Thursday, February 7, 2013

ጥቃቅን ሹመኞችና የገደል ቅራፊ ሚያካክሉ መዘዞቻቸው

በዳዊት ወርቁ

pomjos@yahoo.com


ቱኒዚያዊው የሃያ ስድስት ዓመቱ ወጣት ሙሐመድ ቡዓዚዝ፣ ጋሪ እየገፋ ፍራፍሬና አትክልት በመሸጥ ኑሮውን የሚገፋ የጎዳና ላይ ለፍቶ አዳሪ  ነበር፡፡  በሚያገኛት ጥቂት ፈረንካም የራሱንና የስምንት ቤተሰቡን ነፍስ ይቀልብ ነበር፡፡  ፋይዳ ሃምዲ የተባለች ፖሊስ፣ ዘጠኝ ራሱን መደጎሚያ ጋሪውንና ፍራፍሬውን በግፍ እስክትነጥቀው ድረስም፣ ለሰባት ዓመታት ያህል በደቡብ ቱኒዚያ 300 ኪሎሜትር ያህል ከምትርቀውና ሲዲ ቡዚድ ከምትባለው የትውልድ ስፍራው እንደ ሁለተኛ ዜጋ ተቆጥሮ፣ ማስኗል፣ ተንከራቷል፣ በእሰራለሁ አትሰራም እንካ ሰላንቲያም ከጥቃቅን ሹመኞችጋ እሰጥ አገባ ገብቷል፡፡ በመጨረሻም ውድ ህይወቱን ከፍሏል፡፡

እንዲህ አይነት ተደጋጋሚ ሁኔታ ብዙ ጊዜያት አጋጥሞት የነበረው ሙሐመድ ቡዓዚዝ፣ በቀን ያገኝ የነበረውን 10 ዲናር፣ (በኢትዮጵያ 126 ብር ያህል) ንብረቱን ትመልስለት ዘንድ እንደ እጅ መንሻ አድርጎ የዕለት ጉርሱን ለነጠቀችበት ፖሊስ ፋይዳ ሃምዲ አቅርቦ ነበር፡፡ ነገር ግን፣  የፋይዳ ሃምዲ ምላሽ በህይወት የሌሉትን አባቱን መስደብና የሙሐመድ ቡዓዚዝን ጉንጭ በጥፊ ማጮል ነበረ፡፡ በድርጊቱ ከፍተኛ ውረድት የደረሰበት ሙሐመድ ቡዓዚዝ፣ የደረሰበትን በደል አቤት ለማለት ወደ በላይ አካላት ቢያቀናም፣ የበላይ አካላት ተብዬዎቹ ከእጅ አይሻል ዶማ በመሆናቸው አቤቱታው የውሃ ሽታ ሆነ፡፡

ዘጠኝ ራሱን የሚያኖርበትን ጋሪና አትክልት በግፍ ከተነጠቀ አንድ ሰዓት በኋላም፣ ሙሐመድ ቡዓዚዝ፣ ምን ሊያደርግ እንዳሰበ ለቤተሰቦቹ እንኳ ትንፍሽ ሳይል፣ ልክ ከቀኑ 530 ሲሆን ንብረቱን ወደ ተነጠቀበት አደባባይ በማምራት በገዛ ሰውነቱ ላይ ቤንዝን ካርከፈከፈ በኋላ፣ ከአስተዳደሩ ያጣውን ፍትህ የገዛ ነፍሱን በማጣት ‹‹አግኝቷል››

ለሰላማዊው ለፍቶ አዳሪ ሙሐመድ ቡዓዚዝ ሰላማዊ ጥያቄ፣ ፖሊስ የሰጠው ኢ-ምግባራዊ ምላሽና የባለሥልጣናት ቸልተኝነት ያስከተለው ውጤትም፣ ጅማሬውን በሲኢዲ ቡዚድ ያደረገና በኋላም ቀስበቀስ መላውን ቱኒዚያና ከፊል የዓረብ አገራትን ያካለለ ሕዝባዊ አመጽ ነበር፡፡ አመጹ ሥር ሰዶም፣ በተለይም ፌስቡክና ዩቲዩብን በመሳሰሉ ድረገጾች የሱቅ መስኮቶችን በሰባበሩና መኪኖችን ባወደሙ ወጣቶች ላይ ፖሊስ የወሰደውን ኢሰብአዊ ርምጃዎች የሚያሳዩ ምስሎች እንደሰደድ እሳት ተስፋፉ፡፡


