Tuesday, June 19, 2012

«አዎ! ዛሬም ሰዎች የእምነት ነጻነታቸው ይታፈናል!»


    የዛሬን አያድርገውና አፄ ሱስንዮስ ኮትልከዋል/ካቶሊክ ሆነዋል/ በሚል የምታ ነጋሪት፤ ክተት ሠራዊት ዘመቻ የጎንደር አደባባይ  በደም መጨቅየቱን፤ ሰማዕትነት አያምልጥህ በሚል  ጥሪ በአንድ ቀን ብቻ ከስምንት ሺህ ሰዎች በላይ ማለቃቸውን  ከተዘገበው አንብበናል። አፄ ሱስንዮስም ካቶሊክ ከመሆናቸው የተነሳ እግዚአብሔር ተቆጥቶ ምላሳቸው አንድ ክንድ ያህል ተጎልጉሎና ወደ ቀደመ መጠኑ አልመለስ ብሎ ካስቸገረ በኋላ እያጓጎሩ እንደሞቱ በጽሁፍም፤ በአደባባይም እስከዛሬ ይተረካል። የያኔው ካቶሊክና የዛሬው የኢትዮጵያ ካቶሊክ በእግዚአብሔር ዘንድ ያላቸው ቅጣት ይለያይ እንደሆነ የአፄውን የትረካ ታሪክ ፈጣሪዎችን  እየጠየቅን፤ እኛ ግን እስከሚገባን ድረስ  ሱስንዮስ ካቶሊክ ለመሆን እምነቱን ስለለወጠ  እግዚአብሔር ምላሱን አንድ ክንድ ጎልጉሎ ገደለው የሚለው  ታሪክ የፈጠራ ውጤትና ካቶሊክነት  ከተቀበልክ ምላስህ እየተጎለጎለ ትሞታለህ የሚል  ሽብር በህዝቡ ውስጥ ለመርጨት ረበናት የፈጠሩት ተንኮል እንጂ  ዛሬ በኢትዮጵያ ያሉ ካቶሊኮች ሁሉ ምላሳቸው እየተጎለጎለ በየሜዳው ሞተው ባለቁ ነበር።  እየጨመሩ እንጂ እየጠፉ መሆናቸውን አላየንም።

የሚያሳዝነው ነገር እግዚአብሔርን  ጨካኝና  ርኅራኄ የለሽ አድርጎ በመሳል ይኼው ተረት እስከ ዛሬ በአደባባይ እየተነገረ መገኘቱ ነው።  ሰዎች የእውነትን ወንጌል በተከታዮቻቸው መካከል በማዳረስ ከእምነታቸው ሳይናወጡ፤ ጸንተው ከአምላካቸው ጋር ያላቸው ግንኙነት የጠበቀ እንዲሆን ማድረግ ሲያቅታቸውና ሌላ ተገዳዳሪ እምነት ብቅ ብሎ ቀዬና መንደሩን ሰፈርና ሀገሩን በትምህርቱ ሲበጠብጠው፤  ወዮልህ! ኮንትሮባንድ ሃይማኖት መጣልህ፤ ከእነሱ አዳራሽ ከገባህ አትመለስም፤ ምናምን ያቀምሱሃል! ወደሚል የጭራቅ ሊበላህ ነው ማስፈራሪያ ጩኸታቸው ይገባሉ። ወንጌሉን በሰዎች ልቡና ዘርተው መልካም ፍሬ ማፍራት ሲሳናቸው ከማስፈራሪያው ባሻገር መጤ የተባሉትን ቤተ እምነቶች ወደማፍረስና አማኞቹንም ወደ መግደል ይወርዳሉ። ዛሬ ወንጌላውያን የሚባሉት ኢትዮጵያውያን ቤተ እምነቶች አሁን ላሉበት ደረጃ የደረሱት ተገድለው፤ ተሰደው፤ ታስረው፤ ተገርፈው፤ ተቃጥለው ስለመሆኑ ማንም ኅሊና ያለው ሰው የሚዘነጋው ነገር አይደለም። 

