Monday, February 18, 2013

“ቤተ ክርስቲያን አልተከፈለችም”


..... በሚለው የፕ/ ጌታቸው ኃይሌ  መጣጥፍ መነሻነት የተዘጋጀ….
                                  ከመልዐከ ብሥራት፣ ቨርጂኒያ፣
በቅድሚያ ልባዊ ምሥጋናዬና አክብሮቴ ይድረሳቸው፡፡ በዚህ ጽሑፌ የምናገረው በእውነት ለቤተ ክርስቲያን ለሚጨነቁ ምዕመናንና አገልጋዮች ብቻ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን ላለፉት ሃያ አንድ ዓመታት በታላቅ ፈተና ውስጥ አልፋለች፡፡ አሁንም እያለፈች ነው፡፡ እግዚአብሔር አይበለውና ምናልባት የከፋው ፈተና ያለው ከፊት ለፊታችን ሳይሆን አይቀርም፡፡ የዚህም ሰበቡ ችግሮቻችንን በቅጡ ካለመረዳታችንና ከቸልተኝነታችን የመጣ መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ ለመሆኑ የቤተ ክርስቲያናችን ችግሮች በተለይ በውጪው ዓለም ምንና ምን ናቸው? ችግሮቹአንድ በአንድ ማወቅ ያስፈልገናል፡፡ ስለዚህ ነገሮችን በጥሞናና በሰከነ ሁኔታ እንድንመረመር ወቅቱ ያስገድደናል፡፡ በአገራችን ያለው የፖለቲካ ሁኔታ መክፋት በቤተ ክርስቲያን ላይ የፈጠረው መከራ እንዳለ ማንም ይረዳዋል፡፡ ይሁንና ግርግር ለሌባ ይመቻልና የፖለቲካው መክፋት መልካም ሁኔታ የፈጠረላቸውና ችግራችን እንዲወሳሰብ ያደረጉ ክፍሎች ካሉም ችግሮቻችንን ከመንስዔው ጀምሮ በጥንቃቄ መመርመር የብልህ አካሄድ ይሆናል፡፡
የጦር መሣሪያ የሚፈበርኩ አገሮች በዓለም ላይ ጦርነት ባይኖር ኖሮ ከስረው ይዘጉ ነበር፡፡ የዓለማችን ፖለቲካ አካሄድ እንደሚያስተምረን ከሆነ ደግሞ መሣሪያ ሻጮቹ ገበያውን ሆነ ብለው እንደሚፈጥሩት ማስረጃ መጥቀስ አያሻም፡፡ አቶ ስዬ አብርሃ በአንድ ወቅት ‹‹ኢህአዴግ ጦርነትን መሥራትም ይችላል›› ሲሉ እንደተናገሩት የውስጥ ችግሮቻችንን ሆነ ብለው የሚሠሩ ብሎም የሚያባብሱ፣ ግርግሩ ገበያ ያደራላቸው አካላት መኖራውን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ በአጭሩ ለመናገር ዋናውና ልናስወግደው የሚገባን ችግር አለ ሁላችንም እንስማማበታለን፡፡ ነገር ግን ዋናውን ችግር በሕብረት ሆነን እንዳንመክት ጎዳናውን የሚያወሳስቡ ሌሎች በቅድሚያ ልናስወግዳቸው የሚገቡንን ተጨማሪ ችግሮችም አሉን፡፡ አነዚያን በቅድሚያ ማስወገድ ያስፈልገናል፡፡ ከውጪ ያለብንን ጠላት ከውስጥ አንድ ሳንሆን እንጋፈጠው ብንል ውጤቱ የታወቀ ስለሆነ በፊት የውስጡን ችግር እናስወግድ፡፡ የውጪውን ለመቋም የተሸለ ዝግጅት የሚኖረን ያን ጊዜ ነው፡፡ በዚህ ከተስማማን ወደፊት እንቀጥልና የቤተ ክርስቲያናችንን ችግሮች በቅድሚያ እንደ ጌታቸው ኃይሌ በድፍረት አንጠቁማቸው፡፡ ከዚያም በግልጽ እንወያይባቸው፡፡ ያለዚያ ለውስጥ ደዌአችን ማርከሻ መድኃኒት ሳንወስድ በሥልጣን ላይ ያለውን አስከፊ አገዛዝ ለመቃወምና እርሱን ለማጥቃት ብቻ ብለን የወያኔን ኃጢአቶች ብቻ መላልሰን ብንናገራቸው "ውሃን እንቦጭ" ከማድረግ የዘለለ የምናገኘው ጥቅም አይኖርም፡፡ ስለዚህ ወደ ውስጣችንም የመመልከት ድፍረቱ እንዲኖረን እውነታው ያሳስበናል፡፡ በቅድሚያ ራሳችንንእንመርምር!!! በተጨማሪም ዛሬ ያልተዳሰሰው ችግራችን ነገ ያልተጠበቀ ክፉ ችግር (ካንሠር) ማስከተሉ አይቀርም፡፡ ወደድንም ጠላንም በእስከዛሬው ቸልተኝነታችን የተነሣም አንዳነድ የካንሠሩ ምልክቶችም ችግራችን በተንሠራፋባቸው በተለያዩ የዓለም ክፍሎች መታየት ጀምረዋል፡፡ እርሱን እመለስበታለሁ፡፡
