Friday, February 15, 2013

የቤተክህነቱ የጭለማው ቡድን እየተባለ የሚጠራው ክፍል በፓትርያርክ ምርጫ ላይ እየሰራ መገኘቱ ታወቀ!

 ዘሐበሻ የድረ ገጽ ጋዜጣ የቀጣዩ ፓትርያርክ እጩዎች
/ አባ ሳሙኤል ፪/ አባ ገብርኤል ፫/ አባ ሉቃስ ፬/ አባ ማቴዎስ ፭/ አባ ዮሴፍ ናቸው ሲል የደረሰውን መረጃ በመጥቀስ ዝርዝሩን ይፋ አድርጓል። ከእነዚህም ውስጥ የአባ ሳሙኤል 6ኛ ፓትርያርክነት አይቀሬ መሆኑን ተናግሯል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ኃይለ ኢየሱስ የተባለ ተሳታፊ ስለጨለማው ቡድን የሚነግረን ስላለው ጽሁፉን አቅርበነዋል።
ኃይለ ኢየሱስ አምኃ ከአራት ኪሎ



ከዚህ በፊት በቤተክህነቱ ግቢ ውስጥ ሊቃነ ጳጳሳቱን በመደብደብና በማስደብደብ ወንጀል ሰፊ ልምድ ያለው የቤተክህነቱ የጭለማው ቡድን እየተባለ የሚጠራው አካል የቆየበትን የተሰሚነትና የኃይል ሥፍራ ላለመልቀቅ ከፍተኛ በጀት መድቦ የሚመቸውን ሊቀጳጳስ ወደ ወደፓትርያርክነት ሥልጣን ለማምጣት ሌሊትና ቀን እየሰራ እንደሚገኝ መረጃዎች እየወጡ ናቸው።

ጠላትና ባላጋራ ይላቸው ከነበሩት ከአቡነ ጢሞቴዎስ ጋር በምን ምክንያትና ሰበብ ለመስማማት እንደቻለ ባይታወቅም ይህ የጭለማው ቡድን ከሟቹ ፓትርያርክ ጋር ሰፊ ውዝግብ ውስጥ የነበሩትን አባ ጢሞቴዎስን ይዞ የሚንቀሳቀስ መሆኑም ተገልጿል። እነዚህ እርስ በእርሳቸው ይናጩ የነበሩት ሁለት ተጻራሪ ኃይሎች ዛሬ ድንገት ሰምና ፈትል ያደረጋቸው ምክንያት ምን እንደሆነ ለጊዜው አይታወቅም። ይሁን እንጂ  የቤተክርስቲያኒቱ ችግር ስላንገበገባቸው እንዳልሆነና በቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ እንደመዥገር ተጣብቀው ሲመጠምጡ የቆዩት የንዋይና የሥልጣን ብልግና ዘመናቸው ግብዓተ መሬቱ ተፈጽሞ ማብቂያቸው እንዳይሆን የሚያደርጉት  ትግል መሆኑን  ሁኔታውን በቅርብ የሚከታተሉ ሰዎች እየተናገሩ ነው።  ወይዘሮ ማንትስ በመባል የምትጠራውና ቤተክህነቱን ስታተራምስ የቆየችው ባል አልቦ ሴትዮ በዙሪያው ላይ የተጠናከረ ዘመቻ እያደረገች ሲሆን ረዳቶችዋም «የመጠጥ ቤት በር ዝጉ» በማለት ልምድ ያላቸው የሰካራሞች ማኅበር አባላትም በትወናው ላይ የበኩላቸውን ድርሻ እየተወጡ እንደሚገኝም ለማወቅ ተችሏል።

አፈትልከው የወጡት መረጃዎች እንደሚያሳዩት የጭለማው ቡድኖች ለፓትርያርክነት አጭተው ለማቅረብ የፈለጉት አባት ከእነዚህ ግብረ በላ ቡድን ጋር የሃሳብ፤ የዓላማና የግብ ዝምድና ምንም የሌላቸው መሆኑ የታወቀ ሲሆን ከእነዚህ ቡድኖች ጋር የቀጥታ ግንኙነት የሌላቸውን አባት ለማሾም መሯሯጥ ያስፈለገበት ምክንያት  «ከበጣም ክፉ፤ ክፉ ይሻላል» ከሚል እሳቤ የተነሳ እንደሆነም ምክንያታዊነቱን የገመገሙ ሰዎች ይናገራሉ።  

 በአንድ ወቅት በእነ አቡነ ቄርሎስ ላይ ቤተክህነቱን የባድሜ ጦርነት አድርጎ የቆየው የጭለማው ቡድንና  የአቡነ ሳሙኤል ድጋፍ ሰጪ አካል በዚህ የአዲስ ፓትርያርክ ምርጫ ላይ የመጨረሻ እልባት  እንደሚያገኝ ከግምት በላይ እውን እየሆነ መምጣቱን የሚያመላክተው ነገር የቅድስት ሥላሴ ኰሌጅ ደቀመዛሙርት  ለእጩ ፓትርያርክነት አቡነ ሳሙኤልን በማቅረባቸው ነው።

