Monday, February 13, 2012

ምክራችሁን እሻለሁ!

 ጥያቄ፦

እባካችሁ ወገኖች ምክራችሁን እሻለሁ!

በጌታ የተወደዳችሁ ወገኖቼ ሰላም ለናንተ ይሁን!

ባለትዳርና የልጆች እናት ነኝ፡፡ ባለቤቴ እጅግ የሚወደድና ምስጉን ባህርይ ያለው ሰው ነው፡፡ ስራው የግሉ ንግድ ላይ ሲሆን ብዙውን ጊዜ ለስራው ሲሮጥ ከወዲህ ወዲያ ሲል ለስኬቱም ሲለፋ ነው የሚውለው፡፡ ለኔም ሆነ ለልጆቹ ያለው ፍቅር ሰው የሚቀናበትና እጅግ የሚገረምበት ነው፡፡ ትልቁ ህልሙ ልጆቹን ውጤታማ አድርጎ ለማየት ሲሆን ብዙውን ጊዜም እኔ ባለፍኩበት ልጆቼ እንዲያልፉ አልፈልግም ብሎ ይናገራል፡፡

እኔ ደግሞ በስነ ጥበብ ስራ ላይ ስገኝ ከስራዬ ባህርይ የተነሳ ከብዙ አለማውያን ወንዶች ጋር እገናኛለሁ፡፡ በስራዬ ደግሞ ስኬታማና ስም ያለኝ ሴት ነኝ፡፡ በሃገር ውስጥም ሆነ ከሃገር ውጪ የተለያዩ ግለሰቦችም ሆኑ ድርጅቶች እያዘዙኝ እሰራለሁ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በአንድ የውጪ ድርጅት ውስጥም ተቀጠሬ እየሰራሁ ነው፡፡

ከኢትዮጵያ ውጪ ካሉት አሰሪዎቼ ውስጥ አንደኛው ግለሰብ ብዙውን ጊዜ ወደሃገር ቤት ይመላለሳል፡፡ የስራ ትእዛዞችን ሰጥቶኝና የተሰሩትንም ይዞ ለመሔድ እዚህ በመጣ ጊዜ በተደጋጋሚ እንገናኛለን፡፡ ይሄ ሰው ዳጎስ ያለ ክፍያ የሚከፍለኝ ሲሆን ከውላችን ውጪም ተጨማሪ ገንዘብ በስራዬ መደሰቱን በመግለጽ አልፎ አልፎ ይሰጠኛል፡፡ ባለበት ሃገር ሆኖም ለሰላምታ ይደውልልኛል አልያም ኢሜይል አልፎ አልፎ እንጻጻፋለን፡፡

ከቅርብ ጊዜ ውዲህ ደግሞ በፌስቡክ ላይ ተገናኝተን ቻት እየተደራረግን ቀረቤታችን ለየት ያለ ወሬን ወደማውራት እና ወደመነፋፈቅ ተሸጋገረ፡፡ በወሬያችን እንደሚወደኝ እና ለኔ ለየት ያለ ስሜት እንዳለው ሲገልጽልኝ ባለትዳርና የልጆች እናት መሆኔን እያወቀ እንዲህ አይነቱን ነገር ማሰብ እንደሌለበት ደጋግሜ እናገረዋለሁ አኩርፎኝ እንለያያለን፡፡ (ሳልገልፀው የማላልፈው ጉዳይ ቢኖር እርሱ ትዳሩን ከጥቂት አመታት በፊት የፈታ ሲሆን የልጆች አባትም ነው)፡፡

የሄንን ሰው በስራየ ማጣት የለብኝም ባይሆን ረጋ ብዬ አስረዳዋለሁ እልና በሌላ ጊዜ ኦን ላይን ሳገኘው ረጅም ሰዓት ወስጄ ሃሳብ እንለዋወጣለን፡፡ በሃላም የተረዳኝ መስሎ ለጥቂት ጊዜ ተወኝ፡፡ የምናወራውም እነዴት ነህ እንዴት ነሽ ብቻ ሆነ፡፡ መጻጻፉንም እንደድሮው ሳይሆን ቀነስ አደረገ፡፡

እኔም በራሴ ወስኜ ፌስ ቡክ የሚባለውን ነገር ከስንት አንዴ ከመጠቀም በቀር በአብዛኛው ተውኩት፡፡ የምከፍተውም ከሃገር ውጪ ያሉ አብሮ አደጎቼን ለማግኘትና ከክርስቲያን ወገኖቼ ጋር መንፈሳዊ ነገሮችን ለመዋወጥ ብቻ ነው፡፡ እርሱንም ሊያገኘኝ የማይችልበትን ሰዓት እየተጠቀምኩ ነበር፡፡


