አንዳንዶች ማኅበረ ቅዱሳንን የሕይወታቸው አንድ
አካል አድርገው ይመለከቱታል። የማኅበረ ቅዱሳን ሞት ሞታቸው፤ ሕይወቱ ደግሞ ሕይወታቸው አድርገው ስለሚመለከቱ ሲወቀሱ ወይም ሲተቹ
ኅሊና እንዳለው ሰው ሳይሆን ዛር እንደሰፈረበት ሰው ያንዘፈዝፋቸዋል፤ ያወራጫቸዋል። እስከለሞት ስለሚሟገቱለት ማኅበር፤ ማንነት ተረጋግተው አሳማኝና ማስረጃ ያለው መልስ በመስጠት
በግንዛቤ የተሳሳተ ካለ በመመለስ ወይም እንደጠላት የሚቆጥሩትን ክፍል
የሚንቁ ከሆነም ዝም ብለው እንደትቢያ ቆጥረው ከማለፍ ይልቅ ስድብ፤
ዛቻና ማስፈራሪያ፤ ጴንጤ፤ ተሐድሶ፤ መናፍቅ፤ አህያ፤ ውሻ፤ ደደብ፤ ከሐዲ፤ ሌባ ወዘተ ቃላቶችን በመጠቀም ተቀናቃኝ ነው ለሚሉቱ ሁሉ መጠቀምን ባህላቸውና የእምነታቸው
አንዱ ክፍል በማድረግ ሲጠቀሙበት መመልከት እንግዳ ነገር አይደለም። ከአፍቃሬ ማኅበሩም ይሁን የማኅበሩ አንድ አካል ከሆኑት አባላቶቹ
የሚሰጡን አስተያየቶች የሚያሳዩን ያንን ነውና።
ከዚህ ሁሉ አስተሳሰቦቻቸው የምንረዳው ነገር ቢኖር
የማኅበረ ቅዱሳን አባላትም ይሁኑ የደጋፊዎቹን ማንነት ሲሆን ከእነሱ የተለየ ሃሳብ ላለው ሁሉ መልስ መስጠት የማይችሉ፤ ነገሮችን ሁሉ በኃይልና
በዘለፋ ለመፍታት የሚመኙ፤ «ሁሉም መንገዶች ወደ ማኅበረ ቅዱሳን ያመራሉ» ካልሆነ በስተቀር ሌላ መስማት የማይፈልጉ ስታሊናዊ አመለካከት
የታጠቁ ሰዎች ስብስብ መሆናቸውን ብቻ ነው።
አሁንም ስለማኅበረ ቅዱሳን መሠሪ ማንነት የምናቀርባቸውን
አንዳንድ ነጥቦችን ተከትለው ያንኑ የተለመደ አፋቸውን በመክፈት ከዚያ አልፎ ያለውን የአእምሮአቸውን በር ከፍተው እንደሚያሳዩን በመጠበቅ፤ የማኅበሩን መሠሪነት የሚጠቁሙ ጭብጦችን በአስረጂ
ለማስቀመጥ እንሞክራለን።
1/ ስውር ሚዲያዎችን የመጠቀም መሠሪነት፤
ማኅበሩ በግልጽ የሚታወቁ የራሱ የሆነ የሚዲያ
ኃይሎች አሉት። የጽሁፍና የኤሌክትሮኒክ ሚዲያዎቹ በየጊዜው በሚለዋወጡ
አገልጋይ ሰዎቹ አማካይነት ሌሊትና ቀን ለማኅበሩ የስም ግንባታ ይሰራሉ። እነዚህ የሚዲያ ተቋማት ስለማኅበሩ ማንነት በሰፊው መረጃ
ማድረስ ብቻ ሳይሆን ማኅበሩን በማጠናከር ለፖለቲካ ጡንቻ ግንባታ
የሚያግዝ የገቢ አቅሙንም ያሳድጉለታል። የሕትመት ውጤቶች እንደ ስምዓ ጽድቅና ሐመር መጽሔት፤ መጻሕፍቶች፤ ካሴትና ሲዲ፤ እንዲሁም
