Friday, June 29, 2012

«የታማኝ ወዳጆች መከዳዳት»


 ባንድ አገር የሚተማመኑ ሁለት ሰዎች ነበሩ። ከነዚህም አንደኛው በሀብቱ የገነነ በሽምግልናው የተከበረ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ እየሠራ ከሚያፈራው ከዕለት ምግቡ ካመት ልብሱ የሚተርፈው ገንዘቡን እየወሰደ ባደራ ስም አኑርልኝ እያለ ለባለጸጋው የሚሰጥ ነበረ። ያም ታማኝ መሳዩ ሽማግሌ ያደራውን ገንዘብ እየተቀበለ ሲያስቀምጥለት ቆይቶ አንድ ቀን ባለ ገንዘቡ ለዕለት ችግሩ ካኖረው ሒሳብ ላይ ጥቂት እንዲሰጠው ቢጠይቀው ምን ሰጠኸኝና ትጠይቀኛለህ አላየሁም ብሎ ጨርሶ ካደው፤ እየተመላለሰ በማሳዘን ቢለምነውም አላዘነለትም፣ አልራራለትም። ቁርጡን ካወቀ በኋላ ላገሩ ዳኛ ክስ ለማቅረብ ሄዶ አመለከተ፤ ዳኛውም ስትሰጠው ያየህ ምስክር የሚሆን ሰው አለህን ብሎ ቢጠይቀው ከኔና ከሱ በቀር ማንም ሰው አልነበረም አለው። እንግዲያስ እኔ እጠይቅልሃለሁና ከሦስት ቀን በኋላ ተመልሰህ እንድትመጣ ብሎ አስታወቀው።
ብልኁ ዳኛ አደራ አስቀማጩን ሰው ጠርቶ፣ አሁን ያስጠራሁህ እኔ በድንገት ከዚህ አገር ከሹመቴ ተሽሬ መሄዴ ነው፤ ብጠይቅ ባስጠይቅም ታማኝ ሽማግሌ ባገር ያለኸው አንተ መሆንህን ሰማሁ፡ ስለዚህ ዕቃዬንና ያለኝን ገንዘቤን በሙሉ አንድ ጊዜ አንሥቼ ለመሄድ ስለማይቻለኝ አንተ ዘንድ እንድታስቀምጥልኝና በየጊዜው ሰው ስልክ እንድትሰጥልኝ እለምንሃለሁ አለው።
ሽማግሌውም እንግዲህ ይህ ያገር ዳኛ ትልቅ ሰው ስለ ሆነ ባደራ የሚያስቀምጠው ገንዘብ በብዙ የሚቆጠር ዕቃውም ካይነቱ ብዛት ጋራ የበረከተ ይሆናልና ይኸን ተቀብዬ አላየሁም ብዬ ባለሀብት ባለገንዘብ እሆናለሁ ብሎ ደስ አለውና ለዳኛው እሺ ጌታዬ ሲል መልስ ሰጠው።
ከሦስት ቀንም በኋላ ባለገንዘብ ለዳኛው በቀጠሮዬ መጥቻለሁ ብሎ አመለከተው። እንግዲህ ሂድና አንዳችም ነገር ሳትጨምር ባገሩ ዳኛ ልከስህ ነውና ገንዘቤን ስጠኝ በለው፤ በዚያም ጊዜ ገንዘብህን በሙሉ አንድም ሳያስቀር ጨርሶ ይሰጥሃል አለው። እንደ ተባለውም ሁሉ ሄዶ ቢጠይቀው ይህን አልሰጥም ያልኩት እንደ ሆነ ለዳኛው ሲነግረው ከሓዲነቴን ያውቅብኝና የሱን ብዙውን ገንዘብና ዕቃ ያስቀርብኛል ሲል ገንዘቡን በሙሉ አውጥቶ ሰጠው ይባላል።
እንቅልፍ ለምኔ፣ 3 እትም። ከብ/ጌታ ማኅተመ ሥላሴ። 1960 አርቲስትክ ማተሚያ። /አ። ገጽ 184-185