Monday, February 4, 2013

የሚበልጠውን ይዘናል!!

 ከዲ/ን አሸናፊ መኰንን «የኑሮ መድኅን» መጽሐፍ ገጽ 32 ላይ ተቀንጭቦ የተወሰደ

ዲዮጋን የተባለ የግሪክ ፈላስፋ ኑሮው ጎርፍ በሸረሸረው ፈፋ ውስጥ ነበር። ንብረቱም አንዲት መንቀል /የውሃ መጠጫ ቅል/ ስትሆን አንዲት ውሻም ጓደኛው ነበረች። ታላቁ እስክንድር ዓለምን አስገብሮ ሲመለስ ዲዮጋን የተባለውን ፈላስፋ ማየት አለብህ ስላሉት ሊያየው መጣ። ዲዮጋን ግን ከቤቱ አጠገብ በጀርባው ተኝቶ ፀሐይ ይሞቅ ነበር። ታላቁ እስክንድር አጠገቡ መጥቶ ቢቆም ስንኳ ዲዮጋን ማነው? ብሎ ዓይኑን አልገለጠም። እስክንድርም፤ ዲዮጋን ሆይ፦ ተነስ! እኔ ታላቁ እስክንድር ነኝ። ዓለሙን ሁሉ አስገብሬ ተመልሻለሁ፤ የምትሻውን ለምነኝ፤ የመንግሥቴንም እኩሌታ ቢሆን እሰጥሃለሁ» አለው። ዲዮጋን ግን ዓይኑን እንደከደነ «ይልቅስ አንተ ልትሰጠኝ የማትችለውን ፀሐይ እንዳልሞቅ አትከልክለኝ» አለው ይባላል። ንጉሥ እንኳን የማይሰጠውን ብዙ ስጦታ ስለተቀበልን እግዚአብሔር ይመስገን!
  ሰውዬው  «እግር የሌለውን ሰው እስካይ ድረስ ጫማ ስላልነበረኝ አዝን ነበር» ብሏል። ሰውዬው መለስ ብሎ ራሱን ሲመለከት የሚበልጥ ነገር አገኘ ጫማን ገንዘብ ይገዛዋል፤ እግርን ግን ገንዘብ አይገዛውም።  ጫማም ያማረው እግር ስለነበረው ነው። ለማማረርም የበቃነው ስላለን ነው። ለማማረር እንኳን እድሜ ስላገኘን ልናመሰግን ይገባል። በሣጥናቸው ብዙ ልብስ አጭቀው  ከአልጋዬ ተነሥቼ አንድ ቀን እንኳን በለበስኩት እያሉ የሞቱ ሰዎችን አውቃለሁ። የሚበላው እያለው የሚሞት፤  እንዲሁም የሚበላውን አጥቶ የሚኖር ብዙ ሰው አለ። ባለጠጎች በገንዘባቸው አንድ ቀን እድሜአቸውን ማስረዘም አይችሉም። እናት ለምትወደው ልጇ ቀንሳ የማትሰጠው እድሜ ስላለንና ሰው የማይሰጠውን ስለተቀበልን እግዚአብሔርን ልናመሰግን ይገባል።

