የማኅበረ
ቅዱሳን ቀኝ እጅ የሆነው ዲ/ን ብርሃኑ አድማስ በረጅም ስብከቱ «የተሐድሶዎች መሠረታዊ ስህተቶች» የሚል ስብከት ለታዳሚዎቹ ሲጠርቅ ተመልክተናል።
በመሠረቱ «ተሐድሶ» የሚባል ተቋም የት እንዳለ የሚያውቀው ብርሃኑ ብቻ ሆኖ ስላነሳቸው ነጥቦች ግን ጥቂት ለማለት እንፈልጋለን።
ብርሃኑ
በረጅሙ ስብከት ያነሳቸው ነጥቦች ሲጨመቁ ይህንን ይመስላሉ።
1/ሃይማኖትን
መጠበቅ ግዴታ መሆኑን
2/ ሃይማኖት
የማይታደስ መሆኑን
3/ ስለሃይማኖት
የብርሃኑ አስተምህሮ ትክክል መሆኑን
4/ ስህተትን
በማስተማር ማስተካከል የሚቻል መሆኑን
ያመላከተ
ሆኖ ተገኝቷል። በነዚህ ነጥቦች ላይ ተንተርሰን የምናነሳቸው ነገሮች የሚከተለውን ይመስላሉ።
1/ሃይማኖትን የመጠበቅ ግዴታ፤
በኤፌሶን
4፤4 ላይ አንዲት እምነት በማለት የተገለጸው የጥቅሱ ቃል የትኛውን የእምነት
ክፍል እንደሚወክል ዲ/ን ብርሃኑ አልተናገረም። ምክንያቱም ወንጌሉ «አንዲት እምነት» በማለት በጥቅል ያስቀምጣል እንጂ ይህችኛዋ ነች ብሎ በስም ለይቶ ባለማስቀመጡ ዲ/ን ብርሃኑ ሃይማኖትን ስለመጠበቅ ሲያስተምር «አንዲት እምነት» የሚለውን ቃል ተቀብለናል የሚሉ ሁሉ እኔ ነኝ ህጋዊው የመጽሐፍ ቅዱስ
ተጠሪ ማለታቸው ስለሚታወቅ ሁላችሁም የአንዲት እምነት ተቀባዮች ባላችሁበት ጸንታችሁ ኑሩ የሚል የወል ስብከትን የሚያስተላልፍ ድምጸት የነበረው ዲስኩር ሆኖ ተመዝግቧል።
ስለዚህ
ስለ «ሃይማኖት መጠበቅ» እና የአንዲት እምነትን አስተምህሮ ለማስረጽ የተገባውን ሃይማኖት
ክፍል ምን መምሰል እንዳለበት እንደመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ማብራራት የግድ ይሆንበት ነበር። ከዚያ ባሻገር ስለአንዲት እምነት ጠብቆ መቆየት በክርስትና ዙሪያ የተሰለፉት ሁሉ እኔ ነኝ ለዚያ የተገባሁት የማይል ስለሌለ የዲ/ን ብርህኑ ስብከት ሚዛን የሚደፋ አይሆንም።
የስህተት አስተምህሮዎች ተብለው የሚጠሩትን ሁሉ ባሉበት ጸንተው እንዲቆዩ የኤፌ 4፤4 «የአንዲት እምነት» ጥቅስ በምንም መልኩ እንደጋሻ መጠቀም የሚያስችላቸው ሊሆን አይችልም። አንዲት እምነት የሚል በኤፌሶን መልእክት በመስፈሩ ብቻ ያንን የሚጠቅሱ ሁሉ ማረጋገጫቸው ባለመሆኑ ይህንን የሚሉትን እንዴት ተሳስታችኋል ልንላቸው እንደምንችል? ዲ/ን
ብርሃኑን ስንጠይቅ መልሱ አጓጊ ይሆንብናል።
ስለሆነም ሃይማኖትን ስለመጠበቅ ከማስተማር በፊት የሚጠበቀው ሃይማኖት የእግዚአብሔር ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ የተፈተሸና ከዚያ ጋር ጥላቻና ግጭት የሌለው መሆኑ መመርመር ይኖርበታል። ያለበለዚያ የዲ/ን ብርሃኑ የአንዲት እምነት ስብከት «እኔ ብቻ ትክክል» እንደሚሉት የሁሉ ሃይማኖቶች
መፈክርን እርሱም ከኦርቶዶክስ
