Thursday, February 21, 2013

መንግሥት የፓትርያርክ ምርጫውን እድል ለ50 ሚሊዮኑ ምእመን ይሰጥ!!

  •       መንግሥት እንደፓርቲ ሹም ራሱ ያስቀምጥበት፤ አለበለዚያም ምእመኑ የፈለገውን እንዲመርጥ ጳጳሳቱን አደብ ያስገዛ!!
  • አሁን በተያዘው መንገድ ሄዶ አንዱ ቢመረጥ፤ መንግሥት የፈገለውን ሾመ መባሉ ወይም በቡድን ዘመቻ የተደረገ ምርጫ መሰኘቱ አይቀርም!!
  • ጳጳሳቱ ወደየ ሀገረ ስብከቶቻቸው ተበትነው ሕዝቡ ራሱ ተወያይቶ ይምረጥ!!
አንዳንዶች የአዲስ አበባውን የፓትርያርክ ምርጫ ከእርቅ በፊት መደረጉን ይቃወማሉ። እንደገና ተመልሰው እነ አቡነ እገሌ ወደምርጫው መግባት አይገባቸውም ነበር ይላሉ። ምርጫውን መቃወም አንድ ነገር ነው። እነ አቡነ እገሌ መመረጥ የለባቸውም ማለት ደግሞ ሌላ ነገር ነው። « በማንኪያ ሲፋጅ፤ ሲቀዘቅዝ በእጅ» የሚባለው ይሄ ነው።  እንኳን ሰው ዝንጀሮም ቢሾም ከምርጫ በፊት እርቅ ይቅደም ባዮችን አይመለከታቸውም። በምርጫው ላይ እነማን ይታጫሉ ብሎ ወደመከራከር ከተገባ የምርጫውን አስፈላጊነት እንዳመኑ ያስቆጥራልና። አለበለዚያም ቀድሞውኑ እርቅ ይቅደም ማለት የተፈለገው ለማምታት ነበር ማለት ነው። በአጭር ቃል ሲነገር እርቅ ይቅደም ባዮች በሀገር ቤት ውስጥ ያለውን ምርጫ ሙሉ በሙሉ ከመቃወም በስተቀር እነማን ይወዳደራሉ ብሎ ሚዛን ላይ ማስቀመጥ የለባችሁም።
በሌላ መልኩ ምርጫ መደረግ አለበት ባዮችን የሚያሳስበው ነገር እስከ አሁን ድረስ ከተደረጉ የፓትርያርክ ምርጫዎች ይኽኛው የከፋ ገጽታን የማስተናገዱ ጉዳይ ነው። የአቡነ ሳሙኤል ቡድን በአንድ በኩል፤ የአቡነ ጢሞቴዎስና የመሐመድ ሚስት በሌላ በኩል፤ የማኅበረ ቅዱሳን ቡድን በሦስተኛ ረድፍ፤ የወሎ ማኅበር በዐራተኛ ሰልፍ፤ እንዲሁም ሌሎች በጥቃቅንና አነስተኛ የተደራጁ ቡድኖች ያቺን አንድ ወንበር ለማግኘት ወጥረው ይዘዋል። ገንዘብ ይረጫል፤ ጦርና የጦር ወሬ ይሰበቃል፤ አፋኝና ስለላ ይዋቀራል። ባሎቻቸውን የማስለቀስ የዳበረ ልምድ ያላቸው መበለቶች ቤተ ክህነቱንም ለማስለቀስ ቤት ሽያጭ ድረስ ፉከራ ማሰማታቸው ቤተ ክህነቱ ወደሞት እያዘገመ መሄዱን እንጂ ታታሪ ሰዎች መሰለፋቸውን አያሳይም።
ሐራ ተዋሕዶ እንደዘገበው «በስመ ደኅንነት ያጭበረበሩ 40 ግለሰቦች ምርመራ እየተካሄደባቸው ነው፤ እነንቡረ እድ ኤልያስ የመራጮች ዝርዝር እንዲሰጣቸው ጫና እየፈጠሩ ነው። ለስድስተኛው ፓትርያሪክ ምርጫ እየተደረገ በሚገኘው ቅድመ ዝግጅት፣ የየራሳቸውንምርጥይዘው የቡድን እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ያሉ አካላትን ያስተባብራሉ ለተባሉ ሦስት ሊቃነ ጳጳሳት መንግሥት ጥብቅ ማስጠንቀቂያ መስጠቱ ተሰማ፡፡ ማስጠንቀቂያው የተሰጣቸው ሦስቱ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት÷ የአስመራጭ ኮሚቴው ሰብሳቢ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ እና የምሥራቅ እና ምዕራብ ሐረርጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አብርሃም ናቸው፡፡ በማለት አስንብቦናል።
