Saturday, June 2, 2012

የአንዳንድ የጳጳሳቶቻችን ገበና ምን ይመስላል?

  ምንጭ፦ አባ ሰላማ ብሎግ
የአንዳንድ ጳጳሳቶቻችንን ገበናዎች ይፋ ስናደርግ ሀዘን ነው የሚሰማን። እንዲህ እያደረግን ያለነው ቤተክርስቲያኗ ምን አይነት ምግባረ ብልሹነት እየተስፋፋባት እንደሆነች ለማሳየት ነው እንጂ እነርሱን በግል ለማሳጣት አይደለም። ይህን መደበቅና ማለፍ ጉዳቱ ለቤተ ክርስቲያን እንደሆነ በግልጽ እየታየ ነው፤ ማኅበረ ቅዱሳን ገበናችሁን እሸፍንላችኋለሁ ማለቱ እርሱ የፈለገውን እንዲፈጽሙለትና «በእከክልኝ ልከክልህ» ቃል ኪዳን እንዲተሳሰሩና እንዳሻው እንዲጠቀምባቸው በማድረግ ቤተክርስቲያንን ከጥፋት ወደ ባሰ ጥፋት እየመራት ነው። እንደነዚህ ያሉትን አባቶች አሳፋሪ ታሪክ ማስፈራሪያ እያደረገ የሚሻውን እንዲፈጽሙለት እየተጠቀመበት ያለው ማኅበረ ቅዱሳንም ለጥቅሙ እንጂ ለቤተክርስቲያን እንዳልቆመ አስመስክሯል።
 እንደ እነዚህ ያሉትን «ብፁዓን» «ጻድቃን» «ቅዱሳን» ምንትስ እያለ መሸንገሉም በጥፋታቸው እንዲገፉ አድርጓቸዋል እንጂ በክፉ ሥራቸው እንዲጸጸቱና ንስሃ እንዲገቡ አልረዳቸውም። የራሳቸውን ጉድ ሌላውን አለሀጢአቱ በማውገዝ ለመሸፈን እያደረጉት ያለው ጥረትም ለማኅበረ ቅዱሳን በር እንዲከፈትለትና የሲኖዶሱ የበላይ አካል እንዲሆን ነው ያደረገው። ስለዚህ ገበናቸው እንዲህ ይፋ ቢሆን፣ ጉዳዩ በሕዝበ ክርስቲያኑ ዘንድ ትኩረት አግኝቶ ለቤተክርስቲያኑ አንዳች መፍትሔ ያመጣ ይሆናል በሚል ሐሳብ ገበናቸውን መግለጽ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል። ምናልባት ልብ ገዝተው ንስሃ ይገቡ ይሆናል።

የአፋልጉኝ ማስተወቂያ
ይህ ልጅ አያሳዝንም? ……. አያሳሳም? …… እርሱ ጠፍቶ እንዳይመስለዎ። አባቱን ማግኘት ባይችልም አባቱን ይፈልጋል፤ እንደሌላው በህግ እንደተወለደ ልጅ ከእናቱ ጋር አባቱን ማግኘትና አብሮ ለመኖር አልታደለም። ያለው አማራጭ አባቴ ማነው? እያለ በመጠየቅ ማደግ ነው። ማን ያውቃል? የማንነት ጥያቄው አንድ ቀን ምላሽ ያገኝ ይሆናል።
 
ቢያምኑም ባያምኑም ይህ ልጅ የአንድ ህጋዊ ባለትዳር ልጅ አይደለም። በቤተክርስቲያን ስርአት መሰረት «ከሴት ርቄ ንጽህ ጠብቄ እኖራለሁ» ብለው ቃል ኪዳን ከገቡና ከመነኮሱ በኋላ፣ በሌላ አባባል «ለዓለም ሞቻለሁ» ካሉ በኋላ እንደገና ትንሣኤ አግኝተው ሀሳባቸውን በመለወጥ ከዚህች ሴት ያፈሩት የአንድ ጳጳስ ልጅ ነው። መቼም የዱሮ ጳጳስ መስሎዎት «ኧረ አይሆንም! ጳጳስ እኮ ድንግላዊ ነው መውለድ አይችልም!» ይሉ ይሆናል። እንዲህ ብሎ መከራከር ለአባ ሳሙኤልም አላዋጣም። አባ ሳሙኤል ባለፈው ጊዜ ለሟቹ አባ ሚካኤል የተከራከሩትና በፍርድ ቤት የተረቱት እኮ እንዲህ ብለው ነው። ስለዚህ እንዲህ ማለት ዱሮ ቀረ። ዘንድሮ እንደዚያ አይነት ከስንት አንድ ቢያገኙ ነው። አለቃ ለማም /የገጣሚ መንግስቱ ለማ አባት/ «የመነኩሴ መካን የለውም» ሲሉ መናገራቸው እውነትነት ያለው መሆኑን ለማመን የተገደድንበት ዘመን ላይ ደርሰናል።
እስኪ ይገምቱ … ማንን ይመስላል? … በተለይ አይኑ? … የአባ ዲዮስቆሮስ ነው ካሉ አልተሳሳቱም። ልክ ነው የእርሳቸው ልጅ ነው። ትግራይ ውስጥ ከምትገኘው ሴት የወለዱት ልጅ ነው። ለእዚህች ምስኪን ሴት አንዳንዴ ቀለብ ይሰጧታል። አንዳንዴ ደግሞ ያቋርጡባታል። አባ ዲዮስቆሮስ ልጃቸውን ተቀብለው በሚገባ ቀለብ እየቆረጡለት እንዳስተማሩትና ለቁም ነገር እንዳበቁት እንደአባ ሚካኤል ያሉ ጥሩ አባት አይደሉም ማለት ነው። ከዓመት በፊት የልጁ እናት «አስወልደውኝ ቀለብ አልሰፍርልሽ አሉኝ» ስትል አዲስ አበባ መጥታ ጠቅላይ ቤተክህነት ገብታ አቤት ብትልም ወደሲኖዶስ ጽ/ቤትና ወደፓትርያርኩ እንዳትቀርብ ስለተደረገችና በሮች ስለተዘጉባት አልቻለችም ነበር። በኋላም ባለቤቷ አባ ዲዮስቆሮስ «ሰነድ እንዳትሸጥ» በስልት አስጠርተው ካባበሏትና ገንዘብ ከሰጧት በኋላ ወደመጣችበት እንድትመለስ አድርገዋል።   
ለነገሩ አባ ዲዮስቆሮስ በየሜዳው የሚዘሩ ግን የማይሰበስቡ መሆናቸው ይነገርላቸዋል። እንደ ጉድ ሙዳዩ አባ አብርሃም «ሀጢአቴ ፍሬ አፍርቶ ማየት አልፈልግምና አስወርጂው» የሚሉ ግን አይደሉም። እንዲያውም ያገኟትን ሴት ሁሉ ውለጂልኝ እያሉ የሚዘበዝቡ ናቸው። ለምሳሌ ወ/ሪት ርሻን የምትባልና እዚያው ትግራይ ውስጥ በልማት ኮሚሽን የኤች አይ ቪ ዘርፍ የምትሠራ ሴትን «እባክሽን ውለጂልኝ ከእናንተ ዘር ተቀላቅዬ ወደላይ ከፍ ልበል» ማለታቸውን መናገሯን ውስጥ አዋቂዎች ይናገራሉ። መቼም ጳጳሱ ሰው ናቸውና ለምን ወለዱ አይባልም። ችግሩ እግዚአብሔር በሰው ላይ ያልጫነውና የሩቅ ምሥራቅ ሃይማኖቶች ባህል የሆነው ምንኩስና ሐዋርያው ጳውሎስ ያስተማረውን የድንግልና ሕይወት በመተካት ወደ ጵጵስና መምጫ መንገድ ሆኖ መቀመጡ ነው። ቅዱስ ጳውሎስ የተናገረው፣ ሰው ጥሪው ካለው እንደእኔ በድንግልና ሕይወት ሆኖ እግዚአብሔርን ማገልገል ይችላል ነው። በቤተክርስቲያን እየሆነ ያለው ግን ከዚህ ተቃራኒው ነው። እግዚአብሔር በድንግልና ሕይወት እንዲያገለግሉት የጠራቸው አሉ። በዚያ ሕይወት ነቀፌታ ሳይኖርባቸው እያገለገሉ ይገኛሉ። እግዚአብሔር ሳይሆን ሥልጣንና ገንዘብ የጠሯቸውም የምንኩስናውን መስክ በብዛት ተቀላቅለው «ምንኩስና» ወደተባለው የድንግልና ሕይወት ይገባሉ። እነዚህን የጠራቸው እግዚአብሔር ስላልሆነ ገንዘቡና ሥልጣኑ ሲመጡ ያ ለጊዜው ያፈኑትና ያለ ጥሪ የተሸከሙት የድንግልና ሕይወት የማይችሉት ቀንበር ይሆንና ቃል ኪዳናቸውን ያፈርሳሉ፤ ንጽህናቸውን ያሳድፋሉ፤ ይወድቃሉ። እግዚአብሔር የጠራቸውና ለስብከተ ወንጌል የሚፋጠኑት ግን የጠራቸው እግዚአብሔር ጸጋውን ስለሚያበዛላቸው በተጠሩበት መጠራት ይመላለሳሉ።
