ከዶ/ር አምሳሉ ተፈራ
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፊሎሎጂ ዲፓርትመንት
ረዳት ፕሮፊሰር
ለሁሉ ፈጣሪ ለእግዚአብሔር ራስን መቀደስና ከኃጢአት መለየት ለሰው ሁሉ የቀረበ ጥሪ ነው። ይህን ዘንግተው የነበሩ ሕዝበ እስራኤል ወደ አምላካቸው እንዲመለሱና ሁለንተናቸውን ለእርሱ እንዲሰጡ የተላከላቸው መልእክት ነው ርእሳችን እኛንም ይመለከታልና እንደሚከተለው በዝርዝር እንየው።የሚታየውንም የማይታየውንም የፈጠረ፣ በባሕርም በየብስም ያሉትን ያስገኘ፣ ሰውን ለክብሩ ወራሽነትና ለስሙ ቀዳሽነት የወሰነ፣ ዓለምን ሲፈጥር አማካሪ ያልፈለገ፣ ፍጡሩን በመመገብና በመውደድ ወደር የሌለው፣ ለሰው ልጆች ራሱን አሳልፎ የሰጠ ነው ቸሩ አምላካችን እግዚአብሔር። ይህን ጌታ በምንም ልንለውጠውና ልንተካው አንችልም። አምላክ ነውና ተወዳዳሪ የለውም (ኢሳ. ፵፣ ፲፪ - ፲፬)
የርእሳችን መነሻ የሆነው «እጃችሁን ለእግዚአብሔር ስጡ» የሚለው ትምህርት የተሰጠው፣ ሃያ ዘጠኝ ዓመታት በእስራኤል ላይ በነገሠው ንጉሥ ሕዝቅያስ ነው። ምክንያቱ ደግሞ የእግዚአብሔርን ፋሲካ ለማድረግ የሚደረግ ቅድመ ዝግጅትን ይመለከታል። እግዚአብሔር ንጹሐ ባሕርይ ስለሆነ፤ ወደ እርሱ መቅረብና ማገልገል የሚቻለው በንጽሕና ሆኖ ነው፤ አገልግሎትንም የሚቀበለው ያለቸልታ በትጋት ሲሆን ነው። «ልጆቼ ሆይ በፊቱ ትቆሙና ታገለግሉት ዘንድ፥ ታጥኑለትም ዘንድ እግዚአብሔር መርጦአችኋልና ቸል አትበሉ፤ ብሎ ያዘዘን ለዚህ ነው (፪ዜና. ፳፱፣፲፩)።
«ንጉሡ ሕዝቅያስ ለእግዚአብሔር ፋሲካ እንዲደረግ ወደ እስራኤልና ወደ ይሁዳ ለዐሥራ ሁለቱም ነገደ እስራኤል መልእክት ላከ። ነገር ግን ካህናቱ ገና በሚገባ ስላልተቀደሱ፣ ሕዝቡም በኢየሩሳሌም ተጠቃለው ስላልተሰበሰቡ፤ ፋሲካው በደንብ ሲዘጋጁ በቀጣዩ ወር እንዲከበር ተወሰነ። ለቀጣዩ ወር ግን ሁሉም ከያለበት ከዳን እስከ ቤርሳቤህ ድረስ እንዲሰባሰብ እንዲህ የሚል ዐዋጅ ተነገረ፣ «የእስራኤል ልጆች ሆይ ... እግዚአብሔርን እንደ በደሉ እንደ አባቶቻችሁና እንደ ወንድሞቻችሁ አትሁኑ። አባቶቻችሁም እንደ ነበሩ አንገተ ደንዳና አትሁኑ፤ እጃችሁንም ለእግዚአብሔር ስጡ፤ ለዘላለም ወደ ተቀደሰው ወደ መቅደሱም ግቡ፤ ጽኑ ቁጣው ከእናንተ እንዲመለስ አምላካችሁን እግዚአብሔርን አምልኩ። (፪ዜና ፴፣፯-፰)።
