Friday, June 8, 2012

ቁም ነገር በፈገግታ!

 ቸልተኝነት እና አስተዋዩ ውሻ!

ከውል ውጩ በሚደርስ ኃላፊነት ህግ ውስጥ የቸልተኝነት ጥያቄ ከተነሳ ምላሹ ለብዙ ፍርድ ቤቶች ብዙውን ጊዜ አስቸጋሪ ነው፡፡ በብዙ የህግ ስርዐቶች ውስጥ ተቀባይነት ያገኘው የቸልተኝነት መለኪያ “የአንድ አስተዋይ ሰው ሚዛን” ሲሆን ይህም አንድ አስተዋይ ሰው በተመሳሳይ ሁኔታዎች ውስጥ ቢሆን ኖሮ ምን እንደሚያደርግ በመላምታዊ ፍሬ ነገር ላይ ተመስርቶ ማሰላሰልና ድምዳሜ ላይ መድረስን ይጠይቃል፡፡ እንግዲህ ቸልተኝነትን በአንድ አስተዋይ ሰው እይታ መዝኖ መወሰን አስቸጋሪ ከሆነ ይህን መለኪያ ለአንድ አስተዋይ ውሻ ተፈፃሚ ማድረግ ደግሞ በጣም ፈታኝ ብቻ ሳይሆን አስገራሚም ጭምር ነው፡፡

በአሜሪካም ኢሊዮኒስ ግዛት በኪርካም እና ዊል (Kirkham Vs. Will) መካከል በታየ አንድ የይግባኝ ክርክር ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት በጉዳዩ የተነሳው ጭብጭ የአንድ አስተዋይ ውሻ መለኪያ በመጠቀም እልባት ሰጥቶበታል፡፡ ክሱ የተጀመረው “የተከሳሽ ውሻ በንክሻ ላደረሰብኝ ጉዳት የውሻው ባለቤት የሆነው ተከሳሽ ካሳ ሊከፍለኝ ይገባል፡፡” በሚል ከሳሽ ባቀረበው ክስ ሲሆን ተከሳሹም በበኩሉ ከሳሽ የተነከሰው ውሻውን በመተናኮሉ ስለሆነ በራሱ ጥፋት ለደረሰበት ጉዳት ልጠየቅ አይገባም በማለት ተከራክሯል፡፡ ክሱ በስር ፍርድ ቤት ውድቅ ከተደረገ በኋላ በይግባኝ ክርክሩ ላይ በዋነኛነት የተነሳው ጭብጥ “መተናኮል አለ ወይስ የለም?” የሚለው ጥያቄ ነበር፡፡ ውሳኔውን የሰጡት ዳኛ ይህንን ጭብጥ ለመወሰን እንደመመዘኛ ወይም መስፈርት የተጠቀሙት የተለመደውን የአስተዋይ ሰው ሚዛን ሳይሆን የአንድ አስተዋይ ውሻ መለኪያ ነበርር፡ በዚህ ሚዛን ወይም መለኪያ መሠረት መተናኮል አለ ወይስ የለም የሚለውን ጥያቄ ለመወሰን በተመሳሳይ ሄኔታዎች ውስጥ አንድ አስተዋይ ውሻ ተከሳሽ ካሳየው እንቅስቃሴ አንጻር ምን ዓይነት ምላሽ ይሰጣል? የሚል መላምታዊ ጥያቄ አንስቶ ድምዳሜ ላይ መድረስን ይጠይቃል፡፡ ፍርድ ቤቱ ተፈጻሚ ባደረግው መለኪያ መሰረት የስር ፍርድ ቤትን ውሳኔ አጽንቶታል፡፡

source:  http://abookmedhin.wordpress.com/