በ
Naod ቤተሥላሴ
www. naodlive.com
ዘረኝነት፤
ብሔርተኝነት፤ ጎሰኝነት፤ ጎጠኝነት፤ መንደርተኝነት፤ ቡድነኝነት…የሚባሉ ነገሮች ሁሉ የፍርደ ገምድልነት (Injustice,
prejudice) መጀመርያዎች
እና መገለጫዎች ናቸው ብል ብዙ የተሳሳትኩ አይመስለኝም፡፡ ከዚህ ቀጥዬ የማነሳው ጥያቄ ግን ከላይ በርዕሱ የጠቀኩትን ጥያቄ ነው፡፡ ዘረኛ፤… መንደርተኛ... ያልሆነ ማን ነው?
ከቤተክርስቲያን
ስወጣ፤ አንድ ጓደኛዬ፤ ከሆነ ከማላውቀው ልጅ ጋር አብሮ ወደ እኔ ሲመጣ አየሁት፡፡ ከዚያ ‹‹ተዋወቀው፤ የአዲስ አበባ ልጅ ነው!›› አለኝ፡፡ የአዲስ አበባ ልጅ ካልሆነ ከእኔ ጋር መተዋወቅ የለበትም? አንተ ራስህ የአዲስ አበባ ልጅ ሳትሆን ተዋውቄህ የለም? ብዬ ልገስጸው ከጅዬ ነበር፡፡ ግን ያው ጨዋ ነኝና…‹‹የጎረቤቴ ልጅ ካልሆነ አልተዋወቀውም›› ብዬ ቀልጄ እንግዳውን ተዋወቅኩት፡፡ የፈራሁት ግን አልቀረም…
ከተዋወቅኩት
ልጅ ጋር ያለኝ ጠባያዊም ሆነ ልማዳዊ የጋራ ነገር ‹‹አዲስ አበባ መወለድ ብቻ›› ሆኖ ቀረ፡፡ ኮከባችንም፤ ጨረቃችንም፤ ቅዠታችንም የማይገጥም ሆነና ትውውቃችንን Abort አደረግነው፡፡ ይሄ ገጠመኝ እስከዛሬ ትዝ የሚለኝ ያለ ምክንያት አይደለም፡፡
በትግሬዎች
ዘረኝነት የሚንገፈገፉ ነገር ግን ራሳቸው ከራሳቸው መንደር ከመጣ በቀር ሌላ ጓደኛ የሌላቸው ብዙ ሰዎች ስለማይ ነው፡፡ ባለፈው የጊዮርጊስ ጽዋ ያላቸው ጎረቤቶች አገኘሁና፤ ማኀበር ልገባ ቋመጥኩ /ጠላ ስለምወድ፡)/፤ በጽዋው ዕለት አባላቱ ሁሉ በተገኙበት ተጋብዤ ሄድኩ ‹‹ከጎንደሬ በቀር አንድም ሌላ የሰው ዘር የለበትም››፡፡ ይሄ ግን the tip of the
iceberg ነው፡፡ በሃይማኖተኞች ውስጥ ያለው መንደርተኝነት ከፖለቲካው የበለጠ ስር የሰደደ፤ ስብከትም፤ ስዕለትም፤ ጸሎትም የማያጠፋው ደዌ ነው፡፡
አንዳንዴ
ኢትዮጵያዊ ከኢትዮጵያዊ የሚፈላለገው፤ የመንደሩን ኢትዮጵያዊ እስኪያገኝ ድረስ ይመስላል፡፡ አሁን እኒህ ሰዎች፤ እንደ መለስ ዜናዊ ስልጣን ቢይዙ፤ በራሳቸው መንገድ ጎጠኛ መሆናቸው ይቀራል? ከ20 ጓደኞቹ ውስጥ 19ኙ የመንደሩ ልጆች የሆነ ሰው፤ መርጦ የሚሄድበት ቤተክርስቲያን እንኳን የመንደሩ ልጆች ወደ መሰረቱት ወይ ወደ ሚበዙበት ቤ/ክን የሆነ ሰው፤ ስለ መለስ ዜናዊ ጎጠኝነት፤ ስለ ኦነግ ብሔርተኝነት ማማረር ይገባዋልን? በትግሬዎችስ ዘረኝነት መብከንከንስ ይገባዋል? ፈረንጆችስ ከጥቁሮች እየሸሹ፤ ከብጤ ፈረንጆች ጋር ብቻ ለመጎዳኘት የሚያደርጉትን ጥረት ‹‹ዘረኝነት›› ብሎ መኮነንስ ይገባዋልን? በእኔ ሚዛን ራሱ ዘረኛ ነው፡፡
በእርግጥ፤
ብዙ የጋራ ታሪክ እና ባህል፤ ቋንቋና ለዛ ከምንጋራው ሰው ጋር መወዳጀት ቀላል እና ተፈጥሮአዊ ነገር ነው፡፡ ዘመድ ከዘመዱ…ይባል የለ፡፡ ቢሆንም! ቢሆንም! እኛ የምናደርገውን ያንኑ ነገር ሌሎች ሲያደርጉት ‹‹ዘረኝነት›› ማለት ትክክል አይደለም፡፡ ከዘር፤ ከመንደር…የተሻለ የጥብቅ ወዳጅነት ምክንያት፤ የመተማመን ዋስትና፤ የትውውቅ ሰበብ የሌለ ይመስል፤ ሰፈሬ፤ መንደሬ…ማለት ትክክል አይደለም፡፡
ዘርን፤
መንደርን…ወዘተ ከቁጥር የማያስገቡ፤ ሌላ ብዙ ጥሩ እና በቂ የወዳጅነት ሰበቦች፤ የመተማመን ምክንያቶች አሉ ባይ ነኝ፡፡ ለምሳሌ…ሙያ፤ የኑሮ ዘይቤ፤ አስተሳሰብ፤ ገጠመኝ፤ ርእዮተ ዓለም ወዘተ…እኒህ ሰበቦች፤ ዘርና መንደር ካልነካቸው አይጸኑም ካልተባለ በቀር!