በፍቅር ለይኩን፡፡
የደጀ ብርሃን ጸሐፊዎች «አህያውን
ፈርቶ ዳውላውን» እንዲሉ እባካችሁ የአባቶችን ገመና እና ኃጢአት እንዲህ ጨዋነት በጎደለው መልኩ በየአደባባዩ እያወጣንና እየዘረዘርን
ከመንፈሳዊነት ሕይወት ውጭ አንሁን ይሄ ዓይነቱ መንገድ መንፈሳዊነቱ ቢቀር ኢትዮጵያዊው ጨዋነትና ባሕል አይፈቅደውም እና እንተወው
ለሚል ጹሑፌ የዛሬ ሁለት ዓመት በጻፍኩት ጹሑፍ ተነስተው አንተ በመንግሥት ተቃዋሚ ድረ ገጾች አቡነ ጳውሎስንና ቤተ ክህነቱን እንዳሻህ
ስታብጠለጥል ቆይተህና በአፍቃሪ ማኅበረ ቅዱሳን ብሎጎች ላይ እንዳሻህ ስትሆን ከርመህ ዛሬ እኛ ያሻነውን ብንል ምነው ቆጨህ በማለት፣
ያሻንን በማለት መብታችን ላይ አትምጣብን በማለት የክርክሩን ጭብጥ ለቀቀውና አይወርዱ አወራረድ ወርደው ከቆየ ጹሑፌ ጥቂት መስመሮችን
ብቻ በመውሰድ የጹሑፌ አጠቃላይ ጭብጥና መንፈስ ምን መሆኑን ለአንባቢያን ሙሉ መረጃ በማይሰጥ መልኩ በዘረኝነትና በጎጠኝነት ሊፈርጁኝ
ደፈሩ፡፡
ደጀ ብርሃኖች ለምን እንዲህ ዓይነቱን
መሰሪ አካሄድ እንድመረጡትም ግራ ገብቶኛል፣ ምላሽ ልሰጣቸው አስቤ ነበር ግን ጽንፈኝነት የሞላበትና ሚዛናዊነት የጎደለው የሚመስለው
አካሄዳቸው ስላልጣመኝ ተውኩት ደግሞም አንባቢያን ለሕይወታቸው የሚተርፍ የወንጌል ትምህርት ፍለጋ በሚቃርሙበት ጊዜያቸው የእኛን
ሙግት እንዲያዳምጡ መጋበዝ ሌላ የባሰ ስህተት እንደሆነ አስበኩና አሳቤን ቀየርኩ፡፡ መቼም ቀውስጦስ የተባሉትን አባት «ቀውስና
ጦስ» ናቸው በማለት ተራ የሆነ የቃላት ስንጠቃ ውስጥ በመግባት የሰውን ሞራልና ሰብእና መንካት እንዴት ሆኖ ለቤተ ክርስቲያን ህልውና
ስንል ነው እንዲህ የጻፍነው የሚለው መከራከሪያ አሳብ በምን መልኩ ሚዛን እንደሚደፋ ኅሊና ያለው ሰው ይፍረደው፡፡
ከዚህ የሚብሰው ደግሞ አባ ሳሙኤልና
ሚጡ ተብሎ የተጻፈው ጹሑፍ እንደዛ ልክ እንደ ዓለማዊ ትረካ ልብን በሚሰቅልና ከአሁን አሁን ምን ይከሰት ይሆን በሚል እስከ አንሶላ
መጋፈፍ ያለውን የጓዳ ምስጢር ለመግለጽ ዳር ዳር ያሉበትና አባ ሳሙኤልና ሚጡ ተለዋውጠውታል የተባለው ለጆሮ የሚቀፍ ንግግርን በዝርዝር
መዘገብ በምን መልኩ መንፈሳዊ ለዛ ያለው ለቤተ ክርስቲያን ህልውና የቆመ ጹሑፍ ሊሆን እንደሚችል አንባቢ ይፍረደው ከማለት ውጭ