 ይህም በጭለማው ቡድን ላይ የፈጠረው ድንጋጤና ፍርሃት ጦርነቱን የመጨረሻ ደረጃ ላይ እንዲደርስ አድርጎታል።


 የቅድስት ሥላሴ ኮሌጅ ደቀ መዛሙርትና ማኅበረ ቅዱሳን የአቡነ ሳሙኤልን ፓትርያርክነት የሚፈልጉት ለራሳቸው ዓላማና ግብ መሳካት ከግምት በላይ መናገር ይቻላል።   የኤልዛቤልና የጭለማው ቡድን ከቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ስሩ ተነቅሎ የሚወድቀው አቡነ ሳሙኤል ሲሾሙ ብቻ ነው የሚል እሳቤም ተይዟል። በጭለማው ቡድን በኩል ያለው ጭንቀት ደግሞ  አቡነ ሳሙኤል ተሾሙ ማለት ከቤተክህነቱ ውስጥ ተመንግለን እንደበሰበሰ ግንድ ልንጣል ነው ከሚል ፍርሃት የተነሳ ሲሆን የነፍስ ውጪ፤ ነፍስ ግቢ ትንቅንቅ ማድረግ ዛሬ ነው ከሚል ቁጭትና እልህ ስሜት ሁለት ባላንጣ ቡድኖች  ግብግብ መግጠማቸው ይነገራል። በተለይም በአቡነ ጳውሎስ መንበር ላይ ጠላት የሆኑት አቡነ ሳሙኤል ሲቀመጡ ማየት በጣም ያማል የሚል ንዴት ስለሚገፋቸው  ትኩሳቱን አንሮባቸዋል።  ከዚህ ስር ነቀል ቁርሾና የመረቀዘ ቂም የተነሳ  በጣም እጅግ በጣም ከሚጠሏቸው ከአባ ሳሙኤል  ይልቅ፤ እንኳን የማይግባቡት ሌላ አባት ቀርቶ በግብሩ እንጂ በገጽ የማያውቁት ሰይጣንም ቢሾምም ግድ የለንም ከሚል አስተሳሰብ የመነጨ ትግል እንደሆነ ውስጥ አዋቂዎች ይናገራሉ።  በማኅበረ ቅዱሳንና በጨለማው ቡድን በኩል ግብግቡ ቀጥሏል። አሁን እየተፋጠጠ ባለው ሁለት ከፍተኛ አንጃ የተነሳ የቤተክህነቱ የሙቀት መጠን እየጨመረ መሄዱ እየተነገረ  ሲሆን ምናልባትም መካረሩ በዚሁ ከቀጠለ በተለመደው መልኩ የጌሾ ወቀጣው  ኃይልን  የመጠቀም እርምጃ እንዳይከተል አስግቷል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ድምጻቸውን አጥፍተው ወደሥልጣን ማማው ላይ ሳይታወቅ ቁጭ ብለው ሰሚውን ለማስገረም ውስጥ ውስጡን የሚሰሩ እንዳሉም የታወቀ ሲሆን ለሁሉም የእጩዎቹን ማንነት የካቲት 18 ስለሚገልጣቸው እነዚህን ስውራን ታጋዮችንም ያኔ እናውቃቸዋለን።

የፓትርያርክ ምርጫው ጊዜ አጭር መሆኑ በአንድ በኩል ድብቅ ፍላጎቶቻቸው ሳይታወቅ በዘመቻ መልኩ ካሰቡበት ለመድረስ የሚያግዛቸው ሲሆን ጊዜው ቢረዝም ሊመጣ ከሚችለው ፍጥጫም እፎይ ያደርጋቸዋል።  በሌላ መልኩም ቤተክህነቱ የተለያዩ የአጭር ጊዜ ዓላማን  ያነገቡ አፍጣጭ ኃይሎች ውጥረት ውስጥ እንድትገባ በማድረግ የኃይል ሚዛኑን ባሸነፈ በአንዱ ብርቱ አፍጣጭ  ቢደመደምና ፓትርያርክ ተመርጧል ቢባል የተመረጠው ሰው ሳይሆን ጉልበት እንዳይሆንም  ያስፈራል።  ምርጫው እርግጥ እንደመሆኑ መጠን ማንም ይመረጥ ማን ሽኩቻና ዐመጽ ያስፈለገው ለምንድነው?

የቤተ ክርስቲያኒቱ ችግር ብዙና ውስብስብ ቢሆንም አሁን እየታየ ባለበት ሁኔታ ምናልባትም ችግሩ ከውስብስብነት ባለፈ ለመመለስና ለማስተካከል ከማይቻልበት ደረጃ ውስጥ እንዳይከታት ያስፈራል። የተለያዩ  ቡድኖች ለዚያች አንድ እረፍት የማትሰጥና በችግር ለተዋጠች  የቤተ ክህነቱ ወንበር ለማድረስ የሚሯሯጡት፤ አባታችን የሚሉት አባት የቤተክርስቲያኒቱን ችግር እንዲፈታና ብሩህ ዘመን እንዲመጣ ከማሰብ ሳይሆን የራሳቸውን ዓላማ ግብ በተሿሚው ጀርባ ለማስፈጸም በመፈለግ እንደሆነ የዘመቻውን አካላት ማንነት ገምግሞ መናገር ይቻላል። የፓትርያርክነት ጦርነቱ እያየለ መጥቶ የአምስቶች ፍጥጫ የካቲት 18 ሲታወቅ የካቲት 21 ቀን ደግሞ የፍጥጫው ድምዳሜ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።                                      
 ለመሆኑ የዚህች ቤተክርስቲያን ውስብስብ ችግሮች መፍትሄ የሚያገኙትና የሚያበቁት መቼ ይሆን?


«መንፈስን ለማስቀረት በመንፈስ ላይ ሥልጣን ያለው ሰው የለም፤ በሞቱም ቀን ሥልጣን የለውም፤ በሰልፍም ስንብቻ የለም፥ ኃጢአትም ሠሪውን አያድነውም» መክ ፰፤፰