Monday, February 25, 2013

«በር ድብደባን ያየ፤ እስኪያፈጡበት አይጠብቅም»


ምሁራን ታሪክ ራሱን ይደግማል ይላሉ። አቡነ መርቆሬዎስን የደርግ ጳጳስ በማለትና ከእርስዎ ጋር ከእንግዲህ አብረን ልንሰራ አንችልም ማለቱ የሚነገርለት ኢህአዴግ ዛሬ ደግሞ ያንኑ ታሪክ ደግሞ የኢህአዴግን ፓትርያርክ ለመሾም የቤት ሥራውን ማጠናቀቁን ስናይ ኢህአዴግ ዘመናዊ ደርግ ሆኗል ወይም ደርግ ራሱ ተመልሶ መጥቷል የሚያሰኝ ነው። በአቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክነት ምርጫ ላይ የኢህዴግ ድጋፍ መኖሩ ባይካድም እንደዚህ ዓይነት ዓይን ያወጣ ጣልቃ ገብነት ግን በፍጹም አልነበረም። በወቅቱ ሥልጣኑን በለቀቁት ፓትርያርክ ላይ ቅሬታና ኩርፊያ የነበራቸው ወገኖች ብዙ ስለነበሩ የአዲስ ፓትርያርክ ፊት ለማየት ተፈልጎ ስለነበር አብዛኛው ሰው ስለአቡነ ጳውሎስ ትምህርት፤ችሎታ፤በደርግ እስር መሰቃየትና የመሳሰለውን የህይወት ታሪካቸውን ከግንዛቤ አስገብቶ ድምጹን የሰጠው ወገን ብዙም ውትወታና ልመና አላስፈለገውም  ነበር። በመንግሥትም በኩል ከፈቃደኝነቱ በዘለለ እንደዘንድሮው ዓይነት ግልጽ የሆነ ጣልቃ ገብነት ሳያደርግ ምርጫው መጠናቀቁን እናስታውሳለን።  በቀድሞው ዓይን የዛሬውን ስናየው ደርግ የራሱን ፓትርያርክ ሲያስመርጥ ከነበረው ጋር በተመሳሳይ መልኩ ኢህአዴግ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ሁለተኛው ደርግ መሆኑን እያሳየ ይገኛል። ከሁሉም ነገር ሊገባን ያልቻለው ጉዳይ ኢህአዴግ አቡነ ማትያስን ፓትርያርክ አድርጎ በመሾም የሚያተርፈው ምንድነው? አቡነ ማትያስስ ፓትርያርክ ስለሆኑ ኢህአዴግን የሚጠቅሙት እንዴት ነው፤ የሚለው ጥያቄ ግልጽ አልሆነልንም።
«አትረፍ ያለው በሬ ቆዳው ከበሮ ይሆናል» እንዲሉ ሆኖ ይመሩታል ከሚባለው የምእመናን ኅብረት ጋር  የመረጥነው አባታችን ተብለው ፍቅርና ክብር ካልተቸራቸው፤ እንዲሁም ርዕሰ መንበር ለሆኑለት ቅዱስ ሲኖዶስ  በኢህአዴግ ፓትርያርክነት ተፈርጀው በረባ ባልረባው አተካሮ በማስተናገድ ሰላምና እረፍት በማጣት  የተነሳ ዘወትር ያለኢህአዴግ ድጋፍ መኖር የማይችሉ የዘመመ ቤት ሆነው እሳቸውን ለመደገፍ በመታገል ጊዜውን ከሚጨርስ በስተቀር ኢህአዴግ ምንም ዓይነት ትርፍ  ከአቡነ ማትያስ አያገኝም። አቡነ ማትያስም ኢህአዴግን በምንም ጉዳይ ደግፈው ሊያቆሙት አይችሉም። ጉዳዩ በኢህአዴግ በኩል እኔ የፈለግሁት ፓትርያርክ ይሁን ከሚልና አቡነ ማትያስም ከምእመናን የምርጫ ድጋፍ ይልቅ የኢህአዴግን ጥሪ እንደመንፈስ ቅዱስ ምርጫ አድርጎ የመቀበል የሥልጣን ጥማት  ውጤት ነው።  በማንኛውም ሚዛን የወረደ የደካሞች አእምሮ የፈጠረው ስሌት ከመሆን ውጪ አይደለም። 