 በአሁኑ ጊዜ ጎልተው ለሚታዩት የቤተ ክርስቲያናችን ችግሮች ምንጩ ወያኔ ብቻ ነው ብሎ ማመን ፍፁም የዋህነት ነው፡፡ ጌታቸው ኃይሌ ነካክተውታል፡፡ ይሁን እንጂ ታሪካዊ ስሕተት የፈጸሙት ወያኔዎች ብቻ ሳይሆኑ የውጪ ሲኖዶስ አቋቋመናል ያሉት አምስቱ ጳጳሳት ጭምር ናቸው፡፡ የስደት ሲኖዶስ ማቋቋም ትክክልና ሕጋዊነት እንደሌለው እያወቁ "ውሻ በቀደደው ዥብ ይገባል" እንዲሉ ነገ በቤተ ክርስቲያን ላይ ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ እንዳያስተውሉ የሥልጣን ጉጉት ዓይናቸውን ጋርዶት ወያኔ በቤተ ክርስቲያን ላይ ካደረሰባት በደል የሚከፋውን በደል የፈጸሙት እነሱ ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች ብልሆችና ለቤተ ክርስቲያንና ለቀጣዩ ቅውልድ አርቆ አሳቢዎች ቢሆኑ ኖሮ የጀመሩት ጉዞ ለማንም እንደማይበጅ ተገንዝበው "ወንበሩ ለኛ ይገባል" የሚል መንቻካ ግትርነታቸውን ትተው "የከፋፍለህ ግዛ" አጀንዳን አንግቦ የመጣውን ወያኔን ሕዝቡን አንድ በማድረግ በልጠውት በተገኙ ነበር፡፡ ነገር ግን እልህ የተሞላው የሞኝ ጉዞአቸውና ገታራነታቸው ሳያውቁት የራሱ የወያኔ ዓላማ ተባባሪ አድርጓቸው አረፈ፡፡ አንድ ጥላ ሥር መሰብሰብ የነበረበትን የአንድ ቤተ ክርስቲያን ምዕመን ለሥልጣን ጥማቸው ሲሉ ከፋፈሉት፡፡ የታደለ ወያኔ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ መሥራት የነበረበትን የመከፋፈልና የመበጥበጥ አጀንዳውን በብዙ ፐርሰንት አቀለሉለት፤ እናም ደጋግመው ሳያስቡበት፣ እኔ ከሞትኩ ሠርዶ አይብቀል እንዳለችው እንስሳ በራስ ወዳድነት ያቋቋሙት "ሲኖዶስ" ምዕመኑን ከመከፋፈልና ከማወናበድ እነዲሁም ለግለሰቦች መጠቀሚያ ከመሆን የዘለለ ሃያ አንድ ዓመት ባስቆጠረው ዕድሜው ለቤተ ክርስቲያንና ለበጎቿ ያስገኘው አንዳችም ፋይዳ የለም፡፡
ሰዎች ብዙ ጊዜ፣ አሁን ጌታቸው በጽሑፋቸው እንደጠቀሱት ስለጎሰኝነት የሚያነሱት ነገር አለ፡፡ ስለ ጎሰኝነት ሲወሳ አንድ ነገር በድፍረት ልናነሣ የግድ ነው፡፡ ጣትን ወደ ወያኔ አቅጣጫ ብቻ መጠቆም አግባብም ሞራላዊም አይደለም፡፡ ሌባን "ሌባ!!" ብለን በድፍረት ስንሰድብ እኛ ሌቦች መሆን የለብንም፡፡ ያለበለዚያ ሌባው እየሳቀ "አመድ በዱቄት ይስቃል" በማለት በራሳችን ላይ ማላገጡ የማይቀር ነው፡፡ እና ሁል ጊዜ በጎሰኝነት የምንከሰው ወያኔን ብቻ ነው፡፡ ምክንያታችንም ወያኔ ከአንድ ጎሣ (ከትግራይ) የወጣ፣ በደደቢት የተጠነሰሰ ጠባብ የጎጠኞች ቡድን በመሆኑ ነው፡፡ ሲጠነሰስም በስምንት ሰዎች ነበር፡፡ እነዚህስ አምስቱ ሲኖዶስ አቋቋሚዎች፤ ነፍሳቸውን ይማረውና አቡነ ዜና ማርቆስ፣ አቡነ መልከፀዴቅ፣ አቡነ ኤልያስ፣ አቡነ ጎርጎርዮስ፣ (አቡነ ይሥሐቅ በፊት ተሳስተው አብረዋቸው የነበሩ ቢሆንም ኋላ ግን ነገሩ ሲገባቸው ተለይተዋል) እንዲሁም የቀድሞው ፓትርያርክ ራሳቸው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ፤ የነርሱ ሁኔታስ በምን መነጽር ነው የሚታየው? እነዚህምኮ የመጡት ከአንድ ክፍለ ሐገር ነው፡፡ እንዲያውም ምንጫቸው ከአንድ አውራጃ ነው፡፡ ጎሰኝነት በኛ ላይ ሲሆን ጌጥ፣ በወያኔ ላይ ሲሆን ግን የሚያስጠላ፣ የሚዘገንን ቁስል የሚሆነው እስከመቼ ነው? ያለው ሰው ትዝ አይለኝም፡፡ ስለዚህ እነዚህም ያው ጎሰኞች ናቸው፡፡ አሁንም ቢሆን ስደተኛ በሚሉት ሲኖዶስ ውስጥ በቅርቡ ከተሸሙት 13 ጳጳሳት ውስጥ ለመልክ ከተቀየጡት የሌላ ጎሣ አባላት በስተቀር ሁሉም ለማለት ይቻላል ያው የአንድ አካባቢ ሰዎች ናቸው፡፡ ዝርዝራቸውን ማውጣት ይቻላል፡፡ ወያኔ የጎሰኝነት መልኩን ለመቀየር (ለማጭበርበር) ራሱ ጠፍጥፎ በሠራው ኢህአዴግ በተሰኘ ጭምብሉ፤ እነዚህም ሕጋዊው ሲኖዶስ እያሉ በሚጠሩት ጭምብላቸው ውስጥ እየተሸሸጉ ነው የግል ፕሮግራሞቻቸውን የሚያከናውኑት፡፡ ቢዋጥልንም ባይዋጥልንም ሐቁ ይኸው ነው፡፡ ይህን ችግር ዛሬ በለጋነቱ አፍረጥርጠን እንዲስተካከል ካላደረግነው ነገ ከማይስተካከልበት ደረጃ ላይ ከደረሰ በኋላ ሌላ ችግር ሲፈጥር ሁላችንም ቢያንስ በሕሊና ዳኝነት ተጠያቂ መሆናችን አይቀርም፡፡ "አይ ሠላም፣ በስምሽ ስንት ግፍ ተሠራ" እንደተባለው በዳያስፖራው ማኅበረሰብ ውስጥ በኢትዮጵያና (በጋራ ጠለታችን በወያኔ) ስም በቤተ ክርስቲያን ላይ ስንት ዓይነት ጥፋት ደረሰ !!! እና ትግሬም ይሁን አማራ፣ ኦሮሞም ይሁን ጉራጌ ጠባብ አስተሳሰብ አራማጅ ከሆነ ጎሰናና ጎጠኛ ነው፡፡ ስለዚህ በወያኔ የተኮነነ ጣልቃ ገብነት ላይ ተቃውሞዬ እንደተጠበቀ ሆኖ ነገር ግን የነዚህ ሊቃነ ጳጳሳት በስማችን እየነገዱ አላስፈላጊ የሆነ ሲኖዶስ ማቋቋማቸው ከኩነኔም ኩነኔ እርሱ ነው፡፡ ይህ ድርጊታቸው በወያኔ ተነጠቅን በሚሉት ሥልጣን በኩርፊያ ተነሳስተው በግል ደረጃ ያደረጉት የሞት ሽረት ትንንቅ እንጂ ለቤተ ክርስቲያን ሕልውና አስፈላጊ ስለሆነ የወሰዱት ርምጃ አለመሆኑ በሁላችንም ዘንድ በደንብ መታወቅ አለበት፡፡ ይህም እውነታ ባለፉት የሃያ አንድ የመከራ ዓመታት ውስጥ ሲኖዶሱ አንድም ጥቅም አለመስጠቱን በሚገባ አረጋግጦልናል፡፡ ከነሱ ጦሰኛ ሲኖዶስ መመሥረት ለቤተ ክርስቲያን የተረፋት ነገር ቢኖር ዋናውን የጋራ ጠላት አስቀምጦ እርስ በርስ መከፋፈል፣ የወንድማማቾች ጠብና ክርክር፣ ስድድብና መወጋገዝ ብቻ ነው፡፡ አጋጣሚው በከፈተላቸው ዕድልም የሃይማኖት ተቃማዊዎቻችን በጥሩ ሁኔታ እንደተጠቀሙብን ሌላው የማንክደው ሐቅ ነው፡፡ ጌታቸው ኃይሌ ከተናገሩት ውስጥ "በሀገሪቱ ላይ የዘሩትን ጎሰኝነት ዘረኝነት ከማታውቀው ቤተ ክርስቲያን አስገቡት" ሲሉ ያስቀመጡት አባባል ሐቀኝነቱ እንዳለ ሆኖ ነገር ግን ለዚህ ችግርም መከሰት ተጠያቂው ጎሰኛው የወያኔ መንግሥት ብቻ አለመሆኑን በቅጡ መመልከት ያስፈልጋል፡፡ ይህን ለመመልከት እስቲ ከወያኔ መምጣት በፊት የነበረውን የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ለአንድ አፍታ ወደ ኋላ ተመልሰን እንዳስሰው፡፡ የቀድሞው ፓትሪያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ በሥልጣን ላይ የቆዩበትን ጊዜ ማለቴ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ወያኔ ያደረገውን የቤተ ክርስቲያን ጣልቃ ገብነት ደርግም ሲፈጽመው የቆየ ባሕል መሆኑን ልብ ማለት የስፈልጋል፡፡ ብዙ ሰዎች ይህ ዓይነቱ ተግባር የወያኔ ብቻ ይመስላቸዋል፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ በቀጥታ፣ ደርግ ደግሞ እንደ ወያኔ በሥውር በቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደር ጣልቃ ይገቡ ነበር፡፡
ወያኔዎች ልክ አቡነ ጳውሎስን በመንበሩ ላይ በጉልበት እንደሰየሙ ሁሉ አቡነ መርቆሬዎስንም በሥልጣን እንዲቀመጡ ያደረጉት ደርጎች ነበሩ፡፡ እንዲያውም ለሹመት ያቀረባቸው (ኢንዶርስ ያደረጋቸው) በወቅቱ የጎንደር ፈላጭ ቆራጭ የነበረው የመንግሥቱ ቀኝ እጅ መላኩ ተፈራ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ከአቡነ መርቆሬዎስ በፊት የነበሩት ፓትሪያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተ/ሃይማኖት ባረፉ ጊዜ ይነገር የነበረ አንድ ቀልድ ነበር፡፡ ደርጎቹ መንበረ ሥላጣኑን የሚሰጡት ታማኝ መነኩሴ  (ጳጳስ) ሲያፈላልጉ በነበረ ጊዜ መንግሥቱ ኃ/ማርያም ተናገረ የተባለው ቀልድ ነው ቀልዱ፡፡ "እገሌ አይሆንም ጠማማ ነው" "እገሌ መሐይም ነው" "እገሌም እንዲህ ነው" ወዘተ.. እየተባለ ከጳጳስ ጳጳስ ሲመረጥ በነበረ ጊዜ "ታማኝ" ጳጳስ ፍለጋው ጊዜ ስለወሰደ ነው አሉ፤ አጅሬ "በቃ እንግዲህ እንደፈረደብኝ እኔው ደርቤ እሰራዋለሁ" አለ ይባላል… ፓትሪያርክነቱን….. ወደ ርዕሰ ጉዳዩ እንመለስና በየወቅቱ የነበሩ የኢትዮጵያ መንግሥታት ቤተ ክርስቲያንን መቆጣጠራቸው የታወቀ ልምምድ ሲሆን እንኳን ወያኔ በጉልበቱ (በአፈ ሙዝ) በሥልጣን ኮርቻ ላይ የተወዘፈው መንግሥት ይቅርና ሌላውም ቢሆን ቤተ ክርስቲያንን መቆጣጠር ግድ የሚሆንበት ምክንያት ቤተ ክርስቲያንን እንደ ልቧ ለቅቆ እንደ መንግሥት መቆም እንደማይችል ስለሚታወቅ ነው፡፡


 
 ስለዚህ በአገራችን የመንግሥት በቤተ ክርስቲያንን ጣልቃ መግባት ወያኔ የጀመረው አዲስ ፈሊጥ አይደለም ለማለት ነው፡፡ ይህን ደግሞ ከኛ ከምዕመናን የበለጠ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች አሳምረው የሚያውቁት ሕያው ታሪክችን ሲሆን ይህንን ዓይነቱን ግዙፍ ሐቅ ወደጎን ትቶ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ቀኖና ውጪ ሌላ ሲኖዶስ ማቋቋማቸው ጊዜ በሰጠው ጉልበተኛ የተነጠቁትን ሥልጣናቸውን በግላቸው መልሶ በእጅ ለማድረግ በዳረጉት መፍጨርጨር እንጂ እውነት መንበሩ ከኢትዮጵያ ለመሰደድ የሚያበቃው ችግር ስለደረሰ አይደለም፡፡ በጣም የሚያሳዝነው ነገር ግን ለዚህ የሥልጣን ትግላቸው (ሽኩቻቸው) ፍጆታ ያደረጉት ቤተ ክርስቲያኒቱንና እኛኑ ምዕመናንን መሆኑ ነው፡፡ የጳጳሳቱ አንደበት ለምዕመናን ጆሮ በጣም ቅርብ ስለሆነ "ፓትሪያርክ እያለ ፓትሪያርክ ተሾመ"፣ "ሕግ ፈረሰ!!" ስላሉ ቁጥራቸው ቀላል ያልሆኑ ውስጡን (ሐቁን) ያላወቁ ምዕመናን እውነት ነው ብለው ተቀበሏቸው፡፡ የአይሁድ ጳጳሳትም ክርስቶስን በሰቀሉት ጊዜ የምዕመናንን ቀልብ የሳቡት "ኢየሱስ የሙሴን ሕግ ሽሯል" በማለት ነበር፡፡ ከዚህ ሌላ ደግሞ መታወስ ያለበት ሌላ አንኳር ጉዳይ አለ፡፡ ጌታቸው ኃይሌ "ጎሰኝነትን ከማታውቀው ቤተ ክርስቲያን ዘረኝነትን ያስገቡ" ወያኔዎች ናቸው ይላሉ፡፡ እኔ ደግሞ ልክ ነዎት ወያኔዎች የተባለውን ፈጽመዋል ነገር ግን ይህን ዓይነት አስነዋሪ ሥራ የሠሩ እነርሱ ብቻ አይደሉም እላቸዋለሁ፡፡ ምንም እንኳን ወያኔ በቤተ ክርስቲያን ላይ እያደረሰ ያለው ግፍ ከመጠን ያለፈ ቢሆንና የብፁዕ አቡነ ጳውሎስ አስተዳደር በጎሠኝነትና በሙስና የተጨመላለቀ ቢሆንም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ በሥልጣን ላይ በነበሩበት ጊዜ በቤተ ክርስቲያን ሰፍኖ የነበረው ቅጥ ያጣ የጎሰኝነት አስተዳደር፤ ታሪክ ፈጽሞ ሊረሣው የማይችል የታሪካችን መጥፎ ጠባሳ መሆኑል ልብ ማለት ይገባል፡፡ ያ መጥፎና የተበላሸ አስተዳደር በብዙዎች ዘንድ እጅግ ከፍ ያለ ብሶትና ቁጭት አከማችቶ የነበረና አሁን ያለፈ ታሪክ ስለሆነ ብቻ ቸል ተብሎ ሊታይ የማይችል ሥቃዩ አሁን ድረስ ያልሻረ ችግር እንደሆነም መረዳት ይገባል፡፡ አሁን ድረስ ቤተ ክርስቲያኒቱን እየለበለባት ያለው የዚያን ጊዜው የኮመጠጠ እርሾ ነው፡፡ እነዚያው ሰዎች ናቸው ይኸው ዛሬም መንበሩ ተሰድዷል እያሉ የበደል በደል የሚሠሩት፡፡ አቡነ ጳውሎስ ሲከሰሱባቸው ከነበሩ ችግሮች ዋነኛው ጎሰኝነትን በቤተ ክህነት ውስጥ አስፋፍተዋል፣ ከርሳቸው ጀምሮ እስከ ዘበኛ ድረስ ትግሬ ብቻ እንዲሰገሰግ አድርገዋል፡፡ በየአድባራቱና በዋና ዋና መንፈሣዊ የስራ ኃላፊነት ቦታዎች የሚያስቀምጡት እነዚያኑ ያገር ተወላጆቻቸውን ብቻ ነው የሚል ነው፡፡ ይህ ብቻም አይደለም፤ መንግሥት የንፁሐን ዜጎችን ደም ሲያፈስ በዝምታ ተመልክተዋል፣ በቤተ ክርስቲያን ቅጥር ግቢ ውስጥ በመሣሪያ ሰው ገድለዋል/አስገድለዋል፣ ታጣቂ ናቸው፣ በቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ሙጢኝ ብለው የተጠለሉ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ለፀጥታ ወታደሮች አሳልፈው ሰጥተዋል… ወዘተ…የሚሉት ከብዙዎቹ ከሚሠነዘሩባቸው ክሶች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ የቅርብ ጊዜ ታሪካችን እንደሚያስረዳው ከሆነም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስም ፍፁም ተመሳሳይ የሆነ ክስ ይሠነዘርባቸው ነበር፡፡ በዘመናቸው ከራሳቸው ከፓትሪያርኩ ጀምሮ እስከ ታች ድረስ በቤተ ክህነት ዙሪያና በሌሎችም የኃላፊነት ቦታዎች የመቀጠር ዕድል የነበረው ጎንደሬ ብቻ ነበር፡፡ እንዲያውም የርሳቸው የበለጠ የጠበበ ሲሆን