ዛሬ አንዳንዶቹ ጳጳሳት በዚህ ነገር ተፈትነው የወደቁ መሆናቸውን ከተለያየ አቅጣጫ እየተሰማ ካለው ድብቅ ታሪካቸው እያየን ነው። በዚህ ነገር ስማቸው የሚነሳው ጳጳሳት ጥሪው ሳይኖራቸው «እበላ» እና «እሾም» ብለው የመነኮሱ ናቸው። ጥሪው ኖሯቸው የመነኮሱትና እንደሚገባቸው እየኖሩ ያሉት ግን በዚህ ነገር አይታሙም። በዚህ ነገር ተላልፈው የሚገኙትን ህገ ቤተክርስቲያን ከስልጣናቸው እንዲሻሩና እንዲወገዙ ቢያዝም፤ በዚህ ነገር የተወገዘ እስካሁን የለም። እንደአለቃ ገብረ ሐና ተረት አንዱ ሌላውን «ዋ! እዚያም ቤት እሳት አለ» እያለ ነው መሰል ስለሚፈራሩ «የውሾን ነገር ያነሣ …..» ሆኗል ነገሩ።
መቼም ይህ የምግባር ችግር ነውና ከሃይማኖት ችግር አይብስም የሚሉ አይጠፉም። በተለይም የማኅበረ ቅዱሳን አመራሮችና አባላት ይህ የምግባር ችግር እንጂ የሃይማኖት አይደለም ብለው እንደሚከራከሩና ከምግባር ችግር የሃይማኖት ችግር ይከፋል እንደሚሉ ማንም ያውቃል። ነገሩን ለማቻቻል ካልፈለግን በቀር እውነቱ ግን ይህ ነው። ሃይማኖትና ምግባር ተያያዥነት አላቸው። በጎ ሃይማኖት ማለትም በእግዚአብሔር ቃል ላይ የተመሠረተ ሃይማኖት መልካም ምግባርን ያስገኛል። ይህ መልካም ምግባርም ሃይማኖቱ እውነተኛ፣ ሕያውና የሚሠራ መሆኑን ይመሰክራል። ስለዚህ የመልካም ምግባር ምንጭ የቀና ሃይማኖት፣ መልካም ምግባርም የቀና ሃይማኖት አስረጂና ማረጋገጫ ነው።
ዛሬ ያለችው ቤተክርስቲያን እንዲህ ባለ የምግባር ዝቅጠት ውስጥ ብትገኝም፣ ይህን በተመለከተ መቃወምም ሆነ የንስሀ ጥሪ ማስተላለፍ ክልክል ነው፤ በዜና ቤተክርስቲያን አዘጋጆች ላይ ከሰሞኑ ቁስላቸው የተነካባቸው አንዳንድ ጳጳሳት «ይወገዙ» የሚል ሐሳብ እንዳቀረቡት ይወገዙ ሊያሰኝ ይችላል። ምክንያቱም ዛሬ የሃይማኖትም የምግባር ችግር ባለባቸው የቤተክርስቲያናችን ሰዎች ዘንድ ውግዘት ማስፈራሪያ ሆኗል። ነገር ግን ቤተክርስቲያን ለጳጳስ በማይመጥን የምግባር ችግር ውስጥ የተዘፈቁ ጳጳሳትን አቅፋና ደግፋ ስትይዝ፣ በቤተ ክርስቲያን የሚያድነው ወንጌል ብቻ እንዲሰበክና አምልኮት ሁሉ፣ ብቻውን አምላክ ለሆነው ለሰራዊት ጌታ ለእግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እንዲቀርብ ሲጋደሉ የኖሩትን የቤተ ክርስቲያን ልጆች ማውገዝ፣ አውጋዦቹ ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኙ፣ ምን ያህል ከሃይማኖት እንደራቁና ከሃይማኖት በመራቃቸውም ምግባራቸው ምን ያህል እንደከፋ ያመለክታል።