ወዲያ በማለት ከማስተጋባት የዘለለ አይሆንም። አንድ ክርስቲያን የሚጠብቀው እምነቱ ከእግዚአብሔር
ቃል ጋር ያልተጋጨና ከዚያ ውጪ አለመሆኑን ካላወቀ
ጥበቃው ከንቱ ነው። እስራኤላውያን ከእግዚአብሔር ቃል ጋር ያላቸው ትስስር በወግና በባህል በመሸፈኑ ስለክርስቶስ የተነገሩት ትንቢቶች ሁሉ ተጋርዶባቸው ድኅነት ተሰውሮባቸው ቀርቷል። እነሱ ግን ይናገሩት የነበረው የአብርሃም ልጆችና የአብርሃምን እምነት አጥባቂዎች መሆናቸውን ነው። ስለዚህ በመንፈስ ቅዱስ ጥበብ የተቃኘ የቃሉን እውነት ሳንሸራርፍና ሳንሸቃቅጥ እንደቤሪያ ሰዎች እየመረመርን ያለን እምነት
የምናሳድገው እንጂ እኛ በምናደርገው ድርቅና የሚጠበቅ ተንሳፋፊ ጣራና ግድግዳ አይደለም።
ስለዚህ
እምነትን መጠበቅ ማለት በእውቀትና በመንፈስ ማሳደግ ማለት እንጂ በርን ጠርቅሞ አላስገባም አላስወጣም ማለት አይደለም።
1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 2፥2-3ጌታ ቸር መሆኑን ቀምሳችሁ እንደ ሆነ፥ ለመዳን በእርሱ እንድታድጉ አሁን እንደ ተወለዱ ሕፃናት ተንኰል የሌለበትን የቃልን ወተት ተመኙ።
2/ ሃይማኖት የማይታደስ መሆኑን
እምነት
በሰዎች ውስጥ ሰርጾ የሚገለጽ ተግባር እንጂ በደመና ላይ የተቀመጠ ንፋስ አይደለም። የአንዲት እምነት ማንነት እንደተጠበቀ ሆኖ ሰው በሚያምነው ነገር ላይ ለውጥ ያለው ሕይወት፤ ሰላም የሚሰጥ ስብእና፤ ዘላለማዊነት ያለው ተስፋ ውስጡ ካልታደሰ በስተቀር እምነት የሚባለው ነገር በባዶ ነገር ላይ የተንጠለጠለ ነገር እንዴት ሊሆን ይችላል? በሰው ሰውኛነት የሚኖር እምነት ስህተትም ይሁን እውነትነት ስለሚኖረው ይህንን በእውቀትና በብስለት ራሱን ካላደሰ ንጹህና ብልየት የራቀው ማንነት ሊኖረው በፍጹም አይችልም። ስለሚያምኑት ነገር ባላቸው እውቀት እለት እለት በመንፈስ፤ በብስለትና በመረዳት የሚያድጉ ሰዎች ይህ ሕይወት አብሮአቸው ይኖራል። ጳውሎስ እንዲህ ሲል
ኤፌሶን 4፥23 «በአእምሮአችሁም መንፈስ ታደሱ»
በማለት
የተናገረው ሰው ስላለው እምነት እንጂ ስለስጋዊ ልደት ወይም ደመና ላይ ስለተቀመጠ እምነት አይልነበረም። የአእምሮ እድሳት የሌለው ሰው የሚያምነው ነገር አያውቅም። ከላይ ባቀረብነው ሃይማኖትን ስለመጠበቅ ትንታኔ እንደተቀመጠው ማንም ሰው በውርስ ወይም በዘር የተረከበውን እምነት እንደርስት ጉልት ሳይሆን እንደእምነት በአእምሮ መታደስና በመንፈሳዊ ብስለት ካላወቀው በስተቀር «አንዲት እምነት» የሚለው የጥበቃ መፈክር እንደእግዚአብሔር ቃል ስፍራ ሊኖረው አያስችለውም።
ስለዚህ
ሰው የሚያምነውን ነገር ዕለት ዕለት በእግዚአብሔር ቃል እውቀትና መንፈስ ማደስ ግድ ይለዋል። አሁን ያለው «እኔ ብቻ ትክክል» የሚለው ድምጸት ከየእምነቶቹ ጎራ መሰማቱ በሰዎች ውስጥ የሚገለጸው እምነት አይታደስም በሚል ዝግ አመለካከት የተነሳ ነው። ካቶሊኩ ወይም