ኢህአዴግን ከስውር ፍላጎቱ በላይ እዚህ ድረስ በግልጽ ያስኬደው ነገር የእነ አቡነ ሳሙኤል ቡድን የምርጫውን ሂደት በማጦዝ አቅጣጫውን ለማስቀየር ያለው አቅም እያደገ በመምጣቱ  ሲሆን ይህንን ቡድን ዝም አሰኝቶ በአስመራጮች ላይ ጫና በመፍጠር ከእጩነት ፋይል ላይ እንዲፋቁ እስከማድረግ ድረስ አስገድዶታል።  ይህንን ያህል የጠለቀ እውቀት የሌላቸው የመንግሥት አስመራጮች ተሰብስብው አፄ በጉልበቱ ወደመሆን ተሸጋገሩ እንጂ እነ አባ ሳሙኤልን አርፎ ለማስቀመጥ ምንም ግርግር ሳያስፈልግ እጩዎችን ከመቀበል በፊት  የእጩው እድሜ ከ55 ዓመት በላይ እንዲሆን ማስደረጉ በቂ ነበር።  ይህ እንግዲህ በሁለተኛነት አስጊ የነበሩትን አቡነ ማቴዎስንም የሚያገል የእድሜ ማጣሪያው ጠቃሚ ስልት በሆነላቸው ነበር ። እንግዲህ እየተናገርን ያለነው ስለመንፈሳዊ ምርጫ ሳይሆን ኢህዴግና አስመራጮቹን በቀላሉ መንገድ እጃቸውን ሳይዶሉ ፍላጎታቸውን  ማስፈጸም  የሚችሉበት መንገድ እያለ ለምን እንደተሰወረባቸው ለማስታወስ መሆኑ ከግንዛቤ ይያዝልን።  በእርግጥ ለዝሆን የአይጥ በእግሩ ስር ማለፍ ምኑም እንዳይደለ ሁሉ ጥቃቅኑ ጠቃሚ ነገር ላይታያቸው ይችላል። ከዚያም በማስከተል ስለአቡነ ማትያስ ታላቅነት የሚዲያ ዜና መስራትና ማስተዋወቅ በማስከተል፤  ብዙም ከማይታወቁና እድሜአቸው ከገፉ ጳጳሳት ጋር ማወዳደር፤ ምርጫውን መፈጸም፤ ቆጣሪና አስቆጣሪን ማደራጀት፤ በመጨረሻም የስውሩ እጅ እንቅስቃሴ ሳይታወቅ ፓትርያርክ ማትያስን በእግዚአብሔር ፈቃድ የተመረጡ አባት ብሎ ማስጨብጨብ ፤ አለቀ፤ ደቀቀ። ነበር ነገሩ ግን አልሆነም።  ይህንን ዓይነት ሥጋዊ ጥበብ ከመጠቀም ይልቅ ግልጽ በሆነ የኢህአዴግ የሹመት ደብዳቤ መጻፍ ብቻ ወደቀረው ጣልጋ ገብነት መሸጋገሩን መረጠ። የፈለግነውን ብንሰራ፤ ማን ምን ያመጣል? መሆኑ ነው ነገሩ! አዎ ማን ምን ያመጣል?
ከላይ ከሰማይ ካልመጣ በስተቀር እንኳን እገሌን ምረጡ ተብሎና በደብዳቤ ሳይቀር እገሌን ፓትርያርክ ሾመናል ተብሎ ቢጻፍስ ማን ምን ያመጣል? አዎ አሁን ባለበት ሁኔታ ማንም ምንም አያመጣም። ከላይ ከሰማይ ካልመጣ በስተቀር፤ ማንም ምንም አያመጣምና አቡነ ማትያስን ፓትርያርክ ለማድረግ የምርጫ ሂደቱ እንዳይረሳ ሲባል ብቻ ጳጳሳት ሆይ ወደምርጫው ግቡልን። እኛም ብንመርጣቸው ኖሮ የማንጠላቸው ነገር ግን እኛን ወክሎ መንግሥት ሥራችንን አቅልሎ የመረጠልንን ፓትርያርክ ለመቀበል ዝግጁ ነን። ይደልዎ! ይደልዎ! ኢህአዴግ ይደልዎ ብለናል። የአቡነ ቄርሎስ የዝምታ ሆድ ይፍጀው «በር ድብደባን ያየ፤ እስኪያፈጡበት አይጠብቅም» መሆኑ ነው።