Wednesday, June 20, 2012

ቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ተማሪዎቹን አስመረቀ



(ምንጭ፦ ዐውደ ምህረት)
    መምህር አሰግድ ሳሕሉም ከተመራቂዎቹ አንዱ ነው።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በስሯ ከምታስተዳድራቸው መንፈሳዊ ኮሌጆች መካከል አንዱና 69 ዓመት የዕድሜ ባለጸጋ የሆነው አንጋፋው ቅድስት ሥላሴ ኮሌጅ ያስተማራቸውን ደቀ መዛሙርት ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በተገኙበት አስመረቀ። የምረቃ ፕሮግራሙ ደማቅ የነበረ ሲሆን ተማሪዎቹ ቤተክርስቲያንን በቅንንነትና በመልካም ሥነ ምግባር ለማገልገል ቃል ገብተዋል። አዳራሹ በተመራቂዎችና በቤተሰቦቻቸው የተሞላ የነበረ ሲሆን በእያንዳንዱ ተማሪ ፊትም የሚታየው ደስታ ስሜት ልዩ ነበር። በዕለቱ አባታዊ ቡራኬ የሰጡት  ቅዱስ ፓትርያርኩም  “…ያለፉትን ዘመናት መሰናክሎችን እያለፍን መምጣታችን ስለምናውቅ ያለፉትንም ያለፍነው በራሳችን ስላልሆነ አሻጋሪውን አምላክ ከሁሉ በፊት እናመሰግናለን። እናንተ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ በኃላፊነት ላይ ነው ያላችሁት እያስረከብናችሁ ነው። በዚህ የተመደበ ሌላ ሥራ የለውም የወንጌል ሥራ በትርፍ ጊዜ የሚሰራ አይደለም። ሁሉንም የምንማረው በጊዜ ነው። ከዚህ በፊት ተምረው የወጡ ብዙ ናቸው። በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር ያሉ የገቡትን ኪዳን ይፈጽሙ አይፈጽሙ ተመልካቹ አምላክ ነው። መለኮታዊ አደራ ስለሆነ።….” በማለት አባታዊ መልዕክት አስተላልፈዋል።
አክለውም “…ከየትም ተነስቶ ለሃይማኖት ጠበቃ መሆን አይቻልም። ለሃይማኖት ጠበቃ ለመሆን ከእንደዚህ ካሉ መንፈሳዊ ኮሌጆች ተምሮ መውጣት ያስፈልጋል። በምድር ላይ ብዙ እውቀት ብዙ ትምህርት አለ። ያን እናከብራለን። ከየትም ተነስቶ ሃይማኖታዊ ነገር ለማድረግ አይቻልም። መንፈሳዊ እውቀት ከእንደዚህ አይነት ኮሌጆች ነው የሚወጣው።...
ከእንግዲህ በኋላ የዶግማችን፤ የሥርዓታችን፤ የቀኖናችን ምስክሮች አስተማሪዎች እናንተ ናችሁ። የሚጠበቅብን ትውልድ ማሳረፍ ነው። ከመንፈሳዊው ትምህርት ውጪ በሆነ እውቀት ፍልስፍናና ትምህርት የተራቀቀ ለእኛ ሃይማኖታዊውን እውነት የሚያብራራልን ሰው የለም። ከቤተክርስቲያናችን ሥርዓት ጋር አብሮ መታሰብ ያለበት አገልግሎታችንን የፍቅርና የሰላም ማድረግ ነው። በትዕዛዝ እኛ ያልናችሁን ፈጽሙ የሚል ግዳጅ አይሰራም።
ማኅበራችን አንዲት ናት ከዛ የተለየ ማኅበር የለንም። በርግጥ ታሪክ ራሱን ነው የሚደግመው የአጵሎስና የኬፋ ድሮም ነበር። ድምጽ ያላቸው ገንዘብ ያለቸው ሞንታርቮ ያላቸው ሲመጡ መደንገጥ የለም።
