Sunday, June 3, 2012

ሁለቱን ሃሳቦች ማን ያስማማ?


የሚመራኝ ሳይኖር ይህ እንዴት ይቻለኛል? ………ሕዝቤ እውቀት በማጣት ጠፍተዋል»

አለማወቅ የአእምሮ እውርነት ነው። የአእምሮ እውርነት ደግሞ ከምንም በላይ ይከፋል። ሰው በአእምሮ እውርነት በሽታ ከተጠቃ ሰው ሳይሆን ለማዳ እንስሳ ይሆናል። እግዚአብሔር ደግሞ ሰው ያለውን ጉድለት እንዲሞላ አድርጎ ፈጠረው እንጂ እንደ ለማዳ እንስሳ አንዴ በተሞላለት አእምሮ እድሜውን ሁሉ እንዲኖር አድርጎ አልሰራውም።
ህጻናት ሳለን እንደ ህጻናት እናስባለን፤ እያደግን ስንመጣም ጤነኞች ከሆንን ከእድገታችን ጋር ተመጣጣኝ እውቀት በአእምሮአችን ይሞላል። የቅድሚያውን እውቀት ከቅርብ ወላጅ ከእናታችን እናገኛለን። ከወላጅ አባትና ከአጠቃላይ ቤተሰቦቻችን መረዳቶቻችን ይዳብራሉ። ግንኙነቶቻችን ከቤተሰብ አልፈው ወደ ጎረቤት ሲሻገሩ እንደዚያው እውቀቶቻችንም እየሰፉና እያደጉ ይመጣሉ።
መደበኛም ይሁን መደበኛ ባልሆኑ የእውቀት ተቋማት ስንገባ ደግሞ እውቀታችን ከማለዳዋ ፀሐይ የብርሃን ጸዳል ይበልጥ ሰፍቶ ወጋገኑ ሁሉን እንደሚገልጠው የረፋድ ላይ ብርሃን ሆኖ ለሌላውም መታየት ይጀምራል። እንደዚያ፤ እንደዚያ እያለ ከረፋዱ ወደ ቀትር፤  ከተሲዓት፤ ሰርክና እርበት ድረስ እውቀታችን ከሙላት ወደ ሙላት ይሻጋገራል። ይህ ለሰው እንጂ ለለማዳ እንስሳ የተሰጠ ጸጋ አይደለም። ስለዚህ የሰው ልጅ ክቡር ነው፤ የሚያሰኘው ለማወቅ የተሰራ አእምሮ ስላለው ነው።
 ይሁን እንጂ ሰው ለማወቅ መሪ ያስፈልገዋል። ያለ መሪ ምንም ነው። እግዚአብሔር ሰውን በአርአያውና በአምሳሉ ከመፍጠሩ በፊት የሚኖርበትን ቦታ አስቀድሞ አዘጋጅቶለታል። ለኑሮው ጉድለት ረዳት ሰጥቶታል። በሚኖርበት ሥፍራ ራሱን እንዲያበዛ፤ የሚኖርበትን ቦታ ሁሉ እንዲገዛ አድርጎታል። ይህ ሁሉ የሌለውን እውቀት ምሉዕ ለማድረግ ከእግዚአብሔር የተሰጠው ምሪት መሆኑን ያሳየናል።
ዛሬም እንደዚሁ ነን። ምሪት ያስፈልገናል። በመግቢያችን ላይ እንዳስቀመጥነው ከቤተሰብ፤ ከማኅበረሰብ፤ መደበኛና መደበኛ ካልሆነ የእውቀት ስፍራ ወደእውቀት የሚመራን የሰው ምሪት የግድ ይሆናል ማለት ነው። ለዚህም ይመስላል፤«ሰው ለሰው መድኃኒቱ ነው» የሚባለው።