ሱቆች፤ ሆቴሎች፤ የገቢ ማሰባሰቢያ መድረኰች፤ የመዋጮና የበጎ አድራጎት ገቢዎች በየፈርጁ የተመሰረቱ የገቢ መንገዶች ስለመሆናቸው
ሁሉም የሚስማማበት እውነት ነው። ዘመኑ ደግሞ «ገንዘብ ካለ በሰማይ መንገድ አለ» የሚል ፈሊጥ የነገሠበት እንደመሆኑ መጠን ይህንኑ
ዓለማዊ ብሂል በደንብ የተረዳው ማኅበሩ፤ የሚፈልገውን አፍ በሚገባው ቋንቋ ለማናገርም ይሁን ያስቸገረውን አፍ ደግሞ በአንድ ወቅት ፍልስጤማውያን የይስሐቅን ምንጭ በድንጋይ እንደጠረቀሙት፤
እሱም ለመጠርቀም የሚያስችል የኃይልን ምንጭ አድርጎ ይገለገልበታል። ዘፍ 26፤18
ይህ እንግዲህ የሚታይ የሚጨበጥ የአደባባይ እውነት
ነው። በነዚህ ሁሉ መንገዶች ማኅበሩ ስለመልካም ስሙ ሚዲያዎቹን አይጠቀምም ወይም የገቢ አቅሙን እያሳደገበት አይደለም የሚለን ቢኖር
ይሁንልህ ብለን ከማለፍ ባሻገር ለማሳመን መሞከሩ ነጩን ነገር ጥቁር
ነው ብሎ ከሚከራከር ሰው ጋር መታገል ስለሚሆንብን እናልፈዋለን።
ማኅበሩ ይህን ሁሉ በግልጽ የሚጠቀምበት መንገድ
ሲሆን በስውር የሚገለገልባቸው መንገዶች፤
ዋናው የማኅበሩ ድረገጽና በዓለም ዙሪያ ያሉ የክፍል
ድረ ገጾች በተጨማሪ፤
ሀ/ ደጀ ሰላም
ለ/ አንድ አድርገን
ሐ/ አሐቲ ተዋሕዶ
መ/ አደባባይ
እና ሌሎች መካነ ድሮችን ለዓላማው መሳካት በግልጽና
በስውር ይጠቀምባቸዋል። ደጀ ሰላም ብሎግ ሥራውን ሲጀምር /dejeselam owned by mahibere kidusan/ሲል የነበረውን
ቢቀይረውም ጉግል በኢንዴክስ ውስጥ የመዘገበውን ይኽንኑ ስም ያሳይ እንደነበር አይዘነጋም። እነዚህ ብሎጎች ለማኅበረ ቅዱሳን ተግተው
እንደሚሰሩ የሚያረጋግጠው አንድም ትችት ወይም ነቀፋ በማኅበሩ ላይ አያቀርቡም ብቻ ሳይሆን በቀሳፊው ማኅበር የተጨነቀው ዲ/ን ዳንኤል
ክብረት የደረሰበትን ወከባና የማኅበሩን ማንነት በመዘርዝር በደጀ ሰላም ላይ ያወጣውን ጽሁፍ በሰዓታት ልዩነት መደምሰሳቸው ከምንም በላይ አረጋጋጭ ነው። ማኅበረ ቅዱሳን የሰዎች እንጂ የቅዱሳን መላእክት
ማኅበር ባለመሆኑ አንዳችም ማኅበራዊ ስህተትም ይሁን ግድፈት እንደሌለው በመቁጠር የእርምት ወይም የትችት ዘገባ አለማቅረባቸው እንዲሁም የቀረበበትን ማውረዳቸው፤
