Friday, February 17, 2012

የቤተክርስቲያን መታደስ!


.............................በአሁኑ ወቅት ማንም ሰው ሊያስተውለው እንደሚችል በቤተ ከርስትያን ውስጥ ሁለት የሚጋጩና እርስ በእርሳቸው መጠፋፋት የሚፈልጉ አካላትን እናገኛለን :: አካላት ስንልም ሃሳቦች ናቸው :: ሃሳቦች ግን ሰዎችን ይዘዋል :: ሁለቱ አካላት በእየራሳቸው ለአንድ ዓላማ ይኽውም ለቤተ ክርስቲያን ለመጥቀም እንደሚሰሩ ይናገራሉ ::

ማህበረ ቅዱሳንና ማህበረ ቅዱሳናዊ አስተሳሰብ

ማህበረ ቅዱሳናዊ አስተሳሰብ የምለው ቤተ ክርስቲያን እንከን የለሽ በመሆንዋ ምንም አይነት ትችት ማቅረብ የለብንም የሚለውን እና አብዛኛው የማህበሩ አባላት እንዲሁም ብዙ የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎችም የሚጋሩት ነው :: ይህ ሃሳብ በመሰረተ ሃሳብነት ማነኛውም ኦርቶዶክሳዊ ሊደግፈውና ሊጋራው የሚገባው ነው :: የራስን ቤት ይልቁንም መክራና ዘክራ ያሳደገችንን ቤተ ክርስቲያን እንዲህ ናት እያሉ በእየ ሜዳው ስሟን ማጥፋት ክብሯን ማጉደፍ የማይገባ ስራ መሆኑ እሙን ነው :: በሌላ በኩል ደግሞ ምእመናኑ ወደ ኑፋቄ የሚነጠቁበትን እና በሃይማኖት ያሉትም ደግሞ ወደ ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የማይቀርቡበትን ምክነያት አጥንቶ እነዚህ እንዲህ ይደረግ ይህ ይስተካከል ማለት አግባብ ነው ::

ማህበረ ቅዱሳን በእየ ዜናው መውጣት ከጀመረ አለፈ ከረመ እንዳንዶች አይንህን ላፈረ አይነት ጽሁፍ ሲጽፉበት አንዳንዶች ደግሞ እርሱ ከሌለ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አትኖርም ብለው ክርር ያለ ክርክር ያደርጋሉ :: ታዲያ ሁለቱም ትክክል ሊሆኑ ስለማይችሉ ትክክለኛው የቱ ይሆን ማለቱ አስፈላጊ ነው :: የዚህ ጽሁፍ ጸሓፊ ማህበሩን በሚገባ የሚያውቅ ድክመቶቹንም የማያስተባብል ስለሆነ የማህበሩን በጎ ጎኖችን ሙሉ በሙሉ ዘርዝሮ መጨረስ ባይችልም ዋና ዋና በጎ ጎኖችንና ድክመቶቹን ይጽፋል :: የጽሁፉም አላማ ሰዎች ጥሩውንና መጥፎውን ለይተው ከመልካሙ ጋር እንዲተባበሩ ከመጥፎው ደግሞ እንዲርቁ ነው ::

ማህበረ ቅዱሳን ከሚደነቅባቸው ጥሩ ጎኖች መካክል

1. የተማረው ኢትዮጵያዊ /ኦርቶዶክሳዊ ለእግዚአብሔር እንዲታዘዝና ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዲቀርብ በርትቶ መስራቱ

2. ሁሉም ኦርቶዶክሳዊ የአባቶቹን ትውፊት ተከትሎ የቤተ ክርስቲያንን እንዲያገለግል ማበረታታቱ

3. ለቤተ ክርስቲያን አካላት ለገዳማትና ለአድባራት ልዩ ትኩረት በመስጠት እርዳታዎችን ማድረጉ

4. ቤተ ክርስቲያን በምትፈልጋቸው ማናቸውም የሞያ አይነቶች አባላቱን በማሳተፍ በነጻ አገልግሎት ማበርከቱ

5. ቤተ ክርስቲያን ላይ ደባ የሚጥሉትንና እርስዋን ለማጥፋት የሚንቀሳቀሱትን ሁሉ በአይነ ቁራኛ በመከታተለ ለሚመለከተው አካል ማስረዳቱ