ከዚህ ጽሁፍ ርእስ አንጻር «የሚመራኝ ሳይኖር እንዴት ይቻለኛል?»  ለማለት ተገቢነቱ በእርግጥም  ትክክል ይሆናል። አዎ! ሰው የሚመራው ሳይኖር አዋቂ ሊሆን አይችልም። ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ እንደ አይሁድ ሕግ በዓል ያከብር ዘንድ ከኢየሩሳሌም ተገኝቶ ሲመለስ በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ እንዲገናኘው ከተላከው ከፊልጶስ ጋር በአንድ ሠረገላ ወደ ጋዛ እየተጓዙ ነበር። ጃንደረባው የኢሳይያስን መጽሐፍ ያነብ ነበር። ፊልጶስም «የምታነበውን ታስተውለዋለህን?» ሲል ጠየቀው። ጃንደረባውም ለማወቅ የሚፈልግ ሰው ነበርና «የሚመራኝ ሳይኖር እንዴት ይቻለኛል?» ሲል መልስ ሰጠ። እግረ መንገዱን ለእኛም ማንበብና ማስተዋል ሁለት የተለያዩ ነገሮች መሆናቸውን እየነገረን ነው። ብዙ ጊዜ ያነበብናቸውን ቶሎ ልንረሳ እንችላለን። ወይም የምናነበው ስለምን እየተናገረ እንደሆነ ላይገለጽልን ይችላል። ይህንንም ጃንደረባው የሚመራኝ ሳይኖር! ብሎ ለመፍትሄ መሻቱን አሳይቷል። ስለዚህ ሰው ምሪት ያስፈልገዋል።
ጃንደረባው ስለሚያነበው የኢሳይያስ መጽሐፍ ከሐዋርያው ፊልጶስ የእውቀት ምሪት ተሰጠው። ስለማን እንደተነገረ፤ ለምን እንደተነገረ ተብራራለት። ስለኢየሱስ ከቃሉ ትርጉም የተነሳ በሰፊው ተሰበከለት። ጃንደረባውም  የነበረው  የእውቀት ጉድለት በሐዋርያው ምሪት ሲሞላ «እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ምንድር ነው?» አለ። ብታምን ይቻልሃል! ሐዋርያው መለሰ። በመንገዳቸው ላይ ካለው ምንጭ ወስዶ አጠመቀው! ይለናል ወንጌሉ። ሲያነቡት አጭርና ለመረዳትም ቀላል ጥቅስ ይመስላል። ግን ከዚያም የዘለለ ትርጉም አለው። ጃንደረባው ኢየሩሳሌም የሄደው በክርስቶስ ሞትና ትንሳዔ መዳን ለዓለም ከተፈጸመ በኋላ ሆኖ እሱ ግን በሞት ጥላ ሥር የነበረችውን አይሁዳዊ ሥርዓት ለመፈጸም ነው። ከእውቀት ማጣት የተነሳ ድካሙ ሁሉ ከንቱ ነበር። ለእውቀቱ ጉድለት መሪ ሲያገኝ  ከሞት ወደሕይወት ተሻገረ።ሰው በሕይወት ዘመኑ ሊያገኝ ከሚገባው እውቀት ሁሉ የከበረ እውቀት ነው ያገኘው። ይህንን እውቀት ያገኘው ግን እንዲያው ዝም ብሎ አይደለም።  ከሞት ወደሕይወት መሻገር የደረሰው «የሚመራኝ ሳይኖር እንዴት ይቻለኛል?» ባለው ቃሉ የተነሳ ነው።
ዛሬም ብዙዎቻችን እናውቃለን ስለምንለው ነገር ማስተዋል የለንም። እውቀታችን ምሉዕ ያልሆነ ያህል ሊሰማን ይችላል። የሚመሩን ሰዎች እውቀትም በእኛ ላይ ተጽእኖ መፍጠሩ አይቀርም። የምናውቀው፤ አውቀው እንደነገሩን ሰዎች የእውቀት መጠን ሊሆን ይችላልና ነው። ይሁን እንጂ እውቀት ሁለ ገብ ነው። የአንድ ወገን ሙሌት ብቻ በቂ አይደለም። የጃንደረባውም ሕይወት የሚያሳየን ያንን ነው። የጃንደረባው የአንድ ወገን የእውቀት ሙሌቱ አይሁዳዊ ሥርዓትን መፈጸምና አይሁዳዊ ንባብን መከተል ብቻ ነበር። ካልተጠበቀና ካልታሰበ ቦታ ሌላ እውቀት