የማታ ማታም፣ የሙሐመድ ቡዓዚዝን ነፍስ ለማዳን  በዋና ከተማዋ ቱኒዝ አቅራቢያ በሚገኝ ሆስፒታል ርብርብ ቢደረግም፣ ክፉኛ በመጎዳቱ፣ ታሪቅ ጣይብ ሙሐመድ ቡዓዚዝ ጃንዋሪ 4 2010 (ታህሳስ 26፣ 2002 ዓ.ም.) በተወለደ 26 ዓመቱ፣ እስከመጨረሻው አንቀላፍቷል፡፡

ከህልፈቱ በኋላም የዓረቡ ዓለም ታሪክ ይለወጥ ዘንድ ታላቅ ድርሻ ላበረከቱ ሌሎች አራት ሰዎችን ጨምሮ፣ የሻክሃሮቭን ሽልማት ተሸልሟል፡፡ የቱኒዚያ መንግሥትም ምስሉን በአገሪቱ ቴምብር ላይ በማስፈር ክብር ሲያጎናጽፈው የእንግሊዙ ታይም መጽሔት 2011 የዓመቱ ምርጥ ሰው ብሎታል፡፡

ከጥቃቅን ሹመኞች ዕይታ ውስጥ ያልገባውም የሙሐመድ ቡዓዚዝ ጉዳይም፣ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ዚን ኢል አቢድን ቤን አሊ በትረ መንግሥታቸውን እስከማጣት ድረስ የከበደ፣ ትልቅ ዋጋ እንዲከፍሉ አድርጓቸዋል፡፡

ዛሬ ለማነሳው ነጥብ ይመቸኝ ዘንድ እንደ አብነት የሙሐመድ ቡዓዚዝን ቅንጭብ ታሪክ አነሳሁ እንጂ፣ በዓለማችን፣ በተለይም በአህጉራችን አፍሪቃ፣ ደግሞም በእኛ ኢትዮጵያ በየዘመናቱ የሚፈጠሩትን፣ ሙሐመድ ቡዓዚዚዎችና ፋይዳ ሃምዲን መሰል ተበዳዮችንና በዳዮችን  ዘመንና ታሪክ ሲቆጥሯቸውና ሲያስታውሷቸው ይኖራሉ፡፡

ታዝባችኋል፣ አንዲት እናት በድንገት ምጥ ይዟት፣ አሊያም የሆነ ላገር የሚጠቅም፣ ገና ሮጦ ያልጠገበ ጎረምሳ፣ አንዳች አደጋ ነገር ደርሶበት ወደ አንድ ክሊኒክ አሊያም ሆስፒታል በህክምና ህይወታቸውን ለማትረፍ ሄደው፣ በጊዜው ተረኛው ሐኪም ባለመኖሩ ምክንያት እናቲቱ ምጡ ጠንቶባት፣ ጎረምሳውም ደሙ ፈሶ ለሞት ከተዳረጉ በኋላ፣ ዜጎች፣ ‹‹ አዬ እኛ አገርማ ምን መንግሥት አለ!!›› እያሉ እንባቸውን ወደላይ ሲረጩ? . . .

ታዝባችኋል፣ ዜጎች ለዘመናት ነጭ ላባቸውን አንጠፍጥፈው የሰሩትን ገንዘብ በማጅራት መቺዎች ከተዘረፉ በኋላ፣ ‹‹በገዛ አገራችንኮ ሠርተን መኖር አልቻልንም፣ ንብረታችን የቀማኞች ሲሳይ እየሆነ ለህይወታችን እንኳ እየሰጋን ነው፣ ታዲያ እንዴት ነው የሚቀርጠን መንግሥት ህይወታችን ከተራ የመንደር ሌቦችና ዘራፊዎች ሊታደገን የሚችለው›› ሲሉ? . . .

