Monday, June 4, 2012

ማኅበረ ቅዱሳን እንዲህም ነበር! በቀሲስ መልአኩ


 ካለፈው የቀጠለ.................ክፍል 3

ፕሮቴስታንቶች አንዳችም ሊያደርጉት ያልተቻላቸውንና በሌሎች ሃይማኖት በተከበበች ምድር አስደናቂ እንቅስቃሴ ያደርግ የነበረውን የሰንበት ትምህርት ትምህርት ቤቶች እንቅስቃሴ በድርጅታዊ ፍቅር ታውሮ የበታተነው ማኅበረ ቅዱሳን በሚል ስም የተቋቋምው ድርጅት ነበር ማኅበረ ቅዱሳን ሐረር ላይ ያለውን የሰንበት ትማህርት ቤቶች እንቅስቃሴ በክፉ ዓይን ማየት የጀመረው  ዓለማያ ግብርና ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ገና እግሩን በተከለበት ወቅት ነው በዚህ ወቅት ማኅበረ ቅዱሳን የሚባል ማኅበር በሐረር ስሙም  የማይታወቅ ስለነበረ በሐረር ያሉ ካህናትም ሆኑ ምእመናን ቦታ አልሰጡትም ነበርነገር ግን ጥቂት ቆይቶ ማኅበረ ቅዱሳን ለጠቅላይ ቤተ ክህነትና ለሐረርጌ ሀገረ ስብከት አቤቱታ አስገባ አቤቱታውም ሐረር ውስጥ ያሉት ሰንበት ትማህርት ቤቶች በሙሉ ተሐድሶ ናቸው የሚል ነበር።  ለጊዜው የሀገረ ስብከቱ ጽሕፈት ቤት የማኅበሩን ክስ አጥብቆ ተቃወመ የሐረር ሕዝበ ክርስቲያንም ሁኔታውን ሲስማ አጥብቆ ተቃወመ።
ማኅበረ ቅዱሳንን ሐረር ምድር ላይ ላለማስገባት ከፍተኛ የሆነ እንቅስቃሴ ተጀመረ።  ሁኔታው ያላመረው ማኅበረ ቅዱሳን የሐረር ሕዝበ ክርስቲያንን የሚከፋፈልብትን አንድ ረቂቅ ተንኮል አርቅቆ አወጣ።  ያም በሐረር የሚገኙ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችን የተሐድሶ አባላት የሚያሳይ የሐሰት ሰነድ ነበር።  ሰነዱ በቃለ ጉባኤ መልክ የተዘጋጀ ሲሆን የተሐድሶ አባላት የሆኑ ከመላው ኢትዮጵያ ተሰብሰበው ለሐረር እንቅስቃሴ ከፍተኛ ገንዘብ እንደሚሰጡ ለሐረርም መሪዎችን እንደሾሙ የሚናገርና ስሞችንም የሚዘረዝር ነበር።

በዚህ የሐሰት ሰነድ ላይ መልአከ  ሰላም ጴጥሮስ አዘነን ጨምሮ የሀገረ ስብከቱን ሥራ አስኪያጅ፤ የሀገረ ስብከቱን የመዝገቡ ቤት ኃላፊ፤ ሌሎች ካህናትና ታዋቂ ምእመናን የያዘ ነበር።  በሰነዱ ላይ የተዘረዘሩት ቀንደኛ የሆኑ ማኅበር ቅዱሳንን አላፈናፍንም ያሉ ሰዎች ነበሩ።  በወቅቱ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ሆነው የተሾሙት መምህር ብርሃነ ህይወት (አባ ዜና ማርቆስ የተባሉት በስሜን አሜሪካ ባሉት ታላቅ አባት ምትክ የተሾሙት ) በደስታ ቸኩለው ተሐድሶዎች ቤተክርስቲያኔን ወረዋል በማለት በሸኚ ደብዳቤ የሀገረ ስብከቱን ሥራ አስኪያጅ፤ ካህናቱን፤ የደብር አስተዳዳሪውን ታላቁን ሊቅ መልአከ ሰላም ጴጥሮስ ከስራና ከደሞዝ አገዱአቸው።