ቤተ እምነቶቹ  የትንቢቱ መፈጸሚያ እምነቶች ይሁኑ ወይም እውነተኞች  ፍርዱን ለእግዚአብሔር ሰጥቶ፤  ሰው የራሱን የቤት ሥራ አጥብቆ በመሥራት እውነት የሆነውን ወንጌል ለተከታዮቹ መመገብ ሲገባው፤ እምነትህን ከለወጥክ ምላስህ ተጎልጉሎ ትሞታለህ! የሚያክለፈልፍ ነገር ትቀምሳለህ! የሚል ማስፈራሪቾ  በምንም መለኪያ እግዚአብሔር የሚደሰትበት የሃይማኖት መጠበቂያ መንገድ ሊሆን አይችልም።  የሚያሳዝነው ነገር ዛሬም ይኸው ማስፈራሪያ እንደፍካሬ ዳዊት በየዓውደ ምሕረቱ ነጋ ጠባ መደገሙ ነው።
ይሁን እንጂ  ማስፈራሪያን፤ ስድብን፤ ስደትን፤ ድብደባንና ግድያን  እንደ ሃይማኖት መጠበቂያ መሳሪያ አድርገን እንድንጠቀም እግዚአብሔር አንድም ቦታ በመጽሐፍ ቅዱስ አልተናገረም ብቻ ሳይሆን እንዲያውም ሰዎች ነጻ ኅሊና ያላቸውና የፈቀዱትን እንዲያመልኩ አድርጎ የፈጠራቸው እንጂ እንደባትሪ ቻርጅ በተደረገ ነገር ተሞልተው እንዲኖሩ የተሠሩ ቁሶች አለመሆናቸውን ለማስረገጥ  አበው  እንዲህ በማለት በግልጽ ያስቀምጣሉ።

«እሳተ ወማየ አቅረብኩ ለከ፤ ደይ እዴከ ኀበ ዘፈቀድከ»  እሳትና ውሃን አቀረብኩልህ፤ እጅህን ወደፈቀድከው ስደድ»  በማለት  ሰው የነጻ ኅሊና ባለቤት መሆኑን ከፈቃደ እግዚአብሔር አያይዘው ሲያስተምሩ ከወሬ ባለፈ አምኖ የሚተገብር ሰሚ አልተገኘም።
ወንጌሉም በወርኀ መከር  እንክርዳዱና ስንዴው እንዲለይ እንጂ አሁኑኑ የሚጠፋ እንዳልሆነ ሲገልጽ እንዲህ ይለናል።

ተዉአቸው፤ እስከ መከር ጊዜ አብረው ይደጉ፤ በመከር ጊዜም አጫጆችን። እንክርዳዱን አስቀድማችሁ ልቀሙ በእሳትም ለማቃጠል በየነዶው እሰሩ፥ ስንዴውን ግን በጎተራዬ ክተቱ እላለሁ አለ» ማቴ ፲፫፤፴
ለዚህ ጽሁፍ መነሻ የሆነን ርእስ የተገኘው «አንድ አድርገን» ብሎግ  የኢህአዴግን «አዲስ ራእይ» የተሰኘውን የግንቦት ወር እትም መጽሔት ከገመገመበት  ዓምድ  ነው። የኢህአዴግ የፖለቲካ የቤት ሥራ የራሱ ጉዳይ ሆኖ እኛ ግን ሃይማኖትን በተመለከተ ካቀረባቸው ጽንሰ ሃሳቦች ተነስተን ከላይ ወዳቀረብነው መንደርደሪያ እንገባለን።

