Saturday, June 9, 2012

ማኅበረ ቅዱሳን እንዲህም ነበር! በቀሲስ መልአኩ


ካለፈው የቀጠለ.................ክፍል 4
በድንጋይ መስታወቱን አንዴ ሲያደቁት በበሩ የነበረው ታጣቂ (ቦታው የአስተዳደር አዳራሽ ሰለነበር ነው ) ወደ ሰማይ ለመተኮስ ቢሞክርም አልቻለም።  መጨረሻ ላይ ነፍስ አውጭኝ ብሎ ሸሸ።  ከዚያ በኋላ መራኮት ሆነ።  «ዋናው እሱ ነው፤ እርሱን ያዙት!  የሚል ጩኸት ብሰማም የማላውቃቸው ሰዎች መጥተው ስለሸፋፈኑኝ እኔን ለመግደል ለሞከሩት ሰዎች አልሆነላቸውም ነበር።  «ስለ እመ አምላክ ተዉኝ» ከምትለው ነፍሰ ጡር ጀምሮ «እማዬ የት ነሽ»  እያለ እስከሚያለቅሰው ሕጻን ድረስ ታላቅ ጩኸት በአዳራሹ ውስጥ ሞላ።

መግቢያና መውጫውን እነርሱ ስለያዙት በየትም መውጫ አልነበረም። የአካባቢው ጸጥታ ኃይሎች እስኪመጡ ድረስ ሰዎቹ ይዘዉት በመጡት መምቻ ሁሉ መቱት።  ማን  ምን እንደሆነ ለማወቅ ግን አልቻልንም ነበር። በመጨረሻ የጸጥታ ሰዎች በመጡ ወቅት ግን የተወሰነው እነርሱን ጥግ አድርገን ለማምለጥ ቻልን።  ከአካባቢው እየሮጥኩ ስወጣ ታክሲ ስላገኘሁ የማልረሳውን ቃል ተናገርኩ «ከዚህ ቦታ ወደ ፈለግህበት ውሰደኝ» ምንም እንኳን ለጊዜው ለባለ ታክሲው የተናገርኩት ቢሆንም በዚያ ወቅት ግን ለአምላኬም የተናገርኩት ነበር።  «ብቻ ከዚህ ቦታ ወደ ፈልግህበት ውሰደኝ»  ወንድሞቼ በምላቸው የገዛ ወገኖቼ የአንዲት ቤተ ክርስቲያን ልጆች ስንደበደብ ምን ልበል ? ካሳደገችኝ ቤተ ክርስቲያን ሽሚዜ በደም ጨቅይቶ እንደሌባ በገዛ ሀገሬ ወገኔ ፊት ስሸሽ  ምን ልበል ? (ከልለው ባወጡኝ ሰዎች ደም ጭምር ነበር የዳንኩት! እኔ ብቻ ሳልሆን  እነርሱ ለኔ ደሙልኝ ) የደማሁት ቀላል ቢሆንም  በታክሲ የተቻልኝን ያህል ራቅሁ።  የራቅሁት ግን ሕይወቴን በሙሉ ከሰጠሁበትም ቦታ ነበር።
 
ከድሬዳዋ ድብደባ በኋላ ወዲያው ሐረር ነበር የተመለስኩት። በሐረር ሁኔታው ተሰምቶ ስለነበር ሕዝቡ ሁል አንድ ነገር የሆንን መስሎት ነበር።  በሰላም መመለሳችን ደስታ ቢሆንም የእኛን እግር ተከትሎ አንድ አስደንጋጭ ዜና ደረሰ።  ከተደበደቡት መካከል ሦስቱ በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙና በተለይም አንደኛው በኮማ ውስጥ እንዳለ ተነገረን።  ሁላችንም አለቀስን።