6. ቤተ ክርስቲያን ዘመናዊ አስተዳደር እንዲኖራት ስልጠናዎችን በማዘጋጀት ለልዩ ልዩ የቤተ ክርስቲያን አካላት ማበርከቱ

7. አባላቱ በሚችሉት የቤተ ከርስቲያን አገልግሎት እንዲሳተፉ መገፋፋቱ :: ከሰባኪነት እስከ ገንዘብ እርዳታ እንዲያደርጉ ስልጠናና ምክር መስጠቱ ::

በሌላ በኩል ማህበረ ቅዱሳን አንዳንድ አባላቱ በሚያደርጉት ጫና ምክነያት ለቤተ ክርስቲያን እድገት እንቅፋት እንደሆነ ይነገራል :: ተሓድሶዎች የሚሉትን ትተን ወደ እውነታው ብንገባ ጸሐፊው የሚከተሉትን ዋና ዋና ስህተቶች / ችግሮች ተመልክቷል ::

1. አንዳንዶቹ የማህበረ ቅዱሳን አባላት ስልታዊ አገልግሎት የሚባል አይታይባቸውም :: በቤተ ክርስቲያን ማነኛውም አይነት ለውጥ እንዲደረግ አይፈልግም :: ምእመኑን ባለው ሁኔታ ወደ ቤተ ክርስቲያን ለማቅረብ ብቻ ይጥራሉ :: ይህም ማለት ስህተቶች እንኳን ካሉ እነርሱን ትክክል ለማድረግ የሚያስችል ነገር ይፈልጋል እንጂ ቀኖናዊ ለውጥ መደረግ ይችላል የሚል አስተሳሰብ እንደሌለ ጸሓፊው ተረድቷል :: በተለይ በአንዳንድ በመጽሓፍ ቅዱስ እውቀት የሌላቸው አባላት ::

2. ትውፊት በሚል ሰበብ የኢየሱስስ ስም መጥራት ይከብዳቸዋል :: ወይንም ኢየሱስ ያለ ሁሉ ፕሮቴስታንት እስኪመስል ድረስ ይመለከቱታል :: የቤተ ክርስቲያን መጽሓፍት ግን ቅዳሴውም ኪዳኑም ድርሳኑም ሰአታቱም ኢየሱስ ክርስቶስ መድሃኒዓለም እያሉ በእየቦታው ይጠሩታል :: ይህ ነገር ቀላል ሊመስል ይችላል ግን አይደለም አዳኝ የሆነውን ስም መጥራት የማነኛውም ክርስቲያን መንፈሳዊ ግዴታና ሓብት ነውና :: ኢየሱስ የሚለው ስም የክርስቲያኖች እንጂ የሌሎች መለያ አይደለም ::

3. መናፍቃኑ የቅዱሳንን ነገር እንዳቃለሉት የታወቀ ነው በአንጻሩ ደግሞ የማህበራችን ሰዎች በአብዛኛው ጊዜ ስብከቱም መዘሙሩም ንግግሩም ሁሉ ስለ ቅዱሳን እንዲሆን ይፈልጋሉ :: ምክነያቱ ምን አልባት ቅዱሳንን የሚያቃልሉ ፕሮቴስታንቶች ያሰገቡትን አስተሳሰብ ለማሸነፍ ይመስላል :: ሆኖም ስለ ቅዱሳን መሰረታዊ ነገር ከተያዘ መሰበክ መታወቅ ያለበት እግዚአብሔርና ትእዛዛቱ ቸርነቱ ምህረቱና ፍርዱ ነው ::

4. ማህበረ ቅዱሳን እራሱ ያላጸደቀውን ወይም ከማህበሩ ጋር ግንኙነት የሌለውን ሰባኪ ወይም የቤተ ክርስቲያን ሰው በጥርጣሬ ይመለከታል :: ምንም እንኳን በመዋቅር ደረጃ በሰንበት ት /ቤተ ማደራጃ መምሪያ ስር ቢሆንምና በቲዎሪ ደረጃ ለተቅዋማዊ ስርዓት ታዛዥ ቢመስልም በፕራክቲካል ግን የራሱን አጥር አጥሮ በዚያ የሚጓዝ ነው :: እባብ ያየ በልጥ ይደነግጣል እንደሚባለው ሁሉንም ሰው በጥርጣሬ አይን መመልከት ግንኙነትን በጣም ያሻክራል :: በቤተ ክርስቲያንም ውስጥ መተማመን እንዳይኖር ያደርጋል ::

