ለነ አባ እንቶኔ!!


እመሰ አማን ጽድቀ ትነቡ...


ይድረስ ለነ አባ እንቶኔ፦(geezonline.org)


ሰላም ለክሙእንዳልላችኍ፤ እንደ እኔ ያለ አንድ ምስኪን እንደ እናንተ ላሉ ታላላቆች ከታች ወደላይ ሰላምታ ማቅረብ የማይገባው መስሎ ስለሚታያችኍ፤ ላስቀይማችኍ አልሻምና ይቅርብኝ።ሰላምክሙ ይብጽሐኒብየ እንዳልማጠናችኍም፤ ስንኳን ለሌላ የሚተርፍ ለራሳችኍ የሚበቃ ሰላም እንደሌላችኍ እያየኍ የሌላችኍን ነገር በመለመን እንዳሳቅቃችኍ ኅሊናየ አይፈቅድልኝም። ስለዚህ የሰላምታን ነገር በዚሁ እንለፈው።   

ሰላምታውን በዚሁ ካለፍነው ዘንድ ነገሬን በቀጥታ ልጀምር። ከቅዱሳት መጻሕፍት ትርጓሜ ባገኘኹት ላይ ተመርጉዤ። በሊቃውንት ቋንቋ እንድገልጠው ከፈቀዳችኹልኝ፦ ጳጳሳት አይደላችኍ? ከብሉይ ታሪክ ምሳሌ አምጥቼ ግሥ ልገሥሥላችኍ ነው።

ርግጥ ነው ብዙዎቻችኍ ትርጓሜ መጻሕፍትን በወንበር ተምራችኋል ብየ አላስብም። እውነት ለመናገር ከመካከላችኍ አንዳንዶቹ ተነሹን ከወዳቂ፥ እሚጠብቀውን ከሚላላው፥ በፍቅደት የሚነበበውን በውኅጠት ከሚነበበው በሚገባ ለይታችኍ ማወቃችኍን ስንኳ እጠራጠራለኍ። አዛኜን። ይኹን እንጂ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ እንዲሁም የዐጤ ኀይለ ሥላሴ ስም አጠራራቸው የተመሰገነ ይኹንና አቡኑ አእምሮ፥ ንጉሡ ገንዘብ ኾነው በረድኤተ እግዚአብሔር ያሳተሙትን የዳዊት አንድምታ ከመጽሐፍ መደርደሪያችኍ ፈላልጉና (ድንገት ለነ አቦይ መልእክት ስትፋጠኑ ጊዜ አላደርስ ብሏችኍ እስከዛሬ ያልገዛችኹት ከኾነም፤ ስንኳን አንድ መጽሐፍ አገር ምድሩን የሚገዛ ገንዘብ በየባንክ ቤቱ ስለሞላችኍ ዛሬውኑ ልካችኍ አስገዙና) የምገሥሥላችኍ ግሥ ተስማሚ መኾን አለመኾኑን አረጋግጡ።