ታዝባችኋል፣ የሆነ መንደር መብራት ወይም ውኃ በተደጋጋሚ እየተቋረጠ፣ ዜጎች ‹‹አዬ የኛ መንግሥት፣ በጨለማ ስንዋጥና፣ ውኃ ስንጠማ እንኳ የማያውቅ ከንቱ መንግሥት›› ሲሉ ሲንገፈገፉ፣ ሲማረሩ፣ ሲያለቅሱ? . . . (በነገራችን ላይ የሆነ ቦታ በተደጋጋሚ እንዲህ አይነት ሁኔታ ሲከሰት የሌላ ቀበሌ ሰዎች እንዴት ነው እሱ፣ እናንተ ቀበሌ አንድ የዘመኑ ሰው የለም እንዴ . . . ብለው እርስ በርስ ይጠያየቃሉ፣ ምክንያቱም የዘመኑ ሰው ያለበት መንደር ውሃም ሆነ መብራት ተቋርጦ ስለማይሰነብት )

በሐሰተኛ ሰነድ፣ በተጭበረበረ ማስረጃ፣ በገንዘብና ስጦታ በጉቦኛ የፍትህ አካላት ፍትህ ተጣሞባቸው፣ አቤት የሚሉበት አጥተው በራቸውን ዘግተው ስለሚያነቡ ወገኖችስ ምን ያህል ታዝባችኋል?   . . .

ውበቷን በልባቸው ከቋመጡና ተክለሰውነቷን ባይናቸው ከቀላወጡ በኋላ አልጋ ላይ እንዴት ልትሆን እንደምትችል እያሰላሰሉ፣ ብዙ የውኃ ጋሎን የያዘ የእሳት አደጋ መኪና እንኳ ሊያጠፋው የማይችል የወሲብ እሳት አይኖቻቸው ውስጥ እየተንቀለቀለ፣ ያቀረቡላትን የወሲብ ግብዣ አልቀበልም ስላለቻቸው ብቻ ‹‹ቀልቤ አልወደዳትም›› ወይም ‹‹ለስራው የሚሆን የተሟላ መረጃ አላቀረበችም›› አሊያም ‹‹ቆንጆ ሴት ሥራ አይሆንላትም›› በሚል እንቶፈንቶ ምክንያት ብቻ ለሥራ ያስገባችውን ሲቪ የቅርጫት እራት ስለሚያደርጉ ሹመኘኞችስ? . . .  እኔ ለጊዜው የመጣልኝን አልኩ እንጂ ይኼን ጊዜኮ እናንተ የታዘባችሁት በርካታ ከዚህ የከፉ ጉዳዮች አእምሯችሁን አጣበዋል፡፡

አገራችን በየዘመናቱ በእንደዚህ አይነት ጥቃቅንና አነስተኛ የየዘመኑ ሹመኞች ሰለባ ናት፡፡ ታዲያ ብዙ ጊዜ በነዚህ ሰዎች ምክንያት  ትልቁ መንግሥት በዜጎቹ ይሰደባል፣ ይብጠለጠላል፣ ይታማል፣ ይጠላል፣ ሲያልፍም አመጽ፣ ኩዴታና አብዮት ይነሳበታል፡፡


ወላጅ አባቴ በቀዳማዊ ኃይሥላሴ ዘመነ መንግሥት የኖረ እንደመሆኑ፣ ስለዚያ ሥርዓት በጥቂቱም ቢሆን እንዳ ጫወተኝና እኔም ከተለያዩ ጽሑፎች እንዳነበብኩት፣ ለሥርዓተ መንግሥቱ መጠላት ምክንያት የጥቃቅን ሹመኞች ድርሻ ከፍተኛ ነበር፡፡ ጥቃቅን ሹመኞች ዜጋውን ረግጠውና አፍነው ገዝተውት ነበር፡፡ ባላባቶች ጪሰኛና ገባር እያሉ፣ ደሃውን አንበርክከውት ባርያ አድርገውት ነበር፡፡ እላይ ዙፋን ላይ የተቀመጡት አካላት ይህን አያውቁም ነበር ማለት ባይቻልም፣ ከእነርሱ እውቅና ውጪም ሆነ እያወቁ ዜጋው ብዙ እንግልትና ግፍ እንደደረሰበት የታሪክ ተመራማሪዎች ይናገራሉ፡፡