ሌላ ምን ማለት ይቻላል፡፡
እስቲ ወደ ዛሬ ቁም ነገር ልለፍ፡፡
በደርግ ዘመነ መንግሥት ዶ/ር ፈቃደ አዘዘ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ስነ ቃልና ባሕሎች ላይ የመስክ መረጃ ለመሰብሰብ ወደ ጎንደር ክ/ሀገር
ተጉዘው ነበር እናም ለዚህ ስራቸው መረጃ እያሰባሰቡ ሳለ ወደ አንዲት የገጠር ከተማ ሲጓዙ የአንዲት ገጠር መንደር ነዋሪ ገበሬዎች
በመንገድ ላይ ሲጓዙ ያገኟቸውና ወዴት እየሄዳችሁ ነው በማለት ሲጠይቋቸው፡- «አያ ደርጉን ልናራግም እየሄድን ነው» በማለት እንደመለሱላቸው
በአንድ ቃለ መጠይቃቸው ሲናገሩ መስማቴ ትዝ ይለኛል፡፡ በወቅቱ በገበሬ ማኅበራት የተደራጁ እነዚህ ገበሬዎች ምን ይሁኑ ምን የማያውቋቸውን
ቡርዦችን፣ ኢዲዩን፣ ፊውዳሎችንና ከዛም ባለፈ የአሜሪካንን ኢምፔሪያሊዝም ለማውገዝና ለማራገም በነጋ ጠባ በግዳጅ በቀበሌ ይገኙ
ነበርና ይኸው በየጊዜው ማለቂያ የሌለው በሚመስል ይውደሙ! ይደምሰሱ! ይጥፉ…! እያሉ ጉሮሮአቸው እስኪሰነጠቅ የሚጮኹትን ጩኸት
ነው «ደርጉን ልናራግም ነው» የምንሄደው ብለው ከተሜውን ዶ/ር ፈቃደንና እኛን ጭምር ፈገግ በሚያሰኝ መልኩ የገለጹት፡፡
በዘመናችን እርስ በርሳቸው የተጠራሩ
የሚመስሉ የሚረግሙ፣ የሚያራግሙና የሚያሳቅሉ ብሎጎችና ጸሐፊዎች እየበዙ ነው፡፡ አውደ ምሕረት አሐዱ ያለውን ማኅበረ ቅዱሳንንና
አባቶችን የማራገም ዘመቻ ውሎ ሳያድር ሌላኛው ደጀ ሰላም ይቀበለዋል ከዛም ደጀ ብርሃን ይሰልሰዋል ሌሎች ከሀገር ውስጥ እስከ አውሮፓና
ሀገረ አሜሪካ ያሉ አስተያየት ሰጪዎችና ጸሐፍት ደግሞ ማኅበረ ቅዱሳን የልቡሳነ ሥጋ ስብስብ የሆነ ማኅበረ ሰይጣን ነው በማለት
ሊረግሙና ሊያራግሙም ሰልፉን ይቀላቀሉታል፣ ጉድ ነው… እናም በዚህ መንገድ የፈረደበት ማኅበረ ቅዱሳን ሲረገም ውሎ ሲረገም ያድራል፡፡
ስለ ማኅበረ ቅዱሳን በጎ አመለካከትና ጥሩ የሚናገሩ አባቶችም ሆኑ ሌሎች ሰዎችም ካሉ ከዚሁ እርግማን የሚያመልጡበት መንገድ በፍጹም
ያለ አይመስልም እናም ወይ ከእኛ ወገን ነህ አለበለዚያ ግን… ፡፡
ዛሬም እነዚህ ብሎጎች ከማኅበረ
ቅዱሳንና ከአንዳንድ አባቶች ውጭ ሌላ ርእሰ ጉዳይ የሌለ እስኪመስል የስድባቸውንና የማራገም ዘመቻቸውን አጠናክረው ቀጥለውበታል፡፡