እስላሙ ወይም ፕሮቴስታንቱ ወዘተ ሁሉ በእውቀትና በመንፈስ ቢታደስ ኖሮ እኔ ብቻ «አንዲት እምነት» በማለት እውነትን ከማወቅ ዘወር ባላለ ነበር። ስለ መታደስ ጥሩና ሰፊ ትምህርት የሰጠውን የዲ/ን አግዛቸው ተፈራን «የለውጥ ያለህ» ድንቅ መጽሐፍ እንዲያነቡ ይመከራሉ።
ወንጌል
እንደሚናገረው የኃጢአት ብልየት/እርግና/ ያገኘው የሰው ልጅ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ባይታደስ ኖሮ እስከነበደሉ በሞተ ነበር።
ቲቶ 3፥5 እንደ ምሕረቱ መጠን ለአዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ አዳነን እንጂ፥ እኛ ስላደረግነው በጽድቅ ስለ ነበረው ሥራ አይደለም፤
መታደስን
እንደጦር የሚፈሩ ሰዎች ለህዳሴው ግድብ ገንዘብ ሲያዋጡ ማየት ያስገርማል። ምድራዊው ነገር እንኳን ከውርደት፤ ከድኅነት፤ ከልመና፤ከረሃብና ከእርዛት የሚያስጥል የሃብት እድሳት ሲያስፈልገው ሰማያዊው ነገርማ እንዴት አብልጦ አያስፈልገው?
በአዲስ
ኪዳን የእግዚአብሔር መቅደሶች፤ ቅጥሮች፤ ግንቦችና ሕንጻዎች ክርስቶስ የሞተላቸው ህዝብና አህዛብ ሁሉ ናቸው። እነዚህ ሁሉ በእምነት ወደሚገኘው ድኅነት በእውቀትና በመንፈስ ካልታደሱ እንዴት ዘላለማዊ ህይወትን ሊያገኙ ይችላሉ?
እስራኤል
ዘሥጋ እንኳን በአንድ ወቅት አምላካቸውን በድለው ከነበረበት ባርነት ወደ ልጅነት ሲመለሱ እንዲህ ብለው ነበር።
እዝ 9፥9 ባሪያዎች ነንና፥ አምላካችን ግን በባርነታችን አልተወንም የሕይወት መታደስን ይሰጠን ዘንድ፥ የአምላካችንንም ቤት እንሠራ ዘንድ፥ የተፈታውንም እንጠግን ዘንድ፥ በይሁዳና በኢየሩሳሌምም ቅጥር ይደረግልን ዘንድ በፋርስ ነገሥታት ፊት ምሕረቱን ሰጠን።
ስለሆነም
መታደስ አስፈላጊና ለሰው ልጆች ሕይወት ጠቃሚ ነገር እንጂ የሚፈራና የማያስፈልግ ነገር አይደለም። እነዲ/ን ብርሃኑና ተከታዮቹ የመታደስን ነገር ከፈጣሪ ጋር ለማያያዝ ይፈልጋሉ። እግዚአብሔር ሰው ቢያምነው፤ ባያምነው፤ ቢቀበለው፤ ባይቀበለው፤ ዘመንና ጊዜ የማይቆጠርለት ድካምና እረፍት የማይጎበኘው ሕያውና ዘላለማዊ ስለሆነ መታደስን ከእሱ ጋር ለማያያዝ መሞከር ጅልነት ይሆናል።
መታደስ
ምን ጊዜም የሚነሳው ድካምና ጉድለት፤ በደልና ኃጢአት ከሚስማማው ከሰው ልጅ ባሕርይ ጋር ነው። ስለዚህ ጳውሎስ እንዳለው ከዚህ ዓለም ሰባኪያንና አታላዮች የምንጠበቀበው በልባችን መታደስ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኘው እምነት ምን እንደሆነ ፈትነን በመያዝና በመለወጥ ብቻ ነው።
ሮሜ 12፥2 የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው ነገር ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ።
3/