የተሐድሶ ምንነት

ተሃድሶ በሁለት ትርጉሞች ሊፈታ ይችላል አንደኛ ትርጉሙ ማሻሻል ሲሆን በሌላ መልኩደ ግሞ መለወጥ፡ አዲስ ማድረግ የሚለውን ሃሳብ ያስተላልፋል :: መሻሻል በሚለው ትርጉሙ የተፋለሰውን ማስተካከል የጠፋውን ማቃናት የደከመውን ማበርታት ነው :: መለወጥ በሚለው ትርጉሙ ሙሉ በሙሉ የተሳሳተውን ሃሳብ መተካት አዳዲስ ሃሳቦችን ማስገባት በአዳዲስ ሃሳቦች መመራት አዲስ ሃሳቦችን እንደመመሪያ መቀበልን ያመለክታል ::

ተሃድሶ በሰዎች ላይም ይሁን በተቋማት ላይ ይካሄዳል :: ለምሳሌ የፓለቲካ ፓርቲዎች የያዙት የኢኮኖሚና ይፓለቲካ አካሄድ የማያዋጣ ከመሰላቸው ወይንም አካሄዳቸው የተሳሳተ ከመሰላቸው ታድሶዎ ያደርጋሉ :: ተሃድሶው ፍጹም መለወጥ ሊሆን ይችላል ወይንም ደግሞ መሻሻሎችን የያዘ ሊሆን ይችላል :: ሰዎች ሃሳባቸውን ሊያሻሸሉ ሊያስተካክሉ ወይንም ደግሞ ሙሉበሙሉ በአዲስ ሊለውጡ ይችላሉ ::

ተሃድሶ በመንፈሳዊው ሃሳብ ግን እንዲሁ የሚደረግ አይደለም ምክነያቱ ደግሞ መንፈሳዊው አለም መመሪያው የእግዚአብሄር ቃል መሪው መንፈስ ቅዱስ ስለሆነ :: ከመመሪያውና ከመሪው ጋር መማከር በመሪውና በመመሪያው መደገፍና መታመን ያስፈልጋልና ::

ቤተ ክርስቲያን እንደማነኛውም ተቋም ሰዎች ያሉባት ናት መሪዋ መንፈስ ቅዱስ መመሪያዋ የእግዚአብሄር ቃል ቢሆንም ቅሉ የሰዎች ሃሳብና ስራንም ታስተናግዳለች :: በመንፈስ ቅዱስ የተመሩ ሓዋርያት ጌታ ያስተማራቸውን እምነቶች በማስተላለፍ ቤተ ክርስቲያንን እንድትሰፋ አድርገዋል :: እነርሱን የተከተሉ ቅዱሳን አበውም ሃይማኖትን እያጸኑ ስርአትን እየሰሩ እስከ ዛሬ አድርሰውልናል :: በጎዎቹና መንፈስ ቅዱስን መሪያቸው ያደረጉ እንደነበሩ ሁሉ የራሳቸውን ሃሳብና እምነትም ሲያራምዱ የነበሩ ሰዎች አልነበሩም ማለት አይቻልም ::

ዛሬ ያሉ የተሃድሶ ሃሳብ አይነቶች

በአሁኑ ጊዜ ተሃድሶዊያን ብዙዎች ናቸው :: ፍጹም ኦርቶዶክሳዊያን ከሆኑጀምሮ እስከ ፍጹም ፕሮቴስታንት ድረስ ተሃድሶዎች አሉ :: አንዳንዶች ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ኖረው አድገው ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያንን እምነቷንና ስርትዋን ተምረው አልጥማቸው ሲል እና እነርሱ እንደፈለጉት ስላልሄደ ቤተ ክርስቲያንን ለቀው ከሌሎች ጋር የተቀላቀሉ አሉ :: እነዚህ ሰዎች ስላላመኑበት ሊቆዩ አልፈለጉም ስለዚህም በመውጣታቸው መልካም አደረጉ :: ቤተ ክርስቲያን አንድም ሰው እንዲጠፋ ባትፈልግም እንኳን የማያምኑ ሰዎች ግን መለየታቸው አግባብ እንደሆነ ትናገራለች :: ኑፋቄ ያለባቸውንም አውግዛ ትለያለች ::

