Saturday, February 23, 2013

አማኝ እንጂ አክራሪ አትሁን!


አማኝ ያመነውን የሚኖር በፍቅርም የሚማርክ ጀግና ነው። አክራሪ ግን ጥቂት እውቀቱን ከዱላ ጋር ለማስከበር የሚሞክር ነው። የከረረ ነገር መበጠሱ አይቀርም። የከረረ ነገር ሲከርም ሲበጠስም ስጋት ነው። አክራሪነት የአለሙ ልከኛ ሰው እኔ ነኝ። ከኔ በቀር በአለም ላይ ማንም መኖር የለበትም። ከምስራቅ ስገላበጥ ምእራብ እደርሳለሁ። ከሰሜን ስራመድ ባንድ ስንዝር ደቡብን እረግጣለሁ። ስለዚህ ከኔ ውጪ ማንም መኖር የለበትም ብሎ እንደማሰብ ነው። የአክራሪነት ምንጩ አለማወቅ ነው። አክራሪ ሰው በከሳሽነት መንፈስ የተያዘ እንጂ የሚያሳየው ማራኪ ስራ የሌለው ነው። ጥቂት እውቀቱ ከሰፋች የካደ ስለሚመስለው ላለማወቅ ተጠንቅቆ የሚጓዝ ነው። እርሱ ካለበት ገድጓድ ውጪ አለም ያለ የማይመስለው ። የለመድኩት ሰይጣን ይሻላል ብሎ ከመቃብር ጋር በኪዳን የሚኖር ተስፋ የሌለው ሳይሞት መኖር ያቆመ ሳይቀበር እውቀቱን የጨረሰ ሰው ነው። የአክራሪነት ወንድሙ አለማወቅ ነው።



እኔ ያወቁት ብቻ ትክክል እኔ ከሰማሁት ውጪ ያለው ያተነገረ ነው አለም በኔ ጓዳ በኩል ነው የምታልፈው እኔ ያልገባኝ ነገር እንዴት ልክ ይሆናል? ብሎ የሚያስብ ነው። መሀይም ማለት ያልተማረ ሳይሆን መማር የማይፈልግ ነው። የሰይጣን ትልቁ ግዛቱ ድንቁርና ነው። ሰዎች የህሊናን አይናቸውን ካላሳወረ በቀር አያመልኩትምእና ህሊናቸውን ያጨልማል ። ማወቅ እንደጨረሰ ሰው የምትኖር ከሆነ መኖርህ ምክንያት አልባ መሆኑን አስብ። ባለህበት ጉድጓድ መጠን ሁሉንም ነገር ካየሀው ሁሉም ነገር ይጠብብሀል። ትንሽ እውቀትም የስጋን ሀይልን ይሻልና እውቀትህን አሟላው ።
በጉልበቱ እያስፈራራ ከደጀ ሰላም የሚበላ አንድ ወጠምሻ ሰው ነበረ።


 የሌሊቱን ቁመት ሳይቆም ደግሞም ቅዳሴ ሳይቀድስ ያለ’ፋበትን እንጀራ በመብላቱ ቀሳውስቱ ሁል ጊዜ ቢያጉረመርሙበትም ማንም ደፍሮ የከለከለው አልነበረም። እርሱም ያልተማረ እንደሚሉት ስለሚሰማ እማራለው ብሎ ወደ አንድ መምህር ሄዶ “ አባቴ ዳዊት አስደግሙኝ” ብሎ ይጠይቃቸዋል። እርሳቸውም “ አንተ ተማር እንጂ እኔ ምን ከብዶኝ?” ብለው በደስታ እሺ ብለው ማስተማር ጀመሩ።አርሱም መዝሙረ ዳዊት ምእራፍ አንድ በደንብ እንደቻለ በቃኝ አላቸው። እሳቸውም ገና እኮ ነው ቢሉት “ አይ አባቴ ይህቺህ ትምህርቴ ከዱላዬ ጋር ትበቃኛለች “ አላቸው ይባላል ። ዛሬም ከዱላዬ ጋር ትንሽ እውቀቴ ትበቃኛለች ብለው የሚኖሩ ብዙዎች ናቸው። አንተ ግን እንደ እነርሱ አትሁን።