እስራኤላውያን ከያሉበት ተሰባስበው በኢየሩሳሌም እንዲያከብሯቸው ከታዘዙት አንዱና ዋናው በዓል የፋሲካ ወይም የቂጣ ነው። በእግዚአብሔር ቸርነት ከግብጽ ባርነት የወጡበትን ሁኔታ ይዘክሩበታል። ይህም በኒሳን ፲፬ ቀን (በእኛ ሚያዚያ ወር) የሚከበር ሲሆን፤ በዓሉም ለሰባት ቀናት ይዘልቃል። ለዚህ ነው ይህን ታላቅ በዓል ሲያከብሩ በተለየ መልኩ ራሳቸውን መቀደስና እጃቸውንም ለፈጣሪ መስጠት የሚጠበቅባቸው። ይህ ታሪክ ለእኛ ምን ያስተምረናል? ይህንንም እንደሚከተለው እንመልከት፤
ለመሆኑ እጅን መስጠት ምንን ያሳያል? እጅን መስጠት መማረክን፣ መሸነፍንና በሌላ ነገር አለመወሰድን ወዘተ... ያመለክታል። ሁኔታው ሁለንተናን እና አጠቃላይ ማንነትንም ይመለከታል። እጅን መስጠት የሰላምም ምልክት ተደርጎ ይወሰዳል። ለእግዚአብሔር እጅን መስጠት ለምን ሲባልም? ሰው እጁን ከሰጠ ሐሳቡም፣ ተግባሩም፣ እንቅስቃሴውም ወዘተ... ወደዚያው ነው የሚጠቃለለው። የፈጠረን፣ የሚያኖረን፣ የሚያዝንልን ሁሉ እርሱ ነውና እኛም ሲቸግረን ለማግኘት፣ ሲጎድለን እንዲሞላልን፣ ስንወድቅ እንዲያነሣን እጃችንን በመስጠት ወደ እግዚአብሔር እንጮኻለን። «ኑ፥ ወደ እግዚአብሔር እንመለስ እርሱ ሰብሮናልና፥ እርሱም ይፈውሰናል እርሱ መትቶናል፥ እርሱም ይጠግነናል፤ እጅን ለእግዚአብሔር የመስጠት ምልክቶችን ቀጥሎ እንመለከታለን። ቀዳሚው ራስን መቀደስና ከኃጢአት መጠበቅ ነው። ያኔ ሕዝቅያስ ለእስራኤላውያኑ ያወጀላቸው ካህናቱ ራሳቸውን በሚገባ እንዲቀድሱ፣ ሕዝቡም ከኃጢአት ተጠብቀው ፋሲካውን በንጽሕና እንዲያከብሩ ነው። የእግዚአብሔርን ፋሲካ ከኃጢአት ሳይነጹ ማክበር አይገባምና ለዚህ ቀን ተሰጥቷቸዋል። በዚያም መሠረት ሁሉም እንደሚገባ ተከናውኗል። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚነግረን ሁሉም እጅግ ተቀድሰው ነበርና የፋሲካው በዓል ለተጨማሪ ሰባት ቀናት በደስታ ተከበረ፤ ይህም ከሰሎሞን ዘመን ወዲህ የመጀመሪያው በዓል እንደሆነ ተመዝግቧል፤ (፪ዜና. ፴፣፳፬-፳፮)። ዛሬም ለእግዚአብሔር የምናቀርበው ሁሉ የሚወደድልን አብዝተን ስንቀደስና እጃችንን ለእርሱ ብቻ ስንሰጥ ነው። በዓላትን ስናከብር፣ ወደ ቅዱሳት መካናት ስንጓዝ፣ ለመንፈሳዊ ሥራ ስንሰማራ ወዘተ... ምን ያህል መንፈሳዊ ዝግጅት እናደርጋለን? ለወረት ያህል ጀምረን የተውናቸው ስንቶች ናቸው? በመንፈስ ጀምረን በሥጋ የምንቋጫቸው ምን ያህል ይሆኑ? አንዴ መንፈሳዊ ሌላ ጊዜ ደግሞ ሥጋዊ መሆን የሚያምረን ስንቶቻችን ነን? በአንዱ እጃችን እግዚአብሔርን በሌላኛው ደግሞ ዓለምን የምንጨብጥ ከሆነ አንዱም አይሳካም። ስለዚህ ለፈጣሪያችን እኛነታችንን በመላ ነው ማስረከብ ያለብን። ከእርሱ ቀንሰን ለባእድ የምንሰጠው በፍጹም ሊኖር አይገባም።</p>