ማንነታቸውን ከምንም በላይ የሚያረጋግጥልን ይሆናል። እንዲያውም ማኅበረ ቅዱሳን ሲነካ ወይም ስሙ ሲነሳ አንድ ላይ እየተቀባበሉ
መንጫጫታቸው አስገራሚነቱን ከፍ ያደርገዋል። በገለልተኝነት መታዘብም
የነበረ ወግ ቢሆንም እነርሱ ግን ከዝምታ ባለፈ ልክ ዓይናቸው ውስጥ ጉድፍ እንደገባ ህጻን
ከዳር እስከዳር ጩኸታቸውን እንደማኅበሩ ሕጋዊ ወኪል ማስተጋባታቸው ለራሳቸው የማይታወቃቸውና ሌላውም ይታዘበናል
የማይሉ መሆናቸው ይገርመናል ። ምንም እንኳን መደገፍም ሆነ መቃወም
መብታቸው ቢሆንም እነርሱ ግን በአንድ ድምጽ አንድም ቀን ሳይቃወሙ ሁል ጊዜ በመደገፍ መቆማቸው የማን ተልእኰ ፈጻሚ መሆናቸውን
ተመልክተን ሁሉንም የማኅበረ ቅዱሳን ብሎጎች ናቸው ብሎ መናገር ይቻለናል። ከማኅበረ ቅዱሳን መሠሪ ባህርያትም መካከልም አንዱ በግልጽ ከሚታወቀው መገልገያ መንገዶቹ ውጪ በስውር
እጁ በብዙ ብሎጎች መጠቀም መቻሉ ነው። በዚህም መንገድ ዓላማውን
ያዳርሳል፤ ያስተዋውቃል፤ የሚቃወመውን ይመታበታል፤ ዜናና ዘገባ ይሰራበታል።
ይህንንም ስውር ሚዲያዎችን መጠቀሙን የማኅበሩ
መሰሪ መገለጫ ቁጥር አንድ ብለነዋል።
2/ የሚጠላውን ነውር በመግለጥ ማጥቃት፤ የሚያገለግለውን
ነውር በመሸፈን የመጠቀም መሠሪነት፤
ሌላው የማኅበሩ መሠሪነት መገለጫ ደግሞ ቅዱስ
መስሎ ለመታየት የመሞከሩ ነገር እንደተጠበቀ ሆኖ በግልጽ የራሱን የሚዲያ በመጠቀምም ይሁን በስውር አገልጋይ ሚዲያዎቹ በኩል በኅቡዕ ጽሁፎቹ የሚጠላቸውን አፈር ድሜ እያስጋጠ፤
የሚያገለግሉትን ነውራሞቹን ደግሞ እየካበ መጠቀም መቻሉ ነው። አንዳንድ ጅል ደጋፊዎቹ ማኅበሩ እንደስሙ ቅዱስ እየመሰላቸው ቢሟገቱለትም
ራሱ ነውራም ስለሆነ ነውራም የቤተክርስቲያን ሹማምንት ሊያገለግሉት
ፈቃደኝነታቸውን እስካሳዩት ድረስ ለእዳ በደላቸው ስርየት በመስጠት ሲገለገልባቸው እያዩ፤ አያዩም። እምቢ ያሉትንና የሚቃወሙትን
ደግሞ እዳ በደላቸውንና ኃጢአታቸውን በስውር ብሎጎቹ እየዘገበ፤ የስም ማጥፋት ዱላውን ሲያወርድባቸውም እየሰሙ፤ አይሰሙም። ለምሳሌ
ያህል አባ ሠረቀ ብርሃን ወ/ሳሙኤል፤ መጋቤ ሐዲስ በጋሻው ደሳለኝ፤ መምህር እንቍባህርይ ተከስተ፤ ብጹእ አቡነ ፋኑኤል፤ ብጹእ
ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ፤ ዘማሪት ምርትነሽ፤ ዲ/ን ትዝታው ሳሙኤል፤ ቀሲስ ተስፋዬ መቆያ፤ አባ ወ/ትንሳዔ አያልነህ፤ ዲ/ን ኃይለ