   ቤተክርስቲያኑ ለማንም ወጣት የተከለከለ እንደሆነ አስታወቁ።  በብዙ ሺህ የሚቆጠር የሐረር ህዝብ ስእለ ማርያምን ይዞ በነቂስ ወጥቶ ውሳኔውን ተቃወመ ለቤተክህነት አቤት አለ።  ሰሚ ግን አላገኘም።  እነዚህ በሐረሩ የሐሰት ሰነድ የተጠቀሱት እንደ አዲስ አበባው ዘገባ ዘም ብለው አልተቀበሉትም።  ወዲያውኑ ጉዳዩን ለፍርድ ቤት አቀረቡ። ፎርጅዱን የሠራው ግለሰብ ተያዘ።  ከማኅበረ አባላት አንዱ ይህን እንዲሠራ እንደጠየቀው ተናገረ።  የፖሊስ የምርመራ አባላትም ሰነዱ የሐሰት ሰነድ (ፎርጅድ ) እንደሆነ ለፍርድ ቤቱ አስታወቁ።  ጉዳዩ ፍርድ ቤቱንም፤ የሐረርን ሕዝብ አስቆጣ።  ፍርድ ቤቱም የሐሰት ሰነዱን በሸኚ ደብዳቤ የበተኑት ሊቀ ጳጳሱ ስለሆኑ በኃላፊነት እንደሚጠየቁ ወሰነ።  ከሦስት ዓመት እስከ ሰባት ዓመት ሊፈረድባቸው ፍርዱ እየተጠበቀ እያለ የኢሕአዴግ መንግሥት ጣልቃ ገብቶ ጳጳሱ ይቅርታ እንዲጠይቁና በሐሰት ስማቸው የጠፋውም ክሳቸውን እንዲያነሱና በየስማቸው ከጠላይ ቤተክህነትና ከሀገረ ስብከት ንጹሐን እንደሆኑ ደብዳቤ እንዲጽፍላቸው ተወሰነ።  ሊቀ ጳጳሱም ያሳሳቱኝ ልጆቹ (ማኅበረ ቅዱሳን ) ናቸው ብለው ይቅርታ ጠየቁ።

አሳዛኙ ነገር ግን ይህ ውሳኔ የተሰጠው ድርጊቱ ክተፈጸመ ከሰባት ዓመት በኋላ መሆኑ ነው።  በዚህ ሰባት ዓመት «ተሐድሶ ናቸው» ተብለው ከገዛ ቤተ ክርስቲያናቸው የተባረሩና ቅጽረ ቤተ ክርስቲያን እንዳይደርሱ የተደረጉ፤ ብዙዎቹም ተበሳጭተው መሄጃ አጥተው ዓለም የበላቻቸው፤ ደግሞም በስሕተት አረን ቋ፤ የሰጠሙ በፕሮቴታንቱ ዓለም የተወሰዱ ስንቶች ናቸው?  ለእነዚህ መጥፋት ተጠያቂውና ኃላፊውስ ማነው ?
ይህን ታሪክ የምጽፍላችሁ የዚህች አነስተኛ መጽሐፍ አቅራቢ ተወልጄ ያደግሁት በዚህች ቅድስት ቤተክርስቲያን ውስጥ ነው።  ከህጻንነቴ ጀምሮ በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ኮትኩተው ያሳደጉኝ፤  የቤተክርስቲያን ፍቅር እንዲኖረኝ በማእረገ ክህነት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንዳገለግል ያዘጋጁኝ ኦርቶዶክሳዊው ሊቅ መሪጌታ ባወቀ ተረፈ ናቸው።  ገና ደግና ክፉውን ሳላውቅ እጄን ይዘው እርሳቸው በሚቆሙባት ቅኔ ማኅሌት አጠገብ ከእግራቸው ሥር እንድሆን በማድረግ ፍቅረ ቤተ ክርስቲያንን ፍርሃተ እግዚአብሔርን ተምሬ አድጌአለሁ።
አብዛኛውን የሕጻንነት ጊዜዬን ያሳለፍኩት በደቡቡ የሀገራችን ክፍል ሲሆን በተለይም ባደኩባት በአዋሳ መካነ ሥላሴ ቤተክርስቲያን ገና ከታናሽነቴ ጀምሮ በስብከተ ወንጌል በመቀጠልም ከብጹእ አቡነ በርተሌሜዎስ ማዕረገ ዲቁናን 1976 . . በመቀበል እንደ እግዚአብሔር ፍቃድ ለአራት ዓመት በዲቁና በቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ አገልግያለሁ።

