Sunday, June 10, 2012

«የሰንበት ት/ቤቶች ማ/ መምሪያ በጠራው የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጉባዔ የአቋም መግለጫ፤ የማቅን ደስታ የገፈፈ ነው»

 
ማኅበረ ቅዱሳን ካለው ባህርይ አንዱ በማኅበራት ጉያ ተሸሽጎ ለዓላማው ማስፈጸሚያ እነሱን መጠቀም ተጠቃሽ ስልቱ ነው። ከነዚህም የመጠቀሚያ መሣሪያዎቹ አንዱ «የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጉባዔ» የተባለው የመንፈሳዊያን ወጣቶች ማኅበር ነው። የዛሬን አያድርገውና ማኅበረ ቅዱሳን አፉ ላይ በወርቅ የተለበጠ እስኪመስል ድረስ የሰንበት ት/ቤቶች ጉባዔን ስም ሳያነሳ ውሎና አድሮ አያውቅም ነበር። ይህ ኃይል በወጣቶች የተደገፈ ኃይል እንደመሆኑ መጠን ለቤተክርስቲያን ያለው መንፈሳዊ ቅናት ያለምንም ማጋነን ከየትኛውም ወገን በበለጠ የጠነከረ ነው። ያለውን መንፈሳዊ ቅናት በኃይል እስከማስከበር ድረስ ለመሄድ እንደማያመነታም ማኅበሩ ስለሚያውቅ  ልክ «ሳውል» የተባለው ጳውሎስ ያደርግ እንደነበረው ብዙ ድካምና ጉዞ የማይበግረው ኃይል ስለሆነ  የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጉባዔን የይለፍ ደብዳቤ አስይዞ መንፈሳዊ ቅናቱን ለገዛ ጥቅሙ ሲያውለው ቆይቷል።  ማኅበረ ቅዱሳን ከራሱ ዓላማ አንጻር አሥር ጊዜ «የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጉባዔ» እያለ ለወትሮው ማንሳቱ ብዙም አያስገርምም። «የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጉባዔ ይህን አደረገ፤ ይህንን ጻፈ፤ ተቃውሞውን አሰማ፤ በኃይል ለማስከበር እንገደዳለን አለ………..» ወዘተ ድምጾችን ማኅበሩ ደጋግሞ ሲጮህና በድረ ገጽ ልሳኖቹ ደጀ ሰላምና ሌሎቹ ሲጮሁለት እንዳልነበሩ ያህል ሰሞኑን በተደረገው የአንድነት ጉባዔው ማጠናቀቂያ «የአቋም መግለጫ» ላይ ትንፍሽም ሳይሉ መቅረታቸው የሚያሳየው  የጉባዔው መደረግ የቀማቸው ነገር እንዳለ ነው።