 የተመዘዘ ዘገባ ቁጥር ፩፤

አንዳንድ ኦርቶዶክስ ክርስትያኖች ሌላው ቀርቶ የተለየ አመለካከት ያላቸው ክርስትያኖችንም ቢሆን የሚከተሉትን እምነት ክርስትና አይደለም ብለው ከማመን አልፈው ፤ እነዚህ የተለየ አመለካከት ያላቸው ዜጎች እምነታቸውን በነጻነት እንዳያራምዱ በተለያየ ሽፋን ማፈን ይከጅላቸዋል፡
ከላይ የቀረበው የአዲስ ራእይ የተመዘዘ ዘገባ  ከኢህአዴግ አንጻር በመቅረቡ ብቻ ጭፍን ጥላቻ ካላደረብን በቀር በምድር ላይ ካለው እውነታ ምንም የተጨመረበትና የተቀነሰበት ነገር የሌለው ሐቅ ነው። ለዚህ ማረጋገጫችን አፄ ሱስንዮስ ካቶሊክ ስለሆኑ ምላሳቸው አንድ ክንድ ተጎልጉሎ ሞቱ የሚለው  ፈጠራና እስከዛሬም ይህ ፈጠራ በጽሁፍና በስብከት ቀጥሎ መገኘቱ ነው። የአፄ ሱስንዮስ ካቶሊክ መሆን የተጠላበትንና የዛሬዎች ካቶሊክ ኢትዮጵያውያን ምላስ እንዳይጎለጎል በእግዚአብሔር የተወደደበትን ምክንያት ተራኪዎቹ በአስረጂ ሊያሳምኑ የግድ ይሆናል። አለበለዚያ «አዲስ ራእይ» መጽሔት እንዳለችው ያኔም ይሁን ዛሬ የሚደረገውን «አንዳንድ ኦርቶዶክስ ክርስትያኖች ሌላው ቀርቶ የተለየ አመለካከት ያላቸው ክርስትያኖችንም ቢሆን የሚከተሉትን እምነት ክርስትና አይደለም ብለው ከማመን አልፈው ፤ እነዚህ የተለየ አመለካከት ያላቸው ዜጎች እምነታቸውን በነጻነት እንዳያራምዱ በተለያየ ሽፋን ማፈን ይከጅላቸዋል»  ያለው ትክክል ስለመሆኑ ማስተባበያ የሌለው እውነት ይሆናል።

   በእምነታቸው ምክንያት ብቻ ከቤተሰባቸው የተባረሩ፤ ከማኅበራዊ ኑሮ የተገለሉ፤ ከጎረቤት እሳት እንዳይጭሩ የተከለከሉ፤ የእንዴት አደርክ ሰላምታ የተነፈጉ፤ የተሰደዱ፤ የተደበደቡ የት የለሌ ናቸው። እውነታው ቢያንቀንም ይህ የሆነና የተደረገ ነገር ስለመሆኑ ሸሽገን ማስቀረት አንችለውም።
 ለምሳሌ ያህል ከእነዚህ አባራሪና አሳዳጅ ትልቁና አንጋፋው ተቋም አንዱ የሆነው፤ እየተምዘገዘገ ወደ አናት ላይ የወጣውና የቤተክርስቲያን ጥላና ከለላ እኔ ነኝ የሚለው የነብዩ የዮናስ የሕልም ቅል /ዮናስ ፬፤፲/ የሆነው ማቅ  ለወጣቱና ባለራእይ ሰባኬ ወንጌል መጋቤ ሐዲስ በጋሻው ደሳለኝ ያዘጋጀለት ድግስ ከአራት ወር በኋላ ቢችል እንደሱስንዮስ ምላሱ ተጎልጉሎ ሞቷል ብሎ ለማስነገር፤ ባይችል ግን ገና ምንም ውሳኔ ሳይተላለፍበት አስቀድሞ እንደሰጠው የሽሙጥ ማእረግ «አቶ» እያለ  በደስታ ስካር በቤተክህነቱ አደባባይ እንደሚንጎማለል ከቀደመው ተግባሩ መረዳት የሚከብደን አይሆንም። አንድ አድርገን ብሎግ የገለጸችው የአዲስ ራእይ ኢህአዴጋዊ መጽሔት «…….በነጻነት እንዳያራምዱ በተለያየ ሽፋን ማፈን ይከጅላቸዋል»  ማለቷም  ትክክል ነው።
አዲስ ራእይ መጽሔት የራሷ ዓላማና ግብ ኖሯት የተዘጋጀች መሆኗ ባይካድም ዓላማዋን ለማሳካትና ለመታመን  እውነታዎችን ለማቅረብ መገደዷ አይጠረጠርም። ከነዚህም ውስጥ  ስለማኅበረ ቅዱሳን የተነገረው ጭብጥ እንዲያው በቸልታ የሚታለፍ አልሆነም።