አሁን ልትሔዱ ነው። ወዴት? ልታስተምሩ። የእሱ ደቀ መዛሙርት ከመሆን ሌላ ሌላ መጠሪያ የማያስፈልጋችሁ ናችሁ።ከኛ የተለየ ነው ብሎ ዝም ብሎ ማውገዝ ማሳደድ ከጌታ ትምህርት የተለየ አካሄድ ነው። መጀመሪያ ማስተማር መምከር አንዴ አይደለም። ጌታ ለቅዱስ ጴጥሮስ ሲናገር የሰማናቸው ቁጥሮች አሉ። ደጋግሞ መምከር ዕድል መስጠት ያስፈልጋል። ከዛ በኋላ ነው መለየት የሚባለው ነገር የሚመጣው ዝርዝሩ አስፈላጊ አይደለም። ይገባችኋል የዘመናችን ሁኔታ ግን አንዲህ አይደለም ከጌታችን መመሪያና ከሐዋርያት ትምህርት አፈንግጠናል።
የመጣችሁት በአባቶች እግር ለመተካት ነው። ከሁሉ ጋር በአክብሮት ለመኖር የማይመሳሰሉን ቢኖሩ እንኳ ከእነርሱም ጋር ሀሳባችንን በአክብሮት ልንገልጽ የግድ ነው። መንፈሳዊ ሰው ከዚህ የተለየ መልክ የለውም።
ያልነኩንን አንነካም ቢነኩን እንኳ የምናስረዳ የምናስተምር ነን እንጂ። በአጠቃላይ አምላካችን የሚፈልገው ሁሉ በሰላም ሲኖሩ ማየት ነው። ስንተባበር ስንዋደድ ነው እርሱ ለማየት የሚፈልገው። ቤተክርስቲያን የራስዋ ሥርዓት አላት ዝምብሎ መዘርጠጥ መንቀፍ መሳደብ የቤተክርስቲያን ከመሆን የወጣ ነው።ተርፎን አይደለም እንዲህ አይነቱን ተቋም ያቆምነው ትውልዱን የሚተካ ትውልድ ለማምጣት እንጂ።…” የሚል ሰፊ ትምህርት የሰጡት ቅዱስነታቸው ለምረቃው ዝግጅት ድምቀት ሰጥተውታል።
ከሞላ ጎደል በሁሉም ተማሪዎች ዘንድ ከፍተኛ የደስታ ስሜትን የፈጠረው ትምህርትህን አቁም አላቆምም በሚል ብዙ ውጣ ውረድና የህግ ክርክር ውስጥ የነበረው መምህር አሰግድ ሳህሉ ትምህርቱን ጨርሶ መመረቅ መቻሉ ነው።
መምህሩ በማኅበረ ቅዱሳን አጋፋሪነት ትምህርቱን እንዲያቆም ከፍተኛ ውጊያ ቢገጥመውም በእግዚአብሔር ኃይልና ቸርነት ትምህቱን ጨርሶ ተመርቋል። በተለይም ምርቃቱ የሕግ ክርክሩ እስከ ሰበር ሰሚ ችሎት ደርሶ ባልተቋጨበት ሁኔታ መሆኑና ባለፈው አርብም የፍርድ ቤት ቀጠሮ የነበረው በመሆኑ የተማሪውን የይመረቅ ይሆን? ጥያቄ አርብ ስቅለት ነው እሁድ ደግሞ ትንሳኤ በሚል ንግግር የተደገፈ ነበር። ጉዳዩን በርካታ ቁጥር ያላቸው ተማሪዎች የጸሎታቸው ርዕስ አድርገው ይዘውት የነበረ ሲሆን አርብ ዕለትም የፍርድ ቤቱ ጉዳይ ምን ሆነ? በሚል አብዛኛው ተማሪ እርስ በራሱ ሲጠያየቅ እንደነበረ ታውቋል።
የሰበር ሰሚው ችሎት ቀጠሮ በሌላ ቀጠሮ እንደተተካ ሲሰማም፥  መምህሩ በእውነት በክርስቶስ ፍቅር የሚወዱት ብዙ ወገኖች አሉት በሚያሰኝ መልኩ ተማሪዎች በደስታ ስሜት ተውጠው ነበር። በመማር ማስተማሩ ሂደት ላይ መምህራን ውጤቱን እንዲያበላሹ ጫና ቢደረግባቸውም መምህራኑ ግን በፍጹም ጨዋነትና የሙያ ሥነ ምግባርን በጠበቀ መልኩ ለተማሪያችን የምንሰጠው ያገኘውን ትክክለኛ ውጤት ነው በማለት ተገቢውን ውጤት ሰጥተውታል።