ከመላው ጎንደር እንኳ ቅድሚያ የሚሰጠው ከፋርጣ ለሚመጣው ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪ እንደ አቡነ ጳውሎስ ሁሉ በርሳቸውም ላይ ይሰነዘሩባቸው ከነበሩት ክሶች ውስጥ ደግሞ ከዚህ በታች የተጠቀሱትን እንይ፡፡ ፓትሪያርኩ በ "ኢሕዲሪ" ሸንጎ ላይ በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ባሉ ቁጥር "ኢሠፓው መጣ!" ይባሉ ነበር፡፡ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ምዕመናንን ለማሳለም መስቀል አወጣሁ ብለው ኮልቱን መዘዙት ይባሉ ነበር፡፡ መላኩ ተፈራ ያን ሁሉ ወጣት ሲጨፈጭፍ (እርሳቸው በወቅቱ የጎንደር ሊቀ ጳጳስ ነበሩ) ያገር ሽማግሌዎች ተሰብስበው "አባታችን ምነው ይህ ሁሉ ደም ሲፈስ ዝም ብለው ይመለከታሉ?" ተብለው ተጠይቀው ጭራሹን "የሊቀ መላኩ ሠይፍ እንዳይበላችሁ አርፋችሁ ብትቀመጡ ይሻላል!!" ብለው ሽማግሌዎቹን አስፈራርተዋል ተብሎ ይታሙ ነበር፡፡ ሊቀ መልዐክ የተባለው መላኩ ተፈራ መሆኑ ነው፡፡ እንግዲህ ይህ ሁኔታ ወለል አድርጎ የሚያሳየን ነገር በአቡነ መርቆሪዎስም አስተዳደር ዘመን ጎሰኝነቱና የሙስናው ደረጃ በሕብረተ ሰቡ መካከል በተለይም በቤተ ክህነት አካባቢ ፈጥሮት የነበረው እጅግ የመረረ ብሶት ልክ አሁን በአቡነ ጳውሎስ ዘመን እንደነበረው ተመሳሳይ እንደነበረ ነው፡፡ ስለዚህ ወያኔ አቡነ ጳውሎስን በሥልጣን ማስቀመጡ የማይታበል ሐቅ ቢሆንም ደርግ ተወግዶ ሕዝቡ የመናገርና የመሰብሰብ ነፃነት ባገኘ ጊዜ በቤተ ክህነት ውስጥ ተቀስቅሶ የነበረው አመፅ ከዚያ ታምቆ ከነበረው ቁጭትና ብሶት የተወለደ እንጂ ወያኔ ወገቡን አስሮ ያስተባበረው የለውጥ እንቅስቃሴ አልነበረም፡፡ ሁኔታው ራሱ በስሎ ጊዜውን ሲጠብቅ የነበረ ስለነበር ነገሩ እግዚአብሔር በፈቀደ ጊዜ ሲፈነዳ በአቡነ መርቆሬዎስና በአስተዳደራቸው ላይ የተቀሰቀሰው ከፍተኛ አመጽ ሥልጣናቸውን በፈቃዳቸው እንዲለቁ አስገድዷቸዋል፡፡ ማስረጃም አለ፡፡ በነገራችን ላይ "ከአቡነ መርቆሬዎስ ጋር ለመሥራት እንቸገራለን" ብሎ እግሩ እንደገባ ለቅዱስ ሲኖዶስ ደብዳቤ የፃፈና በጫካ ሲያፈስ የነበረው ደምና ያገኘው "የጦርነት ድል" ያሰከረው፣ የአገሪቱን ሥልጣን በአፈ ሙዝ ተቆጣጥሮ የመጣው የሽፍታ ቡድን በፊት ለፊት (በደረቅ አማርኛ) "ኤርትራ የኢትዮጵያ አካል አይደለችም!! በኃይል፣ በቅኝ የተያዘች ሉዐላዊት አገር ናት" እያለ በከፍተኛ እብሪት ሲደነፋ የነበረው ወያኔ አቡነ መርቆሬዎስን ከሥልጣን ለማባረር ሲል በቤተ ክህነት ውስጥ በካህናት አማካኝነት አመጽ አስተባብሮ በድብቅ ቲያትር የሚሠራበት ምክንያቱም በዚያ ሰዓት ደግሞ ጊዜውም አልነበረውም፡፡ በዚያ ሰዓት የወያኔ ቋንቋ ሁሉ "ዘራፍ!" "ውረድ እንውረድ!"