ኮሚቴው ከሳምንት በፊት በሰጠው ይፋዊ መግለጫ መሠረት ለፓትርያርክነት እጩ ሆነው የሚቀርቡትን አባቶች
ጥቆማ ከተለያየ አቅጣጫ እየቀረበለት መቆየቱን በማውሳት እግዚአብሔር ለቤተክርስቲያን የሚጠቅማትን መንፈሳዊ አባት እንዲሰጣት የጾምና የጸሎት ጊዜውን አጠናክረን መቀጠል ይገባናል በማለት ለመላው የቤተክርስቲያኒቱ ተከታዮች በመግለጫው ላይ በድጋሚ አበክሮ አሳስቧል።
በወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ዛሬ የካቲት 8/ 2005 ዓ/ም የእጩ ተጠቋሚዎች የመቀበያ ጊዜ ማብቃቱን በመግለጽ ከእንግዲህ የሚቀረው ሥራ ሲኖዶሱ በሰጠው ደንብ ላይ ተመርኩዞ ከየካቲት 9 እስከ 14 2005 ዓ/ም ድረስ ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔ የሚቀርቡ 5 እጩዎችን መመልመል መሆኑን በመግለጫው ላይ አመልክቷል።
ይቀርባሉ ከተባለው ብዙ ተጠቋሚዎች መካከል ውስጥ እንዴትና በምን ስሌት መልምሎ 5ቱን እጩ ተጠቋሚዎች ብቻ እንደሚያቀርብ ኮሚቴው የዘረዘረው ነገር ባይኖርም መርጦ ለሲኖዶስ የማቅረብ ስልጣኑ የኮሚቴው መሆኑን ግን ሳይገልጽ አላለፈም።
የኮሚቴውን የምልምላ ስልት ያሟላሉ የተባሉ 5 እጩዎች ለቅዱስ ሲኖዶስ በማቅረብ ሲኖዶሱ ከየካቲት 16 ጀምሮ በሚያደርገው ጉባዔ ላይ የቀረቡለትን የእጩ ፓትርያርኮች
ዝርዝር በይሁንታ በማጽደቅ፤ የካቲት 18/ 2005 ዓ/ም ለሕዝብ ይፋዊ መግለጫ እንደሚሰጥ ይጠበቃል። ምርጫውም የካቲት 21 ቀን እንደሚደረግና በእለቱ ማምሻው ላይ የድምጽ ብልጫ ያገኘው አባት በይፋ ተገልጾ የካቲት 24/ 2005 ዓ/ም ሥርዓተ ሲመቱ በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እንደሚፈጸም ከዚህ በፊት የተገለጸ መሆኑ ይታወሳል። ብዙ ጊዜ ሲባል እንደቆየው የመንግሥት ጫና አለ የሚባለው ነገር እስካሁን በኮሚቴው ላይ ስለመኖሩ የታወቀ ነገር የለም።
እግዚአብሔር የወደደውንና የፈቀደውን ያድርግ!