የተመዘዘ ዘገባ ቁጥር ፪

“በክርስትና ውስጥም በአንድ ወይም በሌላ መልኩ በተለይ ከማህበረ ቅዱሳንም የተወሰኑ ከመሰረታዊ የእምነቱ አስተምህሮ ፈንጠር ያሉ እና በመሰረቱ ጸረ-ህገመንግስት መገለጫ ያላቸው አቋሞች የተላበሱበትና አንዳንድ የእኛ አባላትና አመራሮችም ኢህአዴግነትንም ጸረ ኢህአዴጋዊ አቋሞችን የያዙ ይዘቶችንም የሚያንቀሳቅሱበት ሁኔታ በገሀድ የሚታይ ነው»
ይህም እውነት ቁጥር ሁለት ተደርጎ ተመዝግቧል። አንድ አድርገን ብሎግም ይህንን የአዲስ ራእይ መጽሔትን ዘገባ ስላካፈለን አመስግነናል። ማኅበረ ቅዱሳን በኢህአዴግ ከፍተኛ ሹማምንትና በጸጥታ ኃይሉ አባላት ምልመላ ሌሊትና ቀን እንደሚተጋ፤ በእነዚህም ሰዎች ከለላ ሕጉን ወደ ልቡ መሻት ጠምዝዞ እንደሚጠቀም አሳምረን እናውቃለን። ለዚህም ማሳያ የሚሆነን «ማኅበረ ቅዱሳን ወይስ ማኅበረ ሰይጣን» የሚል መጽሐፍ ያሳተመውን ሰው በህግ አግባብ መክሰስ የልባቸውን መሻት ስለማያረካላቸው፤ በጸጥታ ኃይል አሳፍነው ልቡ እስኪጠፋ ድረስ  እንደጌሾ ያስወቀጡት፤ ማቅ የተባለው ግንባር በመሪዎቹ   በእነባያብል ሙላቱ ፒያሳ ከአንድ ካፌ በስልክ ተጠርቶ እንዴት እንደታፈነ፤ ተበዳዩ  የተናዘዘውን መከራ አንብበን መደመማችን አይዘነጋም። በወቅቱ ነፍሱን ከስጋው ሊለዩ ጦራቸውን በሰበቁበት ወቅት እንዴት አድርጎ ከኢትዮጵያ እንደኮበለለ በቅርብ የምናውቀው እውነት ነው።
ምላሱን አንድ ክንድ ጎልጉለው ራሳቸው ከገደሉ በኋላ በመጽሐፋቸው፤ ማኅበረ ቅዱሳንን ስለዘለፈ ምላሱን እግዚአብሔር ጎለጎለው ብለው ቢጽፉ  «አሜን» እያለ ስሞ የማይሳለም አማኝ አይገኝም ማለት ይህን የዋህ ህዝብ እንዴት እንደሚነዱት አለማወቅ ይሆናል።  ከዚህ አንጻር አዲስ ራእይ መጽሔት ማኅበረ ቅዱሳን ከእምነቱ አስተምህሮ ፈንጠር ያለና በኢህአዴግ አባላቱም እንደሚገለገል መናገሯ በእርግጥም እየሆነ ያለውን ነገር እንጂ ፈጠራ ስላይደለ ዘገባውንና ዘጋቢዎችን በማመስገን እንዳለ እውነት ነው ብለን ተቀብለናል።