በዚህ ወቅትም በውስጤ ያለውን ፍላጎት ብፁዕነታቸው በቤተክርስቲያኒቱ ትምህርት ራሴን እንዳበለጽግ ከፍተኛ የሆነ አባታዊ ምክራቸውና ቅን ሃሳባቸው አልተለይኝም ነበር።  በተለይም ወደፊት ስለሚኖረኝ ሁኔታ ከወላጅ አባት በላይ ስለእኔ በማሰብ በአደባባይ ሳይቀር መልአኩን አዲስ አበባ ልኬ አስተምረዋለሁ በማለት ለእኔ ያላቸውን የወደፊት ሃሳብ ይገልጡ ነበር።

በተጨማሪም መልአከ ሰላም ኃይለ ኢየሱስ ከበደ፤ መልአከ ምሕረት ጳውሎስ ቀጸላ፤ መምህር ኃይለ ሥላሴ ይግዛው፤ ኦርቶዶክሳዊ የስብከተ ወንገል ምን ዓይነት እንደሆነ በማሳየት አርዓያቸውን ተከትዬ እንዳድግ ለስብከተ ወንጌል አገልግሎት ፍቅር እንዲኖረኝ አድርገውልኛል።
በተለይም በቤተክርስቲያን ታሪክ አስተማሪነታቸው ስፍራ ያላቸው መምህር ኃይለ ሥላሴ ይግዛው በአዋሳ የካህናት ማሰልጠኛ በሰጡኝና ቀን በሌት በትጋት ባስተማሩኝ ትምህርት፤ ስለ ቤተ ክርስቲያኔና ስለ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ፍቅር እን ዲያድርብኝ አድርገዋል።
በአዋሳ ለአምስት ዓመት ካገለግለኩ በኋላ በወላጆቼ መካከል የተፈጠረው መለያየት ስለ አሳዘነኝ በዚያ የወጣትነት ወቅት ተንስቼ ወደ ሐረር ሄድኩ።  ወደ ሐረር የሄድኩት በጊዜው በአዋሳ የማውቃቸው ቀሲስ መዘምር የክፍለ ሀገሩ ሥራ አስኪያጅ ሆነዋል የሚል ዜና ስለስማሁ ነበር። በወቅቱ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ የነበሩት ኦርቶዶክሳዊ አባት አቡነ ሳሙኤል የእድሜዬን አነስተኛነት አይተው ወደ ወላጆቼ ዘንድ እንድመለስ መክረውኝ ነበር። ነገር ግን ካደኩባት መንደር ስወጣ ወስኜ ስለ ነበር ብጹእነታቸው በእርሳቸው ሀገረ ስብከት እያገለገልኩ መኖር እንደምፈልግ ነገርኩዋቸው።
በሐረር ለመጀመሪያ ጊዜ በዲቁና ያገለገልኩት በደብረ ገነት መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን ነበር።  በዚያም ከአስተማሪ እጦት የተነሳ ተዘግቶ የነበረውን የሰንበት ትምህርት ቤት በአዲስ በማደራጀትና በዲቁና አገለግል ነበር።
በዚህ መካከል ነበር በዚያን ወቅት ሕይወቴን በአያሌው የለወጠው ነገር የተከሰተው።  ይኸውም በየዓመቱ የሚደረገውን የቀዳም ስዑር በኣል ምክያት በማድረግ ብጹዕ አቡነ ሳሙኤልን እንኳን አደረስዎት ለማለት በሐረር ከሚገኙ አድባራት ተሰብሰን ለዕለቱ የሚገባውን ሥርዓት እያደረስን እያለን የመካነ ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ወጣቶች ልብ የሚነኩ መዝሙራትን አቀረቡ።  ከመዝሙራቱም መካከል«ፍቅሩ አይለወጥም» «የሞት ላብ አላበው» እና የመሳሰሉት ነበሩ።  መልእክትና ዜማቸው እጅግ የሚነካ ስለነበር በዚያ የተሰበሰብውን ምእመን በሙሉ የሳበ ነበር።  ከዚያም በፊት በሩቅ የማውቃቸው የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ሰላም ጴጥሮስ በአባትነታቸው የሚያከናውኑት ነገር ልቤን ስለነካው እርሳቸውን በግል ማነጋገር እንዳለብኝ ወሰንኩ። ሳነጋግራቸውም በወጣትነቴ ቤተ ክርስቲያንን እንዴት ማገልገል እንዳለብኝ መክረውኝ መካነ ሥላሴ ክፍት የዲቁና ቦታ ስላለ እዚያ  እንድመጣ ትምህርቴንም እንድቀጥል ነገሩኝ።

