«የቀረውንም ነገር ሳልቆጥር፥ ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ አሳብ ነው» ፪ኛ ቆሮ ፲፩፤፳፰


 በዘመኑ የግንኙነት መሣሪያ በሆነው መረጃ መረብ ላይ ተቀምጠን ከውድ ጊዜያችን ላይ ቀንሰን የምናካፍለውን መልእክት አንዳንዶች እነሱን ደስ በሚያሰኝ መንገድ እንድናስተላልፍ  ይፈልጋሉ። ገሚሶቹ ደግሞ የሆነ ስውር ዓላማ አንግበን የተሰለፍን  አስመስለው ይስሉናል። አንዳንዶቹም በእግዚአብሔር መንግሥትና አሁን ባለው ምድራዊው የቤተክህነት አስተዳደር መካከል ያለውን ልዩነት በደንብ ያልተረዳን አድርገውም ይገምታሉ። በተለይም የሰሞኑን የፓትርያርክ ምርጫን በተመለከተ የምናወጣቸውን ዘገባዎች የሚያስከፋቸው ሰዎች እንዳሉ ለማወቅ ችለናል። በዚህም ይሁን በዚያ የእግዚአብሔር እቅድና ዓላማ እንዳይሆን የሚከለክል ምንም ኃይል እንደሌለ እያመንን የእኛ ዓላማና ፍላጎትም ምን ጊዜ እግዚአብሔርን የሚያስደስት ሥራና ዘመን  እንዲመጣ ከመፈለግ የመነጨ ትግል ለማድረግ ብቻ እንደተሰለፍን ለሚጠሉንም ሆነ ለሚወዱን ማሳወቅ እንፈልጋለን።
ይህንንም አቋማችን ከሐዋርያው ጳውሎስ ቃል ተውሰን በአጭር ቃል ስናስቀምጠው ««የቀረውንም ነገር ሳልቆጥር፥ ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ አሳብ ነው» ፪ኛ ቆሮ ፲፩፤፳፰ እንዳለው የቤተ ክርስቲያናችን ነገር ብቻ ያሳስበናል።
አንዳንዶችን ቅር የሚያሰኝ፤ ሌሎችን ደግሞ የሚያሳዝን፤ ለገሚሱም ደስታን የሚሰጥ መረጃ ስናወጣ በእኛ በኩል ያለው ስሌት ግን አንድ ሃሳብ ብቻ ነው፤ እሱም የእግዚአብሔር መንግሥት እንዳይስፋፋ መንገድ ላይ ያሉ ጋሬጣዎችን እየነቀስን በማሳየት ሰው በመረጃና በእውቀት እውነቱን እንዲረዳ ማድረግ ነው።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከዓለም ቀደምት ቤተክርስቲያን ተርታ የምትመደብ ቤተክርስቲያን ናት። በእውቀት የበለጸገች፤ በአስተምህሮ የዳበረች፤ በትውፊትና በታሪክ ከፍተኛ ስፍራ የያዘች መሆኗም ለማንም የሚሰወር አይደለም።  ይሁን እንጂ እንደቀደምትነቷ ወደኋላ እየሄደች፤ በአስተምህሮዋ እየደከመች፤ በአስተዳደሯ እየወደቀች፤ በትውፊቷ እየኮሰመነች፤ በታሪኳ እየተሸፈነች መሄዷ በገሃድ የሚታይ እውነት መሆኑንም መካድ አይቻልም።