በደርግ ዘመነ መንግሥትም ምንም እንኳ ከፍተኛ የሆነ የፈላጭ ቆራጭነት ሥልጣን በደርጉ እጅ የነበረ ቢሆንም በከፍተኛ ሁኔታ ዜጎችን ሲያስሩና ሲገድሉ የነበሩት ፊደል እንኳ ያልቆጠሩ አብዮት ጠባቂ ተብዬ እንደነበሩ የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ፡፡

ለመሆኑ ጥቃቅንና አነስተኛ ሹመኞች ክቡር የሰው ነፍስን ያህል ነገር እስከማጥፋት እንዴት የልብ ልብ አገኙ ብለን ስንጠይቅም ሩቅ ሳንሄድ መልሱን እናገኘዋለን፡፡ ምክንያቱም መንግሥታዊ ሥርዓቱ ወይም ‹‹ሲስተሙ›› የተገነባበት መሠረት ዜጎችን ያላማከለና ፍትህን ያላነገበ፣  ብልሹና ዝርክርክ መሠረት በመሆኑ ነው፡፡ የዜጎቹን ህልውና ያላስቀደመ መንግሥታዊ ሥርዓት፣ ጉድጓድና እንቅፋት በበዛበት ጨለማ ውስጥ እንደሚሄድ ሰው ዓይነት ይመስለኛል፡፡

እንደ ቱኒዚያዊቷ ፋይዳ ሃምዲ አይነት ምግባረ ብልሹ ጥቂት ሰዎች፣ እንደ እርሾ መንግሥታዊ ስርአትን የሚያህል ትልቅ ነገር የማቡካትና የማኮምጠጥ ብቃት አላቸው፡፡ እንደ ፋይዳ ሃምዲ አይነት ጥቃቅንና አነስተኛ ሹመኞች፣ እንደ ብቃታቸው ግብራቸውም እንደዚያ ነው፡፡ ጥቂት ነገር ፈልገውብህ ስላላገኙብህ ብቻ የቋመጥክለትን ትልቁን ነገር ያሽቀነጥሩብሀል፡፡

ለምሳሌ ለዘመናት የማሰንክለትና የለፋህበት የውጪ አገር የትምህርት ስኮላርሺፕ ይቀናህና ለኤምበሲ አስፈላጊ የሆነው የቀበሌ መታወቂያህን ታጣዋለህ፣ ትፈልገዋለህ፣ ታስፈልገዋለህ፣ ግና የት እንዳስቀመጥከው ስታጣው የስኮላርሺፑ ጉዳይ ጊዜ ስለማይሰጥህ በቀጥታ ወደቀበሌ ታመራለህ፤ ስትደርስም ከዘበኛው ጀምሮ እስከ ሊቀመንበሩ ያሉ ጥቃቅንና ትናንሽ ባለሥልጣናት ጥያቄያቸውን ይዘው ተሠልፈው ይጠብቁሃል፡፡

ለምሳሌ፣ ዘበኛው ያልተበጠረ ጎፈሬህን ያዩና፣ ‹‹ይሄ ወሮበላ ሳይሆን አይቀርም›› በማለት፣ ከየት እንደመጣህ፣ የት እንደምትኖር፣ አባትህ በየትኛው ዕድር ውስጥ እንዳሉ፣ እናትህ የማንኛው ዕቁብ አሊያም ማህበር ጽዋ እንደሚጠጡ፣ ሊያናዝዙህ  ይችላሉ፡፡ ከቻልህ የጠየቁህን ሁሉ መልሰህላቸው፣ ካልሆነም ለጠጃቸው ጥቂት ነገር አስጨብጠሃቸው እሳቸውን እንደምንም አልፈህ ስትገባ ደግሞ፣ መዝገብ ቤቱ አስር አስር ጊዜ ከጓጎለ ኮቱ ላይ ክምር አቧራ እያራገፈብህ፣ እልፍ ዶሴ ከምሮ፣ ‹‹የዘመኑ ልጆች ስትባሉ አስቸጋሪዎች፣ አሁን ምን ስታረግ መታወቂያህን ጣልከው፣ ይሄኔ ስትራገጥ ይሆናል፣›› እያለ የበኩሉን የዜግነቱን ይወጣብሃል፡፡ ማንነትህን በአሮጌ ማንነቱ ሰንቆ የያዘ ዶሴህ ተገኝቶ፣ ወደ መታወቂያ አዘጋጅ ክፍሉ ስትሄድ ደግሞ፣ እኚያ ሴትዮ፣ . . . መታወቂያ ሚያዘጋጁቱ፣ የሉም፡፡

የት ሄዱ? . . .