በመካነ ሥላሴ ሰንበት /ቤቱን ለማደራጀት ከፍተኛ እንቅስቃሴ ስለነበረ በዚያ ወቅት ወጣቶችን በማስተማር በስብከተ ወንጌልና በዲቁና ማገልገል ጀመርኩ።  በዚያም ያለው የሰንበት /ቤቱ እንቅስቃሴ ወደ ስድስቱም አድባራት ተቀጣጠለ።

ወደ ቅዱስ ጳውሎስ /ቤት መግባቴ

ይህ በእንዲህ እንዳለ የሐረሩ የስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴ ከፍተኛ ደረጃ በመድረሱ ይህንን እንቅስቃሴ በሚገባ ለማንቀሳቀስ በቤተ ክርስቲያኒቱ ከፍተኛ ትምህርት ቤት በሚገባ የተማረ ካህን እንደሚያስፈልግ በማስተዋል ወደ ቅዱስ ጳውሎስ ከፍተኛ የነገረ መለኮት ትምህርት ቤት መዘጋጀት ጀመርኩ።

ወደ ቅዱስ ጳውሎስ ትምህርት ቤትም እንደገባሁ እግዚአብሔር ሁሉን አሟልቶ ከሰጣቸው ከመምህራኖቼ በሃይማኖቴ ላውቀው የሚገባኝን እንደ ካህንነቴም ላስተምረው የሚገባኝን በሚገባ ተምሬአለሁ።
በስዋሰወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ የቴዎሎጂ ትምህርቴን በምከታተልበት ወቅት እንደ አዲስ የተፈጠረው የቡድኝነት ስሜት ነበር።  ዛሬ የልጅነትና የእልክ ዘመን አልፎ በዚያ ውስጥ ያሳለፍኩትን  ያለመብሰል ጊዜ ሳስታውሰው እገረማለሁ።  ለነገሩ የድሮው ስህተት ሳያንስ ዛሬም በማኅበረ ቅዱሳን አባላት መካከል የሚታየው ጭፍን የሆነ ድርጅት ፍቅር ቤተ ክርስቲያን የሚጎዳ እንደሆነ ማን በነገራቸው ?

በዚያ ወቅት በትምህርት ቤቱ ውስጥ የነበርነው ደቀ መዛሙርት ለሁለት የተከፈለ አቋም ነበረን።  አንዳንዶቻችን የሃይማኖተ አበው ልጆች በሚሰበሰቡት በመንበረ ፓትርያርክ ስንሰበሰብ፤ ሌሎቹ ደግሞ በግቢ ገብርኤልና በምስካየ ሐዙናን በሚደረገው የማኅበረ ቅዱሳን ጉባኤዎች ላይ ይሰበሰቡ ነበር።  በተለይም በሃይማኖተ አበው ስበስባዎች ላይ በመገኘት አስተምር ስለ ነበር እኔን በማኅበረ ቅዱሳን ጥቁር መዝገብ ላይ ለማስፈር ጊዜ አልወስደባቸውም ነበር።  ነገሩን ለማርገብ የማኅበረ ቅዱሳንን  ከሚመሩት ጋር ለማነጋገር ሞክሬ ያገኘሁት ምላሽ ከሃይማኖተ አበው ጉባኤ እንዳንሄድና በኦርጋን የሙዚቃ መሳሪያ የሚጠቀሙትንና የመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ስንበት ትምህርት ቤቶችን የአዘማመር ስልት የተከተሉትን ሰንበት /ቤቶችን እንድናወግዝ ነበር።  ይህ ደግሞ የቤተ ክርስቲያናችን እምነትም ሆነ ሕያው የሆነው ታሪኳ ስለማይፈቅድልኝ አልተቀበልኩዋቸውም።

ምንም እንኳን በየአብያተ ክርስቲያናቱ የምሰጠው የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ተወዳጅ ቢሆንም ማኅበረ ቅዱሳን ግን የእኔንም ሆነ በሃይማኖተ አበው እና በሌሎች ሰንበት ትምህርት ቤቶች የምናገለግለውን በመናፍቅነት ከመፈረጅ ወደ ኋላ አላለም ነበር።  በተለይም አገልግሎታችን እየሰፋ ሕዝቡም ስብከታችን ትምህርታችንን እየወደደ ሲመጣ የኛ በአጸደ ቤተ ክርስቲያን መታየት ለማኅበረ ቅዱሳን ሕልውና አደጋ እንደሆነ እየተቆጠረ መጣ።