ከላይ የተገለጸው ታሪክ ያላቸው አባ ዲዮስቆሮስ የራሳቸውን ጉድ ሸፍነውና ከማኅበረ ቅዱሳን ጋር ተዋውለው፣ የጌታን ስም የሚጠሩትንና እውነትን የተናገሩትን የቤተክርስቲያን ልጆች በማውገዛቸው ምን ተሰማቸው ይሆን? ደስታ ወይስ ሀዘን? እፎይታ ወይስ ጸጸት? እንደ ስጋ ሀሳብ ከታየ ደስ ይላቸው ይሆናል። ቤተክርስቲያንን «ከመናፍቃን» አጸዳን ብለው ደምድመው ይሆናል። ነገር ግን ወንጌል ፍሬያማ የሚሆነው እንደዚህ ባለ መከራና ስደት ውስጥ ሲሰበክ ነውና የተጀመረው የወንጌል አገልግሎት ይበልጥ ይጠናከራል እንጂ አይደክምም። በዚህ በሰለጠነ ዘመን ስርአተ ቤተክርስቲያንን ያልተከተለና በግብታዊነት የተሞላ ውግዘት ማስተላለፉ አውጋዡን ክፍል ከማስገመት አልፎ በወንጌል እንቅስቃሴ ላይ የሚያሳድረው አንዳች ተጽእኖ አይኖርም። የዛሬዎቹ ጳጳሳት አባቶች አይሁድ ጌታችን ኢየሱስን በመግደልና በመቅበር ተከታዮቹ እንዲፈሩና ወደኋላ እንዲመለሱ በማድረግ የወንጌልን እንቅስቃሴ ያዳፈኑ መስሏቸው ነበር። ነገር ግን ጌታ ከሙታን ተለይቶ በመነሳቱ የተዳፈነ የመሰለው ወንጌል እንደገና ተቀጣጠለ። ይልቁንም መንፈስ ቅዱስ ከወረደ በኋላ አይሁድ ያወጡትን ልዩ ልዩ አዋጅና ማስፈራሪያ እየጣሰ ወንጌል ብዙዎችን መለወጡን ቀጠለ እንጂ አልቆመም። ዛሬም የወንጌልን እንቅስቃሴ ማቆም የሚችል ውግዘትም ሆነ አዋጅ አይኖርም። ለዚያውም አንድ የጥቅሙ ምንጭ የደረቀ መስሎ የተሰማው ማኅበር አጥንቶ ባቀረበው ክስ ብቻ ላይ ተመስርቶ የቀረበ ውግዘት ከንቱ ነው። ወንጌል ግን ለፍጥረት ሁሉ መሰበኩ ይቀጥላል። ወንጌል የተቃወሙትን እንኳን ማሳመኑ አይቀርም። የሐዋርያት ስራ «የእግዚአብሔርም ቃል እየሰፋ ሄደ፥ በኢየሩሳሌምም የደቀ መዛሙርት ቍጥር እጅግ እየበዛ ሄደ፤ ከካህናትም ብዙ ሰዎች ለሃይማኖት የታዘዙ ሆኑ።» (የሐዋርያት ስራ 6፡7) የሚለው ለዚህ አንዱ ማስረጃ ነው። 
ዛሬ ሊወገዙ በሚገባቸው አንዳንድ የማህበረ ቅዱሳን ተላላኪ ጳጳሳት የተወገዙ ወንድሞች ምን ተሰምቷቸው ይሆን? በወንጌል የተጻፈው ነውና የደረሰባቸው ደስ ሊላቸው ይገባል። አውጋዦቻቸው ለውግዘታቸው የሰጡት ስም ሌላ ቢሆንም፣ ውስጡ ሲፈተሽና ጀርባው ሲጠና ግን የሚገኘው መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያስተምረው «መዳን በሌላ በማንም የለም በኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው ለምን ትላላችሁ?» «ከእግዚአብሔር በቀር ሌላ ማንንም አታምልኩ ለምን ትላላችሁ?» ወዘተ የሚል ነው። እንዲህ ከሆነም ይህ ስለጌታ ስም መነቀፍ የማይገኝ ክብር በመሆኑ ተወጋዦቹ እጅግ ደስ ሊላቸው ይገባል። እንኳንም የጌታ ስም በእነርሱ በመጠራቱ ምክንያት ተነቀፉ፤ እንኳንም በጌታ ስም ምክንያት ተወገዙ። ጌታ በወንጌል እንዲህ ብሏል። «ሲነቅፉአችሁና ሲያሳድዱአችሁ በእኔም ምክንያት ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲናገሩባችሁ ብፁዓን ናችሁ። ሲነቅፉአችሁና ሲያሳድዱአችሁ በእኔም ምክንያት ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲናገሩባችሁ ብፁዓን ናችሁ።» (ማቴዎስ 5፡11-12)።