የዲ/ን ብርሃኑ ሃይማኖት ትክክል መሆኑን
መጋቤ
ጥበብ ሰሎሞን ዘሀገረ ግሸን የጻፉትን መጽሐፍ በማውሳት ያቀረቧቸውን ፍቺዎች ዲ/ን ብርሃኑ ሲተነትን የኔን አስተምህሮ ሰሎሞን በራሳቸው አባባል ውድቅ ካደረጉ
እኔም የሳቸውን አባባል በኔ
ትርጉም ውድቅ አድርጌአለሁ ሲሉ ተደምጠዋል። ስለዚህ የኔ ምን ጊዜም ትክክል ነው ሲሉ ሥነ አመክንዮ በማቅረብ ለመሞገት ይዳዳቸዋል። በእርግጥም የመጋቤ ጥበብ ሰሎሞን መጽሐፍ ስህተት ሊኖረው ይችል ይሆናል። ይሁን እንጂ ስህተቱትን በማስረጃ ውድቅ ማድረግ ከዲ/ን ብርሃኑ ሊጠበቅ የግድ ነው። ከዚያ ባሻገር «የአንተ ትርጉም ትክክል መሆኑን ስላልተቀበልኩ፤ የኔ ትርጉም ትክክል ነው» የሚል አመክንዮ የትም ሀገር የለም።
አንድ
ሰው በፈጸመው ጥፋት ለፍርድ ቤት የሚሰጠው መልስ ከቀረበበት ክስ ነጻ ሊያደርገው የሚችለውን ጭብጥ ያስይዛል እንጂ «በዓለሙ ሁሉ ስንት ጥፋተኛ ሳለ የኔ እንዲህ ይጋነናል» በሚል ሙግት
ተግባሩን እንደቀላል ለማስቆጠር ቢሞክር ለመናገር ካልሆነ በስተቀር ከቀረበበት ክስ ነጻ ሊያደርገው አይችልም። ስለዚህ ዲ/ን ብርሃኑ የእሳቸውን ትክክለኛነት ለማጽደቅ ማስረጃ ከማቅረብ ይልቅ የመጋቤ ጥበብ አስተምህሮ ትክክል መሆኑን
አልተቀበልኩም ስለዚህ የኔ ትክክል ነው በማለት ሲከራከሩ ሰምተን ታዝበናል።
እኔነትን ለማሳደግ ሁሉነትን መጠቅለል
አያዋጣም። ብዙ አእዋፍ
እንቁላል ጣዮች ናቸው፤ ስለዚህ እንቁላል ጣዮች
አእዋፍ ናቸው የሚል አመክንዮ የእኔ ብቻ ትክክለኛነትን መሆን አያረጋግጥም።
4/
የስህተት አስተምህሮን ማስተካከል የሚቻል ስለመሆኑ
ዲ/ን ብርሃኑ መንፈስ ቅዱስ ጸፍቶ አናግሯቸው ካልሆነ በስተቀር ወይም የስህተት ትምህርት አለ የሚለው ወከባ ሲበዛበት የሚመሩበት ድርጅት ማቅ የአቋም ለውጥ አምጥቶ ካልሆነ በስተቀር የስህተት አስተምህሮ የለም፤ ቢኖርም መነካት የለበትም ይሉ እንደነበር ስናውቅ ይህንን ቃል በመተንፈሳቸው እጅግ ተደንቀናል። ብዙዎቹ ሊቃውንት የተሰደዱት፤የተገፉትና የተደበደቡት የስህተት ትምህርቶች መኖራቸውን፤ ማን እንዳስገባቸው ሳይታወቅ በጥንታዊቷ ቤተክርስቲያን ውስጥ ገብቷል ብለው በመናገራቸውና በማስተማራቸው ብቻ ነበር።
ከአንገት በላይ ፈገግ እያሉ አንገታቸውን ደፍተው የሚኖሩት ሊቃውንት እኰ ከአበው ያልሆነ ስርዋጽ ቤተክርስቲያናችን ውስጥ ነግሷል እያሉ ያለፉና
ያሉ መኖራቸውን እናውቃለን። ሊቁ መምህር መጋቤ ብሉይ ሰይፈ ሥላሴ አናታቸውን በከሳሾች ዱላ ተመትተው ዝም እንዳሉ አለፉ።ሊቁ አባት መርሐ ክርስቶስ ደግመው ደጋግመው ተናግረው ፤ የሚሰማቸው ከመጥፋቱም በላይ አቶዎችና ባለወሸባዎች ጳጳስ እንዳይሆኑ እየጮሁ ፤ የሆኑ ጊዜ ግን የቤተክርስቲያን ሞት እንደቀረበ እየተናገሩ የሚሰማቸው እንዳልተገኘ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው።