እዚህ ላይ መጠቀስ የሚገባው ይህ ሁሉ ሲሆን በእኛ በኩል የመላእክት ባሕርይ ይታይብን ነበር ማለት አይደለም።  በተለይም የቤተ ክርስቲያን አባቶች የሚሉንን አለመስማት፤ ችኮላ፤  የሕጻንነት ባሕርይ፤ አለመብሰል ከጉድለቶቻችን ዋናዎቹ ናቸው። ውጊያችን ለዘመናት የቤተ ክህነቱን ሥልጣን ለመጨበጥ ከሚያደባና  ስንት ሊቃውንትን ሲቻለው በአደባባይ፤ ሳይቻለው በስውር ሲያጠፋ ከነበረ ቡድን ጋር መሆኑን አለማወቃችን በብዙ ጎድቶናል።  ያም ሆነ ይህ የዚህ ቡድን ችሎታ የት ድረስ እንደሆነ የተገነዘብኩት ድሬዳዋ በነበረው ግድያ ነው።
በቅዱስ ጳውሎስ በቆየሁባቸው ዓመታት የክረምትን ወቅት የማሳልፈው በመጣሁበት ሀገረ ስብከት ማለትም ሐረርጌና አልፎ አልፎ ደግሞ በወላጆቼ አካባቢ ነበር። ሐረር እንደደረስኩም ከድሬዳዋ የሃይማኖተ አበው ተማሪዎች መልእክት ተቀምጦልኝ ነበር።  መልእክቱም ነሐሴ 21 ቀን 1986 . ጉባኤ እናከናውናለንና  እባክህ መጥተህ ብታስተምረን የሚል ነበር። በእውነቱ በጣም ነበር ደስ ያለኝ። ምክንያቱም እነዚህ ልጆች በብዙ የተገፉ ነበሩና።  በእኔ የልጅነት ሃሳብ የቤተ ክህነት ሰዎች የማኅበረ ቅዱሳንን ውትወታ ሰምተው ከቅጽረ ቤተክርስቲያን ባያስወጡአቸውም አንድ ቀን ወደ ቤተክርስቲያናቸው ሊመለሱ ስለሚችሉ እነዚህን ማጽናናትና ማረጋጋት ይገባል የሚል እምነት ነበረኝ።
ጉባኤው ወደ ሚደረግበት ወደ  ድሬዳዋ የገባሁት አንድ ቀን ቀደም ብዬ ነበር።  በዚያ ያሉ ወጣቶች በሙሉ ልባቸው ለጉባኤው እየተዘጋጁ ነበሩ።  ነገ የሚሆነውን የገመተም ያሰበም የለም።  ሁሉም የሚያስቡት አንድ ቀን የሚወዱት ማኅበራቸው ከተሰደበበት እንደሚነሳ፤ የቤተክርስቲያን አባቶች የእነዚህን ወጣቶች ምኞትና ሃሳብ አንድ ቀን እንደሚያዩት  ነበር። ይህ ነበር የነዚያ የዋሆች ልብ።
ጠዋት ድሬዳዋ እንደ ልማድዋ ደምቃለች።  እኔም ያደርኩበት ቤት በእንግዶች ግርግር ደምቋል።  ከአንዳንዶቹ ጋር በመሆን ወደ ጉባኤው አዳራሽ ሄድን።  ጉባኤው የሚካሄደው በከተማው አስተዳደር መሰብሰቢያ አዳራሽ ነበር።  አዳራሹ ከመቶ ዘጠና እጁ መስተዋት ብቻ የሆነ ውብ አዳራሽ ነበር።
ጉባኤው ምስባክ ተሰብኮ፤ በጸሎተ ወንጌል ከተከፈተ በኋላ የሃይማኖተ አበው ወጣቶች የሀገር ልብሳቸውን እንደለብሱ የዕለቱን መዝሙር አቀረቡ። በዚህ ሁኔታ ላይ እንዳለን ከፍተኛ የሆነ የሕዝብ ጩኸት ሰማን። ወዲያውም  የመጀመሪያው ድንጋይ የተሰበሰብንበትን አዳራሽ መስተዋት ሲሰብር ተሰማን።  የሰዎቹን ቁጥር ለማየት  አዳጋች ቢሆንም ብዙ ሰዎች በግልጥ ይታዩኝ ነበር።
በመጀመሪያ የመጡት ጥቂት ሰዎች ቢሆኑም ያዘው!  ስበረው ! ግደለው! ጩኸት ያሰሙ የነበሩት ግን ብዙ ነበሩ።
ይቀጥላል…………………………….