ሲመጣለት ጃንደረባው እኔ በቂ እውቀት አለኝ፤ ይህንንም ኦሪታዊ ሥርዓቴን በመፈጸም እተገብራለሁ፤ አንተ ደግሞ ማን ነህ? ብሎ ፊልጶስን ገሸሽ አላደረገም። ስላላስተዋለው ነገር እውቀትን ጠይቋል። እድሜውን ሙሉ ያላገኘውን፤ እንዲያውም ሕይወቱን የለወጠ እውቀት ለመገብየት ችሏል። ይህንን እውቀት እናትና አባቱ ወይም የኦሪት መምህሩም ሳይሰጡት ኖሯል። ቀድሞ አውቆ ቢሆን ኖሮ ባልጠየቀ፤ ጠይቆም ካወቀ በኋላ ባልተጠመቀም ነበር። የጃንደረባውን የሕይወት ታሪክ ከወንጌል ላይ ከመጥቀስ በዘለለ ከሕይወት ልምዱ ልንማር ይገባል። ያለኝ እውቀት ይበቃኛል አይባልም። ጉድለት ሊኖረንና  መስተካከልም የሚገባው ሊሆን ይችላል። አበውም «መጠየቅ፤ ያደርጋል ሊቅ» ይሉ የለ!
መጠየቅ የተሳሳተ ነገር ካለን እንድናርም፤ የተሳሳተ ትምህርት ሲመጣብንም ምን እንደሆነ ለመለየት ያስችለናል።
መንፈሳዊ እውቀት እስክንሞት አያበቃም። ሙሉ ሰው ለመሆን የምንሰራውም ዕለት ዕለት በምናገኘው እውቀት ነው። ያለበለዚያ በማመን ያገኘነውን ድኅነት በቅድስና አገልግሎት፤ ፍጹም  የክርስቶስ ህንጻ ሆነን ወደ መሰራት መሆን ልንደርስ አንችልም።

«ሁላችን የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማወቅ ወደሚገኝ አንድነት፥ ሙሉ ሰውም ወደ መሆን፥ የክርስቶስም ሙላቱ ወደሚሆን ወደ ሙላቱ ልክ እስክንደርስ ድረስ፥ ቅዱሳን አገልግሎትን ለመሥራትና ለክርስቶስ አካል ሕንጻ ፍጹማን ይሆኑ ዘንድ» ኤፌ ፬፤፲፪-፲፫
እንዳለው በማመንና በማወቅ ሙሉ ሰው ወደመሆን ሙላት ለመድረስ ሁል ጊዜም ለእውቀት መትጋት ይገባናል ማለት ነው።
አዋቂዎቻችን እነማን ናቸው?
ለኢትዮጵያዊው ጃንደረባ አዋቂው መምህር ሐዋርያው ፊልጶስ ነበር። እንደዚሁ ሁሉ እኛም በዚህ ዘመን መንፈስ ቅዱስ የሚነጥቃቸው ሐዋርያት የግድ እንዲመጡልን ልንጠብቅ አይገባም። ወንጌል እንደነገረን፤
«እርሱም አንዳንዶቹ ሐዋርያት፥ ሌሎቹም ነቢያት፥ ሌሎቹም ወንጌልን ሰባኪዎች፥ ሌሎቹም እረኞችና አስተማሪዎች እንዲሆኑ ሰጠ» ኤፌ ፬፤፲፩ 
 እግዚአብሔር ለቤተክርስቲያን ሐዋርያትን፤ ነቢያትን፤ ሰባኪያንን፤ አስተማሪዎችንና ጠባቂ እረኞችን ሰጥቷል። እነዚህ ሁሉ በቤተክርስቲያን ውስጥ ያለውን የማወቅ ጉድለት ከእግዚአብሔር ቃል ወስደው በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ያሰፋሉ። «የሚመራኝ ሳይኖር እንዴት ይቻለኛል?» ለሚሉ ሁሉ የእውነትን እውቀት ይመግባሉ። አማኞች በሕይወት መንገድ ላይ ጸንተው እንዲኖሩ ያስችላሉ ማለት ነው። ሕዝቡስ እውቀት ከማጣት የሚጠፋው እንዴት ነው?