እንግዲህ ቀደም ሲል እንደቆየው ሁሉ ዛሬ ሁከቱና እሳቱ ተባብሶ ቤተ ክህነት ግቢ እየነደደ ለመሆኑ ማሳያ ነው።ጥንቱንም ቢሆን የቡድን ዘመቻ  እጅ ያልተለየው ቤተ ክህነት፤ ከምርጫ ቦርድ እውቅና በሌለው የጳጳሳት ፓርቲ እየታመሰ መገኘቱ አስገራሚም፤ አሳዛኝም ነው።  ጥቅመኞችና ሥልጣን ፈላጊዎች አባ ሳሙኤልን ይላሉ። ሌቦችና ማጅራት መቺዎች የቤተ ክህነት ችግር በረጂም ጢም የሚፈታ ይመስል አባ ማትያስን ይላሉ፤ አድባዮችና ወላዋዮች ዘክልዔ ልብ አባ ገብርኤልን ይላሉ። ዘረኞችና ነገር ጠምጣሚዎች አባ ማቴዎስን ይላሉ። መንታ መንገድ ላይ የቆሙ አስመሳዮች ደግሞ አባ ሉቃስ ይሁኑልን ይላሉ። ከሥር ደግሞ ፍልፈሎች፤ አይጦችና ወሮበሎች የየድርሻቸውን ሲጥ ሲጥ ይላሉ። ቤተ ክህነት በእንደዚህ ዓይነት ሰዎች ተከባለች። «ከነማን ጋር እንደምትውል ንገረኝና ማንነትህን ልንገርህ» የሚባለው ለዚህ አይደል? እየታየ ያለው የሰዎቹ ግብር፤ ማንነታቸውን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ መስታወት ነው።
 
ሐራ ተዋሕዶ የመረጃ ምንጩን አያይዞ ባቀረበው ዘገባ እንዲህ ይለናል።
«‹‹አቡነ ማቲያስን ለማስመረጥ ቤቴንም ቢኾን እሸጣለኹ›› የሚሉት / እጅጋየሁ በየነ ለአብነት ያህል÷ ‹‹መንግሥት የሚፈልገው አቡነ ማቲያስን ነው፤ አቡነ ማቲያስን መምረጥ አለባችኹ፤ አቡነ ማቲያስን ካልመረጣችኹ እናስራችኋለን፤ እናባርራችኋለን›› በሚል እየተንቀሳቀሱ ያሉት እነ ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ፣ መጋቤ ካህናቱ ኀይለ ሥላሴ ዘማርያም እና / እጅጋየሁ በየነ ምን እያደረጉ ነው? ቡድናዊና ግላዊ ጥቅም፣ ቂምና ጥላቻ የሚገፋቸው እኒህ ግለሰቦች፣ ለፕትርክና ሊመረጡ ይችላሉ ያሏቸውን ሌሎች ብፁዓን አባቶች ስም በየሚዲያው የማጥፋት ዘመቻ ይዘዋል፤ ሚዲያውም ያለአንዳች ሚዛናዊነት የእነርሱን ክሥ ያስተጋባል (የዛሬው ሰንደቅ ጋዜጣ አንዱ ነው፤ በዛሬው ዕለትም እኚህ ሴትዮ  በአድልዎና በሕገ ወጥ መንገድ ከያዟቸው የቤተ ክህነት ቤቶች መካከል አንዱ የኾነውንና በአራት ኪሎ የሚገኘውን ቀራንዮ የጉዞ ወኪል የከፈቱበትን ቢሮ የሰንደቅ ጋዜጣ ማከፋፈያ አስመስለውት ውለዋል)፡፡ በስመ ደኅንነት የሚንቀሳቀሱ ነገር ግን የጸጥታና ደኅንነት ባልደረቦች የሚመስሉ በርካታ በገንዘብ የተገዙ ግለሰቦች መንበረ ፓትርያሪኩን እንዲያጥለቀልቁ ያደረጉት በቀዳሚነት እነእጅጋየሁ ናቸው፡፡
ሟቹን ፓትርያርክ እንደፈለገች ታሽከረከር ነበር የምትባለው እጅግ ነገር የምትሰራው እጅጋየሁ ዛሬም የምታሽከረክረውን ሰው ለማስቀመጥ እነሆ ትሮጣለች። በእነ እጅጋየሁ ሩጫ የሚሾም ፓትርያርክ «ቢጠሩት አቤት፤ ቢልኩት ወዴት» ከማለት ባሻገር አደብ ግዙ ይላቸዋል ተብሎ አይታሰብም። «ከመቀመጫው ላይ ቁስል ያለበት ውሻ እንደልቡ አይጮህም» እንዲሉ።