ጊዮርጊስ ጥላሁን፤ መምህር አእመረ አሸብር፤ መምህር ዳንኤል ሰይፈ
ሚካኤል ወዘተ ዓይነቶቹ ላይ ዘመቻውን ባለ በሌለ ኃይሉ ይጠቀማል። እነዚህንና ሌሎች ተቃራኒዎቼ ናቸው የሚላቸውን ሰዎች በተመለከተ ለነገ ሳይል እዳ በደላቸውን በመዘገብ ይዘምትባቸዋል። ሰሞኑን
እንኳን ገና ለገና ተፎካካሪ ማኅበር ሊያቋቁሙብኝ ነው ከሚል ጭንቀት የተነሳ በእነዚህ ሰዎች ላይ የስድብ አፉን ከፍቷል። እርሱ
ራሱ በቤተክርስቲያኒቱ ላይ የተቋቋመ ማኅበር ሆኖ ሳለ ሌላ ማኅበር በቤተክርስቲያን ውስጥ መቋቋም የሌለበት እስኪመስል ድረስ እንኳን
ክርስትና ሊኖረው ይቅርና ኅሊና ካለው ሰው ባነሰ የጥላቻ ዘመቻ መክፈቱ ማንነቱን ቁልጭ አድርጎ ከማሳየት በዘለለ ምን ዓይነት መሠሪ
እንደሆነ አረጋግጧል። ማኅበር አያስፈልግም የሚል ከሆነ እራሱን ማፍረስ ይጠበቅበት ነበር። ነገር ግን እራሱን በማኅበር ስም አስቀምጦ፤
ለምን ሌላ ማኅበር ይቋቋማል? ብሎ መጮህ በቤተክርስቲያኒቱ ላይ ከተቀመጠበት ማማ ላይ እንዳይወርድ አስቀድሞ በሩን መዝጋት ከሚል ምቀኝነትና ፍርሃት ከወለደው አእምሮ የመነጨ እንደሆነ ለመገንዘብ አይከብድም።
ይህንን አቋሙን ለማራመድም ስውር እጆቹን ይጠቀምባቸዋል። የሚጠላቸውን እንደሚጨፈጭፍበት ሁሉ ነውር የሞላባቸውን ታማኝ አገልጋዮቹን
ግን አንድም ነገር አይተነፍስባቸውም። በአንድ ወቅት ዲ/ን ዳንኤል በበጋሻው ላይ ማኅበሩ የተነሳው ስላልተመቸው እንጂ ስለሃይማኖት ግድ ብሎት
እንዳልነበረ መናገሩ እዚህ ላይ ለዋቢነት ይነሳል።
ስማቸውን እዚህ ጋር መዘርዘር የማያስፈልግ፤ ነገር ግን ብዙ ገመና የሚወራባቸውና
የተገኘባቸው ሰዎች እንዳሉ ቢታወቅም ማኅበሩ አንዳች ነገር በእነሱ ላይ እንዲነገር የማይፈልገው እዳ በደላቸውን ስለማያውቅ ሳይሆን
ከነጉድፋቸው ስለሚያገለግሉት ብቻ ነው። ስለጉድ ሙዳዩ ጳጳስ ማንነት
በተለያዩ ብሎጎች ተጽፎ ሲገኝ፤ ማኅበሩ« የተሐድሶ አቀንቃኝ ብሎጎች ጥይታቸውን ሲጨርሱ ወደ ስም ማጥፋት ገቡ» የሚል መከላከያ
እስከማቅረብ አጋርነቱን አሳይቶላቸዋል። እሱ ሲጠላ ደግሞ «ስለ አባ አእምሮ ሥላሴ ታከለ» መጠን አልባ ወንጀልና ኃጢአት በደጀ
ሰላም ብሎጉ ዜና ሲሰራባቸው ጥቂት አላፈረም። ያሳሰበው የአባ አእምሮ ሥላሴ ወንጀልና ኃጢአት ቁጥር መብዛት ሳይሆን በገቡበት የአዲስ
አበባ ሀ/ስብከት ም/ሥራ አስኪያጅነት የሥራ መደብ ላይ ታማኝ አገልጋይ የመሆን ብቃት ስለሌላቸው አስቀድሞ ጥቅሙን ከማስላት የመነጨ
ስም ማጥፋት እንጂ ለቤተክርስቲያን አስተዳደር ከመጨነቅ አንጻር አይደለም።
በሁለተኛ ነጥብ ለማሳየት እንደተሞከረው ከማኅበሩ
መሠሪ መገለጫዎች ውስጥ አንዱ ይኼው የሚፈልጋቸውን አገልጋዮቹ ነውራሞች ቢሆኑ እንኳን ግድ ሳይለው በእነሱ መጠቀም መቻል ሲሆን፤
የሚጠላቸውን ደግሞ እዳ በደላቸውን በመግለጽ ድባቅ በመምታት ዓላውን
ማሳካት ነው። እሱን እስከጠቀመው ድረስ በቤተክርስቲያን ውስጥ የነውር መስፋፋት ወይም መቀነስ ጉዳዩ አይደለም። ማንም ኅሊና ያለው
ሰው እንደሚፈርደው ማኅበሩ የሚደግፋቸው ነገር ግን በሌሎች ሰዎች ችግር እንዳለባቸው የሚነገርባቸውን ሰዎች ማንነትና ከማኅበሩ ጋር
የተስማሙት ነገር ሲጻፍባቸው እብደት ሲቃጣው፤ እርሱ ደግሞ የማይፈልጋቸውና ያላገለገሉትን ደግሞ በልዩ ልዩ መንገድ ስማቸውን እያጎደፈ መገኘቱን በተነጻጻሪ በመመልከት ስለማኅበሩ
ማንነት መረዳት እንደማይከብድ እንገምታለን። ለዚህም ማሳያ የሚሆነው አቡነ ፋኑኤል ሲሆኑ የእሳቸው ጵጵስና ከማኅበረ ቅዱሳን ደጋፊ
ጳጳሳት የሚያንስ ይመስል እሳቸው ላይ ያለ የሌለ ኃይሉን ሲያወርድ ደጋፊዎቹ ሲነኩ ግን አባቶችን የሚያዋርዱ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶዎች
ናቸው የሚል መከላከያ ሲያቀርብ መመልከቱ ነገሩን ሁሉ አስተዛዛቢ ያደርገዋል።
3/ ሃይማኖታዊና ፖለቲካዊ ስልቱን አስማምቶ የመጓዝ
መሠሪነት፤
የማኅበሩ ዋና ጸሓፊ የሆነው መምህር ሙሉጌታ ኃ/ማርያም
ለእንቁ መጽሔት የሰጠውን ቃለ ምልልስ አስመልክቶ ዲ/ን ዳንኤል ክብረት
ያቀረበው አንዱ ትችት “እውነቱን ለመናገር አብዛኞቹ የማህበረ ቅዱሳን አባሎች የኢሕአዴግ ደጋፊና አባላት ናቸው” የሚለው ንግግሩን
ነበር። መምህር ሙሉጌታ ይህን ስልታዊ ቃል መጠቀም የፈለገው አፍቃሬ ኢህአዴግ መሆኑን ለማሳየት ስለፈለገ ሳይሆን አብዛኞቻችን የኢህአዴግ
ደጋፊ ስለሆንን በእኛ ላይ የሚኖራችሁ ማንኛውም ትኩረት ከጥርጣሬ የጸዳ ይሁን የሚል ማዘናጊያ መልእክት