ሐዋርያው ጴጥሮስም እንዲህ ሲል የሚሰጠውን ምክር መቀበል አለባችሁ። «ወዳጆች ሆይ፥ በእናንተ መካከል እንደ እሳት ሊፈትናችሁ ስለሚሆነው መከራ ድንቅ ነገር እንደ መጣባችሁ አትደነቁ፤ ነገር ግን ክብሩ ሲገለጥ ደግሞ ሐሤት እያደረጋችሁ ደስ እንዲላችሁ፥ በክርስቶስ መከራ በምትካፈሉበት ልክ ደስ ይበላችሁ። ስለ ክርስቶስ ስም ብትነቀፉ የክብር መንፈስ የእግዚአብሔር መንፈስ በእናንተ ላይ ያርፋልና ብፁዓን ናችሁ። ከእናንተ ማንም ነፍሰ ገዳይ ወይም ሌባ ወይም ክፉ አድራጊ እንደሚሆን ወይም በሌሎች ጒዳይ እንደሚገባ ሆኖ መከራን አይቀበል፤ ክርስቲያን እንደሚሆን ግን መከራን ቢቀበል ስለዚህ ስም እግዚአብሔርን ያመስግን እንጂ አይፈር። ፍርድ ከእግዚአብሔር ቤት ተነሥቶ የሚጀመርበት ጊዜ ደርሶአልና፤ አስቀድሞም በእኛ የሚጀመር ከሆነ ለእግዚአብሔር ወንጌል የማይታዘዙ መጨረሻቸው ምን ይሆን? ጻድቅም በጭንቅ የሚድን ከሆነ ዓመፀኛውና ኃጢአተኛው ወዴት ይታይ ዘንድ አለው? ስለዚህ ደግሞ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ መከራን የሚቀበሉ፥ መልካምን እያደረጉ ነፍሳቸውን ለታመነ ፈጣሪ አደራ ይስጡ።» (1ጴጥሮስ 4፡12-19)።
----------------------------------------------
ከደጀ ብርሃን፤
ይህንን መረጃ ማውጣት የቤተክርስቲያንን ክብር ከማዋረድ ጋር ለማያያዝ የሚፈልጉ ወገኖች አሉ። ክብሯን ያዋረዱት ክቡር ነን እያሉ ለክብሯ የሚገባውን ክብር ያልፈጸሙ ራሳቸው የድርጊቱ ባለቤቶች ናቸው። ስለዚህ ይህ ሙግት ከንዴት የሚመነጭ ካልሆነ ነባራዊውን እውነት የሚያሳይ አይሆንም። ሌላው ደግሞ የገቡበትን መሃላ ያፈረሱ እንደነዚህ ዓይነት ጳጳሳት በወንጌል አስተምረው ሕዝቡን ባለበት ማቆየት አይችሉም። ራሳቸው በሰይጣን የተሸነፉ ናቸውና። ከዚያም ባሻገር በእነሱ ኃጢአት የተነሳ እግዚአብሔር ከቤተክርስቲያን ይርቃል። ጋብቻ መልካም ነው። መኝታውም ንጹህ ነው። እነዚህ ሰዎች ራሳቸውን ብጽዓት እንዳደረጉት በንጽህና መቆየት አለባቸው ፤ ወይም ጋብቻቸውን ማጽናት አለባቸው። ስለዚህ አባ ሰላማ ብሎግ የሌሎቹንም እንደዚህ አውጣውና መንገዳቸውን እንዲለዩ ይነገራቸው። ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ እንዲህ ብሎት ነበር።

«ጢሞቴዎስ ልጄ ሆይ፥ አስቀድሞ ስለ አንተ እንደ ተነገረው ትንቢት፥ በእርሱ መልካም ጦርነት ትዋጋ ዘንድ ይህችን ትእዛዝ አደራ እሰጥሃለሁ፤እምነትና በጎ ሕሊና ይኑርህ፥ አንዳንዶች ሕሊናን ጥለው፥ መርከብ አለ መሪ እንደሚጠፋ፥ በእምነት ነገር ጠፍተዋልና፤ከእነዚያም፥ እንዳይሳደቡ ይማሩ ዘንድ ለሰይጣን አሳልፌ የሰጠኋቸው፥ ሄሜኔዎስና እስክንድሮስ ናቸው» 1ኛ ጢሞ 1፤18-20