የምተኩረው በዳዊት መዝሙር ላይ ነው። 57ኛው። ትርጓሜው የመቃብያንን ታሪክ ያስተርካል። ከታሪኩ አኹን የያዝነውን መዝሙር ለመረዳት የሚያሻው ክፍል፦ ስምዖን፥ እልፍሞስ፥ መባልስ የተባሉ ሦስት ንኡሳን ካህናት ለሹመት ሲሉ እስራኤልን የአሕዛብ ንጉሥ አንጥያኮስ እጅ እንዲያደርጋት መምከራቸውን፤ እሱ ስንኳአኹን የተናገራችኹትን ነገር ሳላስበው ውየ ዐድሬ አላውቅም። ነገር ግን እስራኤል ሰዎቹ ጽኑዓን ናቸው፤ አምባቸውም ጽኑ ነው ሲሉ እሰማለኍ። ፈጣሪኣቸውም ይረዳቸዋልና መቅረቴ ስለዚህ ነው እንጂ።ቢላቸው፤እኛ ባወቅነ እናስገባኻለን። አንተም አመንኍ ብለኽ ዐዋጅ ነግረኽ ምስዋዕተ እሪያውን በዃላ በዃላ እያስጎተትኽ ላሙን በጉን በፊት በፊት እያስነዳኽ ብለው መክረውት ኺደው የከተማዋን ቅጥርክፈቱልንያሏቸውን ይመለከታል። በዚህም ምክንያት "ፈጣሪየ የሃይማኖት አብነት ቢያደርገኝ የክህደት፥ የጥብዓት አብነት ቢያደርገኝ የፍርሃት፥ የበጎ አብነት ቢያደርገኝ የክፋት አብነት እኾናለኹን? አይኾንም" ያለው እውነተኛ ካህን አልዓዛር ሰባት ልጆቹ በሰይፍ ሲመቱ ሚስቱም በጡትና በጡቷ መኻል በኩላብ ተሰቅላ በሰይፍ ተቀልታለች። እሱም ይኽን ኹሉ እያየ ስንኳ ከጽናቱ የማይመለስ በመኾኑ በሰም የተጠማ የጋለ ብረት ምጣድ በራሱ ላይ ተደፍቶበት ተንጠቅጥቆ ሙቷል። በዚያኑ ጊዜ ከእስራኤል አራት ዕልፍ ዐብረው ዐልቀዋል፤ አራት ዕልፍ ተማርከዋል፤ አራቱን ዕልፍ ይሁዳ መቅብዩ እየተዋጋ ይዟቸው ወጥቷል። ስለዚህ በዚያን ጊዜ በሃይማኖታቸው የጸኑት ባባታቸው በመቃቢስ መቃብያን ተብለዋል። ዕጉሣን በስደት ጽኑዓን በምግባር ወበሃይማኖት ማለት ነው።


መዝሙር 57 በርእሱ በእንተ መቃብያንይላል። መንፈስ ቅዱስ፦ ዳዊት በመቃብያን ተገብቶ እንዲናገር ያደረገው፤ ስለመቃብያን ያናገረው የትንቢት ቃል ስለኾነ። ስለዚህም መተርጉማኑ በትንቢት መልክ የተነገርውን መዝሙር ዃላ በመቃብያን ከተፈጸመው ታሪክ ጋራ አስማምተው እንዲህ ይተረጉሙልናል፦ እመሰ አማን ጽድቀ  ትነቡ፤
ሦስቱ ካህናት (ስምዖን፥ አልፍሞስ፥ መባልስ) ከጽርእ ወጥተውክፈቱልንአሉ።እስካኹን ወዴት ኼዳችኍ ኖራችዃልአሏቸው።እናንተ ሥጋዊ ሹመትን ብትከለክሉን እኛ በደለኛ ለእግዚአብሔር ይካስ ብለን ጽርእ ወርደን አንጥያኮስን ያኽል ንጉሥ በሃይማኖት ወልደን በምግባር አሳድገን መጣንአሏቸው። ነገራችኍ እውነት አይኾንም (አይመስልም) እንጂ፤ እውነትስ ተናግራችኍ እንደኾነ፤ ማለት፦ እንዲህስ አድርጋችኍ እንደኾነ፤

ወርትዐ ትኴንኑ ደቂቀ እጓለመሕያው።

የሰውን ልጆች በውነት በሚገባ ትገዛላችኍ

እስመ በልብክሙ ኀጢአተ ትገብሩ በዲበ ምድር።

ነገር ግን በልባችኍ ዐስባችኍ በዚህ ዓለም ዕዳ የሚኾንባችኹን ሥራ ትሠራላችኹና በዚህ ምክንያት ይቀርባችዃል እንጂ።

ወጽልሑተ ይጸፍራ እደዊክሙ።

የተፈተለ ከኹለት የተታታ ከሦስትእንዲሉ፤ ከተፈተለ የተታታ እንዲጸና፤ እደ ልቡናችኍ ክዳትን ተንኮልን አጽንቷልና፤ በዚህ ምክንያት ይቀርባችዃል እንጂ፤ እንዲህስ ካደረጋችኍ የሰውን ልጆች በውነት በሚገባ ትገዛላችኍ። የሰው ልጆች እናንተም በውነት በሚገባ ለእግዚአብሔር ትገዛላችኍ።