በዚህ ሰሞን በጻፉትም ጹሑፍም «ማኅበረ ቅዱሳን የሚባል ከዛሬ ሃያ ዓመት በፊት የተፈለፈሉ አንበጣዎች ናቸው…፣ ጥፉ እንላቸዋለን…»
በማለት ሲገልጹ ምንም ዓይነት እፍረትና ድንጋጤ የሚታይባቸው አይመስሉም፡፡ ይሄ ምን ማለት ነው ወገኖች… ጤነኛ አእምሮ ያለው ሰውስ
እንዲህ ብሎ ሊጽፍ ይችላል? ወይስ… እንዴት ነው ነገሩ…፡፡
እነዚህ ነጋ ጠባ ማኅበረ ቅዱሳንን
ሲራገሙ ውለው ሲራገሙ ቢያድሩ የማይሰለቻቸው ግለሰቦችም ሆኑ ማኅበራት ለምን ከማኅበረ ቅዱሳን የተሻለ ነገር ለቤተ ክርስቲያን አለን
የሚሉ ከሆነ ለምን ከሩቅ ቆመው የስድብና የእርግማን አፋቸውን ከሚያላቅቁ ከማኅበረ ቅዱሳንም ሆኑ ከሌሎች የተሻሉ መሆናቸውን በተግባር
ሊገልጹልን አቃታቸው፡፡ እኛም ሆነ ሕዝባችን የራበንና የራበው የፍቅር፣ የሰላምና የእርቅ ወንጌልን የሚሰብኩ እግሮቻቸው በተራሮች
ላይ ያማሩ የተወደደውን የምሥራቹን ቃል የሚያውጁልን በነፍሳቸው የተወራረዱ ቅን የሆኑ አባቶች፣ ወንድሞችና ታማኝ አገልጋዮችን እንጂ
ጥላቻንና እርግማንን የሚሰብኩንማ መች ተቸገርን አውደ ምሕረቱን እንደ ገበያ አጥለቅልቀውታል እኮ፡፡ ለጥላቻው፣ ለመረጋገሙና እርስ
በርስ ለመወጋገዙማ ዓለማውያኑ እስኪበቃን አታክተውን የለ እንዴ… እናም እባካችሁ ጆሮአችንን አታምግሉት… ኅሊናችን አታቆሽሹት…
በፈጠራችሁ…፡፡
እነዚህ ወገኖች የሚሰሙበት ጆሮና
የሚያስተውል ልብ ካላቸው እባካችሁ ስንት የሰውን አእምሮ ሊቀርጽ የሚችል መልካምና ጥሩ መልእክት ልታስተላልፉ የምትችሉበትን ዕድል
እንዴት በእንዲህ ዓይነቱ ተራና በማይረባ ነገር ውስጥ በመዘፈቅ ከሰውነት ክብር ራሳችሁን ታወርዳላቸሁ እናም ወደ ቀናው መንገድ
ተመለሱ የያዛችሁት መንገድ ለማንኛችንም አይበጀንም ልንላቸው እንወዳለን፡፡
እረ ቆም ብለን እንደ ባለ አእምሮ
እናስብ እንጂ ወገን ወዴት ነው እየሄድን ያለነው… እረ ማውራት፣ መጻፍ ካለብን ብዙ ሊያነጋግሩንና ልንወያይባቸው የሚገቡ ስንት
እንቅልፍ የሚነሱን ማኅበራዊና መንፈሳዊ ቀውሶች አሉብን እኮ፡፡ ምናለ ለበጎ ሥራ የሚያነቃቃ፣ ለጸሎት፣ ለትሩፋትና ለመንፈሳዊ ተጋድሎ
የሚያተጋ ነገር ብትጽፉ… እንዴትና እስከ መቼስ በእንቶ ፈንቶና በማይረባ አእርስተ ጉዳይ ጊዜያችንና ጉልበታችንን እንዲህ በከንቱ
እንፈጃለን ወገን…፡፡
ሰላም! ሻሎም!