በቁጥር 75 የእስልምና ሰዎች መካና መዲናን ለቀው ወደኢትዮጵያ ሲሰደዱ ክርስትና የኢትዮጵያ መንግሥታዊ ሃይማኖት ነበር። መንግሥቱንም፤ ጉልቱንም፤ሕዝቡንም ትቆጣጠር የነበረችው ቤተ ክርስቲያን ከኋላዋ የመጣው እስልምና አንድም የዐረብ ተወላጅ ሳይኖረው የሸሪአ መንግሥት ለማቋቋም የሚያስችል ኃይል አለኝ እስከማለት የደረሰው የቤተ ክርስቲያኒቱ እድገት እንደመሠረቱ ከፍ እያለ መጓዙን ሳይሆን እያቆሽቆለቆለ  የመሄዱ አንዱ ማሳያ ነው ብሎ መጥቀስ ይቻላል። እንደዚሁ ሁሉ ከ16ኛው ክ/ዘመን ጀምሮ ብቅ ጥልቅ ይል የነበረው የአውሮፓውያን የወንጌል ሰዎች እንቅስቃሴ በስውር የነበረው ስርጭት ዛሬ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አባላትን ማፍራት የቻለው ይህችው ጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን ቤተ መንግሥቱን፤ ቤተ ክህነቱንና ሕዝቡን እስከጉልተ ርስቱ  የመቆጣጠር አቅም እያላት መሆኑን አይተን ዛሬ ላይ የደረሰችበትን ደረጃ ስንመረምር ሽቅብ ሳይሆን እያቆለቆለች መጓዟን ቢመረንም የሚታየውን እውነታ መቀበል የግድ ይለናል።
በተለይም ቤተ ክርስቲያኗ የነበራትን የክብር ሥፍራና መንፈሳዊ ኃይል ቀስ በቀስ እያጣች በዝናና በስም ብቻ ወደመኖር የደረሰችው ዘርዓ ያእቆብ የተባለውን ሰው ንጉሥ አድርጋ ከተቀበለች ወዲህ ባሉ ዘመናት ውስጥ ስለመሆኑ፤ እውነት በሀሰት ሰርዶ ተሸፍኖ የሌለ ታሪክ እውነት እንዲመስል ከተደረገበት ጊዜ አንስቶ እንደሆነ ታሪክ አፍ አውጥቶ እየተናገረ ይገኛል።  ዛሬ ላይ ቤተ ክርስቲያኒቱ  በአንድ በኩል  ከቅዱሳኖቿ እንደ አንዱ አድርጋ የምትቆጥረው ፤ በሌላ መልኩም በተደለዘው ገድሏ ከሰውነት ተርታ አውጥታ ከውሾች መድባ የምትረግመው ሰማእቱ አባ እስጢፋኖስንና ደቀ መዛሙርቱን እያሳደደች ለ100 ዓመት ባሳረፈችባቸው ሰይፍ የፈሰሰው ደም በዐውደ ምሕረቷ ላይ እየጮኸ እነሆ የሰማይ ክሳት ተለቆባት እየከሳችና እየደከመች በመሄድ ላይ ትገኛለች። የግራኝ ወረራ፤ የድርቡሽ፤ የግብጽ፤ የቱርክ፤ የጣልያን ሰይፍ የወረደው ሳያንስ እርስ በእርስ ስንበላላ ኖረናል።

ልጆቿ ናቸው የተባሉት ጨርቅ ጠምጣሚዎች ተንኮል ተምጥመው በመቅደሷ ውስጥ እርስ በእርስ ይባላሉ። መንግሥታት ይፈሯት ያልነበረውን ያህል ዛሬ ግርማዋ ተንዶ ስሟን እያዋረዱ በደጇ ላይ ያሻቸውን ይሾማሉ፤ ይሸልማሉ። እውነትና ወንጌል ቦታቸውን ለተረትና ምሳሌ ለቀው ምላስና ጊዜ መድረኩን ተቆጣጥረው የቀን ቅዱስ፤ የጭለማ ርኩሰት  ቦታውን ተረክቦ ሳንቲም ሲያንቃጭል የሚነቃ ሰባኪ ተፈልፍሏል። ቆብ ያጠለቁ ቁራዎች በጥቋቁር ላባ ተሸፍነው የመበለቶችን ቤት ይመዘብራሉ፤ ከባህር ማዶ ወደ ሀገር ቤት፤ ከሀገር ቤት ወደባህር ማዶ የጥፋት ድንጋይ ይወራወራሉ። ፈቶችና አመንዝሮች፤ ዘማውያንና ዘራፊዎች ወንበር ላይ ተቀምጠው እየደከመች ያለችውን ቤተ ክርስቲያን ነፍስ እንዘራባታለን እያሉ የደብተራ ገለፈት መጽሐፍ ይገልጣሉ።  እውነቱ ግን ቤተ ክርስቲያን እየሞተች ነው። አንዳንዶች ቤተ ክርስቲያን ትሞታለች የሚለውን አባባል ፍጹም መቀበል አይፈልጉም። ምክንያቱም ቤተ ክርስቲያን ማለት ለእነሱ ሕንጻ ማለት ስለሆነ የሕንጻ ቁጥር በመጨመሩ ቤተክርስቲያን ያደገች ይመስላቸዋል። በተካበው ሕንጻ ውስጥ ያሉት ግን በመንፈስና በግብር የሞቱ ሰዎች መሰብሰባቸውን አያውቁም፤ ወይም ለማወቅ አይፈልጉም። ጳጳሳት የሚባሉ ጥቁር ለባሾች  ከየትኛውም ዘመን በተሻለ ዛሬ በቁጥር ብዙ ናቸው። ይሁን እንጂ የቤተክርስቲያን  አባላት ቁጥርና አስተዳደር እያደገ ሳይሆን ያለው እያሽቆለቆለው ነው።  በቁም የሞቱ ሰዎች ቢበዙ፤ ሰዎች በሕይወት ይኖሩ ዘንድ የሚያበቃ የፈውስና የአስተምህሮ ጸጋው ከየት ይመጣል? ያሉት ሙታናቸውን እየቀበሩ ያሉ ሙታን እንጂ ሕይወት የሚሰጡ አይደሉም።  እግዚአብሔርስ ለዚህች ቤተክርስቲያን የንስሐና የመመለስ ጊዜ ያላደረገው ምን አለ?
 በጥንት ዘመን ለነብዩ ኤርምያስ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተላከ ሸክም ነበረ። ሸክሙም ዘመናትን አሻግሮ እግዚአብሔር ለዚያ ያበቃቸውን ሁሉ  እስራኤላውያን  በመዘንጋታቸውና የተሰጣቸውን ሥፍራ ለተዉ መሪዎች የተነገረ ነበር። ቃሉ እንዲህ ይላል።
«ብዙ እረኞች የወይኑን ቦታዬን አጥፍተዋል፥ እድል ፈንታዬንም ረግጠዋል የአምሮቴን እድል ፈንታ ምድረ በዳ አድርገውታል» ኤር፲፪፤፲
ወይን የተባለው እስራኤል በፈጸመው ኃጢአት ጥፋት ታዞበታል። እግዚአብሔር ፍላጎቱ እስራኤል  መልካም ዘርና ፍሬ እንዲሰጥ ነበር። እሱ ግን እንቢ አለ። ስለዚህም «ለወይኔ ያላደረግሁለት፥ ከዚህ ሌላ አደርግለት ዘንድ የሚገባኝ ምንድር ነው? ወይንን ያፈራል ብዬ ስትማመን ስለ ምን ሆምጣጣ ፍሬ አፈራ? አሁንም በወይኔ ላይ የማደርገውን እነግራችኋለሁ አጥሩን እነቅላለሁ፥ ለማሰማርያም ይሆናል ቅጥሩንም አፈርሳለሁ፥ ለመራገጫም ይሆናል» በሚል የፍርድ ቃል  የተነሳ እስራኤል የ70 ዘመን መከራን በባቢሎን አሳልፏል።
በዘመነ ሐዲስ ኪዳንም መንፈስ የተናገረውን ጆሮ ያለው እንዲሰማ ለሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት መልእክት በዮሐንስ እጅ ተልኮ ነበር። ጆሮ እየሰማ፤ አልሰማም አለ። መከራ ሲመጣ አልሰማም ያለ ጆሮ ይቅርና መልስ አልሰጥ ያለው አፍ ሳይቀር መጮህ ይጀምራል።
የኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን ንስሐ እንድትገባ መልእክትና ጊዜ ተሰጣት። ፈቃደኛ አልሆነችም። መቅረዟም ተወሰደ። ዛሬ ኤፌሶን የፍርስራሽ፤ የቅርስ ምድርና ኢስላማዊ ሀገር ናት። «………..ንስሐም ባትገባ መቅረዝህን ከስፍራው እወስዳለሁ» ራእይ 2፤5 እንደተባለው ሆነ።