ቅዳሜ ማታ የግቢው ደቀ መዛሙርት ተመራቂዎችን ለመሸት በግቢው የተማሪዎች የመመገቢያ ክፍል ውስጥ ባዘጋጁት የምስጋና ፕሮግራም በግቢው ታሪክ ተደርጎ የማይታወቅ የተባለ እና እስከ ምሽቱ አምስት ሰዓት የዘለቀ በውብ ዝማሬዎች የታጀበ የነበረ ሲሆን ተመራቂዎቹንም ሆነ የግቢውን ደቀ መዛሙርት በደስታ የሞላ ነበር። በዕለቱ የግቢው አካዳሚክ ዲን “…ያስተማርናችሁ የምናውቃችሁ እኛ ነን ህይወታችሁንም ሆነ ሃይማኖታችሁን በተመለከተ ሌሎች ምስክር ሊሆኑ አይችሉም። በየትኛውም ሀገረ ስብከት ሆናችሁ ለሚደርስባችሁ ፈተና ከጎናችሁ ነን። ከዚህ በፊት ተማሪዎች ነበራችሁ አሁን ግን መምህራን ናችሁ ቤተክርስቲያኒቱን የሚወክል ድምጽ ከእናንተ ነው የሚወጣውብለው የተናገሩ ሲሆን የዕለቱ መምህርም “---ጎሰኝነት ዘረኝነት እኔነት ጠባብነት መንደር ነው። ጌታ አይነስውሩን አይኑን ዳሶ ምን ታያለህ ሲለው ሰው እንደ ዛፍ ነው ብሎ የመለሰው፤ ዛፍን ከስሙ በቀር አይቶ የማያውቅ ሰው አየሁ ብሎ የመሰከረው ውሸት ነው፤ ሰው እንደ ዛፍ ሊሆን አይችልምና። ዛሬም ያላዩቱን አየን፤ ያልሰሙትን ሰማን እያሉ ውሸት የሚናገሩ ሰዎች አሉ። አጥርቶና አስተውሎ ማየት ካልተቻለ ዝም እንኳ ቢባል ምን አለ?” ብለው የጠየቁት መምህር በመቀጠል “…ሁለተኛ አይኑ ሲዳሰስ ግን አጥርቶ ማየት ችሏል። የእኛንም አይነ ልቦና መድኃኔዓለም ያጥራልን።በማለት ድንቅ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ከምረቃው ሥነ ስርዓት በኋላም ለመምህር አሰግድ አብዛኛዎቹ ተማሪዎች በመመረቁ የተሰማቸውን ደስታ ሲገልጹለት ታይቷል። በግቢው ውስጥ በነበረውና በኮሌጁ መመገቢያ አዳራሽ በተዘጋጀው የተመራቂ ተማሪዎች ፕሮግራም በርካታ ቁጥር የነበራቸው ዘማሪያንና ሰባኪዎች የተገኙ ሲሆን በፕሮግራሙ፥ ለተማሪዎቹ ባደረገላቸው ድንቅ ነገር እግዚአብሔር የተመሰገነበት በከፍተኛ እልልታ የታገዘ እንደ ነበር ለመገንዘብ ተችሏል። በወቅቱ ያስተማሩት መምህርም «ሰባተኛው ቀን» በሚል ርዕስ  ሲሆን ለተመራቂዎቹ እጅግ መልካም የሆነና በመንፈስ ቅዱስ የተመራ ምክር ሰጥተዋል። በግቢው ውስጥ በድንኳን ላይ የነበረው የማህበረ ቅዱሳን ፕሮግራም ግን ለቅሶ ቤት የመሰለ ከምስጋና ይልቅ አላማውን መብላትና መጠጣት ያደረገ ነበር። እነርሱን አጅበው የነበሩ ዘማሪያን ጭምር በነመምህር አሰግድ ፕሮግራም በመሳባቸው ዝማሬውን መጥተው የተቀላቀሉ ሲሆን አለቆቻቸው መጥተው አንድ በአንድ እየጠሩ በማስወጣት አብረው እንዳይዘምሩ አድርገዋቸዋል።
ከሰዓት በኋላም መምህር አሰግድ ሳሕሉ በሥላሴ ኮሌጅ በድግሪ መርሃ ግብር ይከታተል የነበረውን ትምህርት ጨርሶ ለመመረቅ መብቃቱን ምክንያት በማድረግ በጓደኞቹ አማካኝነት የተዘጋጀ የምስጋና ፕሮግራም ተደርጎለታል። ዝግጅቱ የነበረውን ሰው ሁሉ በእጅጉ ያረካ  እና በእውነት እግዚአብሔር ትልቅ ነው ያሰኘ ነበረ። መልካም የሆነው ጌታ መልካምነቱን ለልጆቹ እንዲህ ያሳያል። ሥራው ክስና አሳዳጅነት የሆነውን ጠላት ዲያቢሎስንም እንዲህ ያሳፍራል ያስባለ እና የጠላት ጭካኔና ግፍ በበዛ ቁጥር አብረው የሚሰለፉ ወገኖችን እግዚአብሔር እንዲህ ይሰጣል፤ ያሰኘ የምስጋና ፕሮግራም ነበር። የዕለቱ ፕሮግራም መሪ ፕሮግራሙን ውብ በሆነ አቀራረብ የመራ ሲሆን በርካታ ሰዎችም በፕሮግራሙ ላይ ተገኝተው እግዚአብሔርን በዝማሬና ቃለ እግዚአብሔርን በመስማት አመስግነዋል።