 ስለ ወንድሞቻችን፤ ስለ እህቶቻችን ደግሞም በነፍሰ ገዳዮች እጅ ስለወደቀችው ስለ ቤተ ከርስቲያናችን አለቀስን።  በተለይም በኮማ ውስጥ ያለው አዳም የተባለው ወንድማችን መሆኑን ስሰማ በጣም አዘንኩ።  ብዙ ባላውቀውም በድሬዳዋ በነበረኝ ቆይታ አግኝቼው ነበር።  ቤተ ክርስቲያን የሚወድ የአምቦ ልጅ ነበር። ለሀገሩ፤ ለቤተክርስቲያኑ ታላቅ ፍቅር ስላለው የሀገር ልብሱ በባንዲራና በእመቤታችን ሥነ ሥዕል ያጌጠ ነበር።  ያን ኢትዮጵያዊ ነበር አናቱን በድንጋይ እንደእባብ  የቀጠቀጡት።
የአዳምን ሁኔታም የሌሎችንም ነገር ለማጣራት በተለያየ መንገድ ብንሞክርም ስላልተቻለ በጠዋት እንደገና ወደ ድሬዳዋ ለመሄድ ወሰንን።  ጠዋት ወደ ድሬዳዋ ስንሄድ እነዚያ ሃይማኖተ ጽኑ የተዋህዶ ልጆች በለቅሶ ውስጥ ነበሩ። በኮማ ውስጥ የነበረው የሃይማኖተ አበው ተማሪ ኦርቶዶክሳዊው አዳም አርፎ ነበር።  ማኅበረ ቅዱሳን አንድ ንጹህ ኢትዮጵያዊን  በመግደል ገዳይነቱን በአደባባይ አሳየ። አዳም በሰላም ሀገር፤ በሰላም ቁጭ ባለበት የቀበሌ አዳራሽ፤ ማንንም ሳይነካ ባለበት ቦታ መጥተው የቀን ጅቦች በሉት።  የተወሰኑ የመስሪያ ቤት ልጆች  ገንዘብ አዋጥተው አስከሬኑን ወደ አምቦ  ተላከ። እናትና አባቱም በሕይወት የነበረ ልጃቸውን በገዳዮች ተገድሎ ሬሳቸውን ተቀበሉ። ሃይማኖተ አበው፤ እንደቀደሙት አበው ስለሃይማኖቱ በአላውያን ማኅበር ሕይወት ከፈለ።
ከድብደባውና ከመጋፋቱ በላይ እነዚያን ልጆች የወንድማቸው መገደል እጅግ የጎዳቸው ይመስለኛል። በተለይም ገዳዮቹ ራሳቸውን የኦርቶዶክስ ጠባቂ አድርገው ራሳቸውን የሚያዩት የድሮዎቹ  አጠቃላይ ጉባኤዎች የአሁኖቹ ማኅበረ ቅዱሳን ሲሆኑ የበለጠ ጥቃት ተሰማቸው።  ከተደብዳቢዎቹ መካከል አጠቃላይ ጉባኤ 1970ዎቹ ያደረሰውን ድብደባ የሚያውቁ ነበር። ድብደባውንም በዋናነት የመሩት መምህር ብርሃነ ሥላሴ (አሁን አባ ዜና በታላቁ አባት በአቡነ ዜና ምትክ የተሾሙት ) ቀድሞም በልደታ ለፈሰሰው የዲያቆናት ደም ተጠያቂ እንደሆኑ ይነገር ነበር።  የብዙዎቹንም ወጣቶች አእምሮ በጠበጠው።

በተቻለኝ መጠን ልጆቹን አረጋግቼ ወደ ሐረር ከተመለስኩ በኋላ በሐረር አገልግሎቴን እየሰጠሁ ቆይቼ ትምህርት ቤት ስለ ተከፈተ ስዋሰው ብርሃን ተመለስኩ።  ወደ ትምህርት ቤቱ አደባባይ እንደረገጥሁም ቢሮ እንደምፈለግ ስለተነገረኝ።  ወደ ብጹእ አቡነ መርሃ ክርስቶስ ጽሕፈት ቤት በቀጥታ ሄድኩ። ብጹዕነታቸው መስቀል ካሳለሙኝ በኋላ የድሬዳዋውን ነገር እንደሰሙ፤ የኛም የልጅነት ችኮላ እንዳሳዘናቸው አጫወቱኝ።  