 መሪ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ካልተመራ ደግሞ የሚያስተምረው የስህተት ትምህርትና ኃይል የተለየው ስብከትን ነው።ከዚያም በላይ የጎደለውን የማይሞላ፤ የተጣመመውን የማያቃና፤  የታመመውን የማይፈውስ፤ በጎቹን የማይጠብቅና የሰሙትን ሁሉ ከእውቀት ጥማት የማያረካ ደረቅ ወንዝ ይሆናል። ይህ ችግር ባለበት ቦታ ስደትና መኮብለል፤ ብጥብጥ ነግሶ ሰላም ይርቃል።
አሁን በሚታየው ሁኔታ «የሚመራኝ ሳይኖር ማወቅ እንዴት ይቻለኛል?» ሳይሆን «ወደ ማወቅ የሚመራኝ ማን አለ?» ብለን ከምንጠይቅበት ወቅት ላይ ደርሰናል። ምክንያቱም መሪና ተመሪው አንድ ላይ ወደ አለማወቅ ደርሰናልና ነው።
«እግዚኦ መኑ የኀድር ውስተ ጽላሎትከ፤ ወመኑ ያጸልል ውስተ ደብረ መቅደስከ፤
ዘየሐውር በንጹሕ ወይገብር ጽድቀ፤ ወዘይነብብ ጽድቀ በልቡ ፤
ወዘኢጓሕለወ በልሳኑ፤ ወዘኢገብረ እኩየ፤ ዲበ ቢጹ፤
ወዘኢያጽዐለ  አዝማዲሁ፤ ወዘምኑን በቅድሜሁ፤ እኩይ
ዘያከብሮሙ ለፈራህያነ እግዚአብሔር፤ ዘይምሕል ለቢጹ ወኢይሔሱ፤
ወዘኢለቅሐ ወርቆ በርዴ፤ ወዘኢነሥአ  ሕልያነ በላዕለ ንጹሕ፤
ዘይከብር ከመ ዝ፤ ኢትሀወክ ለዓለም።
ትርጉም፤
አቤቱ፥ በድንኳንህ ውስጥ ማን ያድራል? በተቀደሰውም ተራራህ ማን ይኖራል?