ምድራዊ ተአምር ፈጣሪዋ ወይዘሮን ተከትሎ ከጭለማው ቡድን ውስጥ ስሙ የሚነሳው ከዚህ በፊት እንደዘገብንበት የአዲስ አበቤው ካህን «ኑረዲን ኢሊያስ» እያለ በቅጽል ስም የሚጠራው የንቡረእድ ኤልያስ ነገር ነው። ስለእሱም ሐራ ተዋሕዶ ሰውዬውን ገላጭ የሆነ መረጃ ሰጥቶናል።
እነንቡረ እድ ኤልያስ በአዲስ አበባ አራቱ አህጉረ ስብከት፣ በባሕር ዳር፣ በደሴ፣ በሐዋሳ፣ በድሬዳዋ፣ በአሰበ ተፈሪና በጅጅጋ አህጉረ ስብከት ስልክ እየደወሉ ከጠቅላላው መራጭ 600 በላይ የሚኾኑ መራጮችን ስም ዝርዝር አሳውቁን እያሉ ጸሐፊዎችንና ሥራ አስኪያጆችን እያስገደዱና እያስፈራሩ ነው፡፡ በተወሰኑ አህጉረ ስብከትም ሥራ አስኪያጆቹ የካህናት፣ ገዳማትና አድባራት አበ ምኔቶችና እመ ምኔቶች እንዲሁም የምእመናን ተወካዮችን ሰብስበው ድምፅ መስጠት ያለባቸው ለአቡነ ማቲያስ መኾን እንደሚገባው በማሳሰቡ ረገድ ተሳክቶላቸዋል፡፡ ጉዳዩን በተመለከተ የአዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሁለት ጸሐፊዎችና ሥራ አስኪያጆች ለየሊቃነ ጳጳሳቱ ሪፖርት ያደረጉ ሲኾን ሊቃነ ጳጳሳቱ ብፁዕ አቡነ ዳንኤልና ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ለእነ ንቡረ እድ ኤልያስና ለተላላኪዎቻቸው ስመ ደኅንነቶች ጠንከር ካለ ማሳሰቢያ ጋራ ምላሽ መስጠታቸው ታውቋል፡፡
 እስላሞቹ በቀበሌ ውስጥ ምርጫ አድርገው በሰላም አጠናቀዋል። በመስጊድ ይደረግልን ከሚሉ አክራሪዎች በስተቀር።  በተመሳሳይ መልኩ የጳጳሳቱ ፓርቲ  በቤተ ክህነቱ ግቢ ምርጫ ማድረግ አቅቶታል። ማን ተቆጣጣሪ በሌለበት ቦታ ምርጫ የማድረግ ውጤቱ ይህ ነው። የመንግሥትም ስህተት እዚህ ላይ ነው። የጳጳሳቱ ፓርቲ እንደዚህ ዓይነት ህውከት እንዳያመጣ ኦርቶዶክሶች ምእመናን ተሰባስበው በቀበሌ ውስጥ ምርጫቸውን እንዲያደርጉ መደገፍ ነበረበት። ጥቂትና ስልጣን ላይ የተቀመጡ ሰዎች በቡድን የማናውቀውንና የማይወክለንን ሰው መርጠንላችኋል ብለው የብጥብጥና የዐመጽ ጊዜ እንዳናሳልፍ ከፈለገ መንግሥት አብዛኛውን ሕዝብ ሊያዳምጥ ይገባል። አሁን እየታየ ያለውን የቤተ ክህነት ጦርነት አስቁሞ ኦርቶዶክሳዊ ምእመን በተገኘበት የሚፈልገውን ሰው እንዲመርጥ ቀበሌውን ሊሰጠን ይገባል። እስካሁን የተደረጉ ምርጫዎች ሁሉም የሌላ ወገን እጅ የገባባቸውና በመንፈስ ቅዱስ ምርጫ ስም ፈጣሪን ያታለሉበት በመሆኑ ቢያንስ በጉልበቱ፤ በገንዘቡና በሃሳቡ የሚደግፋት ምእመን የፈለገውን እንዲመርጥ እድል ሊያገኝ ይገባል እንላለን። ደግሞም ወንጌል እንዲህ ይላልና።«ወንድሞች ሆይ በመልካም የተመሰከረላቸውን መንፈስ ቅዱስንና ጥበብን የሞላባቸውን ሰባት ሰዎች ከእናንተ ምረጡ» የሐዋ 63 ስለሚል ምርጫው ለሕዝብ መሰጠት አለበት።