የተመዘዘ ዘገባ ቁጥር ፫

«የመንግስት መስሪያ ቤቶች ቢሮዎች ጠረጴዛዎችና ኮምፒዩተሮችና ግድግዳዎች ላይ ህዝብ እንዲያገለግል የተቀመጠ ኃላፊና ሰራተኛ በራሱ እምነት ምስሎች አጨመላልቆ የምናይበት ሁኔታ መንግስትና ሃይማኖትን ለመለየት የተቀመጠውን ድንጋጌ በቀጥታ በመጻረር በመሆኑ መወገዝ መወገድ የሚገባው ነው፡፡ በአንድም በሌላ መንገድ ይህንኑ አደገኛ መንገድ መከተል መደገፍ ነውና፡፡”
ማንም የመሰለውን ነገር የማምለክ መብቱ የተጠበቀ ስለመሆኑ ከሱስንዮስ ምላስ ወዲህ ሌላ ምላስ እስኪጎለጎል የሚጠብቅ የዋህ ይኖራል ተብሎ አይታሰብም። ይህ የ፳፩ኛው ክ/ዘመን እውነታ በሌላ የታሪክ ሂደት እስኪለወጥ ድረስ አምነን ከተቀበልን  በሀገራችን ያሉ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች አገልግሎት ሰጪዎች እንጂ የእምነት ተቋማት እንዳይደሉ እንስማማለን።
ምክንያቱም በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ያሉ ሠራተኞች  የብዙ ቤተ እምነት ሰዎች መገኛ ሆኖ ፤ ሱስንዮሱ፤ መጤው፤ ጴንጤው፤ ቀጥተኛው፤ጠማማው፤መሐመዳዊው፤ ዋቄፈናው፤ እምነት አልባው ሁሉም ስለሚገኝበት ግለሰቦች ይህንን የጋራ ተቋም የግላቸው የእምነት ምስልና ምልክት የማሳያ ሙዚየም የማድረግ መብቱ እንደሌላቸው ማወቅ እንደሚገባቸው ግንዛቤ ይኖረናል። ሃይማኖት ማለት የማይታየውን እግዚአብሔር  እንዳለ አምኖ በልብ መቀበልና እንደቃሉ መኖር ማለት  እንጂ ለሌሎች በምልክትና በምስል እንዴት እንደሚያምኑት በጉራ የሚያስተዋውቁት ምልክት ባለመሆኑ፤ አዲስ ራእይ   «የመንግስት መስሪያ ቤቶች ቢሮዎች ጠረጴዛዎችና ኮምፒዩተሮችና ግድግዳዎች ላይ ህዝብ እንዲያገለግል የተቀመጠ ኃላፊና ሰራተኛ በራሱ እምነት ምስሎች አጨመላልቆ የምናይበት ሁኔታ መንግስትና ሃይማኖትን ለመለየት የተቀመጠውን ድንጋጌ በቀጥታ በመጻረር በመሆኑ መወገዝ መወገድ የሚገባው ነው» ማለቷ በእርግጥም ተገቢ ነው። 

  በስራ ቦታዎች የሚኖሩ የእምነት ሰዎች ሁሉ  «እንትና አድርጎ እኔስ ለምን ይቅርብኝ»  በሚል ራስን የማስተካከል አባዜ  የተነሳ መሥሪያ ቤቶቹን ወደ ሃይማኖቶች የይገባኛል ዓውድ በማስመሰል ሊለውጡ  እንደማይገባ የፖለቲካ ሀተታ ሳይጨመርበት ኅሊና ያለው ማንም ሰው በሰውኛ አስተሳሰብ የሚቀበለው እውነት ነው።  