ነገር ግን ከበላይ ማለትም ከጠቅላይ ቤተክህነት አንድ ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ ከትምህርት ቤቱ እንደታገድኩ ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ትዕዛዝ እንደመጣላቸውና እርሳቸውም ትእዛዙን ከመጸፈም በስተቀር ምንም ማድረግ እንደማይችሉ ነገሩኝ።  ሁኔታው በጣም ገረመኝ።  የተገደልነው እኛ ! የተደበደብነው እኛ!  አሁን ደግሞ የተከሰስነው እኛ ነበርን።  አባታችን ጉዳዩን በትዕግስት እንድይዘውና ቤተክህነት ሄጄ ደጅ እንድጠና መክረውኝና ጸልየውልኝ መስቀላቸውን ተሳልሜ ከቢሮአቸው ወጣሁኝ።

ሁኔታው በስዋሰወ ብርሃን ለነበሩት ደቀመዛሙርት ድንጋጤ የፈጠረ ቢሆንም ለእኔ ግን እንግዳ አልሆነብኝም። ነፍስ ለማጥፋት ወደኋላ ያላሉ አሁን ደግሞ የቤተክህነቱን ባለ ሥልጣናት ጥግ አድርገው እኝህን አባት አባሩ ብለው በያዙ አያሰደንቀኝም ነበር።  ከትምህርት ቤቱ ከተባረርኩ በኋላ እገዳዬን ለማስነሳት የቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ከሆነው አቶ መርስኤ ሐዘን ዘንድ ደጅ መጥናቴን የተያያዝኩት ወዲያው ነበር።  በሦስተኛውም ቀን ወደ እርሳቸው ጽሕፈት ቤት መቅረብ እንደማልችል በጸሐፊያቸው በኩል ተነገረኝ። ቢሆንም ደጅ ጥናቴን ለአንድ ወር አላቋረጥኩም ነበር።  በዚህ ወቅት ያላሰበኩት ነገር ከሌላ አቅጣጫ ተነገረኝ።  ስለጥፋቴ ሳይነገረኝ፤ ሳልጠየቅ፤ ሳልመረመር፤ ጉድለቴ ምን እንደሆነ ሳይታይ፤ እኔን በደጅ ጥናት ሲያጉላሉ ቆይተው ካደግሁባትና የእውቀት ጡቷን ጠብቼ እንጀራዋን በልቼ ለዚህ ከበቃሁባት ቤተ ክርስቲያን መታገዴን የሚናገር ደብዳቤ በየአቅጣጫው ተበተነ።  ደብዳቤው ደግሞ ወጪ የሆነው እኔ ደጅ ከምጠናበት ከጠቅላይ ቤተክህነት ነበር።  በተለይም ከሁሌ አንጀቴን የቆረጠው ለእኔ አጠገባቸው ሆኜ ደጅ ለምጠናው የእገዳዬንም ሆነ የተወገዝኩበትን ደብዳቤ በእጄ ሳይሰጡ ወይም ሳይነግሩኝ አዋሳ ውርደው አባቴ በሚያገለግልበት በአዋሳ መካነ ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ማንበባቸው ነበር።  ውግዘቱ እኔ ያስተማርኩትን የስህተት ትምህርት አይናገርም። ያወገዘኝንም ጉባኤ አይናገርም።  የሚናገረው ከጠቅላይ ቤተ ክህነት መላኩን ነው።  በኋላም እንደሰማሁት ይህን በከፍተኛ ደረጃ ለማስፈጽም ላይ ታች ይል የነበረው በጊዜው በከፍተኛ የቤተክህነት የሥልጣን እርከን ላይ የተመቀጠው የቀድሞው የአጠቃላይ ጉባኤ አስተባባሪ የነበረው ኃይለ ጊዮርጊስ ዳኘ ነበር።