፣ "መንገዱን ጨርቅ ያድርግላችሁ!" "ነፍጠኛ አማራ፤" በመሳሰሉት የዕብሪት አነጋገሮች የተሞላ እንደነበር የሚያስታውስ ሁሉ አቡነ መርቆሬዎስን ከሥልጣን ለማውረድ ከዚህ የተለየ መንገድ (ለምሣሌ ሥውር ቲያትር ምናምን) ይጠቀማል ብሎ አያምንም፡፡ ወደድንም ጠላንም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለፈነዳው አብዮት እርሾውም መርዙም በወቅቱ የነበረው የተበላሸው የአቡነ መርቆሬዎስ አስተዳደር ያስቀሰቀሰው አመጽ ነበር፡፡ ሕዝቡ፣ በተለይም ካህናቱ ታፍነው ስለነበር በአገሪቱ ነፍሶ የነበረው የለውጥ አየር በውስጣቸው የታመቀውን የቁጭትና የብሶት ስሜት አገነፈለው፡፡ በቃ እውነተኛ ታሪኩ ይኸው ብቻ ነው፡፡ ለቤተ ክርስቲያናችን እውነተኛ መፍትሔ የምንፈልግ ከሆነ ሳንፈራ ልንነጋገርባቸው ከሚገቡን ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ይህ የታሪካችን ክፍል ነው፡፡ የወያኔን ኃጢአት ብቻውን መዘርዘር ፋይዳ የለውም፡፡ በአጠቃላይ አቡነ መርቆሬዎስን ከሥልጣን ለማባረር ከአጀንዳዎቹ አንዱ ቢሆንም ወያኔ ግን አዲስ አበባ ገብቶ ይህን በተግባር ለማዋል ከመንቀሳቀሱ በፊት አብዮቱ ራሱን በራሱ አቀጣጥሎት ነበር፡፡ እነ መለስ ዜናዊ በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ ጥይት አላባከኑም፡፡ አቡነ መርቆሬዎስም ይህን የሕዝቡን ስሜት በሚገባ ከተረዱት በኋላ የርሳቸው ነገር ያበቃለት መሆኑን ከልባቸው ስላመኑበት ቀሪ ዘመናቸውን በንስሐ፣ በአታቸውን ዘግተው ለመኖር በመወሰን በጤና መታወክ የተሳበበ መልቀቂያቸውን ጽፈው ለሲኖዶሱ አቀረቡ፡፡ እርግጥ ነው፤ እርሳቸው ሲወገዱ ወንበራቸውን እናገኛለን ብለው ለቅዱስ ሲኖዶሱ መልቀቂያ እንዲያቀርቡ ያግባቡአቸው የነበሩ የራሳቸው የቅርብ ሰዎች እነ አቡነ ዜና ምርቆስ እንደነበሩ ይታወቃል፡፡ እርሳቸውና ሌሎች ከታች ሆነው ወንበራቸውን ሲጎመጁ የነበሩት ሊቃነ ጳጳሳት መልቀቂያቸውን (በጤና ምክንያት ለመሰናበት የቤተ ክርስቲያን ቀኖና እንደሚፈቅድ ስለሚያውቁ በመከሩአቸው መሠረት ያጻፉአቸውን መልቀቂያ) ከመቅጽበት ተቀብለው ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተው አሰናበቷቸው፡፡ ድርጊቱ ግን በኋላ በወያኔ ተሳበበ፡፡ ሌላው በጣም የሚገርመው ነገር እነ አቡነ ዜና ማርቆስ ወንበሩን እንረከባለን ብለው እርግጠኞች ስለነበሩ ለአሥር ወራት ያህል መንበር ጠባቂ ሁነው ሲሠሩ "ፓትሪያርኩ በጉልበት፣ በሕገ ወጥ መንገድ ተነሱ" ብለው አንዲት ተቃውሞ አለማንሳታቸው ነው፡፡ ነገር ግን ምርጫ እስኪካሄድ ድረስ ጠብቀው በምርጫው ተሣትፈው ሲያበቁ ውጤቱ ያልጠበቁት ሲሆን ጊዜ አቡነ ጳውሎስን "ይደልዎ! (ሹመት ያዳብር) ብለው መርቀው" ከአገር ከወጡ በኋላ (አቡነ መርቆሬዎስ ሥልጣን ከለቀቁ ከአንድ ዓመት በኋላ መሆኑ ነው) የሕግ ጥያቄ አነሱ፡፡ "ፓትሪያርክ እለ ፓትሪያርክ ተሾመ!!" አሉ፡፡ የስደት ሲኖዶስ አቋቋሚዎቹ ሊቃነ ጳጳሳት ከዚህ በኋላ ፓትሪያርኩ የሌሉበት "ሲኖዶስ ተሰዷል" ለማለት ስላልቻሉ በዚህም በዚያም ብለው በተንኮል የፈነቀሏቸውን ፓትሪያርክ እንደምንም ብለው በኬንያ በኩል እንዲወጡና እንዲቀላቀሏቸው አደረጉ፡፡ ይሁን እንጂ ፓትሪያርኩን ከአገር ማስወጣት የተከፈለው መሥዋዕትነት ቀላል አልነበረም፤ ፕሮጄክቱ ከአንድ ዓመት በላይ ወስዶባቸዋል፡፡ በዚህም የተነሣ ወደ ገዳማቸው ሊገቡና በንስሐ ሊታጠቡ ቆርጠው