ከቀበሌው ማዶ ያለች ወዳጃቸው ቡና ጠርታቸው ሊሆን ይችላል፡፡

በሆድህ እየተራገምህ፣ እየተንቆራጠጥህ ስትጠብቃቸው ምሳ ሰዓት ይደርስና ሴትየዋም ሳይመለሱ በዚያው ወደቤታቸው ይነኩታል፤ አንተም የአርባ ቀን ዕድልህን እያማረርህ ወደቤትህ ትመለሳለህ፡፡

ከሰዓት በኋላ ደግመህ ትመጣለህ፡፡

‹‹ጠዋትኮ መጥቼ በእርስዎ ምክንያት . . .›› ፈገግ እያልክ ጥፋታቸውን ልትነግራቸው ትሞክራለህ፡፡

‹‹ታዲያ ምን ችግር አለው፣ የታገሠ ከሚስቱ ይወልዳል ሲባል አልሰማህም? ታግሰህ አገኘኸኝኮ አይደለም እንዴ?›› የሚል ኮስታራ መልስ ይመልሱልሃል፡፡

መታወቂያውን አዘጋጁልህ፡፡ አንድ ነገርም ቀረ፤ የሊቀመንበሩ ፊርማ፡፡

‹‹ኡዉዉዉ!!! . . .›› አለች ልታስፈርም የሄደችው ልጅ ተመልሳ፣

‹‹ደግሞ ምን ተፈጠረ?››

‹‹ለካ እሳቸው የሉም››

‹‹?››

‹‹ሊቀመንበሩ››

‹‹የት ሄዱ?››

‹‹ስብሰባ››

‹‹ስንት ሰዓት ይጨርሳሉ?››

‹‹እንጃ!!››

በጥቃቅን ሹመኞች፣ ጥቃቅን ምክንያት የቋመጥክለት ስኮላርሺፕ እያማረህ ይቀራል፡፡

በጥቃቅንና አነስተኛ ሹመኞች ምክንያት ፍትህ ይዛባል፣ ፍርድ ይጓደላል፣ ሲያልፍም ክቡር የሰው ህይወት ያልፋል፡፡ በጥቃቅንና አነስተኛ ባለሥልጣናት ምክንያት መንግሥት የህዝቡን ልብ ያጣል፣ የህዝቡን አመኔታ ያጣል፣ የህዝቡን ከበሬታ ያጣል፣ በመጨረሻም ህዝቡን ራሱን ያጣል፡፡ በጥቃቅንና አነስተኛ ባለሥልጣናት ምክንያት ዜጎች ቀያቸውን ጥለው ይሰደዳሉ፣ በሰው አገርም አገር እንደሌለው ባይተዋር ይሆናሉ፡፡ ለብዙዎች ምሁራን ስደትና ሞት፣ እስራትና እንግልት ጥቃቅንና አነስተኛ ባለሥልጣናት የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳሉ፡፡ በጥቃቅንና አነስተኛ ባለሥልጣናት ምክንያት፣ ህዝብ ያለቅሳል፣ ህዝብ ይመረዋል፣ ህዝብ አብዮት ያነሳል፣ ህዝብ ኩዴታ ያነሳል፣ ህዝብ ገዢዎቹን አሽቀንጥሮ ይወረውራል፡፡ የመንግሥታት መውደቅና መነሳት ታሪክ የጥቃቅንና አነስተኛ ሹመኞች ሥውር እጅ ናት፡፡ ይህቺ እጅ ብዙ ጊዜ ከመንግሥት የተሰወረች በመሆኗም፣ ወይም ምን ታመጣለች ተብላ ስለምትናቅ መዘዙ  የገደል ቅራፊ ያህል ነው፡፡



                                                © ዳዊት ወርቁ

                                        ጥር 15 2005
                                           አዲስ አበባ