ዛሬ ዛሬ ብዙዎቻችንን በተለይም ወጣቶችን እየተፈታተነን ያለው የምንቆምበትን ቦታ አለማወቅ ነው። ሁሉም ነገር ያምረናል። ባየነው ነገር ሁሉ እንማረክና በቀላሉ እጃችንን እንሰጣለን። ይህ ዓለም የውጊያ ዐውድ ነው። በቀረበልን ሁሉ የምንማረክና እጅ የምንሰጥ ከሆነ ግን ዓላማችንን ስተናል። ጌታችን የዓለምን ፈተና ድል ያደረገልን እኛም በአሸናፊነት መንገድ እንድንጓዝ ሲያጠይቀን ነው (ዮሐ. ፲፮፣ ፴፫)። ስለዚህ ለሕይወት ፈተና እጅ እንዳንሰጥ፤ ለዓላማቢስነት እጅ እንዳንሰጥ፤ ለዝሙትና ርኩሰት እጅ እንዳንሰጥ፤ ለስሜታዊነት እጅ እንዳንሰጥ ወዘተ... መወሰን አለብን። እጅ መስጠት ለአምላክችን ለእርሱ ብቻ ይሁን።
ሁለተኛው ለአምላካችን እጅ የመስጠታችን ዐቢይ መገለጫ የእርሱን ፈቃድ ብቻ ስናደርግ ነው። በሕይወት ጉዞአችን ውስጥ ለሥጋዊ ፈቃድ ስኬት ብቻ ከሮጥን ትርፉ ድካም ብቻ ነው። የራስ ፈቃድ፣ የቤተሰብ ፍላጎት፣ የአለቃ ትእዛዝ፣ የባሕላችን ተጽእኖ፣ የአካባቢያችን ሁኔታ ወዘተ ... ዓይነቱና ኅብሩ ብዙ ነው። ይህን ሁሉ እናሟላለን ብለን ብንሞክርም ዓለም አትሞላምና /በዚያውም ላይ ዕድሜ ካልቀደመን/ በፍጹም አይሳካልንም። ስለዚህ ውጤቱ በኑሮ አለመርካት፣ ብጥብጥ፣ ተስፋ መቁረጥና የመሰለው ነው። ያንዱን ፈቃድ ትተን ሌላውን እንፈጽም ብንልም ውጤቱ አጉል ይሆናል። ነገር ግን የደጉ አምላካችንን ፈቃድ ብንከተል ለቀሪው ችግራችንና ምስቅልቅል ሕይወታችን መፍትሔ ነው። አንዱን የእግዚአብሔር ፈቃድ ስንፈጽም ሌላውን ያቃናልናል። በጀመርነው ጥቂት ነገር ብዙ በረከት ይሰጠናል። ይህን እውነት ሲመሰክር ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ይላል፤ «የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው ነገር ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ። ይልቁንም ወጣቶች የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለማወቅ ልባችንን ሰበር ማደረግ ይገባናል። የእርሱ ፈቃድ ሁል ጊዜ በጎና መልካም ነው። ፈቃዱን እንዴት ልወቀው? ብንል ዳዊት ምላሹን ይሰጠናል። (መዝ. ፳፣፬፤ ፵፣፰፤ ፻፵፫፣፲) እንመልከት።