አብዛኛው ተሃድሶዎች በአንጻሩ ከቤተ ክርስቲያን መውጣት የሚፈልጉ አይደሉም :: ይህም አንዳንዶቹ ለአላማቸው ማሳኪያ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ ከልብ የቤተ ክርስቲያንን መሻሻል እንጂ የሃይማኖት ለውጥን ስለማይፈልጉ ነው :: ሁለቱን የተሃድሶ አይነቶች አላማቸውና ምንነታቸውን እንደሚከተለው እናያለን ::

1. ፕሮቴስታንቱ ተሃድሶ : ፕሮቴስታንታዊ ተሃድሶዎች በቤተ ክርስቲያን አካባቢ የነበሩ አሁንም ሊኖሩ የሚችሉ ሰዎች ያሉበት ሲሆኑ እምነታቸው ከፕሮቴስታንት ጋር አንድ ነው :: ሙሉውን የእግዚአብሄርን ቃል ከመቀበል ይልቅ እንደ ፕሮቴስታንቶች ቁንጽልና አንድን ሃሳብ ብቻ ይዘው የሚሄዱ ናቸው :: የሚለዩት እነዚህ ኦርቶዶክሥ ነን ሲሉ እነዚያ ፕሮቴስታንት መሆናቸው ነው :: አንዳንዶች በምሽትና በድብቅ ከፕሮቴስታንቱ ጋር አምልኮ የሚፈጽሙ ከነርሱ ጋር መልእክት የሚቀያየሩ፡ የበጀት ድጎማ የሚደረግላቸው ናቸው :: እነዚህ ተሃድሶዎች አላማቸው ቤተ ክርስቲያን ውስጠ መቆየትና በሚችሉት መጠን የእነርሱን አስተሳሰብ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ማስገባት ነው :: ግባቸው ቢችሉ የቤተ ክርስቲያንን ዶግማ ጭምር መቀየር እና የፕሮቴስታንት እምነት በቤተ ክርስቲያን ተቀባይነት እንዲኖረው ማድረግ ነው ::

የፕሮቴስታንት ተሃድሶ አባላት ቤተ ክርስቲያን አካባቢ ከተነቃባቸውና ቤተ ክርስቲያን አካባቢ እንደማያዋጣቸው፡ ቦታ እንደማይኖራቸው ካወቁ ሳያወላውሉ ወዲያውኑ ክፕሮቴስታንቶች ጋር ሄደው ይቀላቀላሉ ::

በነገረ ድህነት በጥምቀት በቅዱስ ቁርባን በእምነትና በስራ ስለሚገኝ ጽድቅ ስለክህነት ስለንስሃ ስለቅዱሳን ስለምንኩስና በመሳሰሉ አስተምህሮዎች ላይ ሙሉ በሙሉ ከኦርቶዶክስ የወጣ ትምህርትና ከፕሮቴስታንት አንድ የሆነ እምነት ያምናሉ :: ኦርቶዶክስ ነን የሚሉት ሃይማኖት ለውጠዋል እንዳይባሉና ህዝብ ለመንጠቅ እንዲመቻቸው ብቻ ነው ::

እነዚህኞቹ ተሃድሶዎች ቤተ ክርስቲያንን ፊት ለፊት በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ የሚተቹ ያሳለፈቻቸውን ፈተናዎች ከመናገር ይልቅ ለማጥላላትና ለማጣጣል የሚሰሩ ናቸው :: ለሰው ይምሰል ብቻ ቤተ ክርስቲያንን ታሪካዊት ናት እናታችን ናት ይበሉ እንጂ ንግግራቸው ሁሉ የሰው ልብ ለማጥመድ ብቻ የሚያደርጉት ነው :: በተግባር ከቤተ ክርስቲያን ጋር ሲቆሙ አይታዩም ::