በቅንነት የሚሄድ፥ ጽድቅንም የሚያደርግ፥ በልቡም እውነትን የሚናገር።
በአንደበቱ የማይሸነግል፥ በባልንጀራው ላይ ክፋትን የማያደርግ፥ ዘመዶቹንም የማይሰድብ።
ኃጢአተኛ በፊቱ የተናቀ፥ እግዚአብሔርንም የሚፈሩትን የሚያከብር፥ ለባልንጀራው የሚምል የማይከዳም።
ገንዘቡን በአራጣ የማያበድር፥ በንጹሑ ላይ መማለጃን የማይቀበል። እንዲህ የሚያደርግ ለዘላለም አይታወክም።
የዛሬ መንፈሳዊ መሪዎችና ተመሪዎች የእውቀት ማጣት ችግር ከነዚህ ኃጢአቶች የተነሳ ነው። በእግዚአብሔር ድንኳን ያለን እየመሰለን ነገር ግን ቅንነት፤ ጽድቅ፤ እውነት፤ሽንገላ የሌለው አንደበት፤ ከክፋት የራቀ ልብ፤ ቤተሰብን የሚታዘዝ ኅሊና፤ኃጢአትን የሚጠላ ገላ፤የእግዚአብሔርን ሰዎች የሚታዘዝ ፈቃድ፤ ባልንጀራን የማይከዳና የማይዋሽ ሃሳብ ፤ የሰውን ገንዘብ የማይዘርፍ፤ ጉቦ የማይበላ፤ ንጹሁን የማይበድል ሰው፤  ከመጥፋቱ የተነሳ እውቀት ተሰውራ በቦታዋ ሁከትና ብጥብጥ ተተክቶ ይገኛል።
ጳጳሶቻችን እንኳን የእኛን የእውቀት ጉድለት ሊሞሉ ይቅርና የእነሱን የሁከትና የብጥብጥ ዜና መሸከም ከሚከብድበት ደረጃ ላይ ተደርሷል። ይልቁንም ከመሸከማችን በላይ እኛኑ እንደእንጀራ ይበሉናል።

«ሕዝቤን እንደ እንጀራ የሚበሉ ኃጢአት የሚሠሩ ሁሉ በውኑ አያውቁምን? እግዚአብሔርንም አይጠሩትም» መዝ ፲፬፤፯
እንኳን የእውቀታችንን ጉድለት ለመሙላት ይቅርና ራሳቸው እውቀት የጎደላቸውና የወጣት ጡረተኞች ሆነው ሳይሰሩ የምናበላቸው አንሶ ራሳቸው ተከፋፍለው እኛን የሚከፋፍሉ፤ ራሳቸው ተበጥብጠው እኛን የሚበጠብጡ፤ ራሳቸው መስማማት ሳይችሉ፤ እኛን የሚያውኩ፤ ራሳቸው ተወጋግዘው እኛን የሚያወግዙ፤ ራሳቸውን መመገብ ከብዶን እያለ ያለኪዳን የወለዱትን ልጆቻቸውን ጭምር በምትሸከም መቅደስ ላይ በሥልጣን ተቀምጠው ስናይ እጅግ ያሳዝናል።

የሐዋርያት ሥራ፳፰
በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። በማለት ሐዋርያው የተናገረው እኮ  የማይጠነቀቁ እንደሚነሱ በመንፈስ ተረድቶ ነው። ጊዜውም አሁን ነው። ከእንግዲህ ወዲያ ደግሞ ይብስ እንደሆን እንጂ የተሻለ አይሆንም።ምክንያቱም  ያልዘሩት አይታጨድም!
እኛ ከእውቀት ጉድለት የተነሳ እንደኢትዮጵያዊው ጃንደረባ « ማን ይመራኛል?» ብለን ብንጠይቅ በመንፈስ ቅዱስ እንደሚነዳው እንደ ፊልጶስ እኔ የሚል መሪ እናገኝ ይሆን?
እነሱም አይሉም፤ እኛንም እናውቃቸዋለንና እንዲሉ አንጠብቅም።
ለምስክር የሚበቃ እውነተኛ፤ ንጹህ፤ ከሃሜት፤ ከቡድን፤ከጉቦ፤ ከዘረኝነት፤ ከኃጢአት የራቀ፤ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ለማስተማር የሚበቃ «ፊልጶሳዊ» መምህር ሳይሆን ነፍሱን ከሥጋው እንዲለይልን  የመንፈስ ቅዱስን ኃይል የምንጠይቅበት መሪ ይኖረን ይሆናል።
«የሚመራኝ ሳይኖር እንዴት ይቻለኛል?» የሚል በአንድ በኩል፤ በሌላ ገጹ ደግሞ «ሕዝቤ እውቀት ከማጣት ጠፍተዋል» የሚል  ሁለት ጽንፎች ይታያሉ።ሁለቱን ሃሳቦች ማን ያስማማ? እንዴትስ ይስማማ?