ይህን ኃይል ቤተክርስቲያን ያቋቋመችው ቢሆንም ማኅበሩ በዘመናዊ ስልቱ የራሱ አገልግሎት ፈጻሚ አድርጎት ቆይቷል። «ቤተክርስቲያን ማለት ማኅበረ ቅዱሳን፤ ማኅበረ ቅዱሳን ማለት ደግሞ ቤተክርስቲያን» የሆነ ያህል በወጣቶቹ አንድነት ጉባዔ ውስጥ በመቅረጹ የማኅበሩ ዓላማ አስፈጻሚ በማድረግ ማኅበረ ቅዱሳን ችግር ተከስቷል በተባለ ቦታ ይህን የወጣት ጉባዔ ይልክ እንደነበር ይታወቃል። በአምናው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባዔ ላይ በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ውስጥ በእነ ዲ/ን ትዝታው ሳሙኤል ላይ የተፈጸመውንና «እነ አንድ አድርገን» ብሎጎች አሞካሽተው የጻፉትን የምንዘነጋው አይደለም። በቅርብ የምናውቀው ስለሆነ አሁን በዚያ ላይ ጊዜ ሳናጠፋ ወደተነሳንበት ርእስ እናምራ።
መምህር እንቍ ባሕርይ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጉባዔን ከተያዘበት ወጥመድ በማላቀቅ የቤተክርስቲያኒቱ አገልጋይ ኃይል እንዲሆን የአምስት ዓመት እቅድ ነድፈው ጠቅላላ ጉባዔ በመጥራት  ያለፉትን ሳምንታት ጠቃሚ እርምጃ በመውሰድ የሥራቸውን ጀምረዋል።
ሂደቱ ረጅምና ብዙ ጥረት የሚጠይቅ ቢሆንም ጅምሩ ግን ትልቅ ዋጋ የሚሰጠውና የሚደነቅ ስለሆነ መምህር እንቍባሕርይ  ለሰሩት ለዚህ ትልቅ ሥራ የምስጋና ዋጋ ሳንከፍል አናልፍም።
ይህ የወጣቶች ጉባዔ ከወጣትነት ኃይል የተነሳ በጠቃሚም ይሁን በጎጂ መልኩ መንፈሳዊ ቅናቱን ሊጠቀሙ የሚፈልጉ ኃይሎች እንደመኖራቸው መጠን «ሳውል» ለእግዚአብሔር ቤት እንዳለው ቅናት ዓይነት፤  ቀያፋው ማኅበር ደብዳቤ ሰጥቶት ሲገለገልበት የነበረውን ሁሉ  አስጥሎና በወንጌል ብርሃን  ዓይኑን ገልጦ የቤተክርስቲያን አገልጋይ ማድረግ እጅግ አስፈላጊ ነገር ነው። ለበለጠ ሥራ ለአዲስ አደረጃጀት በመጥራት ታሪካዊ ሊባል የሚችለውን ጉባዔ ማድረጉ በእውነትም የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ከሥጋና  ከደም ጋር አልተማከረም ያሰኛል።  ይህም የሚገለጸው ጉባዔው ውጤታማ ሆኖ መጠናቀቁ ብቻ ሳይሆን ወጣቶቹን ሲጠቀም የነበረው ቀያፋው ማኅበር ጽፎ የሰጣቸውን ደብዳቤ ውድቅ በማድረግ የቤተክርስቲያንን የአቋም ደብዳቤ አንግቦ በመያዝ ማጠናቀቁ ትልቁ ማሳያ ነው።  ጉባዔው ሲጀመር፤ ተጀምሯል እንዳላለ ሁሉ ሲጠናቀቅ ግን አንዳችም ነገር ትንፍሽ ያላለው ቀያፋው ማኅበር በእርግጥም የወጣቶቹ መሰብሰብ ከጨለማው አመራር ነጻ የወጡበት የመንፈስ ቅዱስ ጥሪ እንደነበረ ማረጋገጫ ነው። እነዚያ የማኅበሩ ጭቃ ሹም ድረ ገጾችም ለወትሮው የአንድነት ጉባዔውን ጀግንነትና የሰማእታት ስብስብ የሞላው የወጣቶች ማኅበር ስለመሆኑ ሲጮሁ እንዳልነበር በዚህ አዲሱ ጉባዔ መነሻም ሆነ መድረሻ ላይ ምንም ትንፍሽ አለማለታቸው የሚያሳየው ነገር ማኅበሩ ከዚህ ጉባዔ ተጠቃሚ የሚሆንበት ነገር እንደሌለና ሲለቀልቁ ከነበረው የስም ሙገሳ ተግባራቸው መታቀባቸውም የአሁኑ ጉባዔ የኪሳራቸው ሂሳብ የተወራረደበት፤ ቤተክርስቲያን ግን ያተረፈችበት ትልቅ ጉባዔ ነበር።
ይህ ጉባዔ በጥሩ መንፈስ ተጀምሮ ለሁለንተናዊ እድገት የሚበጅ አቋም በመያዝ በመጠናቀቁ  ለቤተክርስቲያኒቱ  መንፈሳዊ ልማትና ሰላም ትልቅ አስተዋጽዖ የሚያደርግ ሲሆን  እንደዋሻ ይጠቀሙበት ለነበሩ የጥፋት ኃይሎች ደግሞ ትልቅ ውድቀት ነው። የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያውም  የጀመረውን ይህንን መንፈሳዊ ሥራ በቅርብ ክትትልና በተመሳሳይ ውይይቶች የማሳደግ  ተግባር  ከፊቱ ተደቅኗል። ይህን ማድረግ ካልቻለ በዚህ ጉባዔ መልካም ፍጻሜ ላይ ዝምታን የመረጠው የጉባዔው  የቀድሞ የንስሐ አባት፤ አዲስ ስልት እየቀየሰ ካልሆነ በስተቀር የክብር ቅስናውን ይዞ ጸበል እረጫለሁ ማለቱን ስለማይተው ጥብቅ ትኩረት ሊሰጠው  እንደሚገባ ለማደራጃ መምሪያው ከወዲሁ ለማሳሰብ እንወዳለን።
የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጉባዔ ቤተክርስቲያናችን ብቻ እናገለግላለን፤ ከእሷ ብቻ የሚሰጠንን መመሪያ እንከተላለን በማለት በቃላቸው ያረጋገጡበት የአቋም መግለጫ ከታች ቀርቧል። ይህ የአቋም መግለጫ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጉባዔ የአንድ ማኅበር ተላላኪ ሳይሆን የቤተክርስቲያኒቱ አገልጋይ መሆኑን ያረጋገጠበት ስለሆነ ጉባዔው ቃሉን አክብሮ ለቤተክርስቲያኒቱና ለቤተክርስቲያኒቱ ብቻ እንዲገዛ ይጠበቃል።
  የአቋም መግለጫውን ለማንበብ እዚህ ይጫኑ