ለማስተላለፍ ፈልጎ መሆኑን ነው። እንደማኅበሩ ዋና ጸሐፊነት ሊናገረው የሚችለው ኃላፊነት የማኅበሩን ዓላማና ተግባር እንጂ የማኅበሩ
አባላት የግል አመለካከትና የፖለቲካ አቋም ከማኅበሩ ጋር የተሳሰረ ኢህአዴጋዊ ነው ወደ ማለት ባልደፈረም ነበር።
አባላቱ ሲሰበሰቡ ስለማኅበሩ አገልግሎት እንጂ
ስለእያንዳንዳቸው የፖለቲካ አቋም የሚነጋገሩበት የፖለቲካ የአጀንዳ ከሌላቸው ማን የትኛውን ፓርቲ እንደሚደግፍ በምን ያውቃል? ብዛቱንስ
በምን ይለካል? መምህር ሙሉጌታስ ስለምን ይሆን አብዛኛዎቻችን የኢህአዴግ ደጋፊ ነን ለማለት የፈለገው? ብለን ብንጠይቅ የማኅበሩን
መሠሪ ዓላማ በማስተላለፍ ስልታዊ እንቅስቃሴውን ከኢህአዴግ ፊት ለመሰወር ብቻ ይሆናል የሚል መልስ እናገኛለን።
ምክንያቱም ከማኅበሩ አባላት ውስጥ እንዲያውም አብዛኛው ጸረ ኢህአዴግ አቋም ያለው እንደሆነ የሚታወቀው ሙሉጌታ ደጋፊ ነን ከሚለው
በተቃራኒ መልኩ በተለያዩ ብሎጎቹ ጸረ ኢህአዴግ አቋሞቹን ሲያስተላልፍ መገኘቱ የጽሁፍ መድረኮቹ የአፉን ንግግር ፉርሽ ያደርጉበታል። ቆቅ የሆነው ኢህአዴግም ይህ እውነት ይሰወርበታል
ብለን አንገምትም። ከዚያ ባሻገር ከ100ሺህ በላይ አባላት አሉኝ የሚል ማኅበር የተለያየ አመለካከት የያዙ ሰዎች ስብስብ ከመሆን
በዘለለ አብዛኛዎቻችን አፍቃሬ ኢህአዴግ ነን የሚል ዜና ከማኅበሩ መሪ መደመጡ ስልታዊ መሠሪነት እንጂ ሌላ ምን ሊሆን አይችልም።
ለኢህአዴግ የመተማመኛ ቃል በመስጠት ስልታዊ ማፈግፈግን በተለያዩ ብሎጎች መጠቀም ማኅበሩ ሃይማኖትንና ፖለቲካን
አስማምቶ መጓዝ ከመሠሪ መገለጫዎቹ አንዱ ስለሆነ ነው። ኢትዮጵያ ባለው አንድ እግሩ አፍቃሬ ኢህአዴግ ነው፤ አሜሪካ ባለው አንድ እግሩ ደግሞ የተቃውሞ ሰልፍ አስተባባሪ
ነው። ይሁን እንጂ ይህ ስልታዊ እርምጃው፤ ሰለፊያነቱን መሸሸግ አልቻለም።
4/ እራሱን በቤተክርስቲያን ውስጥ አሳይቶ ከቤተክርስቲያን
የመሰወር መሠሪ ስልት፤
ማኅበረ ቅዱሳን የቤተክርስቲያን ልጅ ነኝ ይላል።
ልጅ ራሱን ችሎ ጎጆ እስካልወጣ ድረስ ወላጆቹ ስለልጃቸው ኃላፊነት እንዳለባቸው አያጠያይቅም። ማኅበሩ ሲነግድ፤ ሲያተርፍ፤ ገንዘብ
ሲሰበስብ፤ ሲያስወጣና ሲያስገባ እናቴ የሚላት ቤተክርስቲያን ስትጠይቀው ያንቺ የኔ ነው፤ የኔም ያንቺ ነው በማለት ፈንታ ምን አገባሽ?