አባ
ጳውሎስ እንኳን በአቡነ መርሐ የተሰጣቸውን ምክርና ተግሳጽ ባለመቀበላቸው ጎረምሶቹ እሳት ሲያነዱባቸው «እነሱን መሾም ምነው በቀረብኝ ነበር» እንዳሉ ተሰምቷል።
ከዚህ
አንጻር ሊቃውንቱ በዐረፍተ ዘመን ተወስነው በሞት ጥላ ስር ቢያርፉና የሰው ምንቸት በቀረበት በዚህ ዘመን ላይ ዲ/ን ብርሃኑ የስህተት ትምህርቶች ካሉ እነሱን በትምህርት ማስተካከል ይቻላል ያልከው ተቀባይነት ያለውና ሃሳቡ በራሱ በመቅረቡ የሚመሰገን ነው እንላለን።
ከዚያማ
ውጪ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አስተምህሮ በሐዋርያት፤ በሊቃውንትና በመምህራን አስተምህሮ የበለጸገች፤ የታሪክ፤ የቅርስ፤ የሥነ ፊደል፣ የሥነ ሥዕል ባለቤት መሆኗን እንኳን ወዳጆቿ ጠላቶቿም የሚመሰክሩት የአደባባይ እውነት ነው።
«ሸማ
ይለበሳል በየፈርጁ» ከሚለው ብሂለ አበው ያፈነገጡ የኋላ ሰዎች ከጭለማ መንፈስ ቃል ጋር የእምነት ተዋርሶ አድርገው የራሱን ወደእግር፤ የእግሩን ወደራስ የወሰደው የጠላትን ዓላማ በመፈጸም እምነትን ከባህል፤
ወጉን ከዶግማ፤ ትውፊቱን ከቀኖና፤ ተረትን ከእውነታ፤ ታሪክን ከወንጌል አቀላቅለው፤ ለያዥ
ለገራዥ የሚያስቸግር ውል አልባ ልቃቂት ስላደረጉት እንጂ የሐዋርያቱና የሊቃውንቱማ ትምህርት ምን ወጥቶለት? እነ አባ እስጢፋኖስ ዘገዳመ ቆየጻ ቆዳቸው ተገፎ፤ አፍንጫቸው ተፎንኖ፤ ጆሮአቸው ተቆርጦ፤ እስከነሕይወታቸው ከጉድጓድ ተቀብረው ከብት በላያቸው ላይ የተነዳባቸው ትምህርተ አበው ይጽና ባሉ አይደለምን?
ዲ/ን ብርሃኑ የስህተት ትምህርት ካለ በአስተምህሮ ማስተካከል ጥሩ መሆኑን ብትገልጽም እንደፖለቲካ ፍጆታ ለመነገድ ካልሆነ በስተቀር አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ የት? እንዴት? ማን? ምንና የት? የሚሉትን አጠይቆ የሚመልስ ስላይደለ ሃሳብህ ቅቡል ቢሆንም ተግባራዊ መሆን ስለመቻሉ የሚታይ ነገር ምንም የለውም። ዓውደ ምሕረት ላይ አንተ ያልከውን ለይቶ ማስተማር የሚችል ዛሬ ማነው?
ይህንን
ያህል ትልቅ ቁም ነገር ዝንጀሮ የዋለበት ክምር እንዳታስመስለው እንጂ የስህተት ትምህርት አለ የሚለው ወገን ማንና እንዴት?፤ ስህተት የተባሉት ትምህርቶች ይዘትና ጭብጥ፤ እነዚህ የሚደገፉበት የአበው ትምህርት አስረጂዎች፤ ጉዳዩን የሚመለከቱ የበሰሉ ሰዎች ጉባዔ፤ የሚደረጉ ውይይቶችና የመፍሄ አቅጣጫዎች፤ የመጨረሻ ውሳኔና እርምጃ ወዘተ ያጠቃለለ ቢኖር ኖሮማ በስማ በለው በወንድሞች ከሳሽ ማኅበር ነገሩ ሁሉ የማይጨበ አሎሎ ባልሆነ ነበር። ሁሉም ነገር
ተንከባሎ እዚያው ከመሆን ያልወጣው ለዚህ ይመስለናል። ከዚያ ውጪ የሚያስተምር ቢኖር በዱላ የጀመራችሁትን በዱላ ከምትጨርሱት በስተቀር ሃሳብህ ከጥሩ የጉም ሃሳብነት ባለፈ በምድር ላይ የሚጨበጥ አይደለም።