ይህ ውግዘት መላውን አመለካከቴን ብቻ ሳይሆን ከዚያ በኋላ ከቤተክርስቲያኔ ጋር ያለውንም ግንኙነት ለወጠብኝ።  እንደ ልቤ ቤተክህነት ውስጥ ገባ ወጣ ለማለት መፍራት ጀመርኩ።  ያወገዝነው ግቢ ውስጥ ተገኘ ብለው  ቅዱሳን ማኅበር ነኝ የሚለው ነፍሰ በላ ቢያስገድለኝስ ብዬ በመስጋት መቅረብ አልቻልኩም።  በተለይም የተበተነው ደብዳቤ በብዙ መንገድ ስለጎዳኝ ከእኔ ከእውቀት በላይ ልቤን አሸፈተው ::
ከቤተ ክርስቲያን ስታገድ በግል ሕይወቴ ኑሮዬን የምመራበት አንዳች ነገር ስለሌለኝ ለጊዜው ጥግ የሆኑኝ እንደ እኔው ከየሰንበት ትምህርት ቤቱ በማኅበረ ቅዱሳን ከሳሽነት የተበተኑት የጽዋ ማህበራት ነበሩ።  በመጀመሪያ እንዳስተምራቸው የጠየቁኝ ከቅድስት ሥላሴ የተበትኑት የአዲስ አበባ ልጆች ነበሩ።  እነዚህ ልጆች ከሌሎች ለየት የሚያደርጋቸው በውስጣቸው በእድሜ የበሰሉ  ሰዎችም የቤተ ክርስትያን ሰዎችም ነበሩበት።   ከእነርሱ ጋር ሆኜም አልፎ አልፎ ከማኅደረ ስብሃት ልደታ ለማርያም የወጡትን ልጆች አስተምራቸው ነበር። እነርሱ በሚገባ የተደራጁና በተለይም ይመራቸው የነበረው ከፍተኛ የሆነ ባለሥልጣን በመንግስት ድርጅት ውስጥ የነበረው ቤተክርስቲያኑን የሚያፈቅር ሰው ስለሆነ በብዙም ሳይሆን ጥቂቶቹን ከጥፋት ታድጓቸዋል።  እርሱ ይመራቸው የነበሩት እስከ ዛሬ በሃይማኖታቸው ጽንተው አሉ።
ከሐረርም የምሰማው አስደሳች አልነበረም።  ከዚህ በፊት ታሪኩን በሰፊው እንዳነበባችሁት በሐረርም ያሉት በዚያ ሁሉ መከራ የጸኑትን በሐሰት ሰነድ ከቤተክርስቲያን አባረሩዋቸው።  ከቤተክስርስቲያን መባረር ማለት ቀላል አድርገን የምናየው ካለን ምናልባትም በሚገባ የቤተክርስቲያናችንን ታሪክና የቤተክርስቲያን ትምህርት ማስተዋል ያቃተን ብቻ መሆን አለበት።  ቀደምት አበው ከቤተክርስቲያን ልጆቻቸውን በሆነ ባልሆነው እንደሚያባርሩ ታሪክ አልነገረንም። የተሳሳተ ካለ መክረው ዘክረው፤ የሚያስብበት ጊዜ ሰጥተው ነበር። የካደ ካለ ክዷል እናውግዘው ሳይሉ በሊቃውንቱ ደንብ ይህንን ትምህርት ከየት አገኘኸው ብለው ጉባዔ ሰርተው ነበር እምቢ ካለ ከቤተክርስቲያን አንድነት የሚለዩት። ዛሬ ግን ማኅበረ ቅዱሳን ከሶ ካቀረበ በቃ ማባረር ብቻ ነው። ለአንዲት ነፍስ መጥፋት ግድ የሌለው ጠላት የተከለው ማኅበርን ክስ የሚፈጽሙ አባቶች ካሉበት ዘመን መድረሳችን የውድቀታችን ምልክት ነው። ዘጠና ዘጠኙን ነገደ መላእክት ትቶ የአንዱ በግ መጥፋት አሳስቦት አምላክ ስጋ መልበሱን የምናስተምር ሰዎች፤ ዛሬ ግን ሺዎችን በወሬና በስማ በለው ከሳሾች ከቤት ለማስወጣት መጣደፍ ከሰይጣን ካልሆነ ከእግዚአብሔር የተገኘ ሊሆን በፍጹም አይችልም። ከቤተ ክርስትያን ስንባረር የተባረርነው ከአንድ ድርጅት አባልነት አይደለም።  የተባረርነው ጸጋ ከሚገኝበት ሥፍራ ነው።   ጸጋ ነው በሃይማኖት የሚያቆመው።

አንዳንድ ሰዎች ይህን የመከራና የእንግልት ታሪክ ስነግራቸው ለምን አልጸናችሁም ነበር ይሉናል።  ሌላው ቀርቶ የትናንቱ አሳዶጆቼ በቅርቡ በሬድዮ ላይ ለምን እንደ አባቶቹ በመከራም ቢሆን ለምን አልጽናም፤ ለምን ወደቀ ብለውኛል።  ለዚህ ቀጥተኛ መልሴ በመከራዬ ቀን ወደምጸናበት ሥፍራ አላስደርስ አላችሁኝ የሚል ነው።  ያችም ሥፍራ ቤተ ክርስቲያን ናት።  አበው ይህን ስለሚያውቁ ነው ከቤተክርስቲያን መለየትን የመጨረሻ ፍርድ ያደረጉት። ከቤተክርስቲያን ማባረር ከመግደል ጋር  ፍርዱ  እኩል ነው። ገድለው ሲያበቁ ለምን አልጸናም ነበር ማለት ምን ማለት ነው? አሁን ግን እድሜ ለማኅበር ቅዱሳን ከቤተ ክርስቲያን በመለየት በረሃብና በስቃይ እንድሞት የተፈረደብኝ  ቢሆንም በአምላኬ ግን ሕያው ሆኜ ብዙዎቹን ወጣቶች አስተምር ነበር። ከማስተማር ያቆመኝ አልነበረም።

ከተባረርኩበት ጊዜ ጀምሮ ለተወሰነ ጊዜ በሐረር በናዝሬት በደብረ ብርሃን በአዲስ አበባ ተበትነው በነበሩት ወጣቶች ዘንድ በመገኘት መጽሐፍ ቅዱስ ለማስተማር ሞክሬአለሁ። ነገር ግን ጥላ የሌለውና ተገን ያጣ ወጣት ስለነበር ጉዟችንም እንደ ወጣትነታችን ነበር።
በዚያን ጊዜ ከቤተክርስቲያን በማኅበረ ቅዱሳን ከሳሽነት የወጡትና በስተኋላም በአብዛኛው ወደ ፕሮቴስታንቶችና ልዩ ልዩ የስህተት ትምህርቶች የገቡ ወጣቶችን ታሪክ በዝርዝር ለማቅረብ ባልችልም በአጠቃላይ ግን በነበሩባቸው  ችግሮች መካከል ዋናው፤ ግብታዊነት ነበር። እነዚህ ወጣቶች ከቤተ ክርስቲያን ሲባረሩ ከማኅበረ ቅዱሳን ጋር እልህ ውስጥ መግባታቸውን ነው እንጂ ከየት ወደ የት እንደሚሄዱ አያውቁም ነበር።   ሁሉ ወጣት ተጎዳ።  ዛሬ እነዚያ ወጣቶች ማኅበረ ቅዱሳን ባሳረፈባቸው ዱላ ተመትተው በግብታዊነት ተጋዙ።  ለጥቂት ጊዜ ቢንገታገቱም አቅጣጫ የላቸውም ነበር።  በሐረር ያሉት ግሩማን በሆኑ አባቶች ከለላ ስላገኙ የተረፉት ባለፈው ጊዜ በፍርድ ቤት በተፈረደላቸው ፍርድ መሰረት ወደ ቤተ ክርስቲያናቸው ተመልሰዋል።  አብዛኛዎቹ ግን በፍርድ ቤቱ የሰባት ዓመት ሂደት ወቅት አማኑኤል ቤተ ክርስቲያን ብሎ ራሱን ለሰየመው የናዝሬት ፕሮቴስታንት ድርጅት ቅርንጫፍ ሆኑ።