የነበሩት የቀድሞው ፓትሪያርክ አቡነ መርቆሬዎስ ታሪክ ይቅር የማይላቸውን ታላቁን ስሕተት ፈጸሙ፡፡ ሁሌ በሰው እንደሚመሩ ይታሙ የነበሩት ሰው ይኸውና እስከዛሬ ድረስ የነ አባ ሀብተማርያም መጫወቻ ሆነው ቀሩ፡፡ በድብቅ ከአገር ተሰደዱ" ሲሉ ይተርካሉ፡፡ ባይንቁን ኖሮ ግን ኮብራቸውን እያስነዱ ከአጃቢዎቻቸው ጋር የጠረፍ ወታደሮችን የይለፍ ሠላምታ እየተቀበሉ በሰላም የወጡትን ፓትሪያርክ እንደ አይጥ ሰው ሳያያቸው ወጡ እያሉ ለማውራት ባልደፈሩ ነበር፡፡ ይህ ሁሉ ኃጢአታቸውን ለመሸፈን የተጠቀሙበት ዘዴ እንደሆነ ግን ማንም በቀላሉ ያስተውለዋል፡፡ ከድሮ ጀምሮ አሁን ድረስ የዚህ ሁሉ ኢንጂነር አቡነ መልከፀዴቅና አቡነ ዜና ማርቆስ አንድም ቀን ነገሩን በሠላም ለመፍታትና የተሸለ ነገር ለመፍጠር ፍላጎት አሳይተው አያውቁም፡፡ ከዚህ ጋር አባሪ የተደረጉትን ለጊዜው ይጠቅማሉ ያልኩአቸው ሰነዶች እውነቱን ለመገንዘብ ስለሚረዱ ትመለከቱአቸው ዘንድ እጋብዛለሁ፡፡ እነዚህ ሊቃነ ጳጳሳት ይህን ሁሉ ያደረጉትና እደረጉ ያሉት ቀድሞውንም ቤተ ክርስቲያኒቱን ለመታደግ ሳይሆን ተቀማን ያሉትን ሥልጣን የሚያስመልሱ ስለመሰላቸው ነበር፡፡ ታዲያ ለነሱ የሥልጣል ሽሚያ ምዕመኑን ያስከፈሉት ዋጋ እጅግ በጣም ውድ ሆነ፡፡ እነሆ አነርሱ በቀደዱት ቀዳዳ በመሹለክ በሆነ አገር የሚገኝ አንድ ቤተ ክርስቲያን ምናልባት ወያኔ የወደቀ እንደሆን ተብሎ ወደፊት የሚቋቋመው የትግሬ አፈንጋጭ ሲኖዶስ አካል ለማድረግ ካሁኑ ዝግጅቱን አጠናቋል ይባላል፡፡ በዚህ የተነሣ ቤተ ክርስቲያኒቱን ከቅዱስ ሲኖዶስ የአስተዳደር መዋቅር ነጥሎ "የትግራይ ኮሚኒቲ" ተብሎ የሚታወቅ የትግሬዎች ማኅበር የግል ንብረት አድርጎአታል፡፡ እንግዲህ ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባል ማለት እንደዚህ ነው፡፡ ስለዚህ እነዚህ አምስት ሰዎች ራሳቸው የከፈቷትን ቀዳዳ ራሳቸው የሚደፍኑበትን ሥራ ቀኑ ሳይመሽ የማፈላለግና የመጠገን ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ይህን እንዲያደርጉ የሚያስገድዳቸው ደግሞ የኛ የምዕመናን ግፊት ብቻ ነው፡፡ ያለበለዚያ ዕድሜ ልካቸውን ከታሪክና ከሕዝብ ለመታረቅ ያስቸግራቸዋል፡፡ ከሁሉም በፊት ግን ኃላፊነቱ የምዕመናን ነው፡፡ በስሕተት ጎዳና መመራታችንን ተረድተን "የሕጻናትን ልብ ለዐዋቂዎች፣ የዐዋቂዎችን ልብ ለሕፃናት እሰጣለሁ" ተብሎ በመጻፉ እነርሱ ሊያደርጉ የሚገባቸውን ካላደረጉ ሊደረግ የሚገባውን ነገር ለማድረግ መነሣት አለብን፡፡ በዜሮ ውጤት የተደመረው ያለፈው ዘመን ታሪካችን ከዚህ በላይ ጥፋት ሳያደርስ ይብቃ! እነርሱ እንደሆነ መንበሩ ለነሱ ካልተመለሰ በስተቀር አንድም ጊዜ የዕርቅ ፍላጎት አሳይተው አያውቁም፡፡ አሁንም የላቸውም፡፡ የዋኆች ምዕመናን ግን እርቅ ይመጣል ብለው ተስፋ ሲያደርጉ ኖሩ፡፡ እኛ ካልገፋናቸው እርቁ በራሳቸው አነሳሽነት ይመጣል ብለን እንደ ኅብስተ መና ብናንጋጥጥ እግዚአብሔርም ታሪክም ልጆቻችንም ይወቅሱናልና ሁሉም የተዋህዶ ልጅ ከልቡ ያስብበት ዘንድ አደራ እያልኩ ለጊዜው እሰናበታለሁ፡፡
እግዚአብሔር ይታረቀን