   በዓለም ላይ የሚገኘው ሀብትና ንብረት ሁሉ የእናንተ ይሆናል። ነገር ግን ሁለት ዓይናችሁን መስጠት አለባችሁ ብትባሉ እሺ ትላላችሁ? አምናለሁ! በፍጹም እሺ አትሉም። ግን እኮ የተጠየቃችሁት ሁለት ዓይናችሁን ብቻ ነው። ጆሮአችሁ፤ አንደበታችሁ፤ ልባችሁ፤ እጆቻችሁ፤ እግሮቻችሁ………….. አሉ። አሁንም መልሳችሁ «ዓይን አጥቼ እየዳሰስኩ የኔ የምለው ንብረት እንዲኖረኝ አልፈልግም» የሚል ይሆናል። ታዲያ በዓለም ያለው ሀብትና ንብረት በሙሉ ከሁለት ዓይናችሁ ጋር መወዳደር ካልቻለ እናንተ ሚሊየነር ሳይሆን ቢሊየነር፤ እንዲያውም ከዚያም በላይ ሀብታም ናችሁ! ታዲያ ደሃ ነኝ እያላችሁ
ለምን ትተክዛላችሁ? እግዚአብሔር በዚህ በሰውነታችሁ ላይ በዋጋ የማይተመን ውድ ንብረት አፍስሷል።
  ሁላችንም እኩል ማልቀሳችን፤ ከእኛ ያነሱትን ሰዎች ማየትና መርዳት አለመቻላችን እግዚአብሔርን ያሳዝነዋል። አዎ ያለንን በትክክል ካላወቅን የጎደለንን በትክክል ማወቅ አይቻለንም። ትልቁ ችግራችን መርሳት ነው። መነጽር አድርገን መነጽር እንፈልጋለን። ቁልፍ በእጃችን ይዘን ቁልፍ አምጡ ብለን እንጣላለን። በዕለታዊ ኑሮአችን ያለን ልበ ቢስነት በሕይወት ውስጥ የተጎናጸፍነውንም በጎ በረከት አስረስቶናል። ብዙ የተቀበልን ከብዙ መከራ ወጥተን ለዚህ የደረስን ሰዎች ነን። ግን ስለምንረሳ እንበሳጫለን።
  ክፉ ጌትነት የሚበልጠውን ሰጥቶ በትንሹ ይነፍጋል። ክፉ ተቀባይ የሚበልጠውን ተቀብሎ በትንሹ ያማርራል። እግዚአብሔር መልካም ተቀባይ አጥቷል። በሕይወት ላይ ጽንፈኛነት አይጠቅምም። ሚዛናዊነት ያስፈልጋል። ስለዚህ ያለኝ ይህ ነው፤ የጎደለኝ ደግሞ ነው ማለት ያስፈልጋል። በትክክል ካየን ከጎደለን ያለን ይበልጣል።
   የምንተነፍሰውን አየር መዋዕለ ንዋያቸውን ያፈሰሱበት ባለጠጎች ቢሆኑ ኖሮ  በጎሮሮአችን ላይ ቆጣሪ ተክለው ብንከፍል እንኳን እዘጋዋለሁ የሚለው ማስፈራሪያቸው  በገደለን ነበር። ነገር ግን ከሕይወት ጋር የተያያዙ ነገሮችን እግዚአብሔር በራሱ እጅ አድርጎታል። ምክንያቱም ለሕይወት የሚጠነቀቅ እርሱ ብቻ ነውና። ደግሞም ውድ ነገሮችን ሁሉ በነጻ ሰጥቶናል። ፀሐይን፤ አየርን፤ ትዳርን፤ ልጅን፤ በነጻ ሰጥቶናል። ጥቃቅን ጉድለቶች ቢኖሩም ከያዝነው አይበልጡም።  የአገራችን ሰው የጤና ቀለቡ ትንሽ ነው፤ የሰላም ቀለቡ ትንሽ ነው ይላል። ጤናንና ሰላምን ማንም አያመሰግንበትም። ግለሰቦችና አገራት የጦርነት ወጪያቸው ምን ያህል እንደሆነ ያውቁታል። ስለሰላም ግን አያመሰግኑም።
    ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  « ስለዚህ እላችኋለሁ፦ ስለነፍሳችሁ በምትበሉትና በምትጠጡት ወይም ስለሰውነታችሁ በምትለብሱት አትጨነቁ፤ ነፍስ ከመብል ሰውነትም ከልብስ አይበልጥምንማቴ 625 ብሏል።
 እግዚአብሔር ካልሆነ በስተቀር አትጨነቁ የሚል ማንም የለም። ነገሥታቱ እንኳ ሳይበዛ እንድንጨነቅ በጣቢያቸው
ያዙናል። «ሁሉም ሰው ራሱንና አካባቢውን በንቃት ይጠብቅ» ይላሉ። አትጨነቁ የሚለው በሰላም አገር የሚኖረው ንጉሠ ሰላም ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልክ ደውለው «ያን ጉዳይህን ለእኔ ተውልኝ፤ አትጨነቅ» ቢሉን ባይፈጽሙት እንኳን የእኛን ጉዳይ አጀንዳቸው በመሆኑ ብቻ በደስታ አንዘልም? እንደውም ብለን እንተኛለን። አትጨነቁ ያለን ግን የሰማይ የምድር ንጉሥ የሆነውና በቃሉ ሀሰት፤ በተስፋው እብለት የሌለበት እግዚአብሔር ነው። ይህን አምላክ የንጉሥ ያህል እንኳን እንመነው። አንድ ሰው «እግዚአብሔርን  የመሬት ያህል እንኳን እንመነው» ብሏል። መሬትን ስንረግጣት ትደረመሳለች የሚል ስጋት የለብንም። ስለዚህ ከመራመድ አልፈን እንሮጥባታለን። እግዚአብሔር ደግሞ ታምኖ የማይከዳ፤ ወዶ የማይጠላ ሆኖ ሳለ የመሬትን ያህል እንኳን ታምነንበት ይሆን? እግዚአብሔርን የምናገኘው በእውቀታችን ልክ ሳይሆን በእምነታችን ልክ ነው።
   ብዙዎች ይጨነቃሉ። ዓለም በቃኝ ያሉ መነኮሳት ሳይቀሩ ከባለትዳሮቹ እኩል በፍርሃት ይናጣሉ። የቪዛ ወሬ የብዙ አገልጋዮችን አፍ ሞልቶታል። ኢትዮጵያና ህዝቧ እጆቻቸውን ወደ እግዚአብሔር ሳይሆን ወደ አሜሪካ ዘርግተዋል። መነኮሳቱ እንኳን የሚመኩበት ገዳም ትተው አሜሪካ ገዳማቸው ሆኗል። አሜሪካ ግን ከአንድ ሰው ጋር ተጣልታ የምትባረር ሀገር በመሆኗ ዋስትና ልትሰጥ አትችልም። ከአሜሪካውያን ከአራቱ አንዱ ሰው በመንፈስ ጭንቀት በሽታ የተያዘና መድኃኒት የሚጠቀም ነው። የምንሸሽባቸው ራሳቸው ለመብል ካልሆነ  የሚያረካ ነገር የሌላቸው ሰዎች ናቸው።........................................................................................
የሚበልጠው አለን። ማንም በደግነት ለማንም የማይሰጠው የዘላለም ሕይወት አለን። የልጅነት ጸጋ አለን። መንፈሳዊ ፍቅር፤ የእግዚአብሔር ቤተሰብ የምትሆን መንፈሳዊ ኅብረት አለን። የመረጃ እጥረት ያለብን እንጂ ብዙ ያጣን ሰዎች አይደለንም። ስለኑሮ መባነን ከበዛብን ግን የመንፈሳዊ ጤናችን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ዶክተር ኢሳይያስን ልኮ ከምዕራፍ 49 14-16 ፍቱን መድኃኒቱን አዞልናል!!