የዕለቱ መምህር ስለማዕዘኑ ራስ ክርስቶስ ያስተማሩ ሲሆን “…የመሰረቱ ድንጋይ ላይ ቆሞ አልነቀፍም ማለት አይቻልም። የምስክሩ ዓለት የማዕዘን ራስ የተባለው ክርስቶስ ነው።…” ሲሉ አስተምረዋል፡፡
የመኪና አደጋ በደረሰበት በዓመቱ ምርቃቱን ያከበረው መምህር አሰግድ በሰጠው ምስክርነት “…የዛሬው ዕለት ለሙት ዓመት እንጨት የሚሰበርበት ሊሆን የሚችል የነበረ ቢሆንም ከወገኖቹ ጋር አብሮ በመሆን እግዚአብሔርን እያመሰገነበት መሆኑን ተናግሯል። አራት ጊዜ ከተገለባበጠ መኪና ተርፎ ለእንዲህ ያለ ክብር መብቃት በራሱ ተዓምር መሆኑንም መስክሯል።
እንኳንስ እንዲመረቅ እንዲማርም የማይፈልጉ አካላት ትምህርቱን እንዳይቀጥል ምን ያህል ትግል እንዳደረጉ በማስታወስ ንግግር ያደረገው መምህር አሰግድየማያምን ሰው ወደ እኔ መጥቶ ሊማር ቢፈልግ እንዴት አድርጌ እንደማስተምረው እኔ ነኝ። የማውቀው እንኳን እኔ ቤቴ ነው ብዬ መጥቼ፤ ደግሞም ቤቴ ነው!  ከዚህ ሌላ ቤት አላውቅም፤ የለኝምም።…” ሲል ተደምጧል።
መምህሩ ነገሩን በማብራራትም “…ግቢው የራሱ የህግ ባለሙያ እያለው ማቅ ቀጥሮ ባቆመው ጠበቃ እንደሞገተው እና ባይነካኩን ኖሮ ምርቃቱ ይሔን ያህል ባላማረ ነበር። እየደቋቆሱ እንዲህ አስከበሩን፤ ታሪካችንን አስጌጡት። ምርቃት ብርቅ አይደለም። ምርቃት ብቻ ቢሆን ኖሮ እኛ በዚህ ሁኔታ እዚህ ባልቆምን ነበር። ይህንን ፕሮግራም በቅንነትና በእልህ ያዘጋጁ ሰዎችም እንደዚህ ሆነው አይነሱም ነበር። አሳዳጆቻችን ከነክፋታቸው መቀጠላቸው እነርሱን የበለጠ ቢጎዳቸውም ይጥፉ ግን አንልም። እግዚአብሔር ልብ ይስጣቸው፤ ለኛ ሞገስ ጨምረውናል።ብሏል።
በመቀጠልም “…እኔም ወግ ደርሶኝ በስሙ ተነቅፌያለሁ። 18 ዓመት በፊት ጀምሮ የነበረው ትግል አምላካችንም አሁንም በድል ኣሻግሮናል። 18 ዓመት በፊት የከሰሰሱን ሰዎች መናፍቅ ይሆናል ጴንጤ ይሆናል እያሉ ቢጮሁም ያሉት ሳይሆን ቀርቶ እስከዛሬ ድረስ ቤተክርቲያንን ማገልገሌ የእግር አሳት ሆኖባቸው ከአባታቸው በተማሩት መሰረት ዛሬም ለክስ ዛሬም ለሀሰት ምስክርነት ሲሯሯጡ መመልከት እጅግ አሳዛኝ ነው።ያለው መምህር እንዲህ ያለውን የክስና የጥላቻ መንፈስ “…ሳዖል ዕድሜውን ሙሉ ለዳዊት ጠላት ሆነው የሚለውን ቃል ያስታውሰናል።በማለት የአንዳንድ ሰው የጥላቻ ባህሪ በቀላሉ የማይለወጥ መሆኑን ገልጿል።
ከዝግጅቱ በኋላ በርካታ ሰዎች የአበባ ጉንጉን ለመምህሩ ስጦታ የሰጡ ሲሆን በተለይም «ውሾች ከበቡኝ» በማለት መጽሐፍ የጻፉት መምህር ወንደሰን ለመምህሩ አበባ ሲሰጡ ያዩ ወገኖች በማኅበረ ቅዱሳን ከፋፋይ ሀሳብ ተከፋፍለው የነበሩ ወንደሞችእንዲህ እንደገና መቀራረብ መቻላቸው አስደሳች ነው።በማለት እግዚአብሔርን አመስግነዋል።
በአጠቃላይ ዝግጅቱ የነበረውን ሰው ሁሉ ያረካ በከፍተኛ ዝማሬ የተሞላ የማያቋርጥ እልልታ ያጀበው እጅግ ያማረና ውብ ነበር፡፡