በአብዛኛው የዚህ ቡድን ደጋፊዎች ቤተ ክርስቲያን የምታምነውን ዶግማና ቀኖና በሚገባ ያልተማሩ ሰዎች እንዲሁም የአስተሳሰብ ግጭት የተፈጠረባቸው ሰዎች ናቸው :: በተለይም በክህነት የሚያገለግሉ የነበሩ የቤተ ክርስቲያን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርትና እምነት ያልተማሩ ሰዎች የዚህ አስተሳሰብ ተጠቂዎች ናቸው :: በቤተ ክርስቲያን ጥንቆላ እንዲቆም በእየቀኑ እንደማይሰበክ ድግምተኛና ጠንቋይ የሆኑ መርጌቶች ወደ ዚህ ቡድን ከገቡ በኋላ ቤተ ክርስቲያንን ድግምተኛ ናት ብለው ሲሰድቡ ይታያሉ እነዚህም ብዙዎች የዚህ አባል ከሆኑት ውስጥ ይመደባሉ ::

2. ኦርቶዶክስ ተሃድሶ : እነዚህም በራሳቸው በልዩ ልዩ ምክነያት በቤተ ክርስቲያን ለውጥ ያስፈልጋል ብለው የሚያስቡ ናቸው :: ለውጥ ስንል የአስተዳደር ለውጥ ማለታችን አይደለም :: የአስተዳደር ለውጥ እንዲኖር አብዛኛው ሰው ይፈልጋል :: እነዚህ ተሃድሶዎች የሚፈልጉት የቀኖናና የአስተሳሰብ ለውጥ ነው :: እነዚህን ራሱ በሁለት ይከፈላሉ :: a. አንደኛዎቹ ወገኖች ሙሉበሙሉ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን ዶግማ የሚቀበሉ ነገር ግን በስርአተ ቤተ ክርስቲያን እና በገድላት ላይ ጥያቄ የሚያነሱ ናቸው :: በቀኖና ረገድ ቤተ ክርስቲያንን ዘመናዊ ለማድረግ በእነርሱ አስተሳሰብ ወንጌልን በቀላሉ ለህዝብ ለማስተላለፍ ቤተ ክርስቲያን አንዳንድ የስርአት መሻሻሎችን ማድረግ አለባት ብለው ያምናሉ :: ለምሳሌ ለምእመናኑ ነጻነት የሚሰጡ ነገሮችን ማድረግን ይፈልጋሉ :: ጫማ አድርጎ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንደመግባት ፡ የፈለጉትን እንዲበሉ መፍቀድ፡ የጸሎቱን ይዘት ማሳጠር በአላትንና አጽዋማትን መቀነስ :: ወንጌልን ለማዳረስ በሚል ሳቢያ ዘመናዊ የሙዚቃ መሳሪያ ተጠቅሞ መዘመርን ይደግፋሉ ::

ገድላትና ታምራትን በመሰረታዊነት ቢቀበሉም አግልግሎታቸው ላይ ግን ገደብ እንዲደረግ ይፈልጋሉ :: ለምሳሌ ብዙ ጊዜ ተወስደው የሚነበቡት እንደ ታምረ ማርያም አይነት መጻሕፍት ከአገልግሎታቸው መነሳት አለባቸው ብለው ያምናሉ :: ከተነበቡም የመነበቢያ ጊዜቸው ውስን እንዲሆን ይፈልጋሉ ::

b. ሁለተኞቹ ኦርቶዶክስ ተሃድሶች : እነዚህ ተሃድሶዎች ለማለት ቢከብድም የማስተካከያ ሃሳብ የሚያቀርቡ የቤተ ክርስቲያንን ክብርና ማንነት ስርአትንም ለማስጠበቅ የሚተጉ ናቸው :: እንደ ዳንኤል ክብረት ገለጻ ቤተ ክርስቲያን ህዳሴ ማድረግ (ወደ ቀድሞ ክበሯ መመለስ ) አለባት ብለው የሚያስቡ ናቸው :: ለውጡም ለሰዳቢዎች ምክነያት የሆኑ እና ትክክል ያልሆኑ ነገሮች ይታረሙ የሚል ነው :: ቤተ ክርስቲያን የምትፈተነው በሌሎቹ ጥንካሬ ብቻ ሳይሆን በቤተ ክርስቲያንም ድክመት ጭምር ነው ብለው የሚያስቡ ናቸው :: በመሆኑም ድክመቶችዋ የሆኑት ነገሮች እንዲስተካከሉ የሚፈልጉ ናቸው ::

እነዚህኞቹ ለውጥ ፈላጊዎች ለቤተ ክርስቲያንና ለክርስቲያናዊ ትውፊቷ የሚቆረቆሩ ከመሆናቸውም በላይ በቅዱስ ሲኖዶስ የሚተማመኑ ሲኖዶሱ ራሱ የለውጡ መሪ እንዲሆን የሚማጸኑ ናቸው :: ቅዱስ ሲኖዶስ ያላጸደቀውን ቀኖናም አይፈጽሙም ::

ለውጥ ለቤተ ክርስቲያን ወይስ በቤተ ክርስቲያን ላይ ደባ

ምንም እንኳን እኔ ክፉ ነገር አደርጋለሁ የሚል አካል ባይኖርም ዛሬ ሁሉም የተዘረዘሩት የተሃድሶ አይነቶችም በእርግጥ ለቤተ ክርስቲያን ነው የሚሰሩት ወይስ ለራሳቸው አጀንዳ ብሎ ሰው መጠየቁ አይቀርም :: አንድን አካል ለሌላ አካል ነው የሚሰራው የሚለው መመዘኛው የተጠቃሚውን አካል መብቶች ሲያከበርና ፍላቶቱን ለማሟላትና ለመፈጸም ሲጥር ነው ::

በቤተ ክርስቲያን እንሰራለን በማለት ብቻ ለቤተ ክርስቲያን ይሰራሉ ማለት አይቻልም :: አንድ ለቤተ ክርስቲያን እሰራለሁ የሚል አካል ቤተ ክርስቲያኒቱ የምታምነውን ነገር የመናገር ባይችል ያለመስደብ ግዴታ አለበት :: ስርዓትዋንና ዘይቤዋን መረዳት ተገቢና አስፈላጊ ነው :: ለእርስዋ እስከሆነና በእርስዋ ውስጥ ለመኖር የሚፈልግ አካል ስርአተ ቤተ ክርስቲያንን እና የሲኖዶስን ውሳኔዎች መጠበቅ ሃላፊነት አለበት :: ያን ሳያደርግ ለቤተ ክርስቲያን እሰራለሁ ቢል አባባሉ የተምታታ ይሆናል ::

በሌላ በኩል ደግሞ ስርአት ባለው መልኩ ጥያቄዎችን ለሚመለከተው አካል ማቅረብ ከአንድ ለቤተ ክርስቲያን እሰራለሁ ከሚል አካል የሚጠበቅ ነው :: ችግሮችን ድክመቶችን እና ትችቶችን እያዩና እየሰሙ ለሚመለከተው ክፍል አለማቅረብም ለቤተ ክርስቲያን እሰራለሁ ከሚል አካል አይጠበቅም :: አንድ ልጅ ቤተሰብ ውስጥ ያለውን ችግር ለወላጆቹና ለታላላቆቹ እንዲፈታ መጠቆም የሚገባው ነው :: ቤተሰቡም ተወያይቶ ለልጁ ችግር ሳይሆን ችግር የመሰለውን ያብራራለታል በትክክል ችግሮች ካሉ ደግሞ ይፈታል :: በቤተ ክርስቲያንም እኛ ችግር የመሰለንን ሁሉ ለቅዱስ ሲኖዶስ ማቅረብ ተገቢ ሲሆን ቅዱስ ሲኖዶስ ደግሞ እንደ የበላይ አካልነት ለልጆቹ ተገቢውን መልስ መስጠት ተገቢ ነው ::

በመሆኑም ለውጥ ያስፈልጋል የሚሉ አካላት ለቤተ ክርስቲያን የሚጠቅም ስራ መስራታቸውን ማረጋገጥ ተገቢ ነው :: ለቤተ ክርስቲያን የሚሰሩ ወገኖች የቤተ ክርስቲያንን ክብር አስጠብቀውና ጠብቀው ህጉ በሚፈቅደው መልኩ ተገቢው ለውጥ እንዲመጣ ይጠራሉ :: በለውጥ ስም በቤተ ክርስቲያን ላይ ደባ ያደቡ ሰዎች በሌላ መልኩ ህግና ስርዓት በማይፈቅደው መልኩ ቤተ ክርስቲያንን የሚያሰድብ ምእመናንን የሚያሳቅቅ ነገር በእየለቱ ይሰራሉ ::

በቤተ ክርስቲያን የትኛው ተሃድሶ ያስፈልግ ይሆን ?

ይቀጥላል……………ቄስ ዘእግዚእነ እንደጻፈው(cyber Ethiopia, WARKA)