ከናዝሬት ቅድስት ማርያም የወጡት ለተወሰነ ጊዜ በቀበሌ አዳራሽ  ኦርቶዶክሳዊት አስተምሮና ዝማሬን እያቀረቡ መቆየት ችለው ነበር። በኋላ ላይ ጠባቂና ከለላ የሌላቸውን እነዚህን ወጣቶች፤ የደረሰባቸውን ስደትና እንግልት አስታከው፤አሳዳጆችን አምርረው እንዲጠሉ እያደረጉ  ነጣቂዎች አንድ በአንድ ለቀሟቸው። ግማሾቹም አርፈው እቤታቸው ተቀመጡ። ግማሹም ሃይማኖት የሚባል ነገር አያሳየኝ እያለ ወደዓለም ገባ። አውሬው ማኅበር ክርስቶስ የሞተላቸውን ህጻናትና ያልበሰሉ ወጣቶችን ከቤተክርስቲያን ጠራርጎ ለጠላት አሳልፎ በመስጠት ራሱን አሳደገ። ለእነዚህ ምንም የማያውቁ ህጻናትና ወጣቶች መጥፋት እግዚአብሔር አይገደውም ማለት ነው? ቀን ስላልደረሰ እንጂ ደማቸውን ከአሳዳጁ እጅ አንድ ቀን ይፈልጋል።
አንድ ወዳጄ እንዳስቀመጠው ከሁሉ የሚገርመው ግን በወቅቱ የነበሩት የቤተ ክህነት ሰዎች ሥራ ነበር። ቁጥራቸው ከአምስት እስከ ስምንት ሺህ የሚደርሱትን እነዚህ ወጣቶች መክሮ ገሥጾ አስተምሮ በፍቅር በእርጋታ እንደመመለስ ያደርጉት ነገር ቢኖር ኦርቶዶክስ አይደለንም ብላችሁ  ፈርሙልን ብለው አስተዳደሩ ላይ እነዚያን ወጣቶች መክስሳቸው ነበር።  ይህ ሁኔታ ወጣቶቹን ወደ ሌላ አቅጣጫ ለመምራት ያደቡ ለነበሩት በር ከፈተላቸው።  ሰው ራሱ ሳይጠየቅና እኔ ኦርቶዶክስ አይደለሁም ብሎ ሳይናገር ቤተክህነቶቹ ግን እኔ ኦርቶዶክስ አይደለሁም ብለህ ፈርም ይሉ የነበረው የማባረር ነገር እጅግ ሲገርመኝ ይኖራል። ሃይማኖትህ ምንድነው? በኦርቶዶክስ ዶግማና ቀኖና ታምናለህ? ተብሎ ይጠየቃል እንጂ ሰውየውን ወክለው ኦርቶዶክስ ተዋሕዶን ክጃለሁ ብለህ ፈርምልን እንዴት ይባላል? ክርስቶስ፤ ክርስቲያን እንድንሆን አደረገን እንጂ ክርስትናን አንፈልግም እንድንል አልመጣም። ክርስትናን አንፈልግም ብላችሁ ቃል ግቡልኝ የሚለው ሰይጣን ብቻ ነው። እነዚህኞቹ የኛ ቤተክህነቶቹስ የማንን ተልእኰ ለመፈጸም ነው እንደዚያ ይሉ የነበሩት?
-----------------------------ተፈጸመ-----------------------------------------