤ አይኖር እንደሆነም አልተነገረም። የድምጽ ቆጠራው ስርዓትና እክል ቢኖር አወጋገዱ መንገድ ምን ሊሆን እንደሚችል ማወቅ አልተቻለም። ፓትርያርክን ያህል መንፈሳዊ ሥልጣን የሚይዝ አባት ለማስቀመጥ ጥያቄ የሚያጭሩ ግልጽነት የሚያስፈልጋቸው የሂደቱን ሥርዓት አሳንሶ፤ በመደጋገም 5 እጩ እያሉ፤ ነገሩን ቀለል አድርጎ በማቅረብ የመቻኮሉ ነገር ያስፈራናል። በተለይም ሐዋርያት በይሁዳ ምትክ ለማስገባት በማትያስና በበርናባስ ላይ ያደረጉትን የእጣ ምርጫ ዓይነት ማድረግ ባልተፈለገበት ሁኔታ ማሳሰቡ ምክንያታዊ  ነው እንላለን።