   እንደዚሁ ሁሉ በየትራንስፖርት አገልግሎቱ ውስጥ  ትራንስፖርቱ ከተሰለፈበት ዓላማ ውጪ መንዙማ ወይም ኢየሱስ ጌታ ነው፤ ወይም ሚካኤል አድነኝ የሚል መዝሙር መስማት የተለመደ ነው።  መሳፈር እንጂ መስማት የማይፈልግ ሰው በግድ የማይፈልገውን እንዲሰማ ይገደዳል።  የእምነት አቋሙን በተሳፋሪው ላይ በግድ ለመጫን የሚፈልግ የሰባኪነት ሳይሆን የሹፍርና ፈቃድ ያለው ሾፌር አድራጎት በየመስሪያ ቤቱ የየእምነታቸውን ዓርማ ለማሳየት ከሚታገሉት ጋር ተመሳሳይ ነው። ሰው እምነቱን በግሉ መፈጸም በሚገባው ቦታ ጊዜና ሁኔታ ውስጥ እንጂ  የሌላውንም መብት ባለማክበር በወል ስፍራ የግል ስሜቱን ሊጭን ተገቢ አይሆንም።  በአንድ ወቅት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ መስጊድም፤ ቤተ ጸሎትም፤ ቤተክርስቲያንም፤ የቀብር ሥፍራም፤ ርስትም መብትም ይሰጠን የሚል ጦረኞች ከየእምነቱ ሰዎች የይገባኛል ጩኸት ሲያሰሙ እንደነበር ይታወቃል። ሰው ልኩንና አቅሙን የማያውቅ ሲሆን መሆን የማይገባውን መሆን ይመኛል።
ይህንን  ድርጊት በየመሥሪያ ቤቱ ፤ በየትራንስፖርቱና  በየትምህርት ተቋሙ ማድረግ ትክክል አይደለም ብሎ ለሚናገር ሰው በጡንቻው ለመፈተን ሸሚዙን የማይሰበስብና  አምላኩን ከጥቃት ለመከላከል የማይታገል ሰው ማግኘት ከባድ ነው። ይህንን ዘገባ ያደረሰን ብሎግ እንኳን «አዲስ ራእይ» መጽሔት «የመንግስት መስሪያ ቤቶች ቢሮዎች ጠረጴዛዎችና ኮምፒዩተሮችና ግድግዳዎች ላይ ህዝብ እንዲያገለግል የተቀመጠ ኃላፊና ሰራተኛ በራሱ እምነት ምስሎች አጨመላልቆ የምናይበት ሁኔታ……..» ከሚለው  ሀረግ ውስጥ «አጨመላልቆ» የምትለው ቃል እንዳሳመመችው ተናግሯል።

የተከበረ ነው የሚለውን ስእልና ምስል በሚያከብርበት የግሉ ሥፍራ አክብሮ ማስመጥ ሳይችል ቀርቶ በጋራ ሥፍራ ላይ አኑሮ የሌላውን የማያምን ሰው አክብሮት አለመጠበቅ ማጨመላለቅ እንጂ ሌላ ምን ሊባል ኖሯል?
ጥቂት ቆይቶ ስእልና ምስል አናመልክም ያሉ ሰዎች ምላሳቸው ተጎልጉሎ ወጣ ብሎ ከግሪካውያንና ከሮማውያን የስእል ጥበብ ጋር ከመጋጨት በፊት አስቀድሞ በተገቢው የአምልኰ ስፍራ ጋር አስቀምጦ ባለቤቱ ራሱ ሊያከብረው ይገባል። 
ማንም ሰው በእግዚአብሔር ይጠበቃል እንጂ እግዚአብሔር በማንም አማኝ ጥንካሬና ብርታት የሚጠበቅ አይደለም። እናምነዋለን የምንለውን እግዚአብሔር፤ ከማን ጥቃት ነው የምንከላከለው? 

ወደድንም ጠላንም ዛሬ የሲሶ መንግሥት ዘመን አይደለም። ሰዎች በሃይማኖታቸው ሰበብ ሊታፈኑ አይችሉም። እኔ ያልኩትን ካልተቀበልክ ምላስህ ይጎለጎላል የሚል የታምራት ገለታ ምትሃት ዛሬ ስፍራ የለውም። እኔ ካቶሊክ ባልሆን ካቶሊክ የሆነውን ሰው ምላስህ ይጎለጎላል ልለው መብት የለኝም። ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን ወዶ ማኅበረ ቅዱሳንን መጥላት መብት ነው። ማኅበረ ቅዱሳን ማኅበር እንጂ ቤተክርስቲያን አይደለምና። እየሆነ ያለው ግን በማን በኩል አልፈህ ነው ኦርቶዶክሳዊ መሆን የምትችለው የሚለው የማኅበረ ቅዱሳን የይለፍ ወረቀት ሰጪነት አሰላለፍ፤ ሰው በሚያምነው እንዳይኖር ከማፈን የተለየ አይደለም። አዎ! ዛሬም ሰዎች በሚያምኑት ነገር እየታፈኑ ነው!!! አዲስ ራእይ ላቀረበው ትንታኔና ለአንድ አድርገን ጽሁፍ ምስጋናችን ይድረስ የምንለው ይህንን ዘገባ ለማቅረብ መረጃውን ስለሰጡን ነው!! ልክ ነው! ዛሬም ሰዎች የእምነት ነጻነታቸው ይታፈናል!!!