ከላይ በርእሳችን እንዳመለከትነው የሚያሳስበን የቤተ ክርስቲያን ነገር ነው። ችግሮች ቢኖሩባትም ተወልደንባታልና፤ አንጠላትም። ቃሉን እያነበብን በድንግዝግዝ ውስጥ መኖር ስለሌለብን እውነቱን ከመናገር ደግሞ አንቆጠብም። ልምድና ልምምድን ሕይወቱ ላደረገ ትውልድ ነግሮ ማሳመን ፤ እናት ጡቶቿን ከሕጻን ልጇ ለማስጣል  ከምታደርገው ጥረት የበለጠ ከባድ እንደሆነ ስለምናውቅ አቅማችን የቻለውን ያህል እንደክማለን። በድካማችን መሥራት የሚቻለው እግዚአብሔር የወደደውን እንዲሰራ በፊቱ ራሳችንን እንጥላለን።
ከዚህም የተነሳ አሁን በቤተ ክርስቲያን እየታየ ያለው የሥልጣን ሽኩቻ የመንፈሳዊ ውድቀታችን መገለጫ እንጂ ድንገት ዛሬ የተከሰተ እንግዳ ነገር አይደለም።  የፓትርያርክ ምርጫ የሚያሳስበን የቤተ ክርስቲያን ተግዳሮቶችን የሚረዳና የእግዚአብሔርን ሐሳብ ለመፈጸም የሚችል ሰው እንዲመጣ ከመመኘት አንጻር እንጂ የኛ  የምንለው ነገድና ጎሳ ሥልጣን ላይ ሲወጣ በማየት የምንደሰት ተስፈኞች ሆነን አይደለም። የከፉና ጥመት የሞላባቸው ሰዎች በወንበሩ ላይ ቢቀመጡ የእርግማንና የጥፋት ዘመን እንዳይመጣ አስቀድሞ ያስጨንቀናል። በእግዚአብሔር ስም የሚደረገው፤ ነገር ግን እግዚአብሔር የሌለበት ምርጫ ወደፊት የምናልመውን  የንስሐ ጊዜና የመንግሥቱ ወንጌል  ጋሬጣ እንደሚሆን ስለምናምን አስቀድመን እንጮሃለን። እኛ ስንጮህ እግዚአብሔር ደግሞ ለስሙ ክብር ይረዳናል። እንደዚህ ተብለናልና።
«ወደ እኔ ጩኽ፥ እኔም እመልስልሃለሁ አንተም የማታውቀውን ታላቅና ኃይለኛ ነገርን አሳይሃለሁ» ኤር ፴፫፤፫
ስለሆነም አሁን ለሥልጣን ያሰፈሰፉት ሁሉም የወንጌልና የእውነት ጠላቶች ናቸው። ምክንያቱም አንዳቸውም እውነትን በአደባባይ ሲመሰክሩ አላየንም። አልሰማንም።  የአስተዳደር እንጂ የአስተምህሮ ችግር የለም ባዮች ናቸው። የሙስና ችግር እንጂ የንስሐ ዘመን አያስፈልግም፤ እኛ የእውነት መጋቢ ብጹዓን ነን የሚሉ ትምክህተኞች ናቸው። ገሚሱም እውቀት የጎደለው የተረት አባት ነው። እነ አባ ማትያስን የመሳሰሉት ደግሞ በጥንተ አብሶ ሰበብ ሲገዝቱና በሥልጣን ሰይፍ የሰው ቀሚስ ሲቀዱ የኖሩ ናቸው። ተከድኖ ይብሰል ብለን እንጂ ስንት ነገር ነበር።  ገሚሱ በኮረዳ ሚጡ፤ ገሚሱም ጡረታ በወጡ ሚጡ ያልተመጠመጠ ማንም  የለም። ጺምና መልክ እውነት ሊሆን አይችልም።  ፊት አይተህ አታድላ መባሉስ ለምንድነው? ዘዳ ፲፮፤፲፱ ሰው መመዘን ያለበት በሥራው ብቻ ስለሆነ ነው። ከሁሉም የከፋው ደግሞ ሁሉንም ሥልጣን ናፋቂዎች አንድ የሚያደርጋቸው ወደ ሥልጣን ለመምጣት የሚሄዱበት መንገድ  በዐመጸኞችና በዐድመኞች ዘመቻ  የሚታገዙ በመሆናቸው እንድንጸየፋቸው ያደርጉናል።
ማን ይሾማል? የሚለው የሚያስጨንቀን መጪው ዘመንን  አስተዳደሩን በስማበለው፤ አመራሩን በተለጣፊ፤ የምስራቹን ደግሞ «አብያተ ወንጌላት ይትዐጸዋ» በማለት የሚያስጨንቅ ሰው እንዳይመጣብን  በመስጋት ብቻ ነው።
Share this article :

+ የተሰጡ አስተያየቶች + 1 የተሰጡ አስተያየቶች

Anonymous
February 22, 2013 at 5:52 PM

ምን ልትል እንደፈለክ እንኳን ለሌላ ሰው ለራስህ ከገባህ ድንቅ ነው። እንደ ሙሉጋኔን ፅሁፍ ሁለት ግራ ነው።

Post a Comment

አስተያየቶች

 
Support : | |
Copyright © 2011. ደጀ ብርሃን dejebirhan - All Rights Reserved

Proudly powered by Blogger