ተነክሩ ኀጥኣን እምማሕፀን

ሦስቱ ካህናት ከሕግ ወጡ

እምከርሥ ስሕቱ ወነበቡ ዐመፃ።

ማሕፀንና ከርሥ አንድ ወገን፦ ከሕግ ወጡ። በልሳነ ሥጋ ሐሰት ተናገሩ።እምነቱ ሳይኖርጽርእ ወርደን አንጥያኮስን ያኽል ንጉሥ በሃይማኖት ወልደን በምግባር አሳድገን መጣንማለታቸውን መናገር ነው።...

ወመዐቶሙኒ ከመ ሕምዘ አርዌ ምድር።

በሰው የሚያመጡት መከራ እንደ እባብ መርዝ ነው።... አንድምበራሳቸው የሚያመጡት መከራ እንደ እባብ መርዝ ነው።

ዘእንበለ ይትዐወቅ ሶክክሙ ሕለተ ኮነ።

ይህ ቍጥቋጦ ምክራችኍ ሳይታወቅ ቀርካሃ ቀርካሃ ያኽል ኾኖ ተገኝ።

ከመ ሕያዋን በመዐቱ ይውኅጠክሙ

አለን አለን ስትሉ፤ በመዐቱ ያጠፋችዃል። አንድምእንደ ዳታንና እንደ አቤሮን ነፍሳችኍ ከሥጋችኍ ሳትለይ ወደመቃብር ያወርዷችዃል

ውጹኣን እምሕግ (ከሕግ የወጣችኍ) እነ አባ እንቶኔ ሆይ፦ ይህ እንዲህ ነው፤ የእናንተም ሕይወት በዚህ ግሥ ቢነገር መሥመር በመሥመር ቃል በቃል የሚስማማ ብዙ ዐተታ ተጎልጕሉ እንደሚወጣ ኾዳችኍ ያውቀዋል። ለጊዜው ዝርዝሩን እናቆየውና፦

ይችን ቤተ ክርስቲያን ለሹመት ስትሉ መንግሥት ነን ብለው ለተቀመጡ ዐላውያን ጽሚተ/በጽሚት (በድብቅ በሹልክታ፥ በጥመት በቸልታ) ልታስረክቡ ተስማምታችኍ ስታበቁ ሕግ አክባሪ ሃይማኖተኛ ለመምሰል ደንብ ቅብርጥሶ እያላችኍ የማደናገሪያ ሽርጉድ ብታበዙ ዋጋ ቢስ መኾኑን ሌላ ማንም ሳይነግራችኍ ራሳችኍ አታውቁትምን? ይልቁንም ዓይናችኍ እያየ በምእመናን ላይ መከራን እንደእባብ መርዝ ማምጣታችኍ አይደለምን? በራሳችኍም ላይ እንጂ። የምእመናን መከራስ እንደመቃብያን ኹሉ ዋጋ ያለበት ነው። የእናንተ ግን

 እናሳ? ከመካከላችኍ "ዮም አመ ሰምአ ቃሎ" (እስከ የካቲት ማርያም፤ ዛሬ የምትባል ዕድሜ ሳለችው) ከዚች ጠማማ መንገድ የሚመለስ የሃይማኖት ዐርበኛ ይኖር ይኾን? ልብ በሉ ጊዜው አጭር ነው። እናንተው አሳጠራችኍታ። ያለዚያ ግንሶበ ይውኅጠክሙ በመዐቱ (አለን አለን ስትሉ ያጠፋችኍ 'ለታ) ይሚቀርላችኍ፦ ሐቅየ ስነን ብቻ ይኾናል!!!
Share this article :

+ የተሰጡ አስተያየቶች + 1 የተሰጡ አስተያየቶች

Anonymous
February 27, 2013 at 5:34 AM

Betam grum yehone meleket newu. Silassie abezeto yibarkachu.

Post a Comment

አስተያየቶች

 
Support : | |
Copyright © 2011. ደጀ ብርሃን dejebirhan - All Rights Reserved

Proudly powered by Blogger