ሦስተኛው መንገድ ወደ ቤቱ መምጣት ነው። የሚቀርቡልን ብዙ አማራጮች ጊዜያዊ ደስታን ብቻ የሚሰጡ ናቸውና አብረው አይዘልቁም። እንዲያውም ጸጸትና ቁጭት ያስከትላሉ። በእግዚአብሔር ቤት በቤተ ክርስቲያን መተከል ግን ድርብርብ መልካም ፍሬን ያስገኛል። ሰላም፣ ደግነት፣ ርኅራኄና ይቅርታ ወዘተ... ከቤተ እግዚአብሔር እንጂ ከዓለማዊ ቦታ (ማለትም መጠጥ ቤት፣ ዝሙት ቤት፣ ጥንቆላ ቤት፣ ወዘተ ) አይደለም። በኃጢአት ብንወድቅ በንስሐ፥ ራስን በመውደድ ብንሰቃይ ስለ ሌላው በማሰብ፥ በስርቆት ብንገኝ የራስንም መስጠትን ወዘተ... የምንማርባት ናት ቤተ ክርስቲያን። ስለዚህ በዓለም ካሉ መጠጊያዎች አብልጠን ራሳችንን የምናስጠጋባትና ለእሷም ብቻ እጃችንን ልንሰጥ የሚገባ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ናት። ክቡር ዳዊት «ነፍሴ የእግዚአብሔርን አደባባዮች ትወዳለች፣ ትናፍቅማለች... ከአእላፍ ይልቅ በአደባባዮችህ አንዲት ቀን ትሻላለች። በኃጥኣን ድንኳኖች ከመቀመጥ ይልቅ፥ በእግዚአብሔር ቤት እጣል ዘንድ መረጥሁ በማለት በቤተ እግዚአብሔር መኖር ያለውን ጠቀሜታ ያሳያል (መዝ. ፹፫፣ ፪-፲)
ሌላው መመለስ ያለበት ጥያቄ እጃችንን ለእግዚአብሔር መስጠት ምን ምን ያስገኛል? የሚለው ነው። አንድ ነገር ጥቅም ካልሰጠ መከወኑ ፋይዳ ቢስ ነው። ከዚህ አንጻር የተነሣንበትን ርእስ ስናየው፤ ምላሹንም እዚያው ምዕራፍ ላይ በቀጣዩ ቁጥር እናገኛዋለን። እንዲህ ይላል «አምላካችሁ እግዚአብሔር ቸርና መሐሪ ነውና፥ ወደ እርሱም ብትመለሱ ፊቱን ከእናንተ አያዞርም። ... ልጆቻችሁ ... ምሕረትን ያገኛሉ። ደግሞም ወደዚህች ምድር ይመለሳሉ።» (፪ዜና. ፴፣፱)። እጃችንን ለፈጣሪያችን ከሰጠንና መንገዳችን ከመንገዱ አንድ ከሆነ እርሱ በምሕረት ዐይኑ ይመለከተናል፤ በረከቱም ለልጅ ልጆቻችን ይተርፋል። የምንጓጓለት ሁሉ የሚሰጠን ቅድሚያ ራሳችንን ለእርሱ ስንሰጥ ነው። በፊቱ ሞገስ የምናገኘው ወለም ዘለም ሳንል ስናመልከው ነው። ወደርስት ቦታችን መንግሥተ ሰማያት የሚመልሰን፤ እንዲሁም የምንናፍቀውን ሕይወት የሚሰጠን በሐሳብም በተግባርም ለእግዚአብሔር ብቻ ስንገዛ ነው።
ስለዚህ እግዚአብሔር አምላካችንን ብቻ በማምለክና ለእርሱም እጃችንን በመስጠት ሕይወታችንን እንምራ። ወደእርሱ ከተጠጋን ፈጽሞ አይጥለንም። በነቢዩ አድሮ እንዲህ ብሎናልና፤ «አልጥልህም ያልሁህ ሆይ፥ እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ።(ኢሳይያስ ፵፩፣ ፲)። ለእርሱ ብቻ ታምነን እጃችንን እንድንሰጥ እርሱ ይርዳን።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን!!!
ከሰንበት ት/ማ/መምሪያ ድረ ገጽ የተገኘ