እያለ በእናቱ ላይ የሚያፈጥና የሚቆጣ ልጅ ባለጌ ካልተባለ ምን ሊባል ይሆን?
እንዲያውም ምን አገባሽና ነው እኔን የምትጠይቂው?
ያንቺን ገንዘብ መች አወቅሽውና ነው የእኔን ለማወቅ የምትፈልጊው? የሚል ልጅ በምንም መልኩ የእናቱ አፍቃሪ ወይም የልብ ወዳጅ ሊሰኝ አይችልም። እናቱን የሚፈልጋት ለስምና ለመጠሪያ ካልሆነ በስተቀር። ማኅበረ
ቅዱሳን ያለውን ሀብት ለቤተክርስቲያኒቱ ማሳወቅ የማይፈልገው ለምንድነው? ለምንስ ይሆን ሲጠየቅ ዙሪያ ጥምጥም የሚሄደው? በህጋዊ
የቤተክርስቲያኒቱ የገቢ መሰብሰቢያ ሞዴሎች ላለመሰብሰብ ሲል እንዳልተገራ ወይፈን የሚዘለው ለምን ይሆን? ሰዎችን ለማሳደድ ሲፈልግ
ብቻ እንደመጠቀሚያ መሣሪያ የሚገለገልበት ሊቃውንት ጉባዔ «ሐመርና ስምዓ ጽድቅ» ጋዜጣህን ይመርምር ሲሉት እምቢ፤ አሻፈረኝ ብሎ
እንደባለጌ ልጅ ሳይመቱት የሚያለቅስበት ምክንያቱ ምንድነው?
መቼም ጽድቁ ስለበዛና ቅድስናው ጣሪያ ስለደረሰ
ነው የሚለን እንደማይኖር ተስፋ እናደርጋለን። እስከሚገባን ድረስ ዋናው ምክንያት እራሱን በቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ አሳይቶ ነገር
ግን ከቤተክርስቲያኒቱ ውጭ የመሰወር አንዱ መሠሪ ስልቱ ስለመሆኑ የሚጠራጠር ቢኖር እርሱ ጅል ነው። እንደዚያ ካልሆነ በስተቀር አገልግላታለሁ ከሚላት ቤተክርስቲያን የሚሰውረው
አንዳች ሃብትና ንብረት ሊኖረው ባልተገባ ነበር። አመራሮቹ የሚበቃቸውን
የሚቦጭቁበት የድህነት መቅረፊያ መድረክ እንደሆነ ሲዘገብ ከቆየውና ለልማት አውዬዋለሁ ከሚለው የተረፈውን ደግሞ ለመሰወር ሲፈልግ «ለኅዳሴው ግድብ ቦንድ እገዛለሁ« ሲል በአንድ በኩል የመንግሥት
የትርንስፎርሜሽን እቅድ ደጋፊ መስሎ ለመታየትና በሌላ መልኩ ቤተክርስቲያኒቱ በጎ አላማዬን ለማደናቀፍ ስለገንዘቤ የልማት ጉዳይ ትጨቀጭቀኛለች በሚል ሁለት መሠሪ ስልት ያስቸግር እንደነበር ማደራጂያ መምሪያው መግለጹ አይዘነጋም።
ሲጠቃለል ማኅበሩ የሚነግደውና የሚያስነግደው፤ ቤተክርስቲያኒቱ እንደከለላ
ሆና አካሉን ግን ከደጅ አውጥቶ በሁለት እስስታዊ ጠባይ እንደሚጠቀምባት የሚያስረዳን ሆኖ ተመዝግቧል።
ማኅበረቅዱሳን በእነዚህ መሠሪ ስልቶቹ የረቀቀ
ብልሃት ስለሚጠቀም ሲያዩት ወርቅ ይመስላል። ነገር ግን ቀረብ ብለው ሲያጠኑት በቅብ የቆነጀ ሸክላ መሆኑ ይከሰትለታል።