በቅርቡ በግል ኢሜይሌ የተላኩልኝን መልእክቶች በማየትና ምላሽ በመስጠት ላይ እያለሁ በዚያም ቻት ማድረጊያው ላይ መልእክት መጣልኝ፡፡ ከዚህ በፊት በዚህ ተጠቅሜ ስለማላውቅ በመገረም ሳነበው የእርሱ እንደሆነ ገባኝ፡፡ በመጥፋቴ እንደተጨነቀና እንዳጋጣሚ እንዳገኘኝ ገልጾልኝ ተቀይሜው እንደሆነ ጠየቀኝ፡፡ በፍጹም ቅያሜ በኔ ልብ ውስጥ እንደሌለ ገልጬለት ስለ ስራችን አውርተን ተለያየን፡፡

በሳምንቱ ይመስለኛል ስልክ ደውሎ ለየት ላለ ስራ እንደሚፈልገኝ ገልጸልኝ ስለሁኔታውም አስረድቶኝ ለኔ ቀላልና ልሰራው የምችለው መሆኑን ገለጽኩለት፡፡ እግረ መንገዱንም ስለነበረው ያለፈው ሁኔታ አንስቶብኝ ፈጽሞ እንዲረሳውና ግንኙነታችን እንደቀድሞ እንዲሆን ገልጨለት በዚሁ ተለያየን፡፡ በማግስቱ ኢሜይል አድርጎልኝ አገኘሁ፡፡ ለኔ የተለየ ልብ እንዳለው፤ ፈጽሞ ሊያጣኝ እንደማይፈልግ ፤የሚያጣኝ መስሎት ተጨንቆ እንደነበርና አሁን ግን እረፍት እንዳገኘ የሚገልጽ ነበር፡፡ ምላሽ ግን አላኩለትም፡፡

ረዘም ካሉ ቀናቶች በሁዋላ ኢሜይል ሳደርግ ገብቶ ሰላምታውን አቀረበልኝ፡፡ እንደጠፋሁበትና ስራው ምን እንደደረሰ ጠየቀኝ፡፡ በጣም ሩጫ ላይ በመሆኔ አለማድረሴን ገልጨለት ይቅርታ ጠየቅኩ፡፡ እንደሚረዳኝ ነግሮኝ እንድጨነቅበት እንደማይፈልግና ሌሎች ብዙ ነገሮችን ስለኔ አወራ፡፡ በወቅቱ የነበሩትን ምላሾቼን ሳስታውሳቸው መለሳለስ የጀመርኩ የመስለኛል፡፡ በማግስቱም እንዲሁ ተገናኘን፡ መቀላለድም ጀመርን፡፡ የእርሱ ቀልዶች አንዳንዶቹ ወጣ ያሉ ሲሆኑ ከመናገሩ በፊት ‹አትቆጪኝም አይደል?› እያለ ፈቃዴን ይጠይቃል፡ ስከለክለው ይተዋል፡፡ በተደጋጋሚ መገናኘት ቀጠልን፡፡ እንዳገኘ ማውራትና መቀለድን በፊት አይቻልም ብለውም በሁዋላ ላይ ለቀቅ አደርገው ጀመርኩ፡፡ ኢሜይሌን ከፍቼ ኦንላይን ሳገኘው እኔው ራሴ ጨዋታ ጀማሪ ሆንኩ፡፡ እሱም ‹ቆይ ከሰው ጋር እያወራሁ ነው ጠብቂኝ› ማለት ጀመረ፡፡

እኔም ምን እየሆንኩ ነው ብዬ በራሴ አዝኜ ኢሜይል ጠዋት ጠዋት መክፈቱን እርግፍ አድርጌ ተውኩኝ፡፡ (እሱ ያለበት ሀገር ደግሞ ሰአቱ የመኝታ ሰዓት ነው) መጠቀም ስፈልግ ከሰዓት ላይ ብቻ አደረግኩ፡፡

ከዚህም በተጨማሪ በጸሎት ይህ ነገር ምንድን ነው ብዬም መጠየቅ ጀመርኩ፡፡ አምላኬ ይህን ክፉ ነገር ከኔ አርቅ ብዬም ጸለይኩ፡፡

በጸሎት መቀጠል ግን አልቻልኩም፡፡ ስንበረከክ እንቅልፌ ይመጣ ጀመር፡፡ ምን እንዳልኩ ሳላውቅ አሜን ብዬ እነሳለሁ፡፡ ጠዋት ላይም ለጸሎት ስነሳ ሰዓቱ ሄዶ አገኘዋለሁ፡፡ ልጆችን ት/ቤት እንዲሄዱ ምሳቸውን ማሰሩ፤ ቁርሳቸውን መመገቡ፤ ዩኒፎርም ማልበሱ፤ እንዲሁም መሸኘቱ ያለወትሮው እያዋከበኝ ያለፀሎት ከቤት መውጣት ጀመርኩ፡፡ ባለቤቴን ግራ ሲገባኝ ጸልይልን ድክም ብሎኛል እለው ጀመር፡፡ ያልተለመደ ሁኔታዬ ግራ ቢያጋባውም ነይ ተንበርከኪና እኔ ስጸልይ አሜን በይ ይለኛል፡፡ እሱ እየጸለየ መተኛቴ ግን አልቀረም፡፡ መደመነፍስ ግን አሜን የምል ይመስለኛል፡፡ ታድያ ጸሎቱን ሲጨርስ ንቁ ነኝ፡፡ (ወገኖቼ ከዚህ በፊት ግን በብዙ ነገሮች ላይ ለሰዓታት ተንበርክኬ በጸሎት የማሳልፍ ሴት ነበርኩ )

እስቲ ጉዱን አያለሁ በሚል ስሜት አንድ ቀን ኢሜይሌን በጥዋት ከፈትኩት እሱ አልገባም፡፡ በተከታታይ ቀናት ሳየውም ጠፋ፡፡ እኔም በቃ ስሜቴ ገብቶት ነው ብዬ ነገሩን ሁሉ ረስቼ ባገኘሁት ሰዓት መጠቀም ጀመርኩ፡፡ አንድ ቀን ስከፍት አገኘሁት ዝም ብዬው የተላኩልኝን አንብቤ ዘግቼ ወጣሁ፡፡ በድርጊቴ ተደስቼ ሌላ ጊዜም እንዲሁ አደርግ ጀመር፡፡ አንድ ቀን እባክሽ ዝም አትበይኝ ብሎ ጻፈልኝ፡፡ አይ ከሰዎች ጋር እየተጻጻፍክ ከሆነ እንዳልረብሽህ ብዬ ነው ስል መለስኩለት፡፡ ካንቺ ጋር ሳወራ ነው ደስታዬ እባክሽን ብሎ የቆጡን የባጡን ማውራት ጀመርን፡፡ በጫወታችን ውስጥ ገደብ ያለፉ ነገሮችን እያወራን ነበር እንደወትሮዬም በብዙ አልተከላከልኩም፡፡

ሰሞኑን አለቃዬ ለበላይ ሀላፊው ስለኔ ፈጽሞ ጥሩ ያልሆነ እና ጨርሶ ያልተፈጠረ ነገር ተናግሮ በጣም አበሳጨኝ፡፡ በዚያ ስሜት ውስጥ እያለሁ ኢሜይል ለማየት በጥዋት ከፈትኩ፡፡ እሱም ቀድሞኝ ገብቶ ነበር፡፡ ዝም ብዬው የራሴን ደብዳቤዎች አንብቤ ለወጣ ስል እንዴት ነሽ የሚል መልእክት መጣልኝ፡፡ ሰላምታ አቅርቤ ጫወታ ጀመርን፡፡ የዚህ ቀን ወሬያችን መስመር መልቀቁ እየታወቀኝ እኔም በነገሩ ገፋሁበት፡፡ ፍጹም ልቅና ከኔ የማይጠበቅ ንግግሮችን ተለዋወጥን፡፡ በዝሙት አለም ውስጥ ነበርን ብል ይቀለኛል፡፡ ከሶስት ሰአት በላይ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ነበርን፡፡ ምሳ ሰአት ሲደርስ ቻው! ቻው! ተባብለን ድሮም ይወደኝ እንደነበር አሁን ግን ፍቅሩ እንደጨመረ እዚህ ሲመጣም በተለየ ሁኔታ እንደምንገናኝ ነግሮኝ ተለያየን፡፡

ከዚየን ቀን ጀምሮ በጸጸት ፈጽሞ ልክ አይደለሁም፡፡ ቀድሞም እነዚህ ሁኔታዎች ከተጀመሩ ወዲህ ከውስጤ ጥሩ ስሜቶቼ ጠፍተው ልራቀው አልራቀው እያልኩ በይሉኝታና ሌላም ለኔ ባልገባኝ ስሜት ላይ ነበርኩ፡፡ አሁን ሁኔታዎች ሁሉ በማይሆን መንገድ ሄደዋል፡፡ ከባድ የሆነ የሃጢያተኝነት ስሜት እንቅልፍ እያሳጣኝ በስቃይ ላይ እገኛለሁ፡፡ ድብርትና ጭንቀት የእለቱ ሁኔታዎቼ ናቸው፡፡ ከቤተሰቦቼ ጋር ባግባቡ መጫወት ትቻለሁ፡፡ ባለቤቴንም አይኑን ማየትም እየፈራሁ ነው፡፡ ስራዬንም በአግባቡ መስራት ተስኖኛል፡፡ እባካችሁ ወገኖች ምክራችሁን እሻለሁና በጌታ ብላችሁ እርዱኝ፡፡
  መልስ፦
ሰላም እህቴ

ጥያቄሽን ሳነብብ ወደ ሃሳቢ የመጡትን ሁለት ዋና ዋና ነገሮችን ብቻ ላሳስብሽ እፈልጋለሁ፤ ልብ ብለሽ እንደምታነብቢው ተስፋ አደርጋለሁ።

1) እኔ እንደሚታየኝ አንቺ በፈተና (temptation) እያለፈሽ ነው። የፈተና (temptation) ባህርያት በግልጽ ይታዮብሻል። ማለትም የሄደት መጣ ማለት ስሜት፣ የተከለከለውን ነገር ለመብላት አንዳንዴ የመፈለግ አንዳንዴ ደግሞ የመፍራትና የማፈር፣ አንዳንዴ የተከለከለውን ለመብላት በማሰብና በመጎምዥት መደሰት፣ አንዳንዴ ሊመጣ ያለውን ጥፋት እያዩ የመሸማቀቅ፣ ጨክኖ ያለመጨከን፣ የመጠጋትና የመራቅ ወዘተ ባጠቃላይ የተለመደው (typical) የፈተና (temptation) ባህርያት በህይወትሽ ሲንጸባረቁ ይታያሉ።

እኔ ስለ ፈተና (temptation) በህይወቴ አንድ የተማርኩት ነገር አለ። ይሄውም ፈተና (temptation) የሚመጣው ለሁለት ነገር ነው። ወይ ሊያሸንፍሽ ወይም ልታሸንፊው ነው። ይህ እስካልሆነ ድረስ ፈተና ብዙውን ጊዜውን እንዲህ እያዋዠቀ ይቀጥላል። ሆኖም አንድ ነገር ልብ እንድትዪ እፈልጋለሁ። እኛ አሸንፈነውና ረግጠነው የማናልፈው ፈተና ወደ ህይወታችን በፍጹም አይመጣም። እንዲህ ተብሎ እንደተጻፈ፦

Quote:
1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች
10፥13 ለሰው ሁሉ ከሚሆነው በቀር ምንም ፈተና(temptation) አልደረሰባችሁም፤ ነገር ግን ከሚቻላችሁ መጠን ይልቅ ትፈተኑ(tempt) ዘንድ የማይፈቅድ እግዚአብሔር የታመነ ነው፥ ትታገሡም ዘንድ እንድትችሉ ከፈተናው ጋር መውጫውን ደግሞ ያደርግላችኋል።

ስለዚህ ፈተና ብዙዎች ገና ሲፈተኑ መውደቅን ብቻ አማራጭ እንደሚመስላቸውና መፈተንና መውደቅን ለያይተው ማየት እንደማይችሉ መሆን የለብሽም። መፈተን መውደቅ ማለት አይደለም። ፈተና የሚመጣው ወይ አንቺ ጨክነሽ ጥለሽው እንድታልፊ ነው ወይም እርሱ ከጣለሽ በኋላ በህይወትሽ እንዲጨክንብሽ ነው።

የፈተና (temptation) መውጫው መንገድ አንድ ብቻ ነው። ይሄውም ጌታን መለመንና መጨከን ነው። ጨዋታው የጭካኔ ጨዋታ ነው። አንቺ እንደሚመስልሽ በፈተና (temptation) ጊዜ እንዳለው አይነት ደስ ደስ የሚል ነገር አይደለም ጉዳዩ። ፈተና የሚመጣው አሳስቆ ቢሆንም፤ አላማው ግን አንቺን ጥሎ በህይወትሽ ላይ የጨከኑ ርምጃዎችን ለመውሰድ ነው። ሰይጣን አንዴ ከጣለሽ ለአንቺና በአንቺ ምክንያት ለሚጎዱ ሰዎች ህይወት ርህርሄ የሚባል ነገር አያውቅም። የጭካኔ ጨዋታ ነው የሚጫወትባችሁ። አንቺም ታዲያ ፈተናውን ረግጠሽ የምታልፊው በጭካኔ ብቻ ነው።

ይህ ማለት እንግዲህ በተግባርና በአጭር ቃል፤ ከዚህ ሰውዬ ጋር ያለሽን ማንኛውንም ዓይነት ግንኝነት ጨክነሽ መተው ብቻ ነው መፍትሄው። በዛ መሃል ሊቀሩ የሚችሉ ገንዘብና ወይም ይሉኝታ ወይም የእርሱ ማባበሎች ላይ በሙሉ መጨከን አለብሽ። በፍጹም ከሰውዬው በምንም መንገድ ጨክነሽ ካልሸሽ፤ መወደቅሽ አይቀርም። አሁን አንቺ በኢሜል ያደረግሽው ነው የገረመሽ፤ ሌላም ውስጥ ትወድቂያለሽ። አንዴ ከወደክሽ በኋላ ለአንቺና ለምትወጃቸው ሰዎች ሰይጣን በፍጹም አይራራምና አሁን አንቺ ጨክኚበት። ምንም ዓይነት የማባበያ ምክንያቶችን፤ ለምሳሌ ሰውዬው ባንዴ ስርቀው ይጎዳል ያዝናል ወዘተ የሚሉ ምክንያቶችን በፍጹም አትቀበይ። ወይም ራስን ለማታለል የሚቀርቡና "ምናልባት እግዚአብሔር በዚህ ነገር ዓላማ አለው" ወዘተ የሚሉ ከንቱ ራስን ማታለያየ ምክንያቶችን አትቀበይ። በፍጹም ቆርጠሽና ጨክነሽ መተውሽን መቶ በመቶ ሰይጣን እርግጠኛ እስካልሆነ ድረስ ማባበሉን አይተውም! ምክንያቱም ከላይ እንዳልኩሽ የፈተና ዓላማው ወይም አንቺን ጥሎ በህይወትሽ ላይ መጨከን ነው ወይም አንቺ ጨክነሽ ጠለሽውና ረግጠሽው እንድታልፈው ነው። አንዳችሁ እስክትወድቁ ድረስ ከአንቺ አይሸሽም!
Quote:
1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች
6፥18 ከዝሙት ሽሹ። ሰው የሚያደርገው ኃጢአት ሁሉ ከሥጋ ውጭ ነው፤ ዝሙትን የሚሠራ ግን በገዛ ሥጋው ላይ ኃጢአትን ይሠራል።

ኦሪት ዘፍጥረት
39፥12 ከእኔ ጋር ተኛ ስትል ልብሱን ተጠማጥማ ያዘች እርሱም ልብሱን በእጅዋ ትቶላት ሸሸ ወደ ውጭም ወጣ።

2) በሁለተኛ ደረጃ የማሳስብሽ ነገር ቢኖር ደግሞ፤ ራስሽን ይቅር እንድትዪ ነው። በቅድሚያ መፈተን ማለት መውደቅ ማለት አይደለም። ስለዚህ በኃይለኛ ሁኔታ ተፈትነሻል፤ ሆኖም እስካሁን ባደረግሽው ተጸጽተሽ ራስሽንም ይቅር በይ። አንዳንዴ ድካማችን ራሳችንንም ዝቅ (humble) የሚያደርግና በሰዎችም ቶሎ እንዳንፈርድ የሚያግዝ መሳሪያ እንደሆነ አድርገሽ ተመልክተሽ፤ ጌታ በይቅርታ እንደተቀበለሽ አንቺም ራስሽን በይቅርታ ተቀበዪ። ያለፈው አልፏል! ይልቁንም ይሄን ያህል ሰይጣን የሚፈትንሽ በትዳርሽ ጥሩ ነገር እንዳየ አውቀሽ፤ ትዳርሽን ጠበቅ አድርጊ። ለፈተና የሚበቃ መልካም ነገር በትዳርሽ ስላለ ስለ ትዳርሽ እግዚአብሔርን አመስግኝ፤ ባልሽንና ልጆችሽን አጥብቀሽ ያዢ!

